Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከቤቶች ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ የተመሠረተው ክስ ላይ ብይን ሳይሰጥ ቀረ

ከቤቶች ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ የተመሠረተው ክስ ላይ ብይን ሳይሰጥ ቀረ

ቀን:

– ዳኞች ከችሎት እንዲነሱ ጥያቄ ቀረበ

በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ላይ ሙስና ፈጽመዋል ተብለው በተጠረጠሩ የጽሕፈት ቤቱ የግብዓት፣ የአቅርቦትና የአስተዳደር መምርያ ምክትል ሥራ አስኪያጅና አንድ ነጋዴ ላይ ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ሊሰጥ የነበረው ብይን፣ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የመቃወሚያ ማመልከቻ ምክንያት ብይኑ ሳይሰጥ ቀረ፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. በፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅና ኤቢፕላስት በተባለ ድርጅት ባለቤት ላይ በመሠረተው ክስ የዓቃቤ ሕግ የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች ተሰምተው በመጠናቀቃቸው ለብይን የተቀጠረው ለሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ነበር፡፡

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የቀረበባቸውን የሙስና ወንጀል ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት የነበረ ቢሆንም፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ሦስት ነጥቦችን በማንሳት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 28 (1) መሠረት ማመልከቻ በማቅረብ ብይኑ እንዳይነገር አድርጓል፡፡ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ማመልከቻ ያቀረበበትን ምክንያት እንደገለጸው፣ በአዋጅ ቁጥር 343/97 አንቀጽ 38 (2) መሠረት የምስክሮች ስም በሚስጥር እንዲያዝለት ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ቢያቀርብም ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡ ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሰነድና የሰው ማስረጃ በአንድነት ሳይመረምር ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን አሰምቶ ባጠናቀቀበት ዕለት ማጣሪያ ምስክሮችን ጠርቶ ሰምቷል፡፡ በአጠቃላይ በመዝገቡ የቀጠሮ አያያዝም ሆነ የክርክር ሒደት ኮሚሽኑ በችሎቱ ዳኞች ገለልተኝነት ላይ ጥርጣሬ እንዳደረበት በመግለጽ በሌላ ችሎት እንዲታይለት ጠይቋል፡፡ በሌላ ችሎት እንዲታይለት የጠየቀውም በብይንም ሆነ በፍርድ ሒደት ላይ ፍትሐዊነትን ስለሚጠራጠር መሆኑን ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን የማይቀበለው ከሆነ ለፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔም ያመለከተና ውጤቱን እየተጠባበቀ መሆኑን አስታውቆ፣ ጉባዔው እልባት እስከሚሰጥበት ድረስ በክስ መዝገቡ ላይ ብይን ሳይሰጥበት እንዲቆይ ሚያዝያ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. በጻፈው ማመልከቻ ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ‹‹ብይን እንዳይሰጥብኝ›› አቤቱታ በችሎት ከገለጸ በኋላ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ‹‹የምስክሮቼ ስም እንዲገለጽ ተደርጓል፤›› የሚለውን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ ምስክሮችን በሚመለክት የቀረበው አቤቱታ ዳኞችን ከችሎት ሊያስነሳ እንደማይችል ገልጿል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን ምስክሮች አሰምቶ ከመጨረሱም በተጨማሪ፣ ሌሎች ምስክሮችን አቅርቦ እንዲያሰማ ጠይቆ ተፈቅዶለት ካሰማና ከጨረሰ በኋላ የምስክሮቹ ስም በመገለጹ፣ ማስፈራራት የደረሰባቸው በማስመሰል ያቀረበው ማመልከቻ ተቀባይነትና የሕግ መሠረትም እንደሌለው ገልጿል፡፡ ተጨማሪ ምስክሮችን ጠይቆ ከማሰማት ባለፈ በወቅቱ ምንም ዓይነት ቅሬታ አለማቅረቡን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ በሚሰጠው ብይን ቅሬታ ቢኖረው እንኳ ይግባኝ ከማለት ባለፈ ዳኞች ከችሎት እንዲነሱ የሚያስችል የሕግ መሠረት እንደሌለ ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግ የሰው ምስክሮችንና ሰነድ በአንድነት ሳይመረምር በዕለቱ ማጣሪያ ምስክሮችን መስማቱን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 143 (1) መሠረት ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት በማንኛውም ጊዜ ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ አመቺ መሆኑን ካመነ ተጨማሪ ማስረጃ መጥራት (ማዘዝ) እንደሚችል መደንገጉን ጠቅሶ፣ ፍርድ ቤቱም ያደረገው ይኼንን መሆኑን ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ እንዳለቀ ተጨማሪ ማስረጃ መጥራቱ አግባብ ያለው ሥራ መሠራቱን የሚያሳይ እንጂ ስህተት ወይም አድልኦ መሥራቱን የሚያሳይ ባለመሆኑ ቅሬታ ሊቀርብበት እንደማይገባ ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሠራው ሕግን መሠረት አድርጎ በመሆኑ ዳኞች ከችሎት እንዲነሱ ወይም መዝገቡ በሌላ ችሎት እንዲታይ የቀረበው ማመልከቻ የሕግ መሠረት የሌለው መሆኑን አብራርቷል፡፡

የዳኞችን ገለልተኝነት መጠራጠሩን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ ላቀረበው አቤቱታ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ፣ እንዲያውም መዝገቡ ብዙ ጊዜ የተጓተተው ዓቃቤ ሕግ ፍርድ ቤት የሚሰጠውን ትዕዛዝ አክብሮ ማስረጃዎቹን በጊዜ ሊያቀርብ ባለመቻሉ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ‹‹ፍርድ ቤቱ ለዚህ መዝገብ ከሌሎች መዝገቦች የተለየ ነገር አላደረገም፤›› ብሎ ለመዝገቡ መጓተት ምክንያቱ ዓቃቤ ሕግ መሆኑን ገልጿል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ተጨማሪ ምስክሮችን ለማሰማት አስፈቅዶ ፍርድ ቤት ቀጠሮ ሰጥቶና ምስክሮች ከቀረቡ በኋላ በችሎት እንደማይፈልጋቸው በመናገሩ የቀጠሮ ቀናትን ማባከኑን ገልጿል፡፡ መዝገቡ በትክክል እንዳይመረመር ሲያጓትት የነበረው ዓቃቤ ሕግ ሆኖ ሳለ ምስክሮች በፍጥነት ተሰሙ በሚል፣ ዳኞች ከችሎት እንዲነሱ መጠየቅ እንደማይችልና የሕግ መሠረት እንደሌለው አብራርቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግን ማመልከቻ የማይቀበል ከሆነ ለዳኞች አስተዳደር ጉባዔም አቤቱታ አቅርቦ ውጤት እየተጠባበቀ መሆኑን ጠቅሶ፣ በመዝገቡ ላይ ብይን እንዳይሰጥ ያቀረበውን ማመልከቻ በሚመለከት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አቤቱታ ማቅረብ ማለት ጉዳዩ እንዳይታይ ማድረግ ማለት እንዳልሆነ የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ አንድ ዳኛ ማስረጃ ሰምቶ ከጨረሰ በኋላ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሲይዝ ብይን ሳይሰጥ መዝገቡ ይታገድ ማለት የሕግ መሠረት የሌለው ጥያቄ መሆኑን ገልጿል፡፡ በሕግ የሚፈቀድ አለመሆኑንም ጠቁሟል፡፡ ጥያቄ የሚቀርብበትም አለመሆኑን አክሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ እስከጨረሰ ድረስ ብይን መስጠት እንደሚችል ገልጿል፡፡ ሥራው የፍርድ ቤት እንጂ የዓቃቤ ሕግ ወይም የኮሚሽኑ አለመሆኑንም አስታውቋል፡፡

ችሎቱ በምን ሁኔታ መመራት እንዳለበትና ሥራውን እንዴት መሥራት እንዳለበት የሚወስነው ችሎቱ እንጂ፣ ኮሚሽኑ ወይም ዓቃቤ ሕግ አለመሆኑንና የሕግ መሠረትም የሌለው መሆኑንም አስረድቷል፡፡

 ሦስቱም የችሎቱ ዳኞች እንዲነሱለት ዓቃቤ ሕግ መጠየቁን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ፣ በአዋጁ ተገልጾ የሚገኘው አንድ ዳኛ ከችሎት እንዴት መነሳት እንዳለበት መሆኑን ፍርድ ቤቱ ጠቁሟል፡፡

አንድ ዳኛ ከችሎት እንዲነሳ ከተከራካሪ ወገን የተቃውሞ ማመልከቻ ሲቀርብበት፣ ከችሎቱ የማይነሳበትን ምክንያት በመዝገቡ ላይ ጽፎ ወደ ሌላ ችሎት በመላክ እንዲመረመርና ትዕዛዝ እንዲሰጥበት እንደሚደረግ በአዋጅ 25/88 መደንገጉን ገልጿል፡፡ ሦስቱም ዳኞች እንዲነሱ ሲጠየቅ እንዴት መሆን እንዳለበት ሕጉ ባያስቀምጥም፤ በ18ኛ ወንጀል ችሎት ያሉት ሦስቱም ዳኞች ከላይ በተገለጸው ሁኔታ ከችሎት የማይነሱበትን ሁኔታ አብራርተው፣ በዕለቱ በሬጅስትራር በኩል ወደ ሌላ ችሎት ተመርቶ እንዲመረመርና ትዕዛዝ እንዲሰጥበት አዘዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...