Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ8.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰቡን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የልዩ ሴት ቆጣቢዎች ተቀማጭ ሒሳብ ሦስት ቢሊዮን ብር ደርሷል አለ

ከሚያዝያ 15 ቀን እስከ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ የ2007 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ በባህር ዳር ከተማ ግምገማ ማድረጉን የገለጸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ባለፉት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ከ8.786 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ለመሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ፡፡

ባንኩ ለወጪና ለገቢ ንግድ ዋነኛ ግብዓት የሆነውን የውጭ ምንዛሪ የሰበሰበው 4.4 ቢሊዮን ዶላር ከተለያዩ ምንጮች፣ 3.63 ቢሊዮን ዶላር በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከተላከ፣ 756.1 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ከወጪ ንግድ መሆኑን አብራርቷል፡፡

በሌላ በኩል በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ውጭ ጉዞ የሚያደርጉ ግለሰቦች ወደ ባንኮች ሄደው የሚጠይቁትን የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ እንደማያገኙ ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት አንድ ሺሕ ዶላር ለማግኘት ከፍተኛ ችግር መኖሩን እነዚሁ ግለሰቦች ያስረዳሉ፡፡ አንዳንድ ባንኮችም ከውጭ ምንዛሪ እጥረቱ የተነሳ ወደ ውጭ ለሚሄዱ ግለሰቦች የውጭ ምንዛሪ ሲሸጡ የአገልግሎት ክፍያ ማስከፈል ጀምረዋል፡፡

 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበጀት ዓመቱ ውስጥ የሚያከናውናቸውን የሥራ አፈጻጸም ሒደት በየሦስት ወራቱ ይፋ ሲያደርግ የመገናኛ ብዙኃንን በመጥራት ይሰጥ የነበረውን ማብራሪያ በመተው፣ በኮሙዩኒኬሽንስ ሥራ አስኪያጁ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ፊርማ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙ በሁሉም ዘርፍ አመርቂ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ያልነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደ አገልግሎቱ እንዲመጡ ለማድረግ የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶች በመጀመሩ፣ 422,482 ሴቶች የልዩ ቁጠባ ሒሳብ አገልግሎት ተጠቃሚዎች በማድረግ ሦስት ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ሒሳብ መሰብሰቡን አውስቷል፡፡ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ከከፈቱ 69,217 ደንበኞች 807 ሚሊዮን ብር፣ ከ273,560 ታዳጊ ወጣቶች 353 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን መግለጫው ያስረዳል፡፡

ባንኩ በዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም 27.5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉን፣ የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ በሰኔ 2006 ዓ.ም. ከነበረበት 193.3 ቢሊዮን ብር ወደ 220.8 ቢሊዮን ብር መድረስ መቻሉን ጠቁሟል፡፡ 107 ቅርንጫፎች በመክፈት የቅርንጫፎችን ጠቅላላ ቁጥር 939 በማድረስ፣ ከአዳዲስ ደንበኞች 1.1 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡንም አክሏል፡፡ 1.9 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞች ሒሳብ በመክፈቱ ጠቅላላ የአስቀማጮች ብዛት 10.1 ሚሊዮን መድረሱን አስታውቋል፡፡

ባንኩ 62.9 ቢሊዮን ብር በብድርና በቦንድ ሽያጭ መልክ ማቅረብ መቻሉን፣ በተመሳሳይ 28 ቢሊዮን ብር ከብድር ተመላሽ በማድረግ በዘጠኝ ወራት ውስጥ መልሶ ለኢኮኖሚው በብድር ማቅረቡን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ጊዜ 627 ኤቲኤም ማሽኖች ለተጠቃሚዎች ተደራሽ አድርጎ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ማሽኖቹን በመጠቀም በተደረጉ ግብይቶች 9.6 ሚሊዮን ብርና ከ33 ሚሊዮን ዶላር ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ልውውጥ መደረጉን በመግለጫው ጠቅሷል፡፡ 1,162 ‹‹POS›› ማሽኖችን በተለያዩ የመገበያያ ሥፍራዎች ማስቀመጡን፣ 654,641 ካርዶች በደንበኞች እጅ እንደሚገኙ፣ 144,588 የሞባይል ደንበኞች እንዳሉትና ጠቅላላ የሠራተኞቹ ቁጥር 22,475 መድረሳቸውን በአቶ ኤፍሬም ተፈርሞ የወጣው መግለጫ ያስረዳል፡፡

በአጠቃላይ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ክንውን 15.9 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ መገኘቱን የገለጸው ባንኩ፣ ከታክስ በፊት 9.05 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘት መቻሉንም አስታውቋል፡፡ 4,312 አዳዲስ ሠራተኞች ባንኩን በመቀላቀላቸው ጠቅላላ የሠራተኞች ቁጥር 22,475 መድረሱ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች