Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርት‹‹ሕጉ የግድ በባለሙያ ለመመራት ሲድኒ ላይ የሮጠ ብቻ በአመራር ይቀመጥ አይልም››

‹‹ሕጉ የግድ በባለሙያ ለመመራት ሲድኒ ላይ የሮጠ ብቻ በአመራር ይቀመጥ አይልም››

ቀን:

አቶ አምበሳው እንየው፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ

በቅርቡ በተጠናቀቀው የሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን ዝቅተኛ ውጤት በተመለከተ በተለያዩ ወገኖች ከተርታው ኅብረተሰብ እስከ ታዋቂ ወርቃማ አትሌቶች በቁጭት ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡ ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያቀዱት አራት ወርቅ፣ አራት ብርና አራት ነሐስ ውኃ የበላው መጀመሪያውኑ የእቅድ ምሰሶው መሠረት የሌለው በመሆኑ ነውም ብለውታል፡፡ የቀድሞ ታዋቂ አትሌቶችንና አሠልጣኞችን ያቀፈውና በኃይሌ ገብረሥላሴ የሚመራው ጊዜያዊ ኮሚቴ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲበተን ጥሪ አቅርበውበታል፡፡ የኦሊምፒክ ቡድኑ በ31ኛው ኦሊምፒያድ ይዞ የተመለሰው አንድ ወርቅ ሁለት ብርና አምስት ነሐስ የስኬት መገለጫ ነው በማለት ብሔራዊ ፌዴሬሸኑም ሆነ ኦሊምፒክ ኮሚቴው አወድሰውታል፡፡ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርም የሁለቱን ተቋማት አስተያየት ይጋራል፡፡ እንዲያውም በነሐስ ሜዳሊያዎች ብዛት ካለፉት ኦሊምፒኮች ሲታይ በሪዮ የተሻለ ውጤት ማምጣት ተችሏል፣ በወርቅ ዝቅተኛ ቢሆንም በኦሊምፒክ በራሱ መሳተፍ በጎ ጎን ነው በማለት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አምበሳ እንየው በጽሕፈት ቤታቸው ነሐሴ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡ በኃይሌ ገብረሥላሴ የሚመራውን ጊዜያዊውን የአትሌቶች ኮሚቴ ‹‹አናውቀውም›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ ዳዊት ቶሎሳ አቀናብሮታል፡፡

ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ በ31ኛው ኦሊምፒያድ በአትሌቲክሱ ያሳየችው ውጤት ዝቅተኛ መሆኑ ታምኗል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች መሳተፏ እንደ መልካም ጎን መወሰድ አለበት እንጂ ውጤቱን በሜዳሊያ ብቻ መመዘን አይቻልም ሲባል ምን ለማለት ተፈልጎ ነው?

- Advertisement -

አቶ አምበሳው፡- ቀደም ብሎ በሪዮ ኦሊምፒክ አራት ወርቅ አራት ብርና አራት ነሐስ ለማምጣት ታቅዶ ነበር፡፡ በነሐስ ካለፉት ኦሊምፒያዶች ሲታይ በሪዮ የተሻለ ውጤት ማምጣት ተችሏል፡፡ በወርቅ ግን ዝቅተኛ የሚባል ውጤት ነው ያስመዘገብነው፡፡ በአንጻሩ ግን በኦሊምፒኩ መሳተፋችን ራሱ እንደ በጎ ጎን መታሰብ አለበት፡፡ ምክንያቱም በዝግጅት ወቅት የታሰበው የወርቅ መጠን ‹‹ጅምላ ዕቅድ›› ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ደግሞ በአትሌቲክሱ የታቀደው የሜዳሊያ መጠን ጥልቅ ጥናት ሳይደረግበት ነው፡፡ በ5,000 እና 10,000 ላይ ወርቅ ያመጣሉ ተብለው የታሰቡት አትሌቶች በሥልጠና ወቅት ከብሔራዊ ቡድን ውጪ ነበሩ፡፡ በኦሊምፒክ ላይ አንድ ወርቅ ስለመጣ ብቻ አትሌቲክሱ አሽቆልቁሏል ማለት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ በቀደምቱ ኦሊምፒኮች ከተሳተፈችበት መድረኮች ጋር ለማነፃፀር ያክል ለምሳሌ ከባርሴሎና፣ ሜክሲኮ፣ ቶኪዮና ሮም እንዲሁም ሙኒክ ከነበረው በሪዮ ያመጣነው ነሐስ ሜዳሊያ ቁጥር የተሻለ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በኦሊምፒኩ ታሪክ ካልተሳተፈችበት የሲኦል፣ ሎሳንጀለስ እንዲሁም ሞንትሪያል ኦሊምፒኮች በሪዮ ኦሊምፒክ ብዙ ክፍተቶች ቢኖርብንም በመድረኩ ላይ መሳተፍ መቻሏና አንድ ወርቅ ብቻ ስላመጣች በሜዳሊያ መጠን ብቻ መመዘን ያለባት አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም በጥቂት ስፖርት ዓይነቶች በመሳተፍ ይህን ስምንት ሜዳሊያ ማስገኘቷ ትልቅ ነገር ነው፡፡

ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መሳተፍ ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ በተለይ በረዥም ርቀቱ ያመጣቻቸው ውጤቶች ጥሩ ነበር፡፡ አሁን ያለው የስፖርት ፖሊስ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል እየተባለ ውጤታማ አለመሆኗ በሦስት ስፖርቶች ብቻ ተካፍላ በተሳትፎ ጥሩ ደረጃ ላይ ነች የተባለው ከምን አንፃር ነው?

አቶ አምበሳው፡- ኢትዮጵያ መሳተፍ ከጀመረች ጀምሮ ከተካሄዱት 16 ኦሊምፒያዶች በ13ቱ መሳተፍ ችላለች፡፡ በፖለቲካ አለመመቻቸት ያልተሳተፈችባቸው ኦሊምፒኮች የሚያስቆጭ ጊዜ አድርገን እንወስደዋለን፡፡ አሁን የምንገኝበት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ከፍ ያለ ሆኖ እንዴት ውጤቱ ዝቅተኛ ይሆናል? ለሚለው የስፖርት ዕድገታችን በወርቅ ሊለካ አይችልም እንላለን፡፡ ግን ደግሞ እንደ ኦሊምፒክ ከተሳትፎ ቀጥሎ የሚመጣው ሜዳሊያ ሠንጠረዥ ውስጥ መግባት ነው፡፡ በሪዮ እናመጣዋለን ያልነውን ወርቅ ዝቅተኛ እንደሆነ እንቀበላለን፡፡ በአንፃሩ በስፖርት ኢንቨስትመንት ስንለካ በተሳትፎ፣ በቁሳቁስ ካለፉት ጊዜያት ደህና ሆነን ሻል ያለ ወርቅ ለምን አልመጣም? በሥልጠና ክፍተት ምክንያት ነው፡፡ ሌላው ተሳትፎ ሲባል በብዙ ስፖርቶች መሳተፍ ስንችል ነው የተባለው እውነት ነው፡፡ በሁሉም ስፖርት መሳተፍ አለመቻላችን እውነት ነው፡፡ ግን ደግሞ ከነበረን ተሳትፎ አድገናል፡፡ ድሮ የምንሳተፍበት ማራቶን፣ አሥር ሺሕ፣ ግፋ ቢል አምስት ሺሕ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ስፖርትን ለማስተዋወቅ መንግሥት አይሠራም፡፡ ስፖርትን ማስተዋወቅ የስፖርት ፌዴሬሽን ሥራ ነው፡፡ መንግሥት ድጋፍ ብቻ ነው የሚያደርገው፡፡ ለምን በተለያዩ ስፖርት ዓይነቶች አልተሳተፍንም ስፖርቱ ስላልሰፋ ማሳተፍ አንችልም፡፡ ባልተስፋፋ ስፖርት ላይ መንግሥት ጊዜውን ማቃጠል አይፈልግም፣ የተስፋፉትን ከመደገፍ ውጪ፡፡

ጥያቄ፡- በሪዮ ለተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት መምጣት ክፍተቶቹ ምን ነበሩ?

አቶ አምበሳው፡- በሪዮ ኦሊምፒክ ለመጣው ውጤት የተለያዩ ችግሮች እንደነበሩ ሚኒስቴሩ የታዩትን ክፍተቶች ገምግሟል፡፡ በዚህም መሠረት የሥልጠና፣ የሥነ ልቦና፣ የቡድን ሥራ፣ የአመጋገብ ሥርዓት፣ አትሌቶቹን በማቀናጀት ሥራ ላይ ፌዴሬሽኑ ያሳየው ደካማ አቋም፣ እንዲሁም ኦሊምፒክ ኮሚቴው ቡድኑን መከታተልና መቆጣጠር ላይ ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ መገምገም ችለናል፡፡ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑም የተለያዩ ችግሮች እንዳሉበት ተገልጿል፡፡ የመልካም አስተዳደር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች እንዳለበት ፌዴሬሽኑም አስታውቋል፡፡ በቀጣይ በአሠራር፣ በተጠያቂነት የሚፈቱ ይሆናሉ፡፡

ጥያቄ፡- ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ የውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ብቁ ሆኖ ስላልተገኘ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደማይደረግለት ተገልጿል፡፡ ድጋፍ እንዳይደረግለት የተወሰነበት ምክንያት ምንድነው? እንዲሁም በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑም ተመሳሳይ ችግር ታይቶ ውሳኔ ያልተሰጠበት ምክንያት እንዴት ነው?

አቶ አምበሳው፡- የውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን በተመለከተ ከሪዮ በፊት የተለያዩ ግምገማዎችን አድርገናል፡፡ ከውድድር በፊትም ተነጋግረናል፣ እርምት ወስደናል፡፡ ግን ሊቀበሉን አልቻሉም፡፡ ከዛ በፊት ከአሠልጣኞች የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሲቀርቡልን ነበር፡፡ እንዲያስተካክሉ ነግረናቸዋል፡፡ ከሪዮ መልስም ስለተፈጠሩ ጉዳዮች ዝርዝር መረጃና ማስረጃ እንዲያቀርቡ ጠይቀናቸዋል፡፡ የምንጠይቃቸውን ጥያቄ አለመመለስ ብቻ አይደለም፡፡ አያገባችሁም የማለት ደረጃም ደርሰዋል፡፡ ስለዚህም በማያገባን ነገር ላይ ድጋፍ የምናደርግበት ምክንያት የለም፡፡ በአጠቃላይ ግን በአስተዳደር፣ በሥልጠና፣ በአመራር በመሳሰሉ ጉዳዮች ድጋፎቻችን እንድናቆም ተገደናል፡፡ ፌዴሬሽኑ ያሉበትን ችግሮች በተለይ ከመልካም አስተዳደር፣ ከሥልጠና እንዲሁም በተመሳሳይ ሁኔታዎች ላይ በቀጣይ እንደሚያርም ገልጿል፡፡ በእኛ በኩል ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በአግባቡ ተቀምጦ እንዲያስተካክል ቁጥጥርና ክትትል እናደርጋለን፡፡ በዛ መንገድም ችግሮቻቸውን እንደሚፈቱ ገልጸዋል፡፡

ጥያቄ፡- አትሌቲክሱ በትክክለኛ መንገድ ላይ እየተጓዘ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ አምበሳው፡- በእኛ እምነት አትሌቲክሱ ትክክለኛ መንገድ ላይ ነው፡፡ አትሌቲክሱ እያደገ ነው፡፡ አትሌቲክሱ እየበዛ ነው፣ የአገር ውስጥ ውድድሮችም እየበዙ ነው፡፡ አትሌቶችም በኢኮኖሚ አንፃር ቤተሰቦቻቸውም ጭምር እየተጠቀሙ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ግን ፌዴሬሽኑ ላይ ችግሮች አሉ፡፡ እነሱም በሒደት ይፈታሉ፡፡ በሕግ የሚነሱ ግድፈቶችን ከመፍታት ውጪ በአትሌቲክሱ ፌዴሬሽኑ ላይ ምንም አቋም የለንም፡፡

ጥያቄ፡- የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ወደ ሪዮ ከማምራቱ በፊት እንዲሁም ከኦሊምፒኩም መልስ የቀድሞ አትሌቶች ጊዜያዊ ኮሚቴ በማቋቋም በአትሌቲክሱ ዙሪያ ጥያቄ ማንሳት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ምን ይላል?

አቶ አምበሳው፡- የአትሌቶች ጊዜያዊ ኮሚቴ የሚባለውን አናውቀውም፡፡ ስለዚህ በማናውቀው ነገር ምንድነው ብለን በየቤቱ ዞረን መጠየቅ የለብንም፡፡ ጊዜያዊ ኮሚቴ መሆኑን፣ በማን እንደተጀመረና የምናውቀው መረጃና ዕውቅና የለም፡፡ እኛ እንደመንግሥት የምናውቀው የስፖርት ማኅበር የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ እንዲሁም ደግሞ የሙያ ማኅበር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የአትሌቶች ማኅበርን ነው፡፡

ጥያቄ፡- የስፖርት ፌዴሬሽኖች በባለሙያ መመራት አለባቸው የሚለው አስተያየት ከተለያዩ ግለሰቦች ጥያቄ እያስነሳ ነው?

አቶ አምበሳው፡- በስፖርት ፌዴሬሽኖች ላይ የተሻሉ ሰዎች ወይም በስፖርት ውስጥ ያለፉ የሆኑ የሚለው አስተያየት ጥሩ ሐሳብ ነው፡፡ የተማረ ሰው ሀብት ያለው እንዲሆን፣ ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያለው እንዲሆን እንጂ አትሌት ያልነበረ መግባት የለበትም ብሎ መገደብ አይቻልም፡፡ ለዚህም የአምበሳውን ድርሻ ክልሎች ይወስዳሉ፡፡ የፈለጉትን መርጠው መላክ፣ የመረጡትን ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ሌላው የአገሪቱን ሥርዓተ ትምህርት ባንቀወም ጥሩ ነው፡፡ በስፖርት ሳይንስ ውስጥ ያለፉ ሞያተኞች ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይወጣሉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘርፍም የሚመጡትም ከእነዚህም ባሻገር ደግሞ በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማኅበር ሥልጠና ወስደው የመጡትን እንደ ሞያተኛ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ሕጉ የግድ በባለሙያ ለመመራት ሲድኒ ላይ የሮጠ ብቻ በአመራር ይቀመጥ አይልም፡፡

ጥያቄ፡- ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ በተለይ ከውኃ ስፖርት ጋር የሚነሱ ችግሮች ነበሩ፡፡ አንድ የፌዴሬሽን አመራር ከቦታው ከተነሳ በኋላ ወደ ሌላ ስፖርት ፌዴሬሽን ተመልሶ ሲሠራ በብዙዎች ቅሬታ ሲያስነሳ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው አካሄድ ምን ይመስላል?

አቶ አምበሳው፡- በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱ ይደረጋል፡፡ ስለዚህ ውኃ ስፖርት ላይ የነበረው ልጅ በፊት የነበረበት ቦታ ላይ ባለመስማማቱ ከዛ ተነስቶ ሌላ ቦታ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ፌዴሬሽኑ እንደ አትሌቲክስና እግር ኳስ መቅጠር ስለማይችል፣ እኛ አወዳድረን በሲቪል ሰርቪስ ሕግ መሠረት የትምህርት ደረጃቸውንና አገልግሎታቸው አይተን እንመድባለን፡፡ መዋቅር ሲሠራ አንዱን ከአንዱ ወስደን የምናሸጋግረው ነገር ይኖራል፡፡ በአጠቃላይ ግን የሚቀመጡት ሰዎች በትምህርት ደረጃቸው እንዲቀመጡ መደረግ አለበት፡፡

ጥያቄ፡- መንግሥት ለሪዮ ኦሊምፒክ ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል ወይ? ከኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ምን ተጠቀመች?

አቶ አምበሳው፡- መንግሥት በሪዮ ኦሊምፒክ የሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ከሌሎቹ ኦሊምፒኮች ትልቅ ነው፡፡ ያስፈቀድነውን ገንዘብ ግን ሙሉ በሙሉ አልተሰጠንም፡፡ አዎን መጠኑን መግለጽ ባያስፈልግም፡፡ ድሮ አራትና አምስት ሚሊዮን ብር ነበር የሚፈቅድልን፡፡ አሁን ግን ለኦሊምፒክ ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ ውድድሮች ጭምር የተሻለ በጀት ሰጥቶናል፡፡ በኦሊምፒኩ ኮሚቴ በኩል ምን ያህል አገኙ? ምን ያህል ተጠቀሙ የሚያውቀው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ነው፡፡ በእኛ በኩልም በፊት ከሚሰጠው በጣም የራቀ ባይሆንም የገንዘብ ድጋፍ አድርገናል፡፡

ጥያቄ፡- አትሌቶች ለሪዮ ሲዘጋጁ ካለፉት ውድድሮች በተሻለ መጠን ይዘጋጁ እንደነበር አሠልጣኞቹም ጭምር ሲገልጹ ነበር፡፡ ሚኒስቴሩ ለምን ክትትልና ቁጥጥር ሳያደርግ ቀረ?

አቶ አምበሳው፡- በሥልጠና፣ በዕቅድ ዝግጅትና በውድድር ወቅት ቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ግን በቂ አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ ግን ድጋፍ ማድረግም ኃላፊነታችን እንደሆነ እናውቃለን፡፡

ጥያቄ፡- የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያለ ዋናው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እየተመራ እንዴት ወደ ስፍራው ሊያመራ ቻለ?

አቶ አምበሳው፡- የኦሊምፒክ ኮሚቴው ዋና ጸሐፊ በራሳቸው ፈቃድ ቦታውን ለቀዋል፡፡ ግን መተካት ነበረበት፤ ሳይተካ ቆይቷል፡፡ የኦሊምፒክ ኮሚቴው የሥራ ዘመኑን ስለጨረሰ፣ በቀጣይ ምርጫ ያካሂዳል፡፡ ከዚህ በኋላም በደንባቸው ላይ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ያስፈልጋል? አያስፈልግም የሚለውን ይወስናሉ፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ አገሮች በጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሚመሩ አሉ፡፡ የማይመሩም እንደዛው፡፡ ስለዚህም በቀጣይ የሚታይ ይሆናል፡፡

ጥያቄ፡- በመጨረሻም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገቢ አልነበረም የሚሉ አካላት ነበሩ፡፡ ምን ምላሽ ይሰጣሉ?

አቶ አምበሳው፡- ተገቢ አይደለም የተባለውን አልቀበልም፡፡ እንደእኛ ተገቢ ነው የሚል አቋም አለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...