በሊቢያ በአይኤስ አሸባሪ ቡድን አሰቃቂ ግድያ የተፈጸማባቸውን ኢትዮጵያውያንን ተከትሎ፣ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ መሆናቸው ስለሚሰማውና መውጫ አጥተው በጭንቀት ላይ እንደሚገኙ ስለሚነገረው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉዳይ ከግብፅ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ተወያይተው መመለሳቸው ተገለጸ፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ አካባቢ ወደ ግብፅ የተጓዙት ዶ/ር ቴድሮስ፣ የግብፅ አቻቸውን ሚስተር ሳሜህ ሹክሪና ከሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የተገናኙ ሲሆን፣ በሊቢያና አካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በግብፅ በኩል ወደ አገራቸው ስለሚመለሱበት ሁኔታ ተነጋግረው መግባባት ላይ መድረሳቸውን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ቢሮ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ በአሁኑ ጊዜ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም፣ በከፍተኛ ሥጋትና ችግር ውስጥ ለመሆናቸው በቀላሉ መገመት እንደሚቻል የገለጸው ቢሮው፣ የሁለቱ አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያደረጉት ውይይትና የደረሱበትን ስምምነት በሚመለከት ለጊዜው መግለጽ ቢያስቸግርም በቅርቡ ዜጎቹ ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ሊመቻች እንደሚችል አስረድቷል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ከሱዳንም መንግሥት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን የጠቆመው ቢሮው፣ በቤንጋዚ በኩል ወደ ሱዳን ገብተው ስለሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ጉዳይም ጥሩ ውጤት እየተገኘ መሆኑንም ቃል አቀባይ ቢሮው ጠቁሟል፡፡ እስካሁን ድረስ በሊቢያና አካባቢው ያሉ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል እንደሆኑና በትክክል ያለቡት ቦታ ባይታወቅም፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመትም ተጠቁሟል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ያሉ 30 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ያስታወሰው ቢሮው፣ ከመቶ በላይ የሚሆኑ በፈቃደኝነት ወደ አገራቸው ለመመለስ መመዝገባቸውንና እየተመዘገቡም መሆኑን ገልጿል፡፡