Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ክቡር ሚኒስትር

  [ክቡር ሚኒስትሩ በሪዮ የሚካሄደውን የማራቶን ውድድር ቤታቸው ለመመልከት ቴሌቪዥን ከፍተው ቁጭ ሲሉ ሚስታቸው መጡ]

  • ምን ልታደርግ ነው?
  • ልመለከት ነዋ፡፡
  • ምን?
  • ቲቪ ነዋ፡፡
  • ዛራና ቻንድራን?
  • ዛሬ የአገር ጉዳይ ነው ባክሽ፡፡
  • ምንድን ነው የአገር ጉዳይ?
  • ማራቶን ላይ ነዋ፡፡
  • ምን?
  • ዛሬ የኦሊምፒክ መጨረሻ ነው፡፡
  • እና ማራቶን ቁጭ ብለህ ልታይ?
  • አዎ ምነው?
  • ከሁለት ሰዓት በላይ ነው የሚፈጀው፡፡
  • ነገርኩሽ እኮ የአገር ጉዳይ ነው፡፡
  • ወይ አገር?
  • ደግሞ ምን ሆንሽ?
  • አይ ስለአገር ታስባለህ ወይ ብዬ ነዋ?
  • እንዴት አላስብም?
  • ሥራህ ለአገር የምታስብ አይመስልማ፡፡
  • እና ለማን ነው የማስበው?
  • ለራስህ ነዋ፡፡
  • እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለሁ እንዴ ታዲያ?
  • ረስቼው ነህ ለካ?
  • ይኼን ፖለቲካሽን እዚያው፡፡
  • እናንተው ናችሁ እኮ ይህን ፖለቲካ ያስተማራችሁን፡፡
  • በቃሽ አልኩኝ እኮ፡፡
  • ግን እውነት ለአገር የምታስቡ ከሆነ እንደዚህ ለምን ታደርጋላችሁ?
  • ምን አደረግን?
  • ይኸው በኦሊምፒክ እንኳን ተዋረድን አይደል እንዴ?
  • በምንድን ነው የተዋረድነው?
  • የላካችሁት ዋናተኛ ማለቴ በላተኛ ባለፈው አዋረደን፡፡
  • እሱ እኮ ለገጽታ ግንባታ ነው የተላከው፡፡
  • ይኼ ቀልዳችሁ እኮ ነው ሕዝቡን የሚያስቆጣው፡፡
  • የምን ቀልድ ነው?
  • በሩጫ ራሱ እየተዋረድን አይደል እንዴ?
  • እንዴት ነው የተዋረድነው?
  • በፊት እኮ በወርቅ ነበር የምንታወቀው?
  • አሁንስ ቢሆን ወርቅ በወርቅ አይደለን እንዴ?
  • የምን ወርቅ?
  • የአገሪቷ ወርቅ እየወጣ አይደል እንዴ?
  • እሱስ ቢሆን ግለሰቦች እንጂ መቼ ሕዝቡ ተጠቀመበት?
  • ዋናው ጥያቄ እሱ አይደለም፡፡
  • ታዲያ ምንድን ነው?
  • ግለሰቡ ልማታዊ ነው ወይስ ኪራይ ሰብሳቢ ነው? የሚለው ነው፡፡
  • ሕዝቡ እኮ የሚያምፀው ለዚህ ነው፡፡
  • እንዴት?
  • እኔ ስለኦሊምፒክ ወርቅ ሳወራ አንተ ስለአገሪቱ ወርቅ ታወራለህ፡፡
  • እ…
  • ቀኝ ስትባሉ ግራ፡፡
  • በይ በይ ተይ፡፡
  • እሺ ማራቶኑን እንይ፡፡
  • ሯጩ ምን እያደረገ ነው?
  • ጉድ ጉድ ጉድ ተመለከትከው?
  • ምን እያደረገ ነው?
  • እየተቃወመ ነዋ፡፡
  • ሪዮም ተቃውሞ አለ እንዴ?
  • ኢትዮጵያ ያለውን ተቃውሞ ደግፎ ነው እንጂ፡፡
  • ታዲያ ለምንድን ነው እጁን ከጭንቅላቱ በላይ ያጣመረው?
  • የተቃውሞ ምልክት ነዋ፡፡
  • ኢሕአዴግን ኤክስ አድርጉት እያለ ነው ማለት ነው?
  • እህሳ፡፡
  • እኛው ትኬት ቆርጠን ልከነው እኛኑ ይቃወመናል?
  • ምን ያድርግ?

  [ክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው ሪሞቱን ቲቪው ላይ ወረወሩት]

  • ተው እንጂ፡፡
  • በጣም ነው ያቃጠለኝ፡፡
  • ለምንድን ነው የምትቃጠለው?
  • በዓለም አቀፍ ደረጃ ነው እኮ ያዋረደን፡፡
  • ታዲያ ቲቪው ምን ያድርግህ?
  • ቲቪው ራሱ ሽብርተኛ ነው፡፡
  • ይኼ እኮ ነው ችግራችሁ፡፡
  • ማለት?
  • አታዳምጡም፡፡
  • ይኼንንማ ማዳመጥ አያስፈልግም፡፡
  • እና ምን ማድረግ ነው የሚያስፈልገው?
  • መዳመጥ!

  [ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዳያስፖራ ደወለላቸው]

  • ኪኪኪ …
  • ምን ያስቅሃል?
  • በአደባባይ ተዋረዳችሁ እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ማን ነው ያዋረደን?
  • ሩጫውን አላዩትም እንዴ?
  • ቲቪዬን ሰበርኩት እኮ፡፡
  • ለምን ሰበሩት?
  • ሲቃወም አይቼ ተናድጄ ነዋ፡፡
  • ያን ቲቪ ሰበሩት?
  • ኪራይ ሰብሳቢ ቲቪ ነው፡፡
  • ምን አሉኝ?
  • ቲቪው ኪራይ ሰብሳቢ ነው፡፡
  • ኪራይ የሚሰበስቡት እርስዎ ነዎት እንጂ ቲቪውማ ምን አደረገ?
  • እንዲያውም ሽብርተኛ ቲቪ ነው፡፡
  • እና 250 ሺሕ ብር የገዙትን ቲቪ ሰበሩት?
  • ምን ላድርግ?
  • እና ደግመው ሊገዙ ነው?
  • ታዲያ ኢቢሲ በምን አያለሁ?
  • በጣም የገረመኝ ደግሞ ኢቢሲ ነው፡፡
  • ምን አደረገ?
  • ሁለተኛ ወጥቶ የሯጩ ስም እንኳን አይጠራም?
  • የዚህ ፀረ ልማት ስም፣ በልማታዊ ቲቪያችን ስሙ ሊጠራ?
  • ይኼ እኮ ነው ችግራችሁ?
  • የምን ችግር?
  • አታዳምጡም፡፡
  • ማንን ነው የማናዳምጠው?
  • ሕዝቡን ነዋ፡፡
  • እ…
  • አሁን እኮ ቁጣው ገንፍሎ በአደባባይ ወጣ፡፡
  • ሕዝቡ ከዚህ በላይ ምን እንድናደርግለት ነው የሚፈልገው?
  • ምን አደረጋችሁለት?
  • ግድብ፣ ባቡር፣ መንገድ፣ ኧረ ስንቱ?
  • ራሳችሁን አታታሉ፡፡
  • ምን?
  • እስከ መቼ ራሳችሁን እያታለላችሁ ትኖራላችሁ?
  • እ…
  • ሯጩ ግን ጉድ ሠራችሁ?
  • መግቢያውን ይፈልግ፡፡
  • አልመጣም ብሏል እኮ፡፡
  • ቢመጣማ የሚጠብቀውን ያውቃል?
  • ምን ልታደርጉት?
  • እንሰባብረዋለና፡፡
  • የሚቀጥለው ኦሊምፒክ ማን ይወዳደራል?
  • ራሱ ነዋ፡፡
  • በምን?
  • በፓራ ኦሊምፒክ፡፡
  • እሱም ይኸው እንደሚሆን አውቆ ቀርቷል፡፡
  • አመለጠን፡፡
  • ወደፊት ግን ምን ልታደርጉ ነው?
  • እንዴት?
  • አምናችሁ ሯጮቹን ትልኳቸዋላችሁ?
  • እሱም አለ ለካ?
  • በዚሁ ባለማዳመጣችሁ ከቀጠላችሁ፣ በድጋሚ መዋረዳችሁ አይቀርም፡፡
  • ከዚህ በኋላማ የምናደርገውን እናውቃለን፡፡
  • ምን ልታደርጉ?
  • ከሯጮቹ ጋር አብረን እንልካለን፡፡
  • ማንን?
  • ፌዴራል!

  [የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር አርፍዶ ሊወስዳቸው መጣ]

  • ምን ሆነህ ነው ያረፈድከው?
  • ዛሬ ያው ፆም መፍቻ ነው ብዬ ነዋ፡፡
  • እና ምን ስታደርግ ነበር?
  • ክቡር ሚኒስትር ሥጋው ሥጋ እንዳይመስልዎት፡፡
  • የእኔ ኪራይ ሰብሳቢ?
  • እውነት ሥጋ እንዳይመስልዎት?
  • ማለት?
  • ሽንጥ ቢሉ፣ ዳቢት ቢሉ፣ ሻኛ ቢሉ…
  • እኔ ጠፋሁ?
  • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ጭራሽ በሬ ነው ያረድክልኝ?
  • ክቡር ሚኒስትር በሬ ቢሉ በሬ ነው እንዴ?
  • ከየት አባህ አምጥተህ ነው?
  • ባለፈው እርስዎ ለፆም መያዣ በሬ አረድኩ ሲሉኝ ቅናት ይዞኝ ነበር፡፡
  • እና አሁን ኪራይ ሰብስበህ በሬ አረድክልኝ?
  • አይ ጮማ፡፡
  • እሺ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር መጀመሪያ ዱለቱን፡፡
  • እሺ፡፡
  • ከዛ ጥሬ ሥጋውን፡፡
  • እሺ፡፡
  • ከዛ ደግሞ ጥብሱን…
  • እ…
  • በቃ በአዋዜና በሰናፍጭ…
  • አስጐመጀኸኝ እኮ፡፡
  • ቁርስ አልበሉም እንዴ?
  • ኧረ በልቻለሁ፡፡
  • በቃ ውጬ ውጬ ውጬ ነው የመጣሁት፡፡
  • ምን?
  • ምራቄን!

  [የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]

  • ክቡር ሚኒስትር አዩት?   
  • ምኑን?
  • መግለጫውን፡፡
  • የምን መግለጫ ነው የተቃዋሚዎች ነው?
  • ኧረ የኢሕአዴግን፡፡
  • እሱንማ እኔው አይደል እንዴ የማወጣው፡፡
  • አልመሰለኝም፡፡
  • እንዴት?
  • ከባድ መግለጫ ይመስላል፡፡
  • ማለት?
  • ሙሰኛ ባለሥልጣናት ሊገመገሙ ነው፡፡
  • ምን?
  • ግምገማ ልትቀመጡ ነው፡፡
  • እ…
  • ምነው ደነገጡ?
  • እስቲ የደም ብዛቱን መድኃኒት ስጠኝ፡፡
  • እንኩ፡፡
  • እሺ፡፡
  • ከግምገማው በኋላ ሹም ሽር ይኖራል እየተባለ ነው፡፡
  • ምን አልከኝ?
  • ሹም ሽር አለ፡፡
  • እስቲ ያቺን የስኳሬንም መድኃኒት ስጠኝ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ይኼ ሁሉ መድኃኒት ምንድን ነው?
  • ምን ላድርግ?
  • ቢከፍቱ እኮ ያዋጣዎታል፡፡
  • ምን?
  • ፋርማሲ!

  [አንድ ሀቀኛ ሚኒስትር ለክቡር ሚኒስትሩ ደወሉላቸው]

  • ክቡር ሚኒስትር ሰሙ አይደል?
  • ምኑን?
  • መግለጫውን፡፡
  • አዎን፡፡
  • አሁን አሥራ አንደኛ ሰዓት ላይ ደርሰዋል፡፡
  • ገና አምስት ሰዓት እኮ ነው፣ ወይስ በፈረንጆች መቁጠር ጀምረህ ነው?
  • እኔ የምልዎት የመጨረሻ ሰዓት ላይ ነዎት፡፡
  • ማለት?
  • በየስብሰባው ስነግርዎት አልሰማ ስላሉ፣ አሁን የመጨረሻው ሰዓት ላይ ነዎት፡፡
  • ምን አደረኩ?
  • ሙሰኛ ነዎት፡፡
  • እና ምን ልታደርጉኝ ነው?
  • ከሥልጣንዎት ይወርዳሉ፡፡
  • እሱ ብቻ ነው?
  • ሌላም አለ፡፡
  • ምን አለ?
  • ይታሰራሉ!

  [ክቡር ሚኒስትሩ ሚስታቸው ጋ ደወሉ]

  • ምን ሆነህ ነው ድምፅህ?
  • ኧረ ጉድ ፈልቷል፡፡
  • የምን ጉድ ነው?
  • ልገመገምልሽ ነው፡፡
  • ሁሌ አይደል እንዴ የምትገመገመው?
  • ይኼኛው ግን ከዚያም ሊያልፍ ይችላል፡፡
  • ምን አለው?
  • ልታሰር እችላለሁ፡፡
  • እ…
  • አሁን በአፋጣኝ ያቺን ቤት ጨርሻት፡፡
  • የትኛዋን ቤት?
  • እስር ቤት መግባቴ ስለማይቀር ለእናንተም እንዲቀርባችሁ እንትን አካባቢ ያለችውን፡፡
  • ምን አካባቢ?
  • ቂሊንጦ!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ሰርጌ ላቭሮቭ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ምዕራባውያንን አጣጣሉ 

  የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ለአፍሪካ አገሮች ላደረጉት...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከታክስ በፊት 27.5 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2014 ሂሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 27.5...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ያገኘው ፔይሊንክ አክሲዮን ማህበር ምሥረታውን አካሄደ

  ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያቀደው...

  የተወሳሰበው ሰላም የማስፈን ሒደት

  የደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ብዙም ሳይዘገይ የኬንያው ቀጣይ...

  በግብርና ዘርፍ ለመሰማራት ያቀደው ድርዜማ

  ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ ባሉ የተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች በአክሲዮን ኩባንያ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  [የተቃዋሚ ፓርቲው ትይዩ ሚኒስትር ክቡር ሚኒስትሩ ጋ ደውለው መንግሥት በሙሰኞች ላይ ለመውሰድ ስላሰበው የሕግ ዕርምጃ ሐሳብ እየተለዋወጡ ነው]

  ሄሎ… ማን ልበል? ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ጤና ይስጥልኝ… ማን ልበል? የእርስዎ ትይዩ ነኝ፡፡  አቤት? ያው ፓርቲዬን ወክዬ የፍትሕ ሚኒስትሩ ትይዩ ነኝ ማለቴ ነው፡፡ ኦ... ገባኝ… ገባኝ...  ትንሽ ግራ አገባሁዎት አይደል? ትይዩ...

   [ክቡር ሚኒስትሩ እራት እየበሉ መንግሥትን በሚተቹ ጋዜጠኞች ላይ እየተወሰደ ያለውን ዕርምጃ የተመለከተ መረጃ እየቀረበላቸው ነው]

  ለጋዜጠኞቹ መንግሥትን እንዲተቹ መረጃ የሚሰጧቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው፡፡ እነሱ አይደሉም፡፡ እና የትኞቹ ናቸው? እዚሁ ከተማችን የሚገኙ ምዕራባውያን ናቸው። እንዴት ነው መረጃውን የሚያቀብሏቸው? እራት እያበሉ ነው። ምን? አዎ፣ እራት ግብዣ ይጠሯቸውና መተቸት...

  [ክቡር ሚኒስትሩ ከፕሮፓጋንዳ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢው ጋር ስለ ሰሜኑ የሰላም ስምምነት ትግበራ መረጃ እየተለዋወጡ ነው]

  እኔ ምልህ፡፡ አቤት ክቡር ሚኒስትር? የሰሜኑ ተዋጊዎች ከሠራዊታችን ጋር መቀራረብ ጀመሩ የሚባለው እውነት ነው?  አዎ። እውነት ነው ክቡር ሚኒስትር።  ከማንም ትዕዛዝ ሳይጠብቁ ነው ከእኛ ሠራዊት ጋር መቀላቀል ጀመሩ...