Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ችላ የተባለው የካፒታል ገበያ

ተዛማጅ ፅሁፎች

እ.ኤ.አ. ግንቦት 18 ቀን 2012 ላይ በዓለም ትልቁ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ ፌስቡክ የአክሲዮን ገበያውን ለመጀመርያ ጊዜ መቀላቀሉ ይፋ ተደረገ፡፡ እርግጥ ነው ፌስቡክ ከዚያ በፊት የኩባንያውን አክሲዮን መሸጡ አልቀረም፡፡ የኩባንያው ትልቁ ድርሻ ያለውና የፌስቡክ መሥራች ማርክ ዙከርበርግ እ.ኤ.አ. ከ2012 በፊትም ቢሆን እንደ ጎግል ላሉ ኩባንያዎች የተገደበ የአክሲዮን ሽያጭ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን 2012 ላይ ፌስቡክ በተወሰኑ ባለአክሲዮኖች ባለቤትነት ሥር መቆየት እንደማይችል፣ ይህም በተገደበ ሁኔታ እየሸጠ የቆየው አክሲዮን ከ500 ባለአክሲዮኖች በላይ ሊያስጨምረው እንደማይችል በመረዳቱ ነበር፡፡ የአሜሪካን ሴኩሪቲስ ኤንድ ኤክስቼንጅ ኤጀንሲ ባወጣው መመርያ መሠረት ፌስቡክ አክሲዮኑን ለሕዝብ ክፍት ማድረግ ያለበት ደረጃ ላይ ደርሶም ነበር፡፡ ምንም እንኳን የኩባንያው መሥራች ፍላጎት ባይሆንም ፌስቡክ ለሕዝብ አክሲዮን ክፍት ለማድረግ ዝግጅቱን ጀመረ፡፡

ኩባንያው በይፋ የአክሲዮን ሽያጭን ለሕዝብ ክፍት ሊያደርግ መሆኑ ከተሰማ በኋላም የዓለም የሚዲያ ተቋማትና የፋይናንስ ተንታኞች የፌስቡክ አክሲዮን አንዱ በምን ያህል የመሸጥ ተስፋ እንዳለው፣ ኩባንያው ከሽያጩ ምን ያህል ካፒታል ማግኘት እንደሚችልና የኩባንያው የገበያ ዋጋ በምን ያህል ሊጨምር እንደሚችል መላምታቸው መስጠት ጀመሩ፡፡ ኩባንያው ሊሸጠው ያሰበው ወደ 400 የሚጠጋ አክሲዮን አንዱ ቢያንስ እስከ 45 ዶላር ሊያወጣ እንደሚችል ተገመተ፡፡ አጠቃላይ የኩባንያው አክሲዮን ሽያጭ በዚያው ዋጋ መሠረት ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያወጣል ተባለ፡፡

እንደተገመተው ባይሆንም በመክፈቻው ዕለት የፌስቡክ አክሲዮን ከ43 እስከ 38 ዶላር ድረስ ባለው ዋጋ ተሸጠ፡፡ በዚህም መሠረት ኩባንያው በገበያ ያቀረባቸው ከ400 በላይ የሚሆኑ አክሲዮኖች ተሸጠው ሲያልቁ በጥሬው ከ16 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለመሥራቾቹ ማስገኘት ቻለ፡፡ በመሆኑም ዋናው መሥራች ዙከርበርግ በፎርብስ ቢሊየነር ዝርዝር ውስጥ መግባትና በአንዴ ወደላይ መመንጠቅም ቻለ፡፡

ይህ የካፒታል ገበያ ትሩፋት ዛሬ ላይ በዓለም ቁጥር አንድ የግል ዘርፉ ካፒታል ማሰባሰቢያ መሣሪያ ነው፡፡ ነገር ግን የአክሲዮን ንግድ ብቸኛ አክሲዮን ሻጭ ኩባንያዎች አይደሉም፡፡ እንደውም አንድ ኩባንያ ለመጀመርያ ጊዜ አክሲዮን ለሽያጭ ሲያቀርብ ፈጥነው አክሲዮኖች የሚቀራመቱት ትልልቅ የኢንቨስትመንት ባንኮች፣ የጅምላ የካፒታል ነጋዴዎች (ኢንቨስተሮች) መሆናቸው ይነገራል፡፡ ይህም በዋነኝነት ከኩባንያው እጅ የተገዙት አክሲዮኖች እንደገና ለአነስተኛ ኢንቨስተሮች ስለሚሸጡ፣ ከሽያጩም ጠቀም ያለ ትርፍ ስለሚገኝ ነው፡፡

ይህ የአክሲዮን ገበያን ሁለት ገጽታዎችን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ የመጀመርያው ማለትም እንደ ፌስቡክ መሰል ኩባንያዎች ለመጀመርያ ጊዜ ለገበያ የሚያቀርቧቸው አክሲዮኖች ግብይት የሚፈጸምበት ማለትም የመጀመርያ ደረጃ የአክሲዮን ገበያ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከኩባንያዎቹ አክሲዮኖችን የገዙ ኢንቨስተሮች እርስ በርስ ወይም ከሌሎች ኢንቨስተሮች ጋር የሚያደርጉት በሁለተኛ ደረጃ የአክሲዮን ገበያነቱ ይታወቃል፡፡

በዓለም ታዋቂ የሆኑት የስቶክ ኤክስጅ ገበያዎች በተፈጥሯቸው ሁለተኛ ደረጃ የአክሲዮን ገበያ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ በአሜሪካ ያለው የኒውዮርክ ስቶክ ኤክስቼንጅ፣ የናስዳክ ኤክስቼንጅ (የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አክሲዮን ግብይት የሚፈጸምበት) እንዲሁም ከአውሮፓ እንደ ለንደን የስቶክ ኤክስቼንጅ ገበያዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ገበያዎች በዓመት በቢሊዮኖች የሚቆጠር አክሲዮን ሽያጭ የሚደለል ሲሆን፣ ልምድ ያላቸውና በአክሲዮን ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ደላሎችም ደንበኞቻቸውን ወክለው የአክሲዮኖች ንግድ ሲያከናውኑ ይውላሉ፡፡

በመጀመርያና በሁለተኛ ደረጃ የአክሲዮን ገበያዎች መካከል ያለው ዋነኛ ልዩነትም ሁለተኛው ደረጃ ገበያ በተደራጀ የገበያ መሠረተ ልማት የሚፈጸም መሆኑ፤ የመጀመርያ ደረጃ ደግሞ ገበያው ኩባንያዎች አክሲዮናቸውን ለማስተዋወቅ ከሚያዘጋጁዋቸው ፕሮግራሞችና የማስተዋወቅ ሥራዎች ባለፈ የተደራጀ የገበያ ቦታና መሠረተ ልማትን የማይጠይቅ መሆኑ ነው፡፡

ለግሉ ዘርፍ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ለሚጫወተው ለተደራጀ የአክሲዮን ገበያ ኢትዮጵያ ባዳ ሆና ከቆየች በርካታ አሥርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን እ.ኤ.አ. 1950 የተመሠረተው የአዲስ አበባ፣ የአክሲዮን ንግድ ማኅበር በአፍሪካ ሁለተኛውና ዕድሜ ጠገብ ገበያ ነበር፡፡ በብሔራዊ ባንክ አደራጅነት የተመሠረተው የአዲስ አበባ ሼር ዲሊንግ ግሩፕ በወቅቱ አገር በቀል የነበሩ የአክሲዮን ኩባንያዎች የአክሲዮን ይዞታቸውን በስፋት የሚሸጡበት ማዕከልን ከመፍጠር ባሻገር የተለያዩ የአክሲዮን ንግዱን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሕጎችንና ስታንዳርዶችን ማጎልበት ችሎም ነበር፡፡

የደርግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመምጣቱና አብዛኛው የግል ዘርፍ ተዋናዮች ከመክሰማቸው በፊት በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የሚባሉ ኩባንያዎች ሳይቀሩ ባለአክሲዮን ኩባንያዎች እንደነበሩ ይወሳል፡፡ በተለይ እንደ አዲስ አበባ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ቄራዎች ድርጀት፣ ጠርሙስ ፋብሪካ፣ ኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ፣ ኤችቪኤ ኢትዮጵያ፣ ተንዳሆ እርሻና ሌሎች እ.ኤ.አ. ከ1960 እስከ 1974 ባለው ጊዜ ውስጥ ባንድም ሆነ በሌላ መንገድ አክሲዮን የሸጡ ኩባንያዎች እንደነበሩ መዛግብት ያሳያሉ፡፡

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ ግን ተዳክሞ የነበረው የአክሲዮን ገበያ በኢትዮጵያ ደግሞ ማንሰራራት ጀመረ፡፡ በተፈጠረው አጋጣሚ ቀዳሚ ተጠቃሚ መሆን የቻለው በማደግ ላይ ያለው የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ነበር፡፡ አሁን ላይ 16 የሚሆኑት የግል ባንኮች ሙሉ ለሙሉ ባለአክሲዮን ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ ምናልባትም በትርፋማነትና ኮርፖሬት ገቨርናንስ ረገድ ጠንካራ አቋም ላይ ከሚገኙ ተቋማት ግንባር ቀደም መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡

በወቅቱ በግል ዘርፉ የሚንቀሳቀሱ የንግድ ማኅበረሰቦች እንደሚሉት፣ በአክሲዮን የመደራጀት ዕድል የነበራቸው በአብዛኛው ባንኮችና የኢንሹራንስ ድርጅቶች ናቸው፡፡ የአክሰስ ሪል ስቴት መሥራችና የቀድሞው ቦርድ ሊቀመንበር፣ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ  ይህንን እውነታ በደንብ ያስታውሱታል፡፡ ‹‹ቀደም ሲል በአክሲዮን የመደራጀት ፈቃድ የተሰጠው በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ላሉት ኩባንያዎች ብቻ የነበረ ቢሆንም፣ ኋላ ላይ ግን ቀስ በቀስ በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ተቋማት ወደ አክሲዮን ገበያው መቀላቀል ጀመሩ፤›› የሚሉት አቶ ኤርሚያስ፣ ይህ ሁኔታ መንግሥትም ሆነ የአክሲዮን ገበያ ተዋንያኑ ያላስተዋሉት ችግሮችን ይዞ መምጣቱን ያስረዳሉ፡፡

‹‹የፋይናንስ ዘርፉ የብሔራዊ ባንክ ጠንካራ ቁጥጥር የሚያርፍበት ዘርፍ በመሆኑ ወደ ሥራ የገቡት ኩባንያዎች፣ ያለፉት ሃያ ዓመታት ጉዞ ትርፋማና ጥሩ የሚባል ነው፤›› ይላሉ፡፡ ከፋይናንስ ዘርፉ ውጪ ያሉት የአክሲዮን ማኅበራትን በተመለከተ ግን አዳጋች ሁኔታ ውስጥ የገቡት እንደሚበዙ፣ ይህም ከፋይናንስ ዘርፉ ውጪ ያሉት የአክሲዮን ማኅበሮች ተቆጣጣሪም ተመልካችም ማጣታቸው የፈጠረው ችግር መሆኑን አቶ ኤርሚያስ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በሌላው ዓለም ወደ አክሲዮን ገበያው መግባት በጣም ትልቅ ውሳኔ የሚጠይቅ ነገር ነው፤›› የሚሉት አቶ ኤርሚያስ፣ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አክሲዮን ገበያ የሚያወጡ ኩባንያዎች ማለፍ ያለባቸው መሰናክሎችና ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች ጠንካራ መሆኑ፣ አክሲዮን ገዢዎች ከኪሳራ እንዲጠበቁ ያስችላቸዋል ሲሉ ይከራከራል፡፡

በእርግጥም እንደ ፌስቡክ ያሉ ኩባንያዎች ወደ አክሲዮን ገበያው ከመግባታቸው በፊት ጥሩ ስምና ዝና ያላቸው ኩባንያዎችም ቢሆኑ፣ ለመጀመርያ ጊዜ አክሲዮኖችን ለገበያ ሲያቀርቡ ሊያሟሉ የሚገባቸው መስፈርትን ማሟላት ግድ ይላቸዋል፡፡ እንደ አሜሪካ ባሉ አገሮች ኩባንያዎች ወደ አክሲዮን ገበያው (ኢኒሽያል ፐብሊክ ኦፈሪንግ (IPO) ብለው የሚጠሩት ሒደት) ሲገቡ በቅድሚያ ሊያስቡበት የሚገባው ጉዳይ ቢኖር የራሳቸውን የውስጥ የኩባንያ የቤት ሥራ መጨረስ ስለመሆኑ ባለሙያዎች ያትታሉ፡፡ ከዚህ በጥቂቱ ብቃት ያለው የአስተዳደርና ባለሙያዎች ቡድን መያዛቸውን ማረጋገጥ፣ ተቀባይነት ያለው የአካውንቲንግ መርህ ተከትሎ የተሠራ የኩባንያው ኦዲት ሪፖርት መያዛቸውን፣ ከአክሲዮን ገበያው የሚመጡ ግፊቶችን መቋቋም የሚችል አቅም መገንባታቸውን ማረጋገጥና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

እንደ ባለሙያዎች ገለጻ፣ የአክሲዮን ገበያን መቀላቀል የውስጥ ጉድን እንደማጋለጥ ይቆጠራል፤ በመሆኑም ጉድን አጽድቶ መጠበቅ አማራጭ የሌለው ነገር ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ኩባንያዎች በአብዛኛው ወደ ገበያ በሚወጡበት ሒደት የሚያካሂዳቸው የኢንቨስትመንት ባንክ ወይም የባለሙያዎች ቡድን መቅጠር ይኖርባቸዋል፡፡ ኢንቨስትመንት ባንኮቹ ኩባንያው ሊሸጠው ያሰበው አክሲዮን ተስማሚ የገበያ ዋጋ ምን ያህል ስለመሆኑ የራሳቸውን ዳሰሳ አድርገው ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡

የአክሲዮን ዋጋ ከመወሰን ውጪ ኩባንያው ከባንኩ ጋር በመሆን የኩባንያውን የወደፊት ተስፋ የሚያመላክት ኢንቨስትመንት ፕሮስፔክተስ የተሰኘ ዶክመንት ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ዶክመንት አክሲዮን ለመሸጥ እየተዘጋጀበት ያለው ኩባንያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ተጋላጭነትና ተስፋዎችን መግለጽ የሚጠበቅበት ሲሆን፣ በኋላ ላይ በአገሪቱ የሴኩሪቲና ኤክስቼንጅ ኤጀንሲ አማካይነት ዶክመንቱ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑ ይመረመራል፤ በመጨረሻም ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች ተሟልተው ሲገኝ ሽያጩ ይፈቀዳል፡፡

እንደ አቶ ኤርሚያስ ገለጻ፣ ይህ ዝርዝር አካሄድና ስታንዳርድ በሁለት እግራቸው ለመቆማቸው አጠራጣሪ የሆኑ ኩባንያዎች የአክሲዮን ገበያ ውስጥ ገብተው ኢንቨስተሮችን እንዳያደናግሩና እንዳያከስሩ ትልቅ ሚና እንዳለው መታዘብ ይቻላል፡፡ ‹‹የተቀመጡትን መስፈርቶች ያላሟሉ ኩባንያዎች IPO መሸጥም ሆነ በአክሲዮን ገበያው ላይ መመዝገብ ይቸገራቸዋል፤›› የሚሉት እኚሁ የቀድሞ የኢንቨስትመንት ባንኪንግ ባለሙያ፣ በኢትዮጵያ ይህንን መሰል ሥርዓትና መስፈርት ያለመኖሩ ለአክሲዮን ኩባንያዎች ውድቀት ብሎም የአክሲዮን ገዢዎች ለኪሳራ የሚዳርግ መሆንም አቶ ኤርሚያስ ያስረዳሉ፡፡

ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በኢትዮጵያ በትንሹ ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች መሸጣቸውን የሚያወሱት ደግሞ አቶ ያሬድ ኃይለመስቀል የዋይኤችኤም የኢንቨስትመንት የአማካሪ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ አቶ ያሬድ ማብራሪያ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ፋይናንስ ዘርፉ ገቢ የተደረገ የአክሲዮን ግዥ ወደ 29 ቢሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ ይህ የንግድ ልውውጥ የተከናወነው በካፒታል የመጀመርያ ደረጃ ገበያ አማካይነት ነው፡፡ ከተደራጀ የአክሲዮን ማኅበር ገበያ (ሁለተኛ ደረጃ ገበያ) የሚለየው ደግሞ ራሱ አክሲዮን ሻጩ ኩባንያ ከባንኩ ጋር በመሆን በሚያዘጋጁት ሮድ ሾው ላይ በቀሰቀሱት መሠረት የሚፈጽሙት ሽያጭ መሆኑ ነው፡፡

የመጀመርያ ደረጃ የአክሲዮን ገበያ ከሞላ ጎደል ለትልልቅ ተቋማትና ኢንቨስተሮች እንዲሁም አክሲዮኖች በጅምላ ለሚገዙ ድርጅቶች የሚሸጥ ሲሆን፣ አክሲዮኖቹን በጅምላ የሚገዙ ተቋማት በተዘዋዋሪ ለተደራጁ የአክሲዮን ገበያዎች ማለት በስቶክ ኤክስጄንጆች ላይ በመውጣት እርስ በርስ ይገበያያሉ፡፡

ምንም እንኳን አክሲዮን ባለቤት የሆኑ ኩባንያዎች በስቶክ ኤክስጄንጅ ላይ በሚደረገው ሁለተኛ ደረጃ የንግድ ልውውጥ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ባይኖራቸውም፣ በእነሱ ስም ያሉ አክሲዮኖች ሲሸጡና ሲለወጡ በገበያው ተለዋዋጭነት ዋጋቸው ከፍና ዝቅ ሲል በተዘዋዋሪ የኩባንያዎቹን ዋጋ አመላካች ስለመሆኑ ባለሙያዎች ያትታሉ፡፡

የመጀመርያ ደረጃ የካፒታል ገበያው በኢትዮጵያ ያለቁጥጥርም ቢሆን እየተከናወነ መሆኑን ባለሙያዎች የሚስማሙበት ቢሆንም፣ የመጀመሪያ ደረጃ ገበያው ያለ አባሪ (ሁለተኛ ደረጃ ገበያ) እስከመቼ እንደሚዘልቅ ግን አጠያያቂ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ሁለተኛ ደረጃ የአክሲዮን (የካፒታል) ገበያ ባለፉት ሃያ ዓመታት በኢትዮጵያ መመሥረት ለምን አልተቻለም? የሚለው ጥያቄ ሰሞኑን በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ተነስቶ የንግድ ማኅበረሰቡን ቀልብ የሳበ ውይይት ተደርጎበት ነበር፡፡ በዕለቱ ውይይት ሐሳባቸውን የገለጹት አቶ ያሬድም ቢሆኑ መነሻ ያደረጉት በንጉሡ ዘመን ብቅ ማለት ጀምረው የነበሩትን የአክሲዮን ኩባንያዎችና በወቅቱ ይንቀሳቀስ የነበረው አዲስ አበባ የኤክስቼንጅ ማኅበርን ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1960 የአክሲዮን ንግድ እንቅስቃሴ በኋላ በኢትዮጵያ የተደራጀ የአክሲዮን ገበያ ለማቋቋም የተደረገ ጥረት የለም ማለት አይደለም የሚሉት አቶ ኤርሚያስ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በአዲስ አበባ ቻምበርና በአቶ ኤርሚያስ በኩል እንኳን ተጀምረው ያልተሳኩ የአክሲዮን ገበያ የማቋቋም ጥረቶች ነበሩ፡፡ በተለይ 1990 ዓ.ም. ላይ አዲስ አበባ ቻምበር አዘጋጅቶ በነበረው አንደ ‹‹የካፒታል ገበያ ተስፋ በኢትዮጵያ›› በተሰኘ ስብሰባ ላይ የተጠነሰሰ ፕሮጀክት ተጠቃሽ መሆኑን አቶ ኤርሚያስ ያስታውሳሉ፡፡

ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት ከአሜሪካ ወደ አገራቸው የተመለሱት አቶ ኤርሚያስ በተለይ በቻምበር ስብሰባ ላይ ተናጋሪ ሆነው ሲቀርቡ በአሜሪካ ባካበቱት የኢንቨስትመንት ባንኪንግ ልምድ መነሻነት ነበር፡፡ በስብሰባው የታደሙ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የአቶ ኤርሚያስን ገለጻ ተከትሎ በዚያ አዳራሽ ውስጥ በተሰበሰቡ ሰዎች የሚደገፍ የአክሲዮን ገበያ የማቋቋም ጥረት እንዲጀመር ተወሰነ፡፡

እንደ አቶ ኤርሚያስ ገለጻ፣ በስብሰባው የአክሲዮን ገበያ የማቋቋሙን ሒደት የሚመራ የበላይ ኮሚቴ ከመደራጀቱም በላይ፣ በቀጣዮቹ ሳምንታት በአፋጣኝ ወደ ሥራ ገብቶ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹እኔና በአቶ ታዲዮስ አገረወርቅ የሚመራው ኢስት አፍሪካን ኢንቨስትመንት ሴኩሪቲስ የተሰኘው የማማከር ድርጅት አስፈላጊ የዶክመንት ዝግጅት ሥራውን ማቀላጠፍ ጀመርን፤›› የሚሉት አቶ ኤርሚያስ፣ አባላት የሆኑ ተቋማት የ50,000 ብር መዋጮ በማድረግ በገንዘብ አቅም ጠንካራ የሆነ ፕሮጀክትና ቢሮ የማቋቋም መንገዱን ጀምረውት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ነገር ግን ከዝግጅት መጠናቀቅ በኋላ ካውንስሉ በይፋ የአክሲዮን ገበያ የማደራጀት ሥራውን ለመጀመር ሲንደረደር፣ አንድ ያልተጠበቀ ነገር አጋጠማቸው፡፡ ‹‹ፕሮጀክቱን በይፋ ለማስጀመር ያለመው ካውንስሉ የወቅቱን የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር አቶ ሱፊያን አሕመድን በክብር እንግድነት ጋበዘ፤›› የሚሉት አቶ ኤርሚያስ፣ ምላሹ ያልተጠበቀ ነበር ይላሉ፡፡ ‹‹የተጀመረው የአክሲዮን ገበያ ምሥረታ ሕገወጥ እንደሆነ ተነገረን፤›› ይላሉ አቶ ኤርሚያስ፡፡ በኋላ ላይ ግን መንግሥት ተቆጣጣሪ አካል አደራጅቶ እስኪጨርስ ድረስ እንዲታገሱ ተነግሯቸው የፕሮጀክቱን ዶክመንቶቹ ወደ መደርደርያ ከመለሷቸው ሃያ ዓመታት መቆጠራቸውን አቶ ኤርሚያስ ያብራራሉ፡፡ ‹‹በጣም የሚገርመው ጉዳይ በቅጡ ቁጥጥር በማይደረግበት ሁኔታ የመጀመርያ ደረጃ የአክሲዮን ሽያጭ በተፈቀደበት አገር ላይ እንዲሁም ኢንቨስተሮችና አክሲዮን ገዢዎች በዚህ ምክንያት ገንዘባቸውን እያጡ፣ የራሱ የሆነ ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት ያለው ሁለተኛ ደረጃ ገበያን (አክሲዮን ኤክስቼንጅ ገበያን) መከልከል ለምን አስፈለገ?፤›› ሲሉ የሚከራከሩት አቶ ኤርሚያስ፣ በቀረው ዓለም ‹‹ያልተለመዱ›› አሠራር መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

የሆነ ሆኖ ከሃያ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ሐሳቦችን ያንሸራሸረው ስብሰባ ላይ ወረቀት ያቀረቡት አቶ ያሬድ በበኩላቸው፣ ያለፉት ታሪኮች እንዳለ ሆነው አሁን ባለበት ሁኔታ በኢትዮጵያ የተደራጁ የአክሲዮን ገበያ ፍላጎት አለ ወይ? የሚለውን ጥያቄ አንስተው ጥናት አካሂደዋል፡፡

እንደ አቶ ያሬድ ገለጻ፣ በመጀመርያ ደረጃ ገበያ ላይ ያለው ቁጥጥር አልባነት በሁለተኛ ገበያ መስፋፋት ሊሻሻል የሚችልበት ዕድል በጣም ሰፊ ነው፡፡ ‹‹አሁን በገበያ ውስጥ አክሲዮናቸውን ለገበያ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ከሚሸጡት አክሲዮን በስተጀርባ ያለው ኩባንያቸውን በተመለከተ የሚለቁት መረጃ ፈጽሞ እውነት ያልሆነና የተጋነነ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው አክሲዮን ለመጀመርያ ጊዜ የሚሸጡ ኩባንያዎች ደረጃውን የጠበቀ የኢንቨስትመንት ፕሮስፔክተስ ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ይህን የሚቆጣጠር ባለመኖሩ የተጋነኑና አጓጊ ትርፍ እንዳላቸው የማይገልጹ ኩባንያዎች ትንሽ መሆናቸውን አቶ ያሬድ ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በቅርብ ጊዜያት ይፋ የሚሆኑ የአክሲዮን ሽያጮችን ተከትሎ በአብዛኛው ኢንቨስተር የሚረባረበው ከዚያ አክሲዮን በስተጀርባ ‘ማን እንዳለ’፣ ‘የአደራጆቹ ተዓማኒነት ምን ያህል እንደሆነ’ ጥናት በማድረግ ላይ ተጠምዶ መሆኑን አክለው ያብራራሉ፡፡

በሌላ መልኩ የአክሲዮን አደረጃጀት ሥርዓቱን በተመለከተም በአሁኑ ወቅት ያለው ሥርዓት ኢንቨስተሮችን በከፍተኛ ደረጃ ለምዝበራ የሚያጋልጥ መሆኑንም አቶ ያሬድ በጥናት የዳሰሱት ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ከስድስት እስከ 12 በመቶ የሚሆነው በአክሲዮን ግዢ የተሰበሰበው ገንዘብ በተለምዶ ኢትዮጵያ ውስጥ አክሲዮን እየሸጡ ያሉት ኩባንያዎች ገና ጀማሪ ኩባንያዎች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የሚውለው፣ ለማደራጃ ወጪ መሸፈኛ ነው፤›› የሚሉት አቶ ያሬድ፣ ይህ በራሱ ኢንቨስተሩን ምን ያህል ለምዝበራ ተጋላጭ እንደሚያደርገው የሚያሳይ መሆኑን ያትታሉ፡፡

ነገር ግን በኢትዮጵያ በአብዛኛው አክሲዮን ሽያጭ ላይ የሚገኙት ኩባንያዎች አዳዲስ የመሆናቸውን ጉዳይ ፈጽሞ የሚቃወሙት አንዱዓለም ጥላዬ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ አቶ አንዱዓለም የማክሮ ኢኮኖሚክስ ባለሙያ ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ እንደ ባህል እየተያዘ የመጣውን ጀማሪ ኩባንያዎች ብቻ አክሲዮን የመሸጥ ጉዳይ ስህተት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ወደ ገበያ ገብቶ ያልተፈተነ የኢንቨስትመንት ሐሳብ ይዞ የተነሳ ኩባንያ ወደ አክሲዮን ገበያ መግባት አይችልም፤›› ያሉት ባለሙያው፣ በሐሳብ ደረጃ ያለ ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ድጋፍ የሚደረግባቸው ይህንኑ በሚሠሩ እንደ ቬንቸር ካፒታሊስቶችና ኤንጅል ኢንቨስተሮች ባሉ ተቋማት መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡ ይህም የተደራጀ የአክሲዮን ገበያ ቢቋቋም ሊቀረፍ የሚችል ችግር ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ለአቶ አንዱዓለም ዋናው የተደራጀ የአክሲዮን ገበያ ያለመኖሩ ክፍተት መገለጫ በኩባንያዎች ካፒታል የማግኘትና ያለማግኘት ጥያቄ ዙሪያ አይደለም፡፡ ‹‹ከሌላው በተሻለ ኩባንያዎች ርካሽ የካፒታል አቅርቦት በብድር መልክ ያገኛሉ፤›› የሚሉት አቶ አንዱዓለም፣ ዋናው ጉዳት በደሃውና በደመወዝተኛው ላይ የሚንፀባረቅ ነው ይላሉ፡፡

የአቶ አንዱዓለም ዕይታ የሚያጠነጥነው የተለያየ የገበያ ደረጃ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ገንዘባቸውን የሚቆጥቡበት የቁጠባ መሣሪያ የመኖሩና ያለመኖሩ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ‹‹አሁን ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ውስን የቁጠባ መሣሪያዎች ብቻ ያሉ ሲሆን፣ በተለይ በዝቅተኛ ገቢ ደረጃ ላይ ላሉ ማኅበረሰብ ክፍሎች ከባንክ ቁጠባ የዘለለ ሌላ የቁጠባ መሣሪያ የለም፤›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡ በተቃራኒው የተሻለ የገቢ ደረጃ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ደግሞ እሴት ላይ ሳይቀር ኢንቨስት በማድረግ ቁጠባቸውን አትራፊ እንደሆነ ማስቀጠል ይችላሉ ሲሉ አክለው ይከራከራሉ፡፡ ‹‹የባንክ ቁጠባ ደግሞ ከዋጋ ግሽበት ልኬቱ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ወለድ የሚከፍል ሲሆን፣ ይህም ማለት ዝቅተኛ ገቢ ላለው ቁጠባው ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋ እያጣ፣ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ደግሞ እየጨመረ እንደሚሄድ ማየት ይቻላል፡፡››

እንደ አቶ አንዱዓለም ከሆነ አክሲዮን ገበያ ያለመኖር ለዚህ ዓይነቱ የገቢ አለመመጣጠን እየሰፋ መሄድ ዓይነተኛ ምክንያት እንደሚሆን ግልጽ ነው፤ ‹‹ይህም ደሃ ተኮር ፖሊሲ ለሚያራምድ መንግሥት ተመራጭ አቅጣጫ አይደለም፤›› ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

አቶ ኤርሚያስ እሸቱ የአፍሪካ ሪነሳንስ ቴሌቪዥን ሰርቪስ ዋና ሥራ አስኪያጅና የቀድሞው የምርት ገበያ ድርጅት ኃላፊ በበኩላቸው፣ የተደራጀ የአክሲዮን ገበያ ያለመኖሩ እያደረሰ ያለው ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ቢኖር የሚሰጠው ጥቅም ግን በእጅጉ የላቀ መሆኑን ነው የሚያሰምሩበት፡፡ በአንድ መልኩ ከግል ይዞታ ወደ የጋራ የአክሲዮን ይዞታ የሚሸጋገሩ ኩባንያዎች በአንድም ሆነ በሌላ በኩል የኮርፖሬት ገቨርናንሳቸውን ማሻሻል ግዴታ ይሆንባቸዋል የሚሉት አቶ ኤርሚያስ እሸቱ፣ ይህም የሕዝብ ባለቤትነት በራሱ የአስተዳደር ጥራትን ማስጠበቅ ግዴታ እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡

ከዚያ ባለፈ የተደራጀ የአክሲዮን ገበያ በዋነኝነት የአክሲዮን ፍላጎትን በእጅጉ የሚጨምር ሲሆን፣ የተደራጀ ገበያ በመኖሩ መተማመን የሚሰማቸው ኢንቨስተሮች ቁጥር እየጨመረ ስለሚመጣ መሆኑን ይገልጻሉ አቶ ኤርሚያስ፡፡ በሌላ በኩል የተደራጀ የአክሲዮን ገበያ መንግሥት ከካፒታል ገበያው የሚያገኘውን የታክስ ገቢ በእጅጉ የሚጨምርበት አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ጠቅሰው ይከራከራሉ፡፡

ጥቅምና ጉዳቶቹ በተመለከተ የተለያዩ ባለሙያዎች የተለያየ ነገር ቢያነሱም ለዘመናት በመንግሥት በኩል በአንክሮ የሚነሳው ጉዳይ የአክሲዮን ገበያን የመቆጣጠር አቅምን መፍጠር ያለመቻሉ ነው፡፡ የመቆጣጠር አቅም አልጎለበተም የሚለው ፍራቻ ግን ሪፖርተር ያወያያቸው ባለሙያዎች በብዛት ሊቀበሉት የከበዳቸው ይመስላል፡፡ አቶ ያሬድን በተመለከተ መንግሥት ከድሮም ጀምሮ ይዞት የመጣው የአክሲዮን ገበያን የመቆጣጠር ፍራቻ በእጅጉ የተጋነነና ከእውነታው የራቀ መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡ ‹‹በኒውዮርክ የስቶክ ኤክስቼንጅና በመሳሰሉት የዓለም አቀፍ የካፒታል ገበያዎች ላይ በፍጥነት የሚበሩና የሚጠሩ ኢንዴክሶች እንዲሁም ቁጥሮች ተቋማቱ በጣም ውስብስብ ተግባር የሚያከናውኑ ሊያስመስላቸው ይችላል፤›› የሚሉት አቶ ያሬድ፣ አሁን ባለው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅም ተፈላጊ የሆነው በጣም ዝቅተኛው የአክሲዮን ማገበያያ ማዕከል መሆኑን፣ ይህንን ለመቆጣጠርም ሆነ ለማስተዳደር የተለየ ብቃትን እንደማይጠይቅ ያሰምሩበታል፡፡፡

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የአክሲዮን ገበያ ካላቸው ጥቂት አገሮች ተርታ የምትሰለፍ መሆኗን በመጥቀስ፣ በአፍሪካ ያልተለመደ የምርት ገበያን ዓይነት ተቋም መቆጣጠር ከተቻለ የአክሲዮን ገበያን መቆጣጠር አይቻልም ማለቱ ውኃ የማይቋጥር ክርክር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

እርግጥ ነው በምርት ገበያ ቆይታቸው አቶ ኤርሚያስ እሸቱ የምርት ገበያ መሠረተ ልማትን በመጠቀም አክሲዮንም (በሁለተኛ ገበያ ደረጃ) ሆነ መንግሥት እየተዘጋጀበት ያለውን የቦንድ ሁለተኛ ደረጃ ገበያን ለማገበያየት ፍላጎት አሳይተው እንደበር ይነገራል፡፡ ነገር ግን በብሔራዊ ባንክ በሐሳብ ደረጃ ተይዞ ያለው የሁለተኛ ደረጃ የቦንድ ገበያ ጉዳይም ወደፊት ፈቀቅ ማለት አለመቻሉም ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች