Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበሪዮ ኦሊምፒክ የተገኘውን ውጤት የተቹት ታዋቂ አትሌቶች አመራሮቹ እንዲነሱ ጠየቁ

በሪዮ ኦሊምፒክ የተገኘውን ውጤት የተቹት ታዋቂ አትሌቶች አመራሮቹ እንዲነሱ ጠየቁ

ቀን:

ኢትዮጵያ በሪዮ ኦሊምፒክ ያስመዘገበችውን ደካማ ውጤት የተቹት የቀድሞ ታዋቂ አትሌቶች ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ለመፍትሔው በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲጠራ አሳሰቡ፡፡

በነባርና ታዋቂ አትሌቶች እንዲሁም ከቀድሞ አሠልጣኞች የተውጣጣው የአትሌቶች ጊዜያዊ ኮሚቴ ነሐሴ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በብሔራዊ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተጠናቀቀው የሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ባስመዘገበችው ደካማ ውጤት ተጠያቂው ፌዴሬሽኑ ነው ብሏል፡፡

በ31ኛው አሊምፒያድ ተካፍሎ ከሪዮ በአንድ ወርቅ፣ ሁለት ብርና አምስት ነሐስ ሜዳሊያዎች የተመለሰው የኢትዮጵያ ቡድን ካለፉት ኦሊምፒኮች ያነሰ ውጤትና ደካማ እንቅስቃሴ አሳይቷል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተገቢው መንገድ ሥራውን እየሠራ አይደለም፤ አትሌቲክሱ ወዳልተገባ መንገድ እያመራ ነው፤›› ያለው የጊዜያዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ኢትዮጵያ በሪዮ ኦሊምፒክ ያሳየችው ደካማ አቋም ፌዴሬሽኑ ወደ ሪዮ ከማምራቱ በፊት የተነሱትን ችግር ያለመፍታቱና የአመራሮች ኦሊምፒኩን በትኩረት ያለመመልከት ውጤት ነው ብሏል፡፡

‹‹የአመራረጥ፣ የልምምድ፣ የአሠልጣኞችና የአትሌቶች አመራረጥ ትኩረት ማጣት ከጊዜ ወደ ጊዜ የአትሌቲክሱ ውጤት ላይ ከፍተኛ ማሽቆልቆል እንዲመጣ አድርጓል፤›› ያለው ኃይሌ ገብረሥላሴ ‹‹አትሌቶቻችን ወደ ሪዮ ከመጓዛቸው በፊት ሥጋታችንን ብናስቀምጥም ሰሚ በማጣታችን የፈራነው ነገር ደርሷል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ወደ ኋላ ሳይሆን ወደፊት መሄድ ይገባናል፤›› ብሏል፡፡

ኮሚቴው በመፍትሔነት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ አመራሮቹ እንዲነሱና ባለሙያዎች እንዲተኳቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡ ከየክልሉ የሚወከሉም ሆነ ፌዴሬሽኑን የሚመሩት በአትሌቲክስ ውስጥ ያለፉና አትሌቲክሱን የሚያውቁ መሆን እንዳለበት ኮሚቴው ገልጿል፡፡  

በጋዜጣዊ መግለጫው የሲድኒ ኦሊምፒክ የማራቶን ወርቅ ባለቤት የነበረው ገዛኸኝ አበራ ‹‹እኛ ቤቱን ለመገንባት እንጂ ለማፍረስ አልተነሳንም፣ ይልቁንም ከ16 ዓመት በፊት አራት ወርቅ አምጥተን ዛሬ ላይ ለምን አንድ ወርቅ ብቻ እናመጣለን?›› በማለት ጠይቋል፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2000 በተካሄደው የሲድኒ ኦሊምፒክ በኦሊምፒክ ታሪኳ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችበት ነበር፡፡ ያኔ 4 ወርቅ 1 ብር 3 ነሐስ በድምሩ 8 ሜዳለያዎች አግኝታ ነበር፡፡  

ገዛኸኝ ‹‹አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ከቀድሞ ባለሙያዎች ጋር ተቀራርቦ ካልሠራና በአመራር ቦታ ላይ የተሰየሙትን አካላት በአትሌቲክስ ውስጥ ባለፉ ካልተካ ከዛሬ የባሰ እንጂ የተሻለ ውጤት ይመጣል ማለት ይከብዳል፤›› ብሎም ሥጋቱን አስቀምጧል፡፡

በተለይ በሥልጠና ወቅት አትሌቶቹ በግላቸው በመሥራትና ቀደም ብሎ በአሠልጣኝ ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ ይሰጥ የነበረውን የልምምድ መንገድ ወደ ጎን በማድረግ በተቃራኒው አትሌቶቹ በራሳቸው መንገድ አሠልጣኞቻቸውን የሚያዙበት ጊዜ ሆኗል ያሉት ኮማንደር አበበ መኮንን ናቸው፡፡

ከቀድሞው ዋና አሠልጣኝ ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ ጋር ማሠልጠን የቻሉት ኮማንደር አበበ፣ ‹‹ሥልጠናው ችግር አለበት፡፡ የትኛውም ዓለም የአትሌቲክስ ሥልጠና በቡድን እንጂ በግል አይደለም፡፡ ሥልጠናው በባለሙያዎች ጭምር እንጂ በትምህርት ብቻ ሊከናወን አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

አንጋፋዎቹ አትሌቶች ጋዜጣዊ መግለጫቸውን ያጠቃለሉት፣ አትሌቲክሱን የሚመራው አካል ቀና ምላሽ ካልሰጠና ከውሳኔ ላይ ካልደረሰ መሄድ ያለበት ርቀት ድረስ እንደሚሄድ መዘጋጀታቸውን አስጠንቅቀዋል፡፡ መፍትሔ ለማፈላለግም ወደ ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ላይ እንደሚያነጣጠሩም ተመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን አዲስ አበባ እንደደረሰ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኢንጂነር መሰለ፣ የተገኘው ውጤት የሚያበረታታ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በኦሊምፒኩ ደካማ ሆና ሳይሆን የሌሎች ጠንካራ መሆን ነው፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ ለመጣውም ውጤት ‹‹ምንም ዓይነት ይቅርታ›› ፌዴሬሽኑ እንደማይጠይቅና ወደፊት በጉዳዩ ላይ አስፈላጊው ማብራሪያ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሪዮ ኦሊምፒክ የሰበሰበቻቸው 8 ሜዳሊያዎች ያገኙት አልማዝ አያና (ወርቅ 10,000 ሜትር እና ነሐስ 5,000 ሜትር)፣ ጥሩነሽ ዲባባ (ነሐስ 10,000 ሜትር)፣ ታምራት ቶላ (ነሐስ 10,000 ሜትር)፣ ገንዘቤ ዲባባ (ብር 1,500 ሜትር)፣ ሐጎስ ገብረሕይወት (ነሐስ 5,000 ሜትር)፣ ማሬ ዲባባ (ነሐስ ማራቶን) እና ፈይሳ ሌሊሳ (ብር ማራቶን) መሆናቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...