Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየሴቶችና የወንዶች 10,000 ሜትር ዓርብና ቅዳሜ ይካሄዳል

የሴቶችና የወንዶች 10,000 ሜትር ዓርብና ቅዳሜ ይካሄዳል

ቀን:

–  የአባዲ ሐዲስ ዕድሜ እያነጋገረ ነው

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው 31ኛው ኦሊምፒያድ ከተጀመረ ስድስተኛ ቀን አስቆጥሯል፡፡ ከተለያዩ የዓለም አገሮች የተሰባሰቡት ስፖርተኞች በተገኙበት የዘንድሮው የሪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በድምቀት ሲከፈት፣ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በዋናተኛው አቤል ኪሮስ መሪነት ወደ ስታዲየም ሲገባ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

ኢትዮጵያ በወርቃማ ውጤቷ የምትታወቅበት የረዥም ርቀት ሩጫ ከነገ በስቲያ ዓርብ ነሐሴ 6 ቀን በሚካሄደው የሴቶች 10,000 ሜትር ፍጻሜ ውድድር የሚጀመር ሲሆን፣ አዲሷ ኮከብ አልማዝ አያና፣ ገለቴ ቡርቃ እና የሁለት ኦሊምፒኮች ባለድሏ ጥሩነሽ ዲባባ የአገሪቱን ድል እንደሚያስቀጥሉ ይጠበቃል፡፡ በመካከለኛ ርቀት በ800 ሜትር መሐመድ አማን፣ በ1,500 ሜትር ገንዘቤ ዲባባ፣ ዳዊት ሥዩምና በሱ ሳዶ የመጀመርያ ማጣሪያ ውድድራቸውንም ያከናውናሉ፡፡

ቅዳሜ በሚካሄደው የ10,000 ሜትር ወንዶች ፍጻሜም ይገረም ደመላሽ፣ ታምራት ቶላ እና አባዲ ሐዲስ ሲፎካከሩ፣ በእሑዱ የሴቶች ማራቶን ፍጻሜ ትዕግሥት ቱፋ፣ ማሬ ዲባባና ትርፊ ፀጋዬ ይወዳደራሉ፡፡

የዓርብ ተወዳዳሪ አትሌቶች ነሐሴ 3 ቀን ሪዮ የገቡ ሲሆን፣ የቅዳሜና እሑድ ተፎካካሪዎች ነሐሴ 4 ቀን ወደ ሥፍራው እንደሚያቀኑ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

አነጋጋሪው ዕድሜ

የሪዮ ኦሊምፒክ ከመጀመሩ በፊት ኢትዮጵያን በሚወክሉ አትሌቶች መረጣ ብዙ ማከራከሩ አይዘነጋም፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ በረጅሙ ርቀት ካላት ታሪክ ጋር በተያያዘ ትክክለኛውን አትሌት ወደ ሥፍራው ለመላክ ሽኩቻ መፍጠሩ ይታወሳል፡፡

ዛሬ ወደ ሪዮ ከሚጓዙት የአሥር ሺሕ ሜትር ርቀት ተወዳዳሪ አትሌቶች ውስጥ በግንቦት ወር ቻይና ሻንጋይ ላይ በተደረገ የዳይመንድ ሊግ ዓለም አቀፍ ውድድር የተሳተፈው ወጣቱ አባዲ ሐዲስ ተጠቃሽ ነው፡፡ አትሌቱ በዳይመንድ ሊግ ሲሳተፍ በ17 ዓመት ዕድሜ መወዳደሩ ይታወሳል፡፡

ባለፈው ግንቦት በሻንጋይ በተደረገው የ5000 ሜትር ውድድር ላይ 13 ደቂቃ ከ02.49 ሰከንድ በመግባት አራተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል፡፡ በውድድሩ ላይ ያመጣው ሰዓት ከቀድሞ አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለና ኢብራሂም ጄላን የተሻለ ስለነበር ለሪዮ መመረጥ ችሏል፡፡

በዕለተ ቅዳሜ ነሐሴ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በሚደረገው የ10,000 ሜትር ፍጻሜ ውድድር ላይ ይግረም ደመላሽ፣ ታምራት ቶላና አባዲ ሐዲስ ቀዳሚ ተሰላፊዎች ተደርገው ተይዘዋል፡፡ በሻንጋይ 5,000 ሜትር ውድድር 17 ዓመት የሚታወቀው አባዲ አሁን የ19 ዓመት ወጣት ተደርጎ ኢትዮጵያን እንደሚወክላት እየተገለጸ ይገኛል፡፡ ግንቦት ወር ላይ በ17 ዓመት የተወዳደረው አባዲ እንዴት አሁን በ19 ዓመት ተደርጎ ተወስዶ ሊወዳደር ይችላል? የሚለው የብዙዎቹ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማኅበር አይኤኤኤፍ እንደሚያስቀምጠው፣ የ10,000 ሜትር ደንብ ከሆነ በኦሊምፒክ አንድ አትሌት ከ19 ዓመት በታች ከሆነ ውድድር ላይ መሳተፍ እንደማይችል የተለያዩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ለዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጠባባቂ ባልያዘበት የ10,000 ሜትር ውድድር የዕድሜ ማጣራት ተደርጎ አትሌትውን ከውድድሩ ውጪ ሊሆን ይችላል የሚለው ሐሳብ በብዙዎቹ ዘንድ ሥጋት ፈጥሯል፡፡

ፌዴሬሽኑ በበኩሉ በአትሌቱ ላይ የተነሳው የዕድሜ ችግር ከዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ማኅበር ጋር በመነጋገር ተስተካክሏል ሲል በቅደም የሪዮ ዝግጅት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አብራርቷል፡፡

የብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ስለሺ ብስራት ለሪፖርተር ከሪዮ በማኅበራዊ ድረ ገጽ እንደተናገሩት ከሆነ፣ አባዲ በ19 ዓመት እንደተመዘገበና መቶ በመቶ ውድድር ላይ እንደሚሳተፍ ከስፍራው አረጋግጠዋል፡፡

የረዥም ርቀት አሠልጣኝ ቶሌራ ዲንቃ አትሌቶቹ ለውድድሩ በቂ ዝግጅት እንዳደረጉ ተናግረው ስለ አባዲ የተነገረው የዕድሜ ጉዳይ ፌዴሬሽኑ ከአይኤኤኤፍ ጋር ተነጋግሮ መፍትሔ ላይ እንደደረሰ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ካላት የረዥም ርቀት ውጤት አንፃር በዚህ ወቅት አንደዚህ ያልተጣሩና መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች በመነሳታቸው ብዙዎችን ቅር አሰኝቷል፡፡ በተለይ በአሥር ሺሕ ሜትር ኢትዮጵያ በእንግሊዛዊው ሞፋራህ የተወሰደባትን ብልጫ ስፖርት ቤተሰቡን እንዲሁም የቀድሞ አትሌቶችን ያስቆጨ ክስተት ነበር፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ወቅት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሚከተለው መንገድ በተደጋጋሚ ችግር ሲስተዋልበት ይታያል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በቡድን ውስጥ ልምድ ያላቸውን አትሌቶች እንዲሁም ተተኪ አትሌቶችን አጣጥሞ ለውድድር መዘጋጀት ዋነኛ ሥራ እንደሆነ ባለሙያዎች በተለያየ አጋጣሚ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

ኢትዮጵያ በምታደርጋቸው ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ከዕድሜ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግርና መስተጓጎል ሲደርስ ይስተዋላል፡፡ በዚህም መሠረት ዘንድሮ ደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ላይ በተደረገው የወጣቶች ሻምፒዮና ላይ ትክክለኛ ዕድሜ ያላቸውን አትሌቶች በቴክኒካል ባለሙያዎች ባለመስተካከሉ 19 አትሌቶች ከኤምባሲ ሳይፈቀድላቸው ቀርቶ አራት አትሌቶች ብቻ ተስተካክሎላቸው ወደ ውድድሩ ማምራታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ቀሪዎቹ 15 ተወዳዳሪዎች ግን በሌሎች ተተክተው ወደ ስፍራው ቢያመሩም፣ ዘጠኙ አትሌቶች ደርባን ላይ ባልተለመደ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ በዚያው መቅረታቸው ይታወሳል፡፡ ለዚህም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በአግባቡ አትሌቶችን ለውድድር ያለመ ቅርብ ችግር እንደሆነ ይነገራል፡፡ በመጨረሻም ምንም እንኳ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የአባዲን ጉዳይ ከዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ማኅበር ጋር ተነጋግሬያለሁ ቢልም ልምድ ያላቸው አትሌቶችን በተጠባባቂነት እንኳን ይዞ ባለመጓዝ ቅሬታ ያስነሳ ጉዳይ ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...