Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊመንግሥት በውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ላይ የጣለውን ዕገዳ አነሳ

መንግሥት በውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ላይ የጣለውን ዕገዳ አነሳ

ቀን:

  • ኤጀንሲዎች ለሠራተኞች የደኅንነት ዋስትና የመቶ ሺሕ ዶላር በዝግ ሒሳብ መክፈት ይጠበቅባቸዋል
  • እስካሁን 103 ኤጀንሲዎች ፈቃድ አግኝተዋል

 መንግሥት ለዜጎች ደኅንነት በማሰብ በውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ላይ ለዓመታት ጥሎት የነበረውን ዕገዳ ከማክሰኞ ጥር 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲነሳ ወሰነ።

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ዕገዳው እንዲነሳ ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረቡ የሚታወቅ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከጥር 22 ቀን ጀምሮ ዕገዳው እንዲነሳ መወሰኑን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

ሳዑዲ ዓረቢያ ከአራት ዓመት በፊት በግዛቷ የሚገኙ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን በፀጥታ ኃይሎች እያስገደደች ባስወጣችበት ወቅት ነበር፣ መንግሥት በውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ላይ ዕገዳ የጣለው። በወቅቱ ከ100 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ተገደው የወጡ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን በብዛት ከሚገኙባቸው የዓረብ አገሮች ጋር የኢትዮጵያውያንን መብትና ደኅንነት ማስከበር የሚያስችሉ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችና የሠራተኛ ልውውጥን የተመለከቱ ስምምነቶች ወይም የሕግ ማዕቀፎች እስኪበጁ ነበር ዕገዳው የተጣለው። ይሁን እንጂ ዕገዳው ሕገወጥ ስደትን እንዳባባሰ፣ በአሁኑ ወቅትም በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሳዑዲ ዓረቢያን ለቀው እንዲወጡ በአገሪቱ መንግሥት ተወስኖባቸው፣ ጥቂቶቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ አብዛኞቹ ግን በአሁኑ ወቅት ከሳዑዲ መንግሥት ጋር ድብብቆሽ ውስጥ መሆናቸው ይነገራል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

መንግሥት ሕጋዊ የውጭ ሥራ ሥምሪትን ለዓመታት አግዶ ቢቆይም፣ ሕገወጥ የሥራ ሥምሪቱ ግን ዕገዳው በተጣለባቸው ዓመታት ውስጥ ሲከናወን እንደነበር ማስረጃዎች ያመለክታሉ።

ዕገዳው ተጥሎ በቆዩባቸው ዓመታት መንግሥት ኢትዮጵያውያንን በቤት ሠራተኝነት በብዛት ከሚቀበሉ ከተለያዩ አገሮች ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ሲፈራረም ነበር፡፡ የውጭ ሥራ ሥምሪት የሚመራበት ጥብቅ የሆነ አዋጅም ከሁለት ዓመት በፊት አፅድቋል።

 ይህ አዋጅ ሥራ ፈላጊዎች ማሟላት ስለሚገባቸው መሥፈርቶችና ዝግጅቶች፣ እንዲሁም የግል ሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች ፈቃድ አገኝተው ወደ ሥራ መግባት የሚችሉበትን መሥፈርትና ፈቃድ ካገኙ በኃላ የተጣሉባቸውን ኃላፊነትዎችና ግዴታዎች የሚዘረዝር ነው።

በዚህም መሠረት ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄድ ማንኛውም ሠራተኛ ቢያንስ የስምንተኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀ፣ በሚቀጠርበት የሥራ መስክ አግባብ ካለው የምዘና ማዕከል የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ የያዘ፣ እንዲሁም አሠሪው የሚጠይቃቸውን ሌሎች መሥፈርቶች ማሟላት ይጠበቅበታል።

የግል ሥራ አገናኝ ኤጀንሲ ሆኖ ለመሥራት ሕጋዊ ፈቃድ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ፈቃድ ለማግኘት የሚጠየቀው በግለሰብ ደረጃ ከሆነ አመልካቹ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለውና ከአንድ ሚሊዮን ብር ያላነሰ ካፒታል ሊኖረው እንደሚገባ አዋጁ ይደነግጋል።

አመልካቹ የንግድ ማኅበር ከሆነ የተቋቋመበት ዓላማ በውጭ አገር ሥራና ሠራተኛ የማገናኘት አገልግሎት ለመስጠት ብቻ የተቋቋመ፣ የንግድ ማኅበሩ አባላት በሙሉ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸውና ከአንድ ሚሊዮን ብር ያላነሰ የተዋጣ አክሲዮን ወይም መዋጮ የሚጠየቁ ይሆናል።

በተጨማሪም ከአንድ አገር በላይ ለመሥራት የሚፈልግ ኤጀንሲ ለእያንዳንዱ አገር ፈቃድ ማውጣት ይጠበቅበታል። በተጨማሪም ማንኛውም ኤጀንሲ ለሠራተኞች መብትና ደኅንነት ዋስትና ማስከበሪያ የሚውል አንድ መቶ ሺሕ ዶላር ወይም ተመጣጣኙን የኢትዮጵያ ብር በዝግ ሒሳብ በባንክ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል።

 ይህ ገንዘብ ኤጀንሲዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነቶች ሳይወጡ በሚቀሩበት ጊዜ ሚኒስቴሩ ተቀማጭ ከሆነው የዋስትና ገንዘብ ላይ ወጪ በማድረግ ለተፈለገው ዓላማ የሚያውለው ሲሆን፣ ኤጀንሲው የተቀነሰውን መጠን ገንዘብ በአሥር ቀናት ውስጥ መተካት ይጠበቅበታል፡፡ በውጭ አገሮች የተቀጠሩ ኢትዮጵያውያን የተቀጠሩበትን የሥራ ውል በመጣሳቸው ምክንያት ቀጣሪዎቻቸው የሚያቀርቧቸውን የገንዘብ ክፍያ ጥያቄዎች መሸፈን እንዲቻል፣ የውጭ አሠሪዎች የዋስትና ፈንድ በዚህ አዋጅ መሠረት እንደሚቋቋም ተደንግጓል፡፡

 የፈንዱ መዋጮ የሚሸፈነው ኢትዮጵያዊ ሠራተኛን የቀጠረ የውጭ አሠሪ ለእያንዳንዱ ሠራተኛ 50 ዶላር እንዲከፍል በሕግ ግዴታ የተጣለበት ሲሆን፣ ይህም የውጭ አሠሪዎች የዋስትና ፈንድ ውስጥ ተቀማጭ ይሆናል።

የዋስትና ፈንዱ ጥቅም ላይ የሚውለው በዋነኛነት ውል የጣሱ ሠራተኞች ላይ በአሠሪዎች የሚቀርብ የገንዘብ ክፍያ ጥያቄ ለመሸፈን ቢሆንም፣ እንዳስፈላጊነቱ የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ መግዣና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ ለሚወሰኑ ሌሎች አትራፊና አዋጭ ተግባሮች ሊውል እንደሚችል በሕግ ተደንግጓል።

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ በአዲሱ አዋጅ መሠረት ለመሥራት 722 ኤጀንሲዎች ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የፈቃድ ጥያቄ ያቀረቡ መሆኑንና ከእነዚህ ውስጥ ለ103 ፈቃድ መሰጠቱን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...