Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አገር ሰማንያ አለው እንዴ?

ሰላም! ሰላም! ይኼውላችሁ እኔም በተራዬ ሲጨንቀኝ ሲጠበኝ ጊዜ አንድ ቡቲክ ገብቼ ‹ስኪኒ› ሱሪ ገዛሁ። አገር ተደበላለቀ ነው የምላችሁ። ለነገሩ አገሩም የአገሩ ሰውም ከተደበላለቀ ቆይቷል። ያው የተደባለቀብንና የተደበላለቀብን መለያየት ካልቻልን ድሮስ ምን ልሆን ኖሯል? እና አንበርብር ‹ሲኪኒ› ሱሪ ገዛ ብሎ ሠፈርተኛው ሁሉ ሲያማኝ፣ ገና ምኑን ዓይታችሁ ብዬ ካፖርቴንም አስጠበብኩት። ነገርና ሰው እያደር ሲጠብ ታዲያ እኔ ምን ላርግ? ባይሆን በአለባበስ ልመሳሰላ። አይደለም እንዴ? እና እዚህ ድረስ ያደረሰኝ ብዙ ቢሆንም ያነሳሳኝን ገጠመኝ ላጫውታችሁ። አንድ ወዳጄ በቀደም ቦሌ አካባቢ የሚከራይ ዘመናዊ ሕንፃ ስላለ እንሸቅል ብሎኝ እሄዳለሁ። ሲያገኘኝ ደህና አደርክ ሳይለኝ፣ “አገሪቱ እኮ በቃ ታማ መዳን አቃታት፤” አለኝ። ምን ጉድ ሊያሰማኝ ነው ብዬ አገሪቱን ለማስታወስ ማውጣት ማውረድ ጀመርኩ። ‘አገሪቱ? አገሪቱ? የት ይሆን የማውቃት? መኪና ያጋዛኋት ሴት ትሆን? ወይስ ቤቷን አሻሽጬላት ይሆን? አማቱ ትሆን ምራቱ?’  ጨነቀኝ።

ለራሴ የማስታወስ ችሎታዬ ይኼን ያህል ከከዳኝ መጪዎቹን የብልፅግናና የልማት ዓመታት እንዴት አድርጌ ነው የደላላነት ብቃቴን እያሻሻልኩ ቀናና መልካም አገልግሎት የማበረክተው?’ እያልኩ ራሴን እታዘባለሁ። ኋላ ወዳጄ፣ “አይዞህ አተክዝ አንበርብር። በአንተ ትካዜ ብቻ አትድንም፤” አለኝ። ቢታዘብም ይታዘበኝ ብዬ፣ “እኔ ምልህ አገሪቱ ልትመጣልኝ አልቻለችም፡፡ ማን ናት አገሪቱ?” አልኩት፡፡ ግራ ገባው፡፡ “ስለማን የማወራ መስሎህ ነው? ስለእኔና አንተ አገር ነዋ። እምዬ ኢትዮጵያ. . .” ሲለኝ አንጀቴ እርር። ያልሆነ ነገር ልናረው ብዬ ከአፌ ያስመለሰኝ የባሻዬ ምክር ነው። “አንበርብር ቃላት መሰንጠቁን ተወው። እንኳ ስያሜና ስሜቱ ሊቀናጅ ፀሎቱም እኔና እኔን ሆኗል። ‹ከአባታችን ሆይ› በቀር ሰው እኮ እኛን ማካተት ትቷል፤” ያሉት ትዝ ብሎኝ ነዋ። ግን እረር ብሎ ፈጥሮኝ አረርኩ!

ኋላ ብዙ ነገር አሰብኩ። አንተና አንቺ በተገላበጠበት ዘመን እኔ እንዲህ ብቻዬን በየሄድኩበት ስቆም የምውለው ምን አግብቶኝ ነው? አልኩና ከገጽታ ለውጥ መጀመር እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ ወስኜ ስኪኒ ሱሪ ገዛሁ፡፡ ካፖርቴም በቅርቡ ከቆዳዬ ጋር የተጣበቀ እስኪመስል ጠቦ ይደርሰኛል። እንግዲህ ያኔ በትንሽ በትልቁ አትበድ የሚለኝ ይቀንስ ይሆናል። ትልቅና ትንሽ እብደት ካለ ማለቴ ነው። ዘመኑ በቃ ሁሉን ነገር በመስፈር አስጠምዶን ስማችን ጠፍቶ በኪሎ ሆኗል የምንጠራራው። እውነቴን እኮ ነው። የሚዲያ ሽፋን እጥረት እንጂ ኑሯችን እኮ በሪንግ ያልታጠረ ቦክስ ጨዋታ ሆኖል። እና እዚህ መሀል እኔም፣ እርስዎም፣ አንቺም፣ አንተም አለን፡፡ እንዳልኳችሁ በኪሎ ስለሆነ ጨዋታው አንተና አንቺ እንደ ኪሎአችን ሊገለባበጥ ይችላል።

በቀደም የሆንኩትን ልንገራችሁ። ከዚህ ወዳጄ ጋር ቄራ አካባቢ መጋዘን ልናከራይ ስንሯሯጥ አንድ ታክሲ ብቅ አለ። ሰው አልጫነም። መንደር ለመንደር ይሽሎከለካል። እኛ ደግሞ የቆምንበት ቦታ እንኳን ለመኪና ለእግረኛም በሠልፍ ካልሆነ አያራምድም። ወዲያው ወያላው ብቅ ብሎ፣ “ነፍሴ ትንሽ ፈንጠር በይ እስኪ?” አለኝ። ዞር ብዬ ወዳጄን አየሁት። ከዚያ ወያላው በአገጩ ወደ ወዳጄ እየጠቆመ፣ “ለማለፍ ብቻ ነው። ካላሽቸገርንህ?” አለው። ልዩነቱ ወዲያው ታየኝ። የእኔና የወዳጄ ሥጋ አይወዳደርም። ከእሱ ጋር ትከሻ ለትከሻ ስንቆም ዝሆንና ሰጎን በሉን። ጡንቻም ይበልጠኛል። በዕድሜ ግን የ15 ዓመት ታላቁ ነኝ። ከዚህ በላይ የኪሎ ጨዋታ ምን አለ? ብቻ አይደለም ጨዋታው። ዓይን በሞላና ባልሞላ አሳታፊና ተሳታፊ በሚመረጥበት በዚህ ጎዳና የጋራ መፍትሔ፣ የጋራ መግባባት ብሎ ነገርስ እንዴት ይመጣል? ይኼስ ግራ አይገባም? ነው ለይቶልኛል? የገባው እኔን ግራ ይግባኝ ካለኝ ብቻ እንደ ክፍያ እቆጥርለታለሁ!

የንጭንጭ ካፊያዬን ገታ ላድርግና እስኪ ወደ በዓሉ ልመልሳችሁ። በገና ማግሥት ማንጠግቦሽ ያለልማዷ ሬት ሬት የሚል ቡና አፍልታ ትግተናለች። ባሻዬ ከእነ ልጃቸውና እኔም ተሰባስበናል። “በረካውን ይደግማሉ?” ተባሉ ባሻዬ። ባሻዬ ሲመልሱ፣ “የባህሪውን ተካፋይ አንዴ ቀምሸዋለሁ። እንግዲህ በሦስት የማስረው ምን ብዬ ነው?” ብለው በቅኔ ሲመልሱ ማንጠግቦሽ ሳቋን ለቀቀችው። በሳቋ መሀል ጀበናው ገና በደንብ እንዳልተሟሸ አስረድታ ይቅርታ ጠየቀች። ባሻዬ የሦስትን አንድነት በቡና አሳበው ወደ ሥላሴ ትምህርት ሊገቡ ሲሉ፣ ልጃቸው ተራውን መሀል ገብቶ በአንድነትና በልዩነት አሳቦ ወሬውን ፖለቲካዊ አደረገው። የዘንድሮ ሰው ፈር ሲሰጡት አትሉም? ለነገሩ ሦስቱም የየራሳቸው ዘመን ሰዎች ናቸው። ብቻ የበላነውን ነውና የምንተፋው እንዳማረልን እያጠጋጋን መተንፈስ ተፈጥሮ መሆኑን ልብ በሉልኝ። ይኼን በምን አነሳኸው ብትሉኝ መቼም ጉድ አንድ ሰሞን ነው፣ የሰሞኑን ጉዴን ላጫውታችሁ። አላፊ አግዳሚው ሕፃን አዋቂው ሁሉ በዚሁ የአንድነትና የልዩነት ግብር ተወጥሮ ሲያደርቀኝ ሰነበተ።

ሰው ሁሉ ኅብረት፣ ኅብረት ይለኛል። እኔ ምኑን ሊገባኝ አልቻለም፡፡ “የምን ኅብረት ነው እሱ?” ብዬ ስጠይቅ፣ “ዓደዋን ድል ያደረገው ኅብረት፣ ቀን ቆጥሮ ጊዜ አስልቶ ማይጨውን የተበቀለው ዓይነት ኅብረት፤” ይሉኛል። “እኔ ምለው ግን ሰው መጀመርያ ከገዛ ራሱ ጋር ኅብረት ሳይፈጥር እንዴት ብሎ ነው ከሌላው ጋር ኅብረት የሚኖረው?” ይህን ስል ሁሉም ዳር ዳሩን ይዞራል። ለምን አትሉም? ራሱን ማየት የሚፈልገው ሰው በአቅምም በቁጥርም ቀንሷላ። አንድ ወዳጄ ምን ቢለኝ ሸጋ ነው? “የዘመኑ ሰው በ‹ቻፓ› ዙሪያ ካልሆነ ስለራሱ ማሰብ፣ ራስን ማየት የሚባል ነገር አቅቷል፤” አለኝና ሲቀጥል፣ “በዚህ ጉዳይ ፀሐይ ሳትቀር ትንጨረጨራለች፤” አለኝ። እኔ ደግሞ ፀሐይ ሲል ሰው መስላኝ፣ “ፀሐይ? ፀሐይ?” ማለት። ለካ በፀሐይ ዙሪያ ከሚዞሩ ፕላኔቶች በገንዘብ ዙሪያ የሚሽከረከሩት ፀሐይን አብግነዋት ኖሯል ስላቁ፡፡ ወይ ሰውና ፀሐይ!

በነገራችን ላይ ሽቀላዬን አረሳሁትም። ያልኳችሁን ሕንፃ ሙሉውን አንድ ቱጃር ተከራየው። ሰውዬው ማውራት ይወዳል። ቤቱ አዳማጭ ያለው አልመሰለኝም። ብር ሲበዛ ጆሮ ይቆርጣል እንዴ? መጠናት አለበት እንዳትሉ ብቻ። እናንተም የኮሚቴ ሱስ ያዛችሁ እንዴ? ኧረ ጉድ።  አንድ ሰውዬ ነው አሉ። ቀን ጨለመበት። ቀን ሲጨልም እያሰባችሁ ጨለማውን እንድታልሙት ለእናንተ ልተወው። ጊዜው ደግሞ በአይጥ መርዝ ድው የማለት ፋሽን ተጣብቶታል። ሰውየው የአይጥ መርዝ ሊገዛ ሱቅ ደፍ ላይ ደረሰ። ‹‹ባለሱቅ የአይጥ መርዝ አለህ?›› ይላል። ባለሱቅ መለሰ፣ ‹‹የአይጥ ወጥመድ ብቻ ነው ያለኝ››፣ ሲል በገዛ ፈቃዱ በገዛ ገንዘቡ ሊሰናበት የተሰናዳው ሰውዬ በሳቅ ፈረሰ። እንግዲህ እዚህ ላይ ሰንብች ያላት ነፍስ ለካ በሞላ ገበያ ብቻ ሳይሆን በጎደለም ትሰነብታለች ብሎ፣ ስለጎደሉብን ነገሮች ምሥጋና ማቅረብ የእናንተ ፋንታ ነው።

‹የገበያ ታቦት የለውም› ሲል ፀሐዩ መንግሥታችንም ያለአንድ ምክንያት አይደለም ማለትም ቢሆን ለእናንተው የተወወ ነው። ብቻ እኔ ነገሩን ሳነሳው አንዳንዴ ባላሰብነው መንገድ ለበጎ የሚለወጡልንን ሁኔታዎች በማሰብ ተጠምጄ ስለሰነበትኩ ነው። ታዲያ ሲያቀብጠኝ በቀደም ለባሻዬ ልጅ በጎደሉብን ነገሮች ሳቢያ የምናገኛቸውን በጎ ነገሮች ላመሳክር ባነሳበት ከአፌ ነጥቆ፣ “በል እስኪ በያዘ አፍህ የዶላርና የመብራት መቆራረጥን እንደ ምሳሌ አድርገህ ለበጎ የሆነበትን መንገድ አስረዳኝ?” ሲለኝ አፌ ተሳሰረ። ወዲያው ግን ከየት እንዳመጣሁት አላውቅም፣ “ለምሳሌ ከሥራ ወጥተህ ሊፍት ውስጥ ገብተህ ከአሥረኛ ፎቅ ወርደህ ጨርሰህ አስፋልት ለመሻገር በምትደርስበት እንከን አልባ ደቂቃ ውስጥ አንድ ፍሬን የበጠሰ መኪና ሊደፈጥጥህ ታዞልህ ይሆናል። መብራት ጠፋ። ተረፍክ ማለት አይደል?” ስለው፣ “ዶላሩስ?” ሲለኝ፣ ‹‹እሱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ስንሠለፍ ጠይቀኝ፤›› አልኩታ። ዕድሜ ለኢሕአዴግ ሽወዳን እኮ ጠጥተናታል፡፡

በሉ እንሰነባበት። ከባሻዬ ልጅ ጋር አንድ አንድ ልንል ወደ ግሮሰሪያችን ዘለቅን። ጫጫታው ደርቷል። አንድ ከባሻዬ ዕድሜ በጥቂት አነስ የሚሉ አዛውንት ከአንድ ጽኑ ጠጪ ጋር ያወጋሉ። ወሬያቸው ይሰማናል። “ለመሆኑ አግብተሃል?” አሉት። “አግብቼ ነበር ግን ተፋትቻለሁ፤” አላቸው። አሰብ አድርገው፣ “ቃሉ ሳይኖር ተግባሩ ቀድሞ ምን ታደርጉ? በእናንት አይፈረድ፤” አሉት። “የምኑ ቃል?” አለ አንድ የማያገባው። “እማወራ የሚባለው ቃል ነዋ፡፡ ቃሉ ሳይኖር በተግባር አባወራነቱን የተቀማ ትውልድ ፍቺ ቢበዛበት ይገርማል?” ሲሉት፣ “ተው ተው እንዲያማ አይባልም። ዘመኑ እኮ የእኩልነት ነው፡፡ እማም አባም እኩል ናቸው፡፡ ጊዜው እኮ የመብት እንጂ የገዥና የተገዥ አይደለም፤” አላቸው ደረቱን ነፍቶ። የግሮሰሪዋ ታዳሚ በጠቅላላ ጆሮውን ቀሰረ፡፡ “ተው እንጂ። እኔ ተገዥና ገዥ ነበር፣ አሁንም ይኑር አላልኩም። በመብት ስም ግን እንኳን ቤተሰብ አገር ሲናድ እኔም እናንተም ታዝበናል፡፡ አልታዘብንም?” አሉ ቀና ብለው ዓይን ዓይናችንን እያዩ።

“ልክ ነው. . .” አልናቸው በአንገታችን? “ታዲያስ። እኔ ያልኩት መብት ያለመከባበር፣ መብት ያለመቀባበል አይሠራም ነው። ሳትገነዛዘቡ፣ ሳትተዋወቁና ሳትዋደዱ ቀለበት ታስራላችሁ። ከዚያ ይኼው በየሄዳችሁበት ታሪካችሁ ፍቺ ይሆናል። የበላይና የበታች የለም ትላላችሁ። መልሳችሁ ደግሞ ‘ገዥው ፓርቲ’ እያላችሁ ገሚሶቻችሁ ስታሞግሱት፣ ገሚሶቻችሁ ስትተቹት ትውላላችሁ። እኩልነት፣ እኩልነት እያላችሁ መልሳችሁ እናተው ራሳችሁ ‘ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የለም፡፡ የአንድ ወገን ተጠቃሚነት ብቻ አይሏል’ እያላችሁ ትባላላችሁ። የቤታችሁም የአገራችሁም አባወራ መሆን ስላቃታችሁ ታሪካችሁና ዕድሜያችሁ በፍቺ ደምቋል። እና እኔን ምን አድርግ ነው የምትሉኝ?” ሲሉ ያለልማዱ የባሻዬ ልጅ ጽዋውን አንስቶ፣ “ኧረ አፌ ቁርጥ ይበልልዎ፤” ብሎ ቤቱን በቺርስ ቻቻታ አደበላለቀው። ግን እኔ ምለው ትዳርስ ትዳር ነው። ፍቅር ሲያልቅ አለቀ ነው። አገር ሰማንያ አለው እንዴ? መልካም ሰንበት!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት