Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አንጋፋ አትሌቶች ያነሱት ጥያቄ ተገቢ ነው አለ

የኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አንጋፋ አትሌቶች ያነሱት ጥያቄ ተገቢ ነው አለ

ቀን:

የኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አንጋፋ አትሌቶች ያነሱት ጥያቄ ተገቢ ነው በማለት፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ላይ ከጊዜያዊው የአትሌቶች ኮሚቴ ጋር መነጋገር እንዳለበት ገልጿል፡፡

ሐሙስ ነሐሴ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. የእሬቻ በዓል ታላቁ ሩጫን በተመለከተ በኦሮሚያ ባህል ማዕከል ፌዴሬሽኑ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ አስፈላጊውን ምላሽ መስጠት አለበት ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ችግር ውስጥ ስለመግባቱ ቀደም ብሎ በጉዳዩ ላይ ‹‹የኦሮሚያ አትሌቲክስ ከየት ወዴት?›› በሚል ርዕስ በተጠና ጥናት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ችግር ውስጥ መዘፈቁን የገለጹት የኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዳኛቸው ሽፈራው፣ አትሌቲክስ ከፍተኛ ችግር እንዳለበት ቀድሞውኑ አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

በመላ አገሪቱና በክልሎች ያለውን የአትሌቲክስ ስፖርት ችግር ለመፍታት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ራሱን በመገምገምና ተግዳሮቶችን በማጣራት፣ ችግሩ ሥር ሳይሰድ በፊት መፍትሔ መስጠት እንዳለበት አቶ ዳኛቸው አሳስበዋል፡፡

- Advertisement -

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ 19ኛው ጠቅላላ ጉባዔውን ሲያካሂድ በአትሌቲክሱ ላይ የታዩትን ችግሮች ለመቅረፍ እንዲረዳው መነሻ ሐሳቦችን እንዳቀረቡ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ከሪዮ ኦሊምፒክ ቀደም ብሎ ለመወያየት ዕቅድ ተይዞ እንደተለያዩም ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት በአትሌቲክሱ ላይ እያንዣበበ ያለውን ችግር በማጣራትና በመለየት በማን ይፈታል? የሚለውን ጭምር በማጣራት፣ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል በማለት በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት አብራርተዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን የአትሌቶቹም ጭምር ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የቀድሞ አትሌቶች ያነሱትና ‹‹ፌዴሬሽኑ በባለሙያዎች ይመራ›› የሚለው ጥያቄ ትክክል ነው በማለት ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በብሔራዊ ፌዴሬሽኑና በአንጋፋ አትሌቶች መካከል የተነሳውን አለመግባባት ለመፍታት ተቀራርቦ መነጋገር እንደሚያስፈልግ አቶ ዳኛቸው አሳስበዋል፡፡

በዚህም መሠረት ቀድሞ ሲስተዋል የነበረው የአትሌቲክሱ ችግሮች አደረጃጀት፣ ሥልጠና፣ አቅምና ታዳጊዎችን በተገቢው መንገድ አለመያዝ ዋናዎቹ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

‹‹ተተኪዎች የሉም ተብሎ ለሚነሳው ጥያቄ ተተኪዎች አሉ፡፡ በእነሱ ላይም ለመሥራት የአደራጃጀት ችግርን መፈተሽ ያስፈልጋል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተርና በአሁኑ ወቅት የኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዱቤ ጁሎ በጉዳዩ ላይ በተነሳላቸው ጥያቄ መሠረት፣ ‹‹አትሌቶቹ አቶ ዱቤ ጁሎ ወደ አመራርነታቸው ይመለሱ ብለዋል ብለው ያቀረቡት ጥያቄ የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍራቸው አይደለም፡፡ ምክንያቱም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ በባለሙያ ይመራ ማለት ኃጢዓት አይደለም፤›› በማለት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሰባት የዓለም ሻምፒዮናና 19 የአገር አቋራጭ ውድድሮችን መምራት የቻሉት አቶ ዱቤ፣ ‹‹ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሕገወጥ በሆነ ሥራ ተጠያቂ ነህ ብሎ የእኔን ስም መወንጀሉ ተገቢ አይደለም፡፡ አቶ ዱቤ ጥፋተኛ ነው ካሉ ግን በሕግ መጠየቅ ይችላሉ፤›› በማለት በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የሪዮ ኦሊምፒክን ውጤት በተመለከተ ጥያቄ የተነሳላቸው አቶ ዱቤ፣ የተመዘገበው ውጤት እንዳሳዘናቸውና በውድድሩ ላይ የታየው ክፍተት ከሥልጠና ክትትል ጉድለት የመጣ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ገንዘቤ ዲባባን ቀርበው ባለመንገራቸው ወይም ዕርዳታ በመንፈጋቸውና በወንዶቹ በኩል በሞ ፋራህ የተወሰደው ብልጫ እንዲሁም የዓለም ሪከርድ ባለቤቷ አልማዝ አያና በ5,000 ሜትር ውድድር ወቅትና ስምንት ዙር እየቀራት በመወጣት አቅሟን ስትጨርስ ዝም ብሎ መታየቱ፣ ለውጤቱ ዝቅተኛ መሆን ለሥልጠና ችግር አመላካች ነበር ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጀው የእሬቻ ታላቁ ሩጫ መስከረም 21 ቀን በቢሾፍቱ ከተማ የሚካሄድ ሲሆን፣ በውድድሩም የአትሌቶችና የሕፃናት ውድድር እንደሚደረግ ፌዴሬሽኑ አስታወቋል፡፡

አሥር ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን የተነገረው የአዋቂ አትሌቶች ውድድር፣ የአካባቢው ነዋሪ፣ የአቅራቢያ ከተማ ነዋሪዎችና አምባሳደሮችም እንደሚሳተፉበት ተገልጿል፡፡

ለአሸናፊ አትሌቶች ከ20 ሺሕ ብር እስከ 10 ሺሕ ብር የሚደርስ ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን፣ ክልልና አገርን ሊወክሉ የሚችሉ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ይጠቅማል ተብሏል፡፡ የእሬቻ ታላቁ ሩጫ በየዓመቱ በቢሾፍቱ ከተማ ከሚከበረው የእሬቻ በዓል ጋር አንድ ላይ እንዲካሄድ በማድረግ አትሌቲክሱ ከስፖርትም ባሻገር ባህላዊ ለዛ እንዲኖረው ታልሞ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡ በውድድሩ 50 ሺሕ ተሳታፊዎች እንደሚጠበቁ የተገለጸ ሲሆን፣ እስካሁን 12,650 ተሳታፊዎች መመዝገባቸው ተገልጿል፡፡

በእሬቻ ታላቁ ሩጫ ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ በአዲስ አበባ በኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ በቢሾፍቱና በአሰላ ከተማ ቲሸርቱን በ150 ብር ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...