Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትኦሮሚያ ሁለት ታላላቅ የውስጥ ውድድሮችን ማራዘሙ ለምን?

ኦሮሚያ ሁለት ታላላቅ የውስጥ ውድድሮችን ማራዘሙ ለምን?

ቀን:

የኦሮሚያ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቅርቡ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች በተፈጠረው ግጭት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ የክልሉ ተወላጆች ገቢ ማሰባሰቢያ ከ200,000 በላይ ተሳታፊዎች የሚሮጡበት ውድድር አዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም፣ ውድድሩ ወደ የካቲት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲራዘም አድርጓል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ለወትሮው በዚህ ወር መጀመርያ ጀምሮ በመደበኛነት ሲያከናውነው የቆየው የመላ ኦሮሚያ ጨዋታዎችም በተመሳሳይ ለአንድ ወር ያህል እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ ክልሉ በተለይ በአትሌቲክሱ ጠንካራ ተፎካከሪዎችን በማፍራት የሚታወቀውን ያህል፣ አሁን ላይ ግን የመቀዛቀዝ አዝማሚያ እየታየበት መሆኑ የሚናገሩ አሉ፡፡ በክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊና የኮሙዩኒኬሸን ዳይሬክተር አቶ ሁሴን ዝናቡ በበኩላቸው፣ የኦሮሚያ ክልል በተለይም በአሁኑ ወቅት ለአትሌቲክሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ስፖርቶች ከፍተኛ ትኩረት እየሰጠ መሆኑ፣ በመሠረተ ልማት ደረጃም ከፍተኛ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን በማስገንባት ላይ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና በሰንዳፋ በኬ አካባቢ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሰጠው መሬት ለዓመታት ሳይለማ ተቀምጧል በሚል በከተማ አስተዳደሩ አማካይነት መሬቱ ለመሬት ባንክ ገቢ እንዲሆን መወሰኑ ይታወቃል፡፡ ሌላው ደግሞ ክልሉ በቅርቡ በአፋር ክልል ይከናወናል ተብሎ ለሚጠበቀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ የመጀመርያዎቹን ዕጩዎች ቀይሮ አዳዲስ ዕጩዎችን ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አቶ ሁሴን ዝናቡን ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኦሮሚያ ክልል ወትሮ የነበረው የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ እየተዳከመ ነው የሚሉ አሉ፡፡ በቅርቡም በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ገቢ ማሰባሰብ በሚል ተይዞ የነበረውና እስከ 200,000 ታዳሚዎች ይሳተፉበታል የተባለው የሩጫ ውድድር ለሌላ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉ ይነገራል?

አቶ ሁሴን፡- የኦሮሚያ ክልል በተለይም ለአገሪቱ አትሌቲክሱ ዋነኛ ግብዓት መሆኑ እውነት ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን አሁን ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ከስፖርቱ መሠረተ ልማት ጀምሮ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ የተለያዩ አደረጃጀቶችና አወቃቀሮች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ ተተኪ ስፖርተኞች በብቃትና በጥራት እንዲፈሩ ክልሉ የተለያዩ አካዴሚዎች ግንባታን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ አንፃር ሲታይ እየተዳከመ ነው የሚለው ተዓማኒነት አይኖረውም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሪፖርተር፡- ከመሠረተ ልማት አኳያ በተጨባጭ በክልሉ ያለውን እውነታ ቢገልጹልን?

አቶ ሁሴን፡- የአምቦ ጎል ፕሮጀክት፣ በአሰላ በቆጂ የሚገኘው የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ አካዴሜና በአሁኑ ወቅት ክልሉ ከፍተኛ በጀት በመበጀት እያስገነባው የሚገኘው የሱሉልታ አካዴሚ ከአገሪቱም አልፎ በሰሜን አፍሪካ አገሮች እንደሚገኙት አካዴሚዎች መጠቀስ የሚችል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሁለት ትልልቅ ውድድሮችን ሰርዛችኋል የሚሉ አሉ?

አቶ ሁሴን፡- አንደኛውና ከ200,000 በላይ ተሳታፊዎች እንዲሳተፉበት በዕቅድ የተያዘው ከሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች ገቢ ማሰባሰቢያ የሚውለው የሩጫ ውድድር ነው፡፡ ውድድሩ በዋናነት በክልሉ አትሌቲክስና በኦሮሚያ አትሌቶች ማኅበር ትብብር የሚዘጋጅ ነው፡፡ ሩጫው ለየካቲት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሩጫው ገቢ ማሰባሰቢያ እንደመሆኑ በቂ ጊዜ ወስዶ ስፖንሰሮችንም ከማሳተፍ አኳያ ለመዘጋጀት በሚል ነው፡፡ ሌላው የመላ ኦሮሚያ ጨዋታ ሲሆን፣ ይህም በዚህ ዓመት በትግራይ ክልል አስተናጋጅነት በመጋቢት ወር የሚካሄደው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ለአንድ ወር እንዲራዘም በመደረጉ ኦሮሚያም ጊዜ ወስዶ ጠንካራ ተፎካካሪ አትሌቶችን ለማፍራት ያመቸው ዘንድ ነው ለአንድ ወር እንዲራዘም ያደረገው፡፡

ሪፖርተር፡- የገቢ ማሰባሰቢያው ውድድር ከክልሉም አልፎ በእህት የክልል ከተሞች እንደሚደረግ የሚናገሩ አሉ?

አቶ ሁሴን፡- በአማራ ክልል በተወሰኑ ከተሞችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ይካሄዳል፡፡ የውድድሩ ስያሜም የኦሮሚያ ታላቁ ሩጫ ነው፡፡ የፕሮግራሙ ዋና ዓላማም ከፌስቲቫል ባለፈ ለወገን ወገን ደራሽ መሆኑን ለማረጋገጥ ያለመ ነው፡፡ በትንሹ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማሰባሰብም ታቅዷል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በቅርቡ የአመራር ምርጫ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ክልላችሁ ቀደም ሲል ያቀረባቸውን ዕጩ ተወዳዳሪዎች በሌሎች ቀይሯል፡፡ ምክንያቱ ይታወቃል?

አቶ ሁሴን፡- እንደሚታወቀው ክልሉ ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቀደም ሲል ያቀረበው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ትልቅ ስም ያላቸው አቶ አንተነህ ፈለቀ ነበር፡፡ ይሁንና ተወካያችን በክልሉ ከፌዴሬሽኑ ጀምሮ እስከ ክለቦች ያላቸው ተሳትፎ ሲታይ አነስተኛ በመሆኑ ማስቀጠል አልተቻለም፡፡ በምትካቸው አቶ ኢሳያስ ጅራ እንዲተኩ ነው የተደረገው፡፡

ሪፖርተር፡- የክልሉ ዕጩ ተወካዮች ቢመረጡ ምን ሊሠሩ እንዳቀዱ የስምንት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን እንዲያዘጋጁና እንዲያስተቹ አድርጓል፡፡ ግብረ መልሱ እንዴት ነበር?

አቶ ሁሴን፡- ክልሉ ዕጩዎቹ ለምርጫ ከመቅረባቸው በፊት፣ ከአገሪቱ እግር ኳስ ነባራዊ እውነታ በመነሳት ቢመረጡ እግር ኳሱን መቶ በመቶ ኅብረተሰባችን ወደ ሚፈለገው ደረጃ ያደርሳሉ ብለን ባናምንም፣ ከቀን ወደ ቀን እየዘቀጠ ያለውን ስፖርት ለመታደግ ግን በተለይ ከታዳጊ ፕሮጀክቶች ጀምሮ ትኩረት በመስጠት ተጠያቂነትና ግልፀኝነት ያለበት ሥርዓት እንደሚዘረጉ እምነታችን ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ባለው ተሞክሮ ዕጩዎች ሲቀርቡ ከቃላት ባለፈ እንዲህ ዓይነት ለቁጥጥርና ለክትትል በሚያመች መልኩ በሰነድ የተረጋገጠ ነገር ስለሌላቸው፣ በተወሰነ መልኩም ቢሆን አካሄዱን መልክ ለማስያዝ በሚልም ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የክልላችን ዕጩዎች ቢመረጡ ካቀረቡት ሰነድ በመነሳት የሠሩትን ነገር መገምገምና መጠየቅ እንዲቻል ለማድረግ ነው፡፡ አሠራሩና ሰነዱ ለሌሎችም ክልሎች ጭምር ግብዓት ይሆን ዘንድ የተዘጋጀም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴሬሽኑ ምርጫ ለሦስተኛ ጊዜ ተራዝሟል፡፡ እንደ ክልል ምንድነው ያላችሁ አስተያት?

አቶ ሁሴን፡- ቀደም ሲልም እንደምንለው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሕጋዊ አሠራሮችን ተከትሎ እንዲሄድ ጽኑ እምነት አለን፡፡ ምክንያቱም የዕጩ ተወዳዳሪዎች አቀራረብና አመላመል ላይ አንዳንድ ቅሬታዎች እንዳሉ ስለምናውቅ ማለት ነው፡፡ ይህንኑ አቋማችንን ለፌዴሬሽኑ በሰነድ በማስደገፍ ጭምር ግልጽ አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከዛሬ 17 ዓመት በፊት ሰንዳፋ በኬ ከተማ አስተዳደር መሬት መውሰዱ ይታወቃል፡፡ ይሁንና መሬቱ ለታለመለት ዓላማ ሊውል አልቻለም በሚል የከተማው አስተዳደር መሬቱን ወደ መሬት ባንክ ገቢ እንዲሆን ማድረጉ ተምቷል?

አቶ ሁሴን፡- ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ መሬቱን ሲወስድ ግንባታውን አከናውኖ አትሌቲክሱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በሚል መሆኑ አያከራክርም፡፡ በመሆኑም የአካባቢው አርሶ አደሮች መሬቱን ሳያንገራግሩ ነው አሳልፈው የሰጡት፡፡ ያም ሆኖ በክልል ደረጃም ባይሆን በከተማ አስተዳደሩ ደረጃ ፌዴሬሽኑ መሬቱን እንዲያለማ ከሁለትና ሦስት ጊዜ በላይ ፌዴሬሽኑን በደብዳቤ መጠየቁ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ሁሉ ሙከራ በኋላ ዕርምጃው መወሰዱ ነው ያለን መረጃ የሚያሳየው፡፡ ክልሉ ለዓመታት ተይዘው መልማት ያልቻሉ የኢንቨስትመንት ቦታዎች ላይ ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንደ ከተማ አስተዳደሩ ፌዴሬሽኑ ስላልሠራ ብቻ ሳይሆን የመሥራት ዓላማም እንደሌለው ነው የሚያምነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ አቅም እንደሌለው በመግለጽ ጉዳዩ መንግሥትን ጨምሮ የሁሉ ክልሎች እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዚህ አኳያ የኦሮሚያ ክልል አቋም ምንድነው?

አቶ ሁሴን፡- እንደ ክልሉ የሰንዳፋ የአትሌቲክስ መንደር ቢለማ ለአገሪቱ ስፖርትና በተለይም ለወጣቱ ትልቅ ሚና ያለው ጉዳይ በመሆኑ እንዲቀየር ፍላጎት የለውም፡፡ ለዚህም ክልላችን በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜን ዕቅድ ለስፖርትና ለወጣቱ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለስፖርትና ለወጣቱ እያወለም ይገኛል፡፡ ፌዴሬሽኑ ስለ ሰንዳፋ አትሌቲክስ መንደር ዓላማውን በግልጽ የማሳወቅና የመንቀሳቀስ ችግር ያለበት ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሲባል እንደተባለው የሁሉም ክልሎች ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የአሳታፊነቱን ሚና መጫወት የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሊሆን ይገባል፡፡ ፌዴሬሽኑ ችግሩ የአቅም ከሆነ እኔ እስከማውቀው ድረስ እስካሁን ከክልሉም ጋር ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ እንደ አጀንዳ አስይዞ መታገዝና መደገፍ በሚችልበት ደረጃ ላይ የሠራው ሥራ የለም፡፡ የሰንዳፋ አትሌቲክስ መንደር የያዘው ቦታ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ለሁለት አሠርታት ያህል ያለምንም ጥቅም ነው ታጥሮ የተቀመጠው፡፡ በእርግጥ በቀጣይ ምን ይሁን? በሚለው በጋራ ውሳኔ የሚኬድበት ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኦሮሚያን ጨምሮ በሌሎችም ክልሎች ለስፖርቱ መዳከም ወጣትና ስፖርት የሚለው አደረጃጀት እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ አደረጃጀቱ በዋናነት ትኩረት የሚሰጠው ወጣት ለሚለው ዘርፍ መሆኑን በምክንያትነት የሚጠቅሱ አሉ?

አቶ ሁሴን፡- ግምቱ ስህተት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በእኛ ክልል ባለው ተጨባጭ ነገር ወጣቱን ብቻውን ከማግኘት ይልቅ ወጣቱን በስፖርቱ ስለምታገኘው ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ለስፖርቱ ነው፡፡ በበጀትም ቢሆን እንደዚያው ነው፡፡ በመሠረታዊነት ግን ሁለቱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው፡፡ ተነጣጥለው የሚታዩ አይደለም፡፡ የበለጠ ውጤታማ መሆን የሚቻለው ሁለቱንም ዘርፎች በጋራ አቀናጅቶ መሥራት ሲቻል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኦሮሚያን ጨምሮ በአገሪቱ ካለው የወጣቱ ድርሻ አኳያ በስፖርቱ ውጤታማ እየሆንን ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ሁሴን፡- በአገር ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶ አካዴሚዎች፣ ወጣት ማዕከላትና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ይገንቡ እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ መሆን የሚችሉ ተተኪዎች ላይ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ ተሠርቷል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ዝንባሌን መሠረት ያደረገ ትኩረት በመስጠት ረገድ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ከመሠረተ ልማት አኳያም ተደራሽነት ላይ ብዙ መሥራት ይጠይቃል፡፡ በኦሮሚያ ከ30 በላይ የወጣት ማዕከላት በከተማና በዞን ደረጃ እንዲሠሩ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ ግንባታዎችም እየተገነቡ ነው፡፡ ይህ ማለት ክልሉ ወጣቱን ጥቅም ላይ ለማዋል እያደረጉ ያለውን ጥረት የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሙያተኞች አንፃርስ?

አቶ ሁሴን፡- ክልላችን በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጥሩ አፈጻጸሞች እንደነበሩ አይቷል፡፡ በሁለተኛ ደግሞ ከነበረው ክፍተት በመነሳት የተሻለ አፈጻጸም በማሳየት ሙያንና ሙያተኛን ያማከሉ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ጭምር ከወረዳ ጀምሮ እስከ ላይ የወጣቶችና ስፖርት መዋቅሮችን በመዘርጋት ለስፖርቱ ከስፖርት ባለሙያተኞች ውጪ ምደባ እንዳይደረግ ለማድረግ ነው ዕቅዳችን፡፡ ይህም ሲባል የባለቤትነት ጉዳይ ግምት ውስጥ በማስገባት ማለት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ስፖርቱ በተለያዩ ስፖርታዊ መድረኮች ላይ የሚታየው የተመልካቾች ሁኔታ፣ መልኩና ይዘቱ እየተለወጠ የውዝግብና የብጥብጥ መድረክ እየሆነ ይገኛል፡፡ ለዚህ መነሻ የሚሉት ይኖራል?

አቶ ሁሴን፡- እንደሚገባኝ ስፖርት ወንድማማችነትንና አብሮነትን ለመስበክ ምቹ መድረክ መሆኑን ነው፡፡ አሁን አሁን ግን ይህ መድረክ ፍፁም ተጥሷል ማለት ይችላል፡፡ ውድ ከሆነው ከሰው ልጆች ሕይወት ጀምሮ ቀላል የማይባል ንብረት መውደም ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ ይኼ መወገዝ የሚገባው ነው፡፡ አደረጃጀቶችን ፈጥሮ በትልቁ ሊሠራበት የሚገባ ሆኗል፡፡ ወጣቶቻችን የስፖርት ትርጉም ሊገባቸው ይገባል፡፡ በተለይ አሁን አሁን አካሄዱ ጥሩ ስላልሆነ ብዙ ነገር መልኩ ከእጅ እንዳይወጣ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...