Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የድል በዓል ሐቻምና በአዲስ አበባ ሚያዝያ 27 አደባባይ ሲከበር ከቀረቡት ትርዒቶች አንዱ

ትኩስ ፅሁፎች

እምቢ!፡ አለች፡ ኢትዮጵያ፥ ቈንዳላ፡ ተሠርታ

ቼኮስሎቫኪያ፡ ገበረች፥ ራሷን፡ ተላጭታ፤

ነምሳ፡ ጧት፡ ገበረች፥ ራሷን፡ ተላጭታ፤

ፖሎኝም፡ ገበረች፥ ራሷን፡ ተላጭታ፤

ኢጣሊያ፡ ገበረች፥ በጧት፡ እጇን፡ ሰጥታ፤

ሁንጋሪያ፡ ዐበረች፥ እባርነት፡ ገብታ፤

ሩማንያ፡ ዐበረች፥ እባርነት፡ ገብታ፤

ቡልጋርያም፡ ዐበረች፥ እባርነት፡ ገብታ፤

ሆላንድ፡ ገበረች፥ ራሷን፡ ተላጭታ፤

ዳንማርክ፡ ገበረች፥ ራሷን፡ ተላጭታ፤

ኖርቬዥም፡ ገበረች፥ ራሷን፡ ተላጭታ፤

ዩጎዝላቭ፡ ገበረች፥ ራሷን፡ ተላጭታ፤

ግሪክም፡ ገበረች፥ ራሷን፡ ተላጭታ፤

ሉክሳምቡር፡ ገበረች፥ ራሷን፡ ተላጭታ፤

ፈረንሳ፡ ገበረች፡ ራሷን፡ ተላጭታ፤

እንቢ!፡ አለች፡ ኢትዮጵያ፥ ቈንዳላ፡ ተሠርታ።

ታረቀኝ፡ ተፈሪ

(የክብር፡ ዘበኛ፡ ፲፡ አለቃ፤ ሰቈጤ)፤

ኻርቱም፥ መስከረም፡ ፲፯፡ ቀን፥ ፲፱፻፴፫፡ ዓ.ም.።

*********************

«የንግግር ብዛት በአህያ አይጫንም»

እባክዎ አባቴ ከርስዎ ጋር ብነጋገር እወዳለሁና፣ አንዳንድ ነገር እንድጠይቅዎ ፈቃድዎ ይሁን አልኳቸው፡፡

አዬ ልጄ «የንግግር ብዛት በአህያ አይጫንም» ዛሬ በሥራ ከሚገለጸው በንግግር ብቻ የሚተረከው እየበዛ ንግግርና ሥራ ሳይገናኙ ይኖራሉ፡፡ በእኔ ዕድሜ ካሉ ጠይቆ መማር በተጠላበት ጊዜ እንዴት አንተ እኔን በማነጋገር በዕድሜህ የማታውቀውን ለማወቅ ፈለግህ? ልጄ በዕድሜዬ ያየሁትንና የተማርሁትን ብነግርህ በወደድሁ፡፡ ይሁንና የትም የት ብትሄድ ንግግር ብቻ ትሰማለህ፤ ንግግር ካልተሰራበት በኖ ይቀራል፡፡

ዘመኑ የረቀቀ ዘመን ነው፡፡ በዱሮ ዘመን፣ ሰውን ሰው በንግግር ብቻ ያሳምን ነበር፡፡ የዛሬ ዘመን ሰው ግን በዓይኑ ካላየ፣ በእጁ ካልዳሰሰ በንግግር ብቻ አያምንም፡፡ እኔም በወሬ የሰማሁትን ሳይሆን በዓይኔ ያየሁትን ብነግርህ እኔ የነገርኩህን በቃልም ሆነ በጽሕፈት ብታወራው ተቀባይ ላታገኝ ምን አታከተህ፡፡

እንደዚህ ያለ የተጠራጣሪና የተመራማሪ ዘመን ይመጣል ብሎ የገመተ የለም እንጂ፣ በየዋህነት ከመመራት መጠራጠር ቢኖር ኖሮ፣ የላሊበላ ታሪካዊ ሕንፃ ሥራ ዛሬ ለሚያየው ሁሉ እያጠራጠረ ራስ ምታት የሆነውን ራሱ ቅዱስ ላሊበላ እንደምን አድርጎ እንደሠራው በዘመኑ የነበሩት ሰዎች አብራርተው ይጽፉት ነበር፡፡

ታሪክ ፀሐፊ እውነትን እንጂ ከእውነት የራቀ ያልሆነውን እንደሆነ አድርጎ አጋኖ ቢጽፈውም የሰውን የመመራመር አስተያየት ወደ ጥርጣሬ ከመምራት በቀር ተቀባይነት አያገኝም፡፡ ታሪክ በአጻጻፍ ላይ ቁልምጫ የማይፈልግ ሥራንና አሠራርን ብቻ የሚያስተዋውቅ ዘለዓለማዊ መታሰቢያ ስለሆነ ሐቀኛ ሰው ይፈልጋል፡፡

– መኮንን ዘውዴ ‹‹ኢትዮጵያዊው›› (የቀኃሥ 44ኛ ዘመነ መንግሥት)

    *

«ግልብጥ ነኝ»

ወይዘሮ መድኃኒት አዳነ የተባለችው እመቤት ረጅምና ወፍራም ስለነበረች ባለቤቷ አቶ በላይ ሲኞሬ «ዘጋምባ» እያለ ይቀልድባት ነበር፡፡ አቶ በላይ «ሲኞሬ» የተባለው በጣልያን ዘመን ዕንቁላል ከሚኖርበት የገጠር መንደር የጣልያን ጦር ወደ ሰፈረበት ካምፕ እየወሰደ «ሲኞር ዕንቁላል አለ. . . ሲኞር ዕንቁላል አለ» እያለ በልጅነቱ ለጣሊያኖች ይሸጥ ስለነበር ነው፡፡  በሕልሙ ሳይቀር «ሲኞር ሲኞር. . .» ሲል ቤተሰቦቹ ስለሰሙት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በላይ ተሰማ መባሉ ቀርቶ በላይ ሲኞሬ ተባለ፡፡

ከዕለታት በአንዱ በላይ ካምቦ /ደጀን ከተማ/ ቅምጥ አለቺው መባልን ባለቤቱ ወ/ሮ መድኃኒት ሰምታና አጣርታ ስለደረሰችበት በቀን ምድር በር ዘግታበትና ከመደብ ላይ አጋድማ ስትደበድበውና ስታሸው «የጎበዝ ያለህ ርዳ ጎበዝ! ተጋደልን እኮ» ብሎ ይጮሃል፡፡ እርሷም «ለይ» በማለት ስትደበድበው ጎረቤት ተሰበሰበና በሩን ከፍቶ ሲገባ «ባሏን ደበደበችው» በሚል ሰው እንዳያመነጥጣት /ስሟን በክፉ እንዳያነሳው/ ከላዩ ላይ ተነስታ ከሥር ትሆናለች፡፡ በላይ ሲኞሬም አጥቂ በመምሰል ከላይዋ ላይ ሆኖ እንደ ዶሮ ሲንፈራፈር አንድ ገላጋይ ይይዘዋል፡፡ ሲኞሬም የልቡን ሳያደርስ ገላጋይ በመሃል በመግባቱ ተናድዶ «አያ ዳምጤ ተወኝማ የአሁን ግልብጥ ነኝ» ብሎ ተናገረ ይባል፡፡

ታደለ ገድሌ ‹‹ቅኔ እና ቅኔያዊ ጨዋታ ለትዝታ›› (1997)

*********

የድል በዓል አከባበር በዘውዱ ዘመን

በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የነበረው የበዓሉ አከባበር ፕሮግራም እንዴት ነበር ብለው መጠየቃቸው እንደማይቀር እርግጠኞች ነን፡፡ ስለሆነም፣ የበዓሉን አከባበር በተመለከተ የነበረውን መርሀ-ግብር ከአዲስ ዘመንና ከኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጦች ባገኘነው መረጃ መሠረት እናቀርብላቸኋለን፡፡ ልክ ከጧቱ 12፡00 የክብር ዘበኛና የፖሊስ ማርሽ ቡድኖች ሰልፋቸውን ከአራት ኪሎ እስከ ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ድረስ ይይዛሉ፡፡ ልክ ከጧቱ 12፡15 ሲሆን መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ሚኒስትሮችና ወይዛዝርት በምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ቦታ ቦታቸውን ይይዛሉ፡፡ ከጧቱ 1፡00 ሲሆንም፣ ጃንሆይ ከኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥታቸው (ከውጭ ጉዳይ ዝቅ ብሎ ከሚገኘው) ተነስተው ወደ ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በሞተረኛ ታጅበው ይሄዳሉ፡፡ ከጧቱ 2፡00 ሰዓትም ሲሆን የክብር ዘበኛ፣ የጦር ሠራዊት፣ የፖሊስና የሀገር ፍቅር የሙዚቃ ተጫዋቾች በአዲስ አበባ ሬዲዮ ጣቢያ ተገኝተው ልዩ ልዩ ሙዚቃዎችን ያሰማሉ፡፡ ከጧቱ 2፡45-3፡00 ሲሆን ደግሞ ከምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን እስከ ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ድረስ ያለው መንገድ ለትራፊክ ዝግ ሆኖ፣ ንጉሠ ነገሥቱ በሞተረኛ ታጅበው ከቅዳሴ የሚመለሱበት ሰዓት ይሆናል፡፡ ከ3፡00-3፡05 ባሉት አምስት ደቂቃዎች ውስጥ ዕለቱን በማሰብ የአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት ደስታቸውን ያለማቋረጥ ደወላቸውን በመደወል ይገልጣሉ፡፡ ከረፋዱ 4፡00 ወይም አንዳንዴ ከቀኑ በ6፡00 ሰዓት ሲሆን የውጭ አገር መንግሥታት ወኪሎችና ታላላቅ የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪዎች በተዘጋጀላቸው የክብር መዝገብ ላይ ፊርማቸውን ያኖራሉ፡፡ ልክ 5፡00 ሲሆንም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ፣ በከተማው ሕዝብ ስም በድል ሐውልት ላይ የአበባ ጉንጉን ያስቀምጣሉ (አዲስ ዘመን፣ ሚያዝያ 26/1945 ዓ.ም.፣ 1953፣ 1966 ዓም.)፡፡

  • ሰሎሞን ተሰማ ‹‹ሰምና ወርቅ›› (2013)

**************

‹‹እሺ ነገ ወደ ጄኔቭ ሄዳ ኦራይትንና ቱሞሮን… ወለደች››

የአምስቱን ዘመን የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ለመቀልበስና ነፃነትን ለማረጋገጥ ከጦራዊ ተጋድሎ በተጓዳኝ ዲፕሎማሲያዊ ትግሉ እልህ አስጨራሽ ነበር፡፡ በጄኔቭ የዓለም መንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ብዙ ምልልስ ነበር፡፡

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ በ1931 ዓ.ም በካርቱም ሳሉ፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ በጄኔቭ ላይ ቀርቦ ነገ ተነገ ወዲያ እየተባለ በመዘግየቱ እያዘኑ የዘረፉት መወድስ በ‹‹አማርኛ ሰዋስው›› መጽሐፍ የተጻፈው ቀጥሎ የተመለከተው ነው፡፡ የቅኔው ምሥጢር እሺ ነገ ወደ ጄኔቭ ሄዳ ኦራይትንና ቱሞሮን፣ አፍተር ቱሞሮን ወለደች ማለት ነው፡፡ (ኦራይት= እሺ፣ ቱሞሮ= ነገ፣ አፍተር ቱሞሮ= ተነገ ወዲያ፡፡)

‹‹. . .ወዲያና ወዲህም ሳትንገላታ

በየበራችን ለትቁም የዝግባ ሣንቃ ይሉንታ

በጄኔቭሂ አመ ተፀንሰ ዘኢትዮጵያ አለኝታ

[በጄኔቭ የኢትዮጵያ አለኝታ በተፀነሰ ጊዜ]

የቱሞሮ እናት እሺ ነገ ለብሂለ ኦራይት ወለደታ

ወእሺ ነገ እኅትነ እምድኅረ ወለደት መንታ

     ሕማማ ኢትዜከር ወአፍተር ቱሞሮ ተቀበለታ፡፡››

 

 

**********

 

 

ባዶ ክብር

የገረመኝ መዋሸቱ ሳይሆን ከዚህ በኋላ ላምነው አለመቻሌ ነው፡፡ አንድ ጊዜ አንዲት እውነት ማውራት የማይሆንላት ወጣት፣ እጮኛዋና እርሷ ስላሳላፉት ጥሩ ጊዜ ለጓደኛዋ ስታወራላት እንዲህ አለች፡- ‹‹እጮኛዬ ፓይለት እንደሆነ ታውቂያለሽ አይደል?›› (ልብ በሉ! ጓደኛዋ ፓይለት አይደለም)፡፡

‹‹አንድ ቀን በግሉ አይሮፕላን ሊያንሸራሽረኝ ፈልጎ ጠዋት ከቦሌ ተነሥተን እየበረርን ሰበታ አረፍን›› አለቻት፡፡ የምታዳምጣት ጓደኛዋም ‹‹እንዴ!… አንቺ? ሰበታ አይሮፕላን ማረፊያ አለ እንዴ?›› ስትላት ልጅቷም ‹‹ውይ! ሰበታ አልኩ እንዴ ወልቂጤ እኮ ማለቴ ነው›› በማለት ሸመጠጠች፤ አሁንም ጓደኛዋ ‹‹አንቺ! አሁንስ አበዛሽው! ወልቂጤ እኮ አይሮፕላን ማረፊያ የለም!›› ብትላትም ‹‹አይ አይደለም ተሳስቼ ነው ሱሉልታ ማለቴ እኮ ነው›› ብላ የውሸት ድፍረቷን ቀጠለች፡፡ በዚህ ዓይነት ብዙ ከተሞችን ስትጠራ ከቆየች በኋላ በመጨረሻም አላፈናፍን ያለቻት ጓደኛዋ ‹‹… ዛሬ በሰማይ ላይ ስትበሪ ትቆያለሽ እንጂ አታርፊያትም…›› ብላ ቀለደችባት፡፡

አንዳንድ ጊዜ ብዙ ሰዎች የመዋሸት ምክንያት ሳይኖራቸው ዝም ብለው የሚቀጥፉበት አጋጣሚ አለ፡፡ መዋሸት ግን ከመከበር ይልቅ ያዋርዳል፡፡ በሰዎች ዘንድ ከፍ ከመደረግ ይልቅ በተቃራኒው ሐፍረትን ያከናንባል፡፡

የሰው ክብሩና መመዘኛው ‹‹እኔ እንደዚህ ነኝ!›› ‹‹እንዲህና እንደዚህ ዓይነት ሀብት አለኝ›› የሚለው ባዶ ክብር አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት የውሸት ተግባራት ከመከበር ይልቅ ውርደትን ያመጣሉ፡፡

በውሸት ራሳችንን ከፍ ስናደርግ ባዶነታችንን ማሳየታችን እንደሆነ ማወቅ አለብን፡፡ አበው ‹‹ባዶ ዕቃ ብዙ ድምጽ ያሰማል!›› ይላሉ፡፡ ባዶ የሆነ ሰው ስለራሱ ብዙ ጉራዎችን መንዛቱ መታወቂያው ነው፡፡ ስለራሳችን ጉራ ስንነዛ ግን ባዶነታችንን ትልቅ ማድረጋችን እንደሆነ እናስተውል፡፡ ፊኛ ትልቅ ቢመስልም በመርፌ ነካ ሲደረግ ግን ውስጡ ባዶ ነው፡፡ ሀሰተኛ ሰውም እንደፊኛ ራሱን ከፍ ቢያደርግም አንድ ቀን በእውነት መርፌ ሲነካ ባዶ መሆኑ ይገለጥበታል፡፡

  • ዳንኤል ዓለሙ ‹‹ራስን የመለወጥ ምሥጢር›› (2005)

************

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች