Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትወጣቶቹ በፖላንድ ተተኪነታቸውን አሳይተዋል

ወጣቶቹ በፖላንድ ተተኪነታቸውን አሳይተዋል

ቀን:

ቡድኑ ዛሬ አዲስ አበባ ይገባል

ከሐምሌ 12 እስከ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በፖላንድ-ባይድጎሽ ከተማ ሲካሄድ በቆየው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከዓለም ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀቀች፡፡

በውድድሩ ኢትዮጵያውያን ወጣት አትሌቶች ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በወንዶች በአምስት ሺሕ ሜትር በሰለሞን ባረጋ ወርቅ፣ በሴቶች በአምስት ሺሕ ሜትር በቃልኪዳን ፈንቴ ወርቅ፣ በ3000 ሜትር ሴት በበየኑ ደገፈ ወርቅ አምጥታለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአንድ ሺሕ አምስት መቶ አዳነች አንበሴ ወርቅ በማምጣትና ሁለት የብር እንዲሁም አራት ነሐስ በድምሩ አሥር ሜዳሊያን በመሰብሰብ ከዓለም አሜሪካና ኬንያን በመከተል ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡

- Advertisement -

ከአፍሪካ ደግሞ ኬንያን በመከተል ሁለተኛ ደረጃ መጎናጸፍ ችላለች፡፡ 20 ዓመት በታች አትሌቶችን ብቻ በሚያሳትፈው የዓለም አቀፍ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ሜዳሊያ ቁጥር ከኬንያ ቢበልጥም ኬንያ አምስት ወርቅ በማምጣቷ ምክንያት ነበር ተከታዩን ደረጃ ለማግኘት የቻለችው፡፡

በ3000 ሜትር ጌትነት ዋለ ሁለት ጊዜ ወድቆ በመነሳት በኬንያ አትሌት ብልጫ ባይወስደበት ከአፍሪካ የአንበሳ ድርሻውን መውሰድ በተቻለ ነበር፡፡ በ16ኛው የዓለም አቀፍ ከ20 ዓመት በታች ውድድር 1688 አትሌቶች ከ155 አገሮች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በዚህ ሻምፒዮና አሜሪካ በአጠቃላይ 11 ወርቅ፣ 6 ብርና 4 የነሐስ በድምሩ 21 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በአንደኝነት አጠናቃለች፡፡

ጎረቤት አገር ኬንያ ደግሞ አምስት ወርቅ፣ 2 የብርና 2 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን አግኝታለች፡፡ የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ከወንዶቹ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 በተደረገው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአሜሪካ ኦሪጎን ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ 3 ወርቅና 3 የብር ሜዳሊያ በድምሩ 6 ሜዳሊያዎችን በማምጣት ያጠናቀቀች ሲሆን፣ ዘንድሮ አሥር ሜዳሊያ በማምጣት ልዩነቱን በአራት ከፍ ማድረግ ችላለች፡፡

ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ ወጣት ተተኪዎችን ማግኘቷን እንዳሳየ ተነግሮለታል፡፡ አትሌቶቹ በውድድሩ ላይ ልምዳቸውን ለማዳበርም እንደሚረዳቸው ተነግሯል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በውድድሩ ላይ ለታየው የአትሌቶቹ ልምድ ማነስ ኃላፊነቱን ወስዶ በቀጣይ በሥልጠና ማዳበር የሚያስችሉ ሥራዎችን ለማከናወን ቃል ገብቷል፡፡

ወጣቶች በሚሳተፉባቸው ውድድሮች ቀደም ብሎ በአገር ውሰጥና በአፍሪካ ሻምፒዮናዎች ላይ ልምድ እንዲያገኙ ማድረግ የፌዴሬሽኑ ሥራ ነው፡፡ በዚህም አብዛኞቹ አትሌቶች በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ መሳተፋቸው ልምድ እንዲያገኙ የረዳቸው ቢሆንም፣ በተለይ በዚህ ውድድር የመጀመሪያውን የብር ሜዳሊያ ያስመዘገበው ተሬሳ ቶሎሳ 1,500 ሜትር ውድድር ከኋላ ተነስቶ ለማሸነፍ ያደረገው ጥረት በሁሉም አትሌቶች ሊተገበር የሚገባው ነገር እንደሆነ የብዙዎቹ አስተያየት ነው፡፡

ወጣት አትሌቶች 31ኛ የሪዮ ኦሊምፒያድ ሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ ጥሩ ውጤት ማምጣት መቻላቸው አበረታች እንደሆነ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ተናግረዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2008 በፖላንድ በተደረገው ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ሁለት የወርቅ፣ 3 የብርና 5 የነሐስ በደምሩ 10 ሜዳሊያዎች በማምጣት ከዓለም አምስተኛ ሆና ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡ በወቅቱም በ5,000 ሜትር ሴቶች ሱሌ ኡታራ ርቀቱን 16፡15-59 በማጠናቀቅ የመጀመሪያውን ወርቅ ማግኘት ስትችል፣ በወንዶች 5,000 ሜትር በአብርሃም ጨርቆስ አማካይነት ሁለተኛ ወርቅ መገኘት ተችሏል፡፡ ኢትዮጵያ በወጣቶች ዓለም ሻምፒዮና እያስመዘገበች ያለችው ውጤት በተለይ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ከሦስት ወርቅ በላይ ለማምጣት ስትቸገር ትስተዋላለች፡፡ እ.ኤ.አ. 1996 በኦስትሪያ በተዘጋጀው ሻምፒዮና ላይ 4 ወርቅና 2 ነሐስ በድምሩ 6 ሜዳሊያ በማምጣት አሜሪካና ጀርመንን በመከተል ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡

ከዓለም ሦስተኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሐምሌ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ምሽት ይገባል ተብሎ ቢጠበቅም በበረራ መዘግየት ሐምሌ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...