Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ክቡር ሚኒስትር

  [ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር እያወሩ ነው]

  • ምንድን ነው የሚሸተኝ አንተ?
  • ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምንድን ነው የሚገማኝ አልኩህ እኮ?
  • የደላዎት ነዎት እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንዴት ማለት?
  • የት እንደምንኖር ረሱት እንዴ?
  • አዲስ አበባ ነዋ፡፡
  • ምን አሉኝ?
  • አዲስ አበባ፡፡
  • አሮጌ ቆሻሻ ማለትዎት ነው፡፡
  • አንተ ፀረ ልማት፡፡
  • ምን አጠፋሁ?
  • ከተማዋ አሮጌ ቆሻሻ ናት ነው ያልከኝ?
  • እህሳ፡፡
  • ተጠንቀቅ!
  • እውነቴን እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አልገባኝም?
  • ከተማዋ በቆሻሻ ክምር ተውጣ የለ እንዴ?
  • እ…
  • ለዛ እኮ ነው ስሟ ተቀይሯል ያልኩዎት፡፡
  • ወሬማ ትችልበታለህ፡፡
  • ለነገሩ እርስዎ አሮጌ ቆሻሻ ከተማዋን አያቋትም፡፡
  • እንዴት ማለት?
  • ክቡር ሚኒስትር የእርስዎ ሠፈር እኮ ንፅህናው አውሮፓ ወይም አሜሪካ ነው የሚመስለው፡፡
  • አውሮፓንና አሜሪካን በምን አወቅካቸው? ወይስ ሄደህልኝ ነበር የእኔ ኪራይ ሰብሳቢ?
  • ኧረ ድሮ በቴሌቪዥን ያየሁትን አስታውሼ ነው፡፡
  • ድሮ?
  • እህሳ፡፡
  • አሁን ቲቪ ማየት ትተሃል እንዴ?
  • ዕድሜ ለመንግሥት ትቻለሁ፡፡
  • ደግሞ መንግሥት ቲቪ አትዩ አለ?
  • መብራት ከሌለ በምን አያለሁ?
  • በጄኔሬተር ነዋ፡፡
  • ለነገሩ በእሱ ማየት እችላለሁ፡፡
  • አንተ ኪራይ ሰብሳቢ ጄኔሬተር አለህ እንዴ?
  • ኧረ እኔ እየቀለዱ መስሎኝ ነው እንጂ ከየት አምጥቼ ክቡር ሚኒስትር?
  • ዘንድሮ ምን ይታወቃል?
  • ለነገሩ ኪራይ ሰብሳቢዎች በየስብሰባ አዳራሽ ስለማይጠፉ መጠርጠሩ አይከፋም፡፡
  • እና መንግሥት ከለከለኝ ነው የምትለው?
  • በቃ መብራት ብልጭ ድርግም እያለ ሲያስቸግረኝ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፍኩ፡፡
  • የምን ትዕዛዝ?
  • ቲቪዬን እንዳይቃጠል እንዳይከፈት ብዬ ነዋ፡፡
  • እኮ ለምን?
  • ቲቪውን እኮ ቆጥቤ ነው የገዛሁት፡፡
  • ሰው ቆጥቦ ቤት ይሠራል፣ አንተ…
  • ያው እንደ ተረቱ ነዋ የምኖረው፡፡
  • የትኛው ተረት?
  • እንደ ቤትህ እንጂ እንደ ጐረቤትህ አትኑር በሚለው፡፡
  • አሁን የጠየቅኩህን ጥያቄ መልስልኝ?
  • ክቡር ሚኒስትር እንዳልኩዎት እርስዎ አውሮፓ መሰል ሠፈር ስለሚኖሩ ነው፡፡
  • ኒዮሊብራል ሆነህልኛል ልበል?
  • ኧረ በፍጹም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እና ምን እያልከኝ ነው?
  • ከተማው ጠቅላላ ገምቷል፣ ሸቷል፡፡
  • እኮ ለምን?
  • ይኼንን ጥያቄማ እርስዎ ነዎት ሊመልሱ የሚገባዎት፡፡
  • እየሰደብከኝ ነው?
  • ማለት ክቡር ሚኒስትር?
  • እኔ ቆሻሻ ጠራጊ ነኝ፡፡
  • አልወጣኝም፡፡
  • እና ምን እያልክ ነው?
  • ይኸው ከተማው ውስጥ ያለው ቆሻሻ በየቦታው ተከምሯል፣ ለዚያ ነው የሚሸትዎት፡፡
  • እኔ የሸተተኝ መኪናዬ ውስጥ እኮ ነው፡፡
  • መኪናው ውስጥማ ሁለት አይጥ ሞቶ ነው፡፡
  • የምን አይጥ ነው? አይጥ ማርባት ጀመርክ እንዴ?
  • የሚያዋጣ ከሆነማ አይደለም አይጥ ጉርጥም አረባለሁ፡፡
  • እና የምን አይጥ ነው?

   

  [ሹፌሩ ሁለት እግሮቹን ወደ ላይ ከፍ አድርጐ አሳያቸው]

  • እነዚህ አይጦች ናቸው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እነዚህማ እግሮችህ ናቸው፡፡
  • የሚሸትዎት ካልሲዬ ነው፡፡
  • አንተ …፡፡
  • ልክ ነዎት ግን ወድጄ አይደለም፡፡
  • አንተ አሁን የክቡር ሚኒስትር ሾፌር ለመሆን ትመጥናለህ?
  • ለነገሩ የክቡር ደላላ ሹፌር መሆን ነው ያለብኝ፡፡
  • ለምንድን ነው የማትታጠበው?
  • በመንግሥት ችግር ነዋ፡፡
  • አንተ እንድትሸት መንግሥት እጁ አለበት?
  • በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እኮ ምን አድርጐ ነው እንድትሸት ያደረገህ?
  • ውኃ ከልክሎኝ፡፡
  • ምን?
  • ይኸው ውኃ ከጠፋ ሁለት ሳምንቴ በምን ልታጠብ?
  • ክረምት አይደል እንዴ?
  • ቢሆንስ?
  • የዝናብ ውኃ አጠራቅመህ አትታጠብም?
  • እሱን እንዳልጠቀም የመንግሥት እጅ አለበት፡፡
  • ደግሞ ዝናብ የሚያዘንበውም መንግሥት ነው እንዳትለኝ?
  • ይኸው አተት ስለገባ የዝናብ ውኃ መጠቀም አቆምኩኝ፡፡
  • እና ለሁሉ ነገር ተጠያቂው መንግሥት ነው?
  • ታዲያ ማን ነው?
  • ዋናው ችግራችን ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
  • ምንድን ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና ድህነት ናቸው፡፡
  • እኮ እነዚህ የጥቅል ስም አላቸው፡፡
  • ምን የሚሉት?
  • መንግሥት፡፡
  • እውነትም ቀልደኛ ሆነሃል፡፡
  • ምን ላድርግ?
  • ለምን ፊልም አትሠራም?
  • ኑሮ በሚባለው ፊልም ዋነኛ ተዋናይ አይደለሁ እንዴ?
  • በጣም አስቂኝ ሆነሃል፡፡
  • እንዲያው ከሆሊውድ የኦስካር ሽልማት ሳልቀበል አልቀርም፡፡
  • አንተ ባክህ የስካር ሽልማት ነው የሚሰጥህ፡፡
  • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
  • ይኸው ሳትጠጣ ድብን ብለህ የሰከርክ ሰው ነህ እኮ፡፡
  • ኑሮ ነዋ ያሰከረኝ፡፡
  • እና የሸተትኩት ውኃ ስለጠፋ ነው የምትለው?
  • አሁንማ ቢመጣም መጠቀም የምትችል አይመስለኝም፡፡
  • ለምን?
  • የውኃ ክፍያ ሊጨምር ነዋ፡፡
  • አገር ሲያድግ እኮ ሁሉ ነገር ይጨምራል፡፡
  • ለነገሩ እውነትዎትን ነው የእኔም ጨምሯል፡፡
  • ምንህ?
  • ድህነቴ!
  • ካካካ…
  • ምነው ሳቁ?
  • አስቀኸኝ ነዋ፡፡
  • እናንተ ሳቁ፣ እኛ እየተሳቀቅን እንኑር፡፡
  • እኮ አሁን ዋናው ችግሬ ውኃ ነው የምትለው?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለእሱ መፍትሔ አለኝ?
  • ምን ዓይነት ክቡር ሚኒስትር?
  • በሃይላንድ ተጠቀም!

  [የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]

  • ክቡር ሚኒስትር ይኸው፡፡  
  • ምንድን ነው ይኼ?
  • ባለፈው ይዘጋጅ ያሉኝ ሰርኩላር፡፡
  • የምን ሰርኩላር ነው?
  • በአዲሱ በጀት ዓመት ሠራተኞቻችን መከተል ያለባቸውን አቅጣጫ የሚያሳይ ሰርኩላር ነው፡፡
  • ማን አዘዘህ?
  • እንዴ ክቡር ሚኒስትር አዘጋጅ ያሉኝ እኮ ራስዎ ነዎት?
  • ኧረ እኔ አልወጣኝም፡፡
  • ይኸው ያንብቡት፡፡

  [ክቡር ሚኒስትሩ ሰርኩላሩን አነበቡት]

  • አሪፍ ሰርኩላር ናት ባክህ?  
  • አሁን ሲቃወሙት አልነበር እንዴ?
  • በቃ እፈርምባታለሁ፡፡

  [የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ደብዳቤዎች ይዛ ገባች]

  • ምንድን ነው አንቺ?
  • ባለፈው ይጻፉ ያሉኝ ደብዳቤዎች ናቸው፡፡
  • የምን ደብዳቤዎች ናቸው?
  • የምስጋና ደብዳቤዎች፡፡
  • የምን የምስጋና ደብዳቤዎች?
  • ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ላላቸው የውጭ ባለሀብቶች ደብዳቤ ይጻፍ ብለውኝ ነበር፡፡
  • ኧረ እኔ አልወጣኝም፡፡
  • እስቲ ያንብቧቸው?
  • ለነገሩ እነዚህ የእኛ ወዳጆች ናቸው፡፡
  • ስለዚህ ፈርሟቸው፡፡
  • እነዚህን ግን አልፈርምም፡፡
  • እንዴ እነዚህ እኮ ከአሜሪካ የመጡ ከፍተኛ ባለሀብቶች ናቸው?
  • እኔ ለኒዮ ሊብራሊስቶች የምስጋና ደብዳቤ አልጽፍም፡፡
  • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ባለፈው ኩባንያዎቹ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ሲገልጹ በጣም ደስተኛ ነበሩ፡፡
  • ማን እኔ?
  • አዎን ደግሞ ሌሎች መሥሪያ ቤቶች የምስጋና ደብዳቤ እየጻፉላቸው ነው፡፡
  • በቃ አምጪው ልፈርመው፡፡

  [አማካሪያቸው በድጋሚ ቢሯቸው ገባ]

  • ክቡር ሚኒስትር ባለፈው ያቀረብኩት ሪፖርት ላይ አስተያየት እንዲሰጡኝ ነበር፡፡
  • ስማ እያጭበረበርከኝ ነው?
  • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
  • አምጣ እንደምልህ አውቀህ የሰጠኸኝ ለማስመሰል ነው?
  • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት ተቀብለውኝ አስተያየቴን እነግርሃለሁ ብለውኝ ነበር፡፡
  • ዛሬ ተይዘሃል አልኩኝ፡፡
  • መሳቢያዎት ውስጥ ይዩት፡፡
  • መሳቢያዬንም ትበረብርልኛለህ ማለት ነው?
  • ኧረ ሲከቱት ስላየሁ ነው፡፡
  • የት አለ ታዲያ?
  • ያው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እሺ በኋላ እደውልልህና ሐሳቤን እነግርሃለሁ፡፡

  [ከሰዓታት በኋላ አማካሪው ደወለላቸው]

  • ምን ፈልገህ ነው? ምሳም መብላት አልችልም?
  • በኋላ ደውልልኝና ሐሳቤን እነግርሃለሁ ብለውኝ ነበር፡፡
  • የምን ሐሳብ?
  • ሪፖርቱ ላይ ያለዎትን ሐሳብ፡፡
  • መቼ ነው ያልኩህ?
  • ዛሬ፡፡
  • በፍጹም አላልኩም፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ዛሬ ሰላም ነዎት? ማለቴ ጤናዎት…
  • አንተ ዶክተሬ እኮ አይደለህም፡፡
  • እሱማ አማካሪዎት ነኝ፡፡
  • በቃ አትዘባርቅ፡፡
  • እንትናን እየመሰሉኝ መጡ፡፡
  • ማንን?
  • ዶናልድ ትራምፕን!

  [ክቡር ሚኒስትሩ መሥሪያ ቤታቸው ግቢ ውስጥ የወዳደቁ ካኖች አዩና የሕንፃ አስተዳዳሪውን አስጠሩት]

  • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እዚህ ግቢ ድግስ ነበር እንዴ?
  • ለዚያውም ድል ያለ ነዋ፡፡
  • እኔ ሳላውቀው መደገስ ጀመራችሁ?
  • እኛ ደግሰን ሳይሆን ያው አዳራሹ ለሠርግ ተከራይቶ ስለነበር ነው፡፡
  • አዳራሹ ለሠርግ ይከራያል እንዴ?
  • ክቡር ሚኒስትር ቅዳሜና እሑድ አርፎ አያውቅም እኮ፡፡
  • እንዴት ሪፖርት አታደርጉልኝም ታዲያ?
  • ይኼ እኮ እርስዎን አይመጥንዎትም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለማንኛውም የፋይናንስ ኃላፊውን ጥራልኝ፡፡

  [የፋይናንስ ኃላፊው ቢሯቸው ገባ]

  • አንተ ዊኬንድ ላይ አዳራሹን ታከራየዋለህ እንዴ?
  • ባለፈው ይከራይ ባሉኝ መሠረት ሥራ ፈትቶ አያውቅም፡፡
  • ለሠርግ ብቻ ነው የሚከራየው?
  • ኧረ ለግብዣና ለተለያዩ ፕሮግራሞች ይከራያል፡፡
  • አሁን በሥራ ቀን ከአሥራ አንድ ሰዓት በኋላ ማከራየት አለብን፡፡
  • ለምን?
  • ለለቅሶም ቢሆን መከራየት ይችላል፡፡
  • አይ ክቡር ሚኒስትር የቢዝነስ ሰው ነዎት እኮ እርስዎ፡፡
  • በል የአዳራሹን ኪራይ ገቢ ሪፖርት አድርግልኝ፡፡
  • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
  • ሐሳቡን ስላመነጨሁ እወስዳለኋ፡፡
  • ምንድን ነው የሚወስዱት?
  • ኮሚሽን!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

  የትጥቅ  መፍታት ሒደትና የሰላም እንቅፋቶች

  የትግራይ ተራሮች ከጦር መሣሪያ ጩኸት የተገላገሉ ይመስላል፡፡ በየምሽጉ አድፍጠው...

  በሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው

  ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ በክልሎችም ሊቋቋም ነው በቅርቡ ተቋቁሞ ወደ...

  የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚመራና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ተቋም የመመሥረት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ

  የኢንሹራንስ (መድን) ዘርፍን የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...

  ዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን በበይነ መረብ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ

  በሁሉም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሐ ግብሮች የሚመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር! ቀድሜ ቀጠሮ እንዲያዝልኝ ስጠይቅ እንደገለጽኩት በተቋሙ ሠራተኛ ተወክዬ ነው የመጣሁት። እንዴ? አንተ የእኛ ተቋም ባልደረባ አይደለህም...

  [የተቃዋሚ ፓርቲው ትይዩ ሚኒስትር ክቡር ሚኒስትሩ ጋ ደውለው መንግሥት በሙሰኞች ላይ ለመውሰድ ስላሰበው የሕግ ዕርምጃ ሐሳብ እየተለዋወጡ ነው]

  ሄሎ… ማን ልበል? ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ጤና ይስጥልኝ… ማን ልበል? የእርስዎ ትይዩ ነኝ፡፡  አቤት? ያው ፓርቲዬን ወክዬ የፍትሕ ሚኒስትሩ ትይዩ ነኝ ማለቴ ነው፡፡ ኦ... ገባኝ… ገባኝ...  ትንሽ ግራ አገባሁዎት አይደል? ትይዩ...

   [ክቡር ሚኒስትሩ እራት እየበሉ መንግሥትን በሚተቹ ጋዜጠኞች ላይ እየተወሰደ ያለውን ዕርምጃ የተመለከተ መረጃ እየቀረበላቸው ነው]

  ለጋዜጠኞቹ መንግሥትን እንዲተቹ መረጃ የሚሰጧቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው፡፡ እነሱ አይደሉም፡፡ እና የትኞቹ ናቸው? እዚሁ ከተማችን የሚገኙ ምዕራባውያን ናቸው። እንዴት ነው መረጃውን የሚያቀብሏቸው? እራት እያበሉ ነው። ምን? አዎ፣ እራት ግብዣ ይጠሯቸውና መተቸት...