Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አየር መንገዶች ከሚፈቅዱት የመንገደኞች ሻንጣ በላይ የሚይዙ ሙሉ የቀረጥ ነፃ መብት ተጠቃሚ እንደማይሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ነጋዴዎች የተፈቀደውን የቀረጥ ነፃ መብት ለመመዝበር እየሞከሩ ነው ተብሏል

ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን መንገደኞች በተወሰኑ ዕቃዎች ላይ የቀረጥ ነፃ መብት እንዲያገኙ በቅርቡ ከተወሰነ በኋላ የቀረጥ ነፃ መብቱን የመመዝበር ሙከራ በመታየቱ፣ በአየር መንገዶች ከሚፈቀደው የመንገደኞቹ የሻንጣ ክብደት በላይ የያዙ ቀረጥ የመክፈል ግዴታ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የባለሥልጣኑ የቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ጉምሩክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገብረ ሕይወት ገብረ ሥላሴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የገቢ መንገደኞችን እንግልት ለመቀነስ ታስቦ ሰሞኑን የተፈቀደውን የቀረጥ ነፃ መብት መንገደኛ በመሆን ብቻ ንብረቶች በገፍ ማስገባት እንደሚቻል አድርገው ነጋዴዎች ለመመዝበር እየሞከሩ ነው፡፡ ከቅርንጫፉ የጉምሩክ ሠራተኞች ጋር ንትርክ እንደሚፈጥሩም አስረድተዋል፡፡ በርካታ የሚባሉ ነጋዴዎች በዋናነት ዱባይ፣ ባንኮክና ቱርክ በመጓዝ አልባሳትንና ሌሎች ጨርቆችን በጭነት አውሮፕላን ጭምር በማስገባት ለመንገደኞች ነፃ የቀረጥ መብት መንግሥት የፈቀደ በመሆኑ፣ ቀረጥ እንዴት እንጠየቃለን በማለት አተካራ እየፈጠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በቅርቡ ያወጣው የመንገደኞች የቀረጥ ነፃ መብት መመርያ መሠረታዊ ዓላማ፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ኢትዮጵያዊያንን ሻንጣ ለማይረባ ታክስ ሲባል መበርበር ለእንግልት እየዳረገ በመሆኑና የአገሪቱን ገፅታም እያጎደፈ ስለመጣ የተወሰነ መሆኑን አቶ ገብረ እግዚአብሔር አስረድተዋል፡፡

በዚህ መመርያ የሻንጣው የኪሎ መጠን ሳይገለጽ የመንገደኞች ሻንጣ ተብሎ የተቀመጠው አንቀጽ፣ ነጋዴዎች ለመመዝበር እየሞከሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የተጓዦች ሻንጣ ተብሎ ክፍት ሆኖ የተቀመጠውን ሐረግ የመመዝበር ሙከራ ሊኖር እንደሚችል ቀድሞውኑ ግንዛቤ ቢኖርም፣ እንዲህ እንዲቀመጥ የተወሰነው ለጥቂት የኪሎ ግራም ለውጥ መንገደኞች ዳግም እንዳይጉላሉ ታስቦ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የተጓዦች ሻንጣ ማለት አየር መንገዶች በትኬት ሽያጭ ላይ የሚፈቅዱትን ነፃ የሻንጣ ሚዛን መጠን፣ እንዲሁም ከዚህ መጠን በላይ በክፍያ የሚፈቅዱትን የሻንጣ ሚዛን መጠን ብቻ የሚያካትት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የተጓዡ ትኬት የተለጠፈበት ሻንጣና በተጓዡ በእጅ የሚንጠለጠል ሻንጣ ብቻ የቀረጥ ነፃ መብት የመጠቀም ዕድል እንደሚኖራቸው አስታውቀዋል፡፡

የቀረጥ ነፃ መብቱ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ ግን ነጋዴዎች ወደ ውጭ በመጓዝ፣ በጭነት አውሮፕላኖች ጭምር እያስጫኑ የመንገደኞችን የቀረጥ ነፃ መብት ለመጠቀም ሙግት ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ እንደማይቻል ሲገለጽላቸውም የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱን በአቤቱታ ማጨናነቃቸውን፣ ቀረጥ አንከፍልም ብለው ንብረቶቻቸውን ጉምሩክ ላይ ጥለው መሄዳቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ይህ ለገቢ መንገዶች ብቻ የተፈቀደ መብት ነው፤›› ያሉት አቶ ገብረ እግዚአብሔር፣ ‹‹በመንገደኛ አውሮፕላኖች ውስጥ የሚያስተናግዱና ሌሎች የበረራ ቡድን አባላት እንኳን እንደ ተጓዥ ስለማይቆጠሩ የመብቱ ተጠቃሚ አይደሉም፤›› ብለዋል፡፡

በቅርቡ የወጣው ይህ መመርያ በመንገደኞች የሚዘወተሩ ናቸው ተብለው የተለዩ 321 የቁሳቁስ ዓይነቶችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ዕድል ሰጥቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች