Thursday, April 18, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያዊነት በጠላት ፊት እንዳይንበረከክ!

ኢትዮጵያዊነት በጠላት ፊት የተንበረከከበት ጊዜ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ስትወረር እንጂ፣ የሰው አገር ስትወር አትታወቅም፡፡ ለወረራ የመጡ ኮሎኒያሎስቶችና የተለያዩ ዓላማ የነበራቸው ጠላቶች አፍረውና ተዋርደው ተመለሱ እንጂ፣ በቅኝ ገዥነት አልቆዩባትም፡፡ ይህ ኩሩና ጀግና ሕዝብ አገሩን አንዴም አስደፍሮ አያውቅም፡፡ በታሪክም አልተመዘገበም፡፡ ሕዝባችን በተለያዩ ዘመናት በተነሱ ጨቋኝ ገዥዎች አፈና ውስጥ ሆኖ እንኳን አገሩን ለባዕዳን አሳልፎ አልሰጠም፡፡ ይልቁንም በደሉንና መከራውን ችሎ አገሩን ከጠላት ሲከላከል ኖሯል፡፡ አሁንም ይህ ዓይነቱ አኩሪ ገድል በዚህ ትውልድ መቀጠል አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊነት በጠላት ፊት መንበርከክ የለበትም፡፡

ኢትዮጵያ አገራችንን ከባዕዳንና ከወራሪ ኃይሎች ስንከላከል በመካከላችን ልዩነት መኖሩ ሊገርም አይገባም፡፡ ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችን ይበልጥ ያስተሳስረናልና፡፡ ነገር ግን የዚህ ዘመን ልዩነት ከመነጋገርና ከመደማመጥ በላይ እየሆነ ክፍተት እየፈጠረ ነው፡፡ ይህ ክፍተት ደግሞ ሕዝባችን የሚታወቅበትን የአትንኩኝ ባይነትና አገርን በጋራ የመጠበቅ አኩሪ ባህል እየተገዳደረ ነው፡፡ ልዩነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከማስተናገድ ይልቅ የጥላቻና የእርግማን መዓት ማውረጃ ማድረግ ተመርጧል፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና በኃይል የሚደረገው ትግል መሀል ያለው ልዩነት በውል የማይታወቅ እየመሰለ ነው፡፡ ይኼ ፀንቶ ለኖረው ለኢትዮጵያ አንድነት አይስማማውም፡፡

እስኪ አንዳንድ ጉዳዮችን እናንሳና እንነጋገርባቸው፡፡ በቅርቡ በሊቢያ ምድር በወገኖቻችን ላይ አረመኔያዊ ድርጊት የፈጸመው አይኤስ የተባለው ርኩስ ለሁላችንም የማንቂያ ደወል ሊሆነን ይገባል፡፡ መንግሥት አይኤስን በተመለከተ የሚወስደው ዕርምጃና ምላሹ በጥንቃቄ መሆን ሲገባው፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ ግለሰቦች እንደዚሁ ጥንቃቄ ያሻቸዋል፡፡ አይኤስ በአሰቃቂና በአረመኔያዊ ድርጊቱ በፈጃቸው ሰማዕታት ወገኖች ምክንያት በተጠራው የውግዘት ሠልፍ ላይ መጠነኛ ቢሆንም ረብሻ መፈጠሩ አይዘነጋም፡፡ ይህም ረብሻ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት አግኝቶ ነበር፡፡ ያ ረብሻ ለአይኤስና ለመሰሎቹ የሚፈጥረውን ስሜት በውል ተገንዝበነዋል?

በመላው ዓለም በሚፈጥራቸው ‘ካሊፌቶቹ’ ወይም ‘የእስልምና መንግሥታት’ ብሎ በሚጠራቸው አማካይነት ሥርወ መንግሥቱን ለመመሥረት ያሰበው አይኤስ፣ በወገኖቻችን ላይ በፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት ለማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት አለ፡፡ ለዘመናት ያልተበገረችውን አገርና ሕዝቧን ማንበርከክ፡፡ አይኤስ ኢትዮጵያን መውረር ስለሚፈልግ ወደፊትም በኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት ከመፈጸም አይመለስም፡፡ በዚህም በኢትዮጵያውያን መካከል አለመግባባቱ እንዲካረር በማድረግ ለወረራ ያመቻቻል፡፡ በመጀመሪያ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በወንድሞቻቸውና በእህቶቻቸው ሙስሊሞች ላይ እንዲነሱ የተቻለውን ጥረት ያደርጋል፡፡ የአይኤስ አረመኔያዊ ድርጊትና የሰላም ምልክት የሆነው እስልምና በጭራሽ እንደማይገናኙ እየታወቀ፣ በኢትዮጵያውያን መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የዋሆችን ይጠቀማል፡፡

ዋና ዓላማው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ለማንበርከክ ስለሆነ በመጀመሪያ አገሪቱ ውስጥ ብጥብጥ መፍጠር ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ሲል ነው ክርስቲያን ኢትዮጵያውያንን በጥይት ሲደበድብና በሥለት ሲቀላ የሚያሳየውን ነውረኛ ተግባሩን ለዓለም በቪዲዮ የለቀቀው፡፡ ክርስቲያኖች በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ላይ ቂም በመቋጠር ለበቀል እንዲነሳሱ ማለት ነው፡፡ ለዘመናት የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው ተጋብተው የተዋለዱትን ኢትዮጵያውያን በዚህ ዓይነት አረመኔያዊ ድርጊት ካልከፋፈለ በሌላ ስለማይቻለው፣ ነውሩን ለዓለም ይፋ አድርጓል፡፡ ከአንድ ማዕድ እየተቋደሱ የሚበሉትን፣ በደስታም ሆነ በመከራ የማይለያዩትን፣ ከዕምነታቸው ልዩነት ይልቅ ለአገራቸው አንድነት በጋራ የሚቆሙትን ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች መለያየት እንደማይችል ማሳየት የኢትዮጵያዊነት ክብር መገለጫ ነው፡፡ በጠላት ፊት ያለመንበርከክ ትልቅ የሞራል ልዕልና ነው፡፡

በፖለቲካው ዓውድ ይህን ጉዳይ ስናነሳ ደስ የማይሉ ነገሮች ይታያሉ፡፡ በፖለቲከኞች መካከል ሊኖር የሚገባው ልዩነት ጤናማ ካልሆነ ጦሱ ለአገር ይተርፋል፡፡ ልዩነቱ በጠላትነት ላይ ተመሥርቶ መሠረታዊ የሚባል ቅራኔ ውስጥ ተዘፍቋል፡፡ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን አረመኔያዊ የግፍ ግድያ በአንድነት ቆሞ ከማውገዝ ይልቅ፣ ለጠላት በር የሚከፍት ድርጊት ተስተውሏል፡፡ ይህ አረመኔያዊ ጠላት ክርስቲያኖችንና ሙስሊሞችን ለማፋጀት የወጠነው ዕቅድ በፖለቲከኞች ዘንድ ሊስተዋል ባለመቻሉ፣ የተፈጠረው ግርግርና ረብሻ ማንኛውም ዓይነት ስያሜ ቢሰጠውም በጊዜ ካልታረመ አደጋ አለው፡፡ አደጋው ኢትዮጵያዊነትን በጠላት ፊት ማንበርከክ ነው፡፡ ከሥልጣን በላይ የሆነችው ታላቋ አገርና ይህ ጨዋ ሕዝብ መከበር ነበረባቸው፡፡ በሐዘን የተሳቀቁ ቤተሰቦችና ዘመዶች ሊከበሩ ይገባ ነበር፡፡ በጠላት ፊት ትዕግሥት ማጣት ፈተና ያመጣል፡፡ አገርንና ሕዝብን ያንበረክካል፡፡

ያ ጠባሳ ግን እንዲሁ ማለፍ የለበትም፡፡ ትምህርት ሊቀሰምበት ይገባል፡፡ የመጀመሪያው መንግሥት እንዲህ ዓይነት ድንገተኛ ነገሮች ሲከሰቱ የተጠና አካሄድ ሊኖረው ይገባል፡፡ በድንገተኛ ክስተቶች ላይ የሚሰጣቸው ምላሾች የሕዝብን ስሜት እንዲያማክሉ ኃላፊነት አለበት፡፡ ቁጣን የሚቀሰቅሱ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ መንግሥት ባለበት ኃላፊነትና ግዴታ መሠረት ኢትዮጵያውያንን የሚያስከብር ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ መግለጫውም ሆነ የተለያዩ መልዕክቶቹ በዚህ መንፈስ መተላለፍ አለባቸው፡፡ ረብሻና ግርግር ሲፈጠርም በተቻለ መጠን ጉዳት ሳይደርስ ማብረድ፣ ቁጣቸውን በሰላማዊ መንገድ መግለጽ ለሚፈልጉም ሥርዓት ባለው መንገድ ማስተናገድ ይለመድ፡፡ ይህ የተጠና አካሄድ በሕዝብ ውስጥ ሊኖር ይችላል ተብሎ የሚታሰበውን መከፋፈል እንደሌለ ማሳያ ይሆናል፡፡ በጠላት ፊት ኢትዮጵያዊነት እንዳይንበረከክም ይረዳል፡፡ ከዚያ ውጪ የኃይል አማራጭን ብቻ መጠቀም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ እዚህ ላይ ብርቱ ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ ከአገር በላይ ምንም ነገር የለም፡፡

ዜጐች ከአገር እየኮበለሉ ለምን ይወጣሉ የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ ብርቱ ጥናት እየተደረገበት፣ የሥራ አጥ ዜጐች ችግር እንዲቀረፍ ከፍተኛ ርብርብ መደረግ አለበት፡፡ ይህ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ተግባር በአዝጋሚው ቢሮክራሲ ተጠልፎ እንዳይወድቅ፣ የሚመለከታቸው ወገኖች በሙሉ መንግሥትን ማሳሰብ አለባቸው፡፡ በአነስተኛና በጥቃቅንም ሆነ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ዜጐች ያለምንም አድልኦና መገለል የሚስተናገዱበት አሠራር ካልተዘረጋ፣ በፖለቲካ ወገንተኝነት የሚደረገው አሳዛኝ ተግባር ለጠላት በር ይከፍታል፡፡ ዜጐችን ወደማይፈለግ ዓላማ ይገፋቸዋል፡፡ በገዛ አገሩ አድልኦ የሚፈጠርበት ዜጋ ሳይወድ በግድ አገሩን እንዲጠላ ከተደረገ፣ የጠላት መሣሪያ ላለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ ማግኘት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ዜጐች በአገራቸው ይከበሩ፡፡ አድልኦና መድልኦ ይወገዱ፡፡ ዜጐችን ያገለለ ልማት አይኖርም፡፡ ቢኖርም አይጠቅምም፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መፍትሔ ይፈለግ፡፡ በድርጊቱ እየበለፀጉ ያሉ ግለሰቦችና የጥቅም ሸሪኮቻቸው የሆኑ ባለሥልጣናት ጭምር ይጋለጡ፡፡ ኢትዮጵያውያን በፍቅርና በደስታ የሚኖሩባት አገር ትፈጠር፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊነት በጠላት ፊት የማይንበረከክ መሆኑ በተግባር ይረጋገጥ!     

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...