– ድርጅቱ የተጣለበት ወለድና ቅጣት እንዲነሳለት ጠይቋል
የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት 73.5 ሚሊዮን ብር ፍሬ ግብር ከነወለዱና ከነቅጣቱ እንዲከፍል በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተጠየቀ፡፡ ድርጅቱ በበኩሉ ግብሩን ያልከፈለው በሕግ ትርጉም ስህተት በመሆኑ ወለድና ቅጣቱ እንዲነሳለት ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ለኮንስትራክሽን ሥራ፣ የተለያዩ ማሽነሪዎችን ሲከራይ፣ በኪራይ ዋጋ ላይ ታስቦ ሊከፍል ይገባ የነበረን ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍለው አከራይ ድርጅት ጥያቄ ሲያቀርብ፣ የውኃ ሥራዎችና ኮንስትራክሽን ድርጅት ሳይከፍለው ቆይቷል፡፡ በመሆኑም አከራዩ ድርጅት በፍርድ ቤት በመክሰሱ፣ ፍርድ ቤቱ 21,428,782 ብር የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት እንዲከፈለው ወስኗል፡፡ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የተጠቀሰውን ገንዘብ ሳይከፍል በመቆየቱ፣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በሰጠበት ፍሬ ግብር ላይ ወለድና ቅጣት 52,153,637 ብር ጨምሮ እንዲከፍለው ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ክፍያውን በአስቸኳይ የማይከፍል ከሆነ፣ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የድርጅቱን ንብረቶች በማሳገድ ወደ ገንዘብ ለውጦ ለራሱ ገቢ እንደሚያደርግ በጻፈው ደብዳቤ አሳውቋል፡፡
ድርጅቱ የአገር ዕዳ እየከፈለ እንደሚገኝ ለሪፖርተር የገለጹት የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አትክልት ተካ፣ ለባለሥልጣኑ በሰጡት ምላሽ ድርጅቱ እያንቀሳቀሳቸው የሚገኙ ግዙፍ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክቶች በገንዘብ እጥረት ምክንያት እንዳይስተጓጎሉ፣ ባለሥልጣኑ የጣለበትን 52.1 ሚሊዮን ብር ወለድና ቅጣት እንዲያነሳለት ጠይቋል ብለዋል፡፡
ድርጅቱ ለሠራቸውና እየሠራቸው ለሚገኙ የስኳር ልማት የሚውሉ ሰፋፊ የግድብ፣ የመስኖ ልማትና ተዛማጅ ግንባታዎች ለሚከራያቸው ተሽከርካሪዎች ተጨማሪ እሴት ታክስ ሳይከፍል የቆየው፣ በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 2(ቸ) መሠረት ከታክስ ነፃ የሚለውን ድንጋጌ ተከትሎ መሆኑን በምላሹ ደብዳቤ ጠቅሷል፡፡
ይህንንም ድንጋጌ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 79/85 አንቀጽ 28 ስላረጋገጠው፣ አከራይ ድርጅቶችም ተመሳሳይ ግንዛቤ እንደነበራቸው አክሏል፡፡ ነገር ግን ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርን ሲጠይቅ፣ ገልባጭ ተሽከርካሪዎች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ መሆን እንደማይችሉ በሚያዝያ ወር 2001 ዓ.ም. በጽሑፍ በማሳወቁ፣ ድርጅቱም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለሚያከራዩት ድርጅቶች መክፈል መጀመሩን፣ በዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ አትክልት ተፈርሞ ለባለሥልጣኑ የደረሰው ደብዳቤ ያስረዳል፡፡
የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅትን በኃላፊነት ተረክበው መሥራት ከጀመሩ ሁለት ዓመት እንዳልሞላቸው የሚናገሩት አቶ አትክልት፣ ድርጅቱን እሳቸው በኃላፊነት በሚረከቡበት ወቅት ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ውስጥ ነበር፡፡ በመሆኑም ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ የአገር ዕዳ እየከፈለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የተጠየቀው ቅጣትና ወለድ ተገቢ አለመሆኑን የሚናገሩት አቶ አትክልት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅት ከመሆኑ አንፃር እንዲነሳለት ለሚመለከተው አካል ማመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ እስካሁንም ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑንም አክለዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የድርጅቱ ቅሬታ ከአምስት ዓመታት በፊት የነበረ ችግር አሁንም ሸክም መሆኑ አግባብ አለመሆኑን የሚናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ባለሥልጣኑ እየሠራ ያለው ሕጉንና መመርያውን ተከትሎ ቢሆንም፣ ከግምት ውስጥ ማስገባት ያለበት ነገር እንዳለም ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ ከኪሳራ የሚወጣበትን አሠራር በመከተል ጥሩ እየሠራና በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ መንግሥት ሳይቀር የሚያውቀው መሆኑን የጠቆሙት አቶ አትክልት፣ መንግሥት የሚቀርብለትን ማስረጃ በመመልከት ጥሩ ድጋፍ እያደረገ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የድርጅቱ ካፒታል ከ3.7 ቢሊዮን ብር ወደ 16 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሎ በነሐሴ ወር 2006 ዓ.ም. እንደ አዲስ መቋቋሙንም አስረድተዋል፡፡
ድርጅቱ በውኃ ሥራ ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ ያለውና ብቃትና ልምድ ያላቸው ሠራተኞች ያሉት በመሆኑ ለአገር ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ፕሮጀክቱም ሆነ ቀደም ብሎ ድርጅቱ የገባው ዕዳ ገንዘብ ስለሚፈልጉ፣ ሁለቱን እያስታረቁና ቀስ እያሉ ከኪሳራ በመላቀቅ ጎዳና ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ከጎናችን ስለሆነ ድርጅቱ በአጭር ጊዜ ከኪሳራ ይወጣል፤›› ሲሉ አቶ አትክልት ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡