Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርመፍትሔ አልባው የአዲስ አበባ ቤቶችና የይዞታ ጉዳይ

መፍትሔ አልባው የአዲስ አበባ ቤቶችና የይዞታ ጉዳይ

ቀን:

ከመሬት ይዞታና ከመኖሪያ ቤት ጉዳይ በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ በተለይም በየካ ክፍል ከተማ ያለውን ችግር በተመለከተ፣ ሰሞኑን በአዲስ ቴሌቪዥን የቀረበው ፕሮግራም ነገሩን ለማያውቀው አስገራሚ ሊሆንበት ይችላል፡፡

ችግሩ ለገጠመውና ለደረሰበት ግን የተለመደ ነው፡፡ በተላፈው ፕሮግራም እንደታየው ከሆነ፣ በክፍለ ከተማው ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም. ያላለቀ የመሬትና የቤት ጉዳይ አለ፡፡ 26 ዓመት ሙሉ አንድ ጉዳይ መፍትሔና ፍጻሜ አለማግኘቱ ለግለሰቡ የዕድሜ ልክ ስቃይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥት በየጊዜው መሬትን በተመለከተ ጥሩ መመርያ ያወጣል፡፡ ፈጻሚዎቹ ግን መመርያዎችን በትክክል መረዳት ስላልቻሉ እንደሆነ አይታወቅም ሕዝቡን ማሰቃየታቸውን ቀጥለዋል፡፡

 ነገሩ በየካ ክፍለ ከተማ ላይ የቀረበ ቢሆንም፣ በአዲስ አበባ ከተማ በድፍኑ የሚታይ ችግር ነው፡፡ በተለይ በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሃና ማርያም አካባቢና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወርቁ ሰፈር አካባቢ የሚታየው ችግር እጅጉን የበረታ ነው፡፡ በየጊዜው ሰው ድህነትን በመሸሽ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከየአቅጣጫው ወደ አዲስ አበባ ስለሚፈልስ የቤት ፍላጎት እጅግ አንገብጋቢ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ወደ አዲስ አበባ የሚሰደደው አብዛኛው ሰው ዝቅተኛ ኑሮ ያለው፣ የቀን ሠራተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ በወር 3,000 ብር የማይሞላ ገንዘብ የሚያገኝ፣ ለቤት ኪራይ፣ ለቀለብ፣ ለልብስ፣ ለትራንስፖርት፣ ለሕክምና ወዘተ የሚያወጣው ወጪ ሲታሰብ ለነገው ምን ሊተርፈው እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ በመሆኑም አብዛኛው ሰነድ አልባ ቤት የሚገነባው እንዲህ ዓይነት የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኘው ዜጋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከድህነት በሚደረገው ሽሽት ሳቢያ በርካቶች ለጭንቀት፣ ለሥጋት ብሎም  ለስቃይ የሚዳረጉበት፣ የቤትና የቦታ ችግር (በተለይ ሰነድ አልባዎቹ) የማይፈታ እንቆቅልሽ ሆኖ የሚገኘው ለምንድነው? ቢባል፡-

በመጀመርያ ደረጃ፣ ሰነድ አልባ ቤት እንዳይገነባ በመከልከሉ ነው፡፡ ቦታዎችን በደንብ አስከባሪና በአካባቢው ዘቦች ማስጠበቅ አንዱ ነው፡፡ ለችግርኛ የሚሆን ጊዜያዊ ማደሪያዎችን ማዘጋጀት መፍትሔ በሆነ ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የተገነቡትን ሰነድ አልባም ሆኑ ነባር ቤቶችን ሕጋዊ ማድረግ በተለይም ከብዙ ዓመታት በፊት ተሠርተው የቆዩ፣ የክፍለ ከተሞች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያላቸውና በቅሬታ ወይም በተፈጠረ ስህተት ምክንያት ካርታ እንዲመልሱ የተደረጉ ወይም ከረዥም ጊዜ በፊት ተሠርተው ሕጋዊ ሳይደረጉ የቀሩ ቤቶችና ይዞታዎች በአግባቡ መስተናገድ ነበረበት፡፡

 ይኼ ግን እየተደረገ አይደለም፡፡ ለዚህም ዋነኛ ተጠያቂዎች የክፍለ ከተሞች የመሬት ይዞታ አስተዳደር፣ የሠነድ አልባ ይዞታዎች መስተንግዶ ሠራተኞች ናቸው፡፡ ምክንያቱም የቤትና የቦታ ጉዳይ የሚመለከተው የወረዳና የክፍለ ከተማ ኃላፊዎችን በመሆኑ ነው፡፡

ነገሮች የሚበላሹት፣ ሕዝቡም በቤትና በቦታ ጉዳይ ማለቂያ ወደሌለው ስቃይ የሚገባው በእነዚህ አካላት ነው፡፡ ሰው ችግር ውስጥ የሚገባው የክፍለ ከተማና የወረዳ መሬት አስተዳዳር የግንባታና የሰነድ አልባ ይዞታ መስተንግዶ ሠራተኞች በሚፈጥሩት ስህተት ነው፡፡ ሠራተኞቹ ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡ ችግሩ የራሳቸውም ይሁን የሥራ ባልደረቦቻቸው በይዞታና በቤት ጉዳይ ላይ የተፈጠረን ችግር የማስተካከል ፍላጎት የላቸውም፡፡ ስህተትን በማረም ፈንታ ማጥፋት ወይም ከሰነድ ዶሴ ውስጥ እጅግ ጠቃሚ ሰነዶችን እንዳልባሌ ነገር መጣልና ማጥፋት ከሚፈጽሟቸው ድርጊቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የሚፈጥሩት ስህተት ከታች የተዘረዘሩትን መረጃዎች ከመሬት ይዞታው ጋር ማገናኝት አለመቻል ነው፡፡ እንደ GIS፣ CIS፣ GPS በመሳሰሉት ቴክኖሎጂዎች የታገዘውን መረጃ፣ የቦታውን ልኬት በካሬ ሜትር ለማስቀመጥ ከአውሮፕላን በሚደረግ ቅኝት የተነሳ ፎቶግራፍ አካቶና ቦታው ላይ ቤት ከተሠራም ይህንኑ የቦታ መጠን ቁጥር (ፓርሴል ቁጥር) የሚሰጠው ሲሆን፣ ባለይዞታው ግን ስለእነዚህ መረጃዎች ብዙም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ሥራው ግን እነዚህን መረጃዎች ማጠናቀርን ይጠይቃል፡፡ መረጃዎቹ ቢሮ ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ ባለሙያዎች በአካል ቦታው ድረስ ሄደው ከመሬት ይዞታ ጋር መገናኘት ያለባቸው ሥራ ነው፡፡ ይኼን ማድረግ ለአንድ ይዞታ ቢበዛ 30 ደቂቃ ቢፈጅባቸው ነው፡፡ መፍትሔው ይኼ ይመስለኛል፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸውን የባለይዞታን ፋይልን አስፈላጊዎችን ዳታዎች GIS፣ CIS፣ የመሬት ልኬትና ስፋት፣ የቦታው ፓርሴል ቁጥር ወዘተ. ጽፎና ተፈራርሞ ሰነዱን ከባለይዞታው ጋር መለዋወጥና ይህም ሲደረግ ባለይዞታው እያንዳንዱን የተጻፉፈውን ነገር ስለመረዳቱ ማወቅ ይጠበቃል፡፡ ይህንኑ ካርታ መሥራት ነው፡፡

ሌላው ሰነድ አልባ ቤቶችን የገነቡ ሰዎች በአብዛኛው የከፋ ድህነትና የቤት ችግር እንዳለባቸው ስለሚታሰብ፣ ለረዥም ጊዜ ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎችን ሰነድ ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም ቦታውን ወደ መሬት ባንክ በማስገባት የልማት ተነሺዎች እንዲጠቀሙበት ማድረግ መፍትሔ ሊሆን የሚችል ዕርምጃ ነው፡፡ በአጠቃላይ ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥበት ለማለት እፈልጋለሁ፡፡

(ዘውዱ፣ ከአዲስ አበባ)

* * *

ክብር ለእናቶቻችን!

በኢቢኤስ የማለዳ ኮከቦች ፕሮግራም የተውኔት ተወዳዳሪዎች ሽልማት የገና በዓል ዕለት መተላለፉ ይታወሳል፡፡ በሽልማቱ ሥነ ሥርዓት ላይ አሸናፊ ሆነው የተሸለሙ ተወዳዳሪዎች ከመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት፣ አንጀታቸውን ጨምቀው ትኩስ እንባ እያነቡ ነበር፡፡ የሁሉም ተሸላሚዎች መልዕክት በአንድ ቃል ስለ እናት ውለታና ክብር የሚገልጽ ነበር፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ተመካክረው የመጡ በሚመስል አኳኋን፣ ለዚህ ክብር ያበቃቸው የእናቶቻቸው ጥንካሬ፣ ፍቅርና በጎ አመለካከት እንደሆነ አሳይተውናል፡፡

በዚች ደሃ አገር የፆታ እኩልነት ከቃል አልፎ ወደ ተግባር ባልተቀየረበት  ዘመን፣ እናቶች የኢኮኖሚ ጫናውን ችለው ልጆቻቸውን ለማሳደግና ለወግ ማዕረግ ለማብቃት ያሳለፉትን መከራና እንግልት ፍንትው አድርገው አሳይተውናል፡፡ እናቶቻችን እኛን ለማሳደግ እንደ ሻማ ቀልጠው፣ ለራሳቸው ሳይኖሩ እኛን አኑረው ለዚህ ክብር እንዳደረሱን ተሸላሚዎቹ በአንድ ቃል በለቅሶና ሳግ አቅርበውልናል፡፡

ይኼንን ፕሮግራም በመከታተል ላይ እያለሁ፣ አንድ ልብ የሚነካ ነገር በዓይነ ህሊናዬ ድቅን አለበኝ፡፡ እናቶቻችን እጅግ ፈታኝና መራራ የሕይወት ውጣ ውረድ አልፈው፣ የማይሆነውን ሆነው ይህን ትውልድ ለዚህ አብቅተውታል፡፡ ታዲያ በየቤተ ዕምነቱ ደጃፍ፣ በገበያ መሀልና አደባባይ ቆመው በመሳቀቅና በሐፍረት ስሜት እጃቸውን ለምጽዋት ዘርጋ መለስ የሚያደርጉ እናቶችን ምነው መታደግ አቃተን? በደሳሳ ቤት አቅማቸው ተዳክሞ፣ በበሽታ ተይዘው የሚላስ የሚቀመስ ያጡ እናቶቻችንን መጎብኘት ምነው ተሳነን?

ይኼ የስግብግብና የራስ ወዳድ ስሜታችን ገዝፎ የእናቶቻችንን ውለታ ስለጋረደው፣ አቅመ ደካማነታቸውን ዘንግተን ቁራሽ እንጀራ ነፍገናቸዋል፡፡ በርግጥ እነሱን የሚደግፍና የሚያግዝ የኢኮኖሚ አቅም አጥተን ሳይሆን፣ ግለኝነት ስሜታችን ሸብቦ ቸበርቻቻ ስለበለጥብን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ የእናቶቻችንን ውለታ ዞር ብለን ማሰብና ማስታወስ የሁሉም ዜጋ የውዴታ ግዴታ በመሆኑ፣ እናቶቻችንን በማንኛውም ጊዜና ቦታ እናስባቸው እላለሁ፡፡ ያለፈውን ዘመን መለስ ብለን እናስብ፡፡ ክብር ለእናቶች እላለሁ፡፡

(ፈለቀ የሺጥላ፣ ከአዲስ አበባ)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...