Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየውኃ ዋና አሠልጣኙ አበበ ቢቂላን ያገለለው የሪዮ ኦሊምፒክ ጉዞ

የውኃ ዋና አሠልጣኙ አበበ ቢቂላን ያገለለው የሪዮ ኦሊምፒክ ጉዞ

ቀን:

በዕለተ ዓርብ ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በልዩ ሥነ ሥርዓት ለሚጀመረው 31ኛው ኦሊምፒያድ ላይ የሚሳተፉት የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድኖች ሐምሌ 27 ጀምሮ ወደ ስፍራው ማምራት ይጀምራሉ፡፡

ኢትዮጵያ ከምትሳተፍባቸው ሦስት የስፖርት ዓይነቶች አንዱ በሆነው የውኃ ዋና ውድድር፣ በሴቶች ሐምሳ ሜትር ነፃ ቀዛፊ ራሔል ፍሥሐ፣ በወንዶች መቶ ሜትር ነፃ ቀዛፊ ሮቤል ኪሮስ ወደ ስፍራው እንደሚያመሩ ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

በዚህም መሠረት በመጀመሪያ ጉዞ ሐምሌ 27 ወደ ስፍራው ከሚያመራው ቡድን ጋር ውኃ ዋና አንዱ መሆኑ ታውቋል፡፡ የውኃ ዋና አሠልጣኙ አበበ ቢቂላ ወደ ሥፍራው እንደማያመሩና ቡድኑ ያለ አሠልጣኝ እንደሚጓዝ ተረጋግጧል፡፡

- Advertisement -

እንደ አሠልጣኝ አበበ ቢቂላ ገለጻ ከሆነ ብሔራዊ ውኃ ዋና ፌዴሬሽን ለሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ይረዳው ዘንድ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ለመቅጠር የካቲት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ማስታወቂያ አውጥቶ ነበር፡፡ ባወጣው ማስታወቂያ የምርጫ መስፈርት መሠረት አበበ ቢቂላ ከክልል አብላጫ ድምፅ በማግኘታቸው የብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ መሆናቸው ፌዴሬሽኑ ሚያዝያ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ለጋምቤላ መስተዳድር ትምህርት ቢሮ የላከው ደብዳቤ ያረጋግጣል፡፡

አሠልጣኙ ወደ አዲስ አበባ መጥተው የልምምድ ፕሮግራምና የማረፊያ ክፍል ባይመቻችላቸውም ጉዳዩ እስኪወሰን ድረስ ለረዥም ጊዜ ሲጠባበቁ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አሠልጣኙ የውኃ ዋናውን በመምራት ወደ ሪዮ ለመጓዝ ተስፋ ቢያደርጉም በእሳቸው ቦታ የኢትዮጵያ ውኃ ዋና ስፖርቶች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢንያም ወንድሙ መተካታቸው ተገልጿል፡፡

አሠልጣኙ ጉዳዩን በተመለከተ ለሚመለከታቸው አካላት ባቀረቡት ቅሬታ መሠረት፣ አቶ ቢንያም ቀርተው አሠልጣኙ እንዲተኩ መደረጉን ተናግረው፣ ይሁን እንጂ ብሔራዊ ሆቴል ገብተው ዝግጅታቸውን ለመጀመር ሲጠባበቁ እንደቆዩና ለመዘግየቱ ብዙ ሰበብ ሲቀርብላቸው እንደቆየ አልሸሸጉም፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተሰብስቦ ወደ ስፍራው መጓዝ የሚችለው ሰው ውስን ስለሆነ አቶ አበበ ቢቂላ አዲስ አበባ ላይ ላወጡት ወጪ የአሥር ሺሕ ብር ቼክ እንዲሰጣቸው በማድረግ ወደ ሪዮ ኦሊምፒክ ሳይሆን ወደፊት ካናዳ በሚካሄደው ሻምፒዮና ላይ ቡድኑን ይዘው እንዲጓዙ መወሰኑን የገለጹት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኪሮስ ሀብቴ ናቸው፡፡

እንደ አሠልጣኝ አበበ ገለጻ ከሆነ ወደ ሪዮ ለማምራት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ደብዳቤ እንዲያመጡ መጠየቃቸውንና የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቢሮው ውስጥ ማኅተሙ ላይ ቆልፎበት ወደ ኬንያ ስለሄደ ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ላቀረበለት ጥያቄ፣ ሁሉም ፌዴሬሽኖች ተወዳዳሪ ስፖርተኞችና ልዑካን ቡድን ቁጥር ሲያሳውቁ ወደ ስፍራው የሚጓዘውን አካል ጉዳይን ማስፈጸም ብቻ ሥራው እንደሆነ አብራርቷል፡፡

የብሔራዊ ውኃ ዋና ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የውኃ ዋና ቡድን መሪ አቶ ኪሮስ ሀብቴ ገለጻ ከሆነ፣ አሠልጣኙ ከሪዮ ውጪ የሆኑት ቀደም ብሎ ወደ ስፍራው ለመጓዝ ኮንትራት እንዳልተፈራረሙና ኦሊምፒክ ኮሚቴውም የተጓዥ ቁጥር ውስን መሆኑን በማስታወቁ ከጉዞ እንዲቀር መደረጉን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አሠልጣኝ አበበ ቅሬታቸውን ለወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አምበሳው እንየው ያቀረቡ ሲሆን፣ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ቢኒያም ባይኖርም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትና የቡድኑ መሪ አቶ ኪሮስ ደብዳቤውን እንዲጽፉ ተነግሯቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አቶ ኪሮስ ደብዳቤውን እንዲጽፉ ከአቶ አበበ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቀደም ብለው ያቀረቡትን ቅሬታ ማንሳት እንዳለባቸው እንደተነገራቸው አሠልጣኙ አብራርተዋል፡፡

አቶ አበበ ከፌዴሬሽኑ ገንዘቡን ከተቀበሉ በኋላ ሐሳባቸውን ቀይረው ወደ ሪዮ ሆን ተብሎ እንዳይሄዱ እንደተደረገ አድርገው ‹‹የስም ማጥፋት ዘመቻ›› እንደተደረገባቸው አቶ ኪሮስ አውስተዋል፡፡

አቶ አበበ ፌዴሬሽኑ ሆነ ብሎ ነገሮች እንዲጓተቱ በማድረግ ለሪዮ ኦሊምፒክ ተጠርተው ‹‹ለሌላ ውድድር አሠልጥን›› በሚል ማስተባበያ በደል እየተፈጸመባቸው እንደሆነም አስረግጠው ይናገራሉ፡፡

ምንም እንኳ ከዚህ ውጣ ውረድ በኋላ አሠልጣኙ ወደ ሪዮ ለመጓዝ የሚያስፈልጋቸውን አክሬዲቲሽን ቀነ ገደብ እንደተጠናቀቀ ቢገለጽም፣ ቅሬታቸውን ግን ለወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቅርበው ፍትሕ እየጠበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...