በሐረር ከተማ ‹‹አው አባድር›› የተሰኘ ዘመናዊ ሁለገብ ስታዲየም በ1.8 ቢሊዮን ብር እየተገነባ ነው፡፡ የስታዲየሙ ዲዛይን (በፎቶው እንደሚታየው) የሐረሪ የውድ ጌጣጌጥ ማስቀመጫ ባህላዊ ሙዳይ ቅርፅ ይዞ እንደሚገነባና ባህላዊ አልባሳትን የሚወክል እንደሚሆንም ተነግሯል፡፡ እስከ 50 ሺሕ ተመልካች የሚይዘው ይህ ስታዲየም እግር ኳስን ጨምሮ ሌሎች ስፖርቶችን፣ የተለያዩ የስብሰባ አዳራሾችና የስፖርት ምርምር ማዕከሎችን ያካትታል፡፡ እንዲሁም በውስጡ እስከ 350 አልጋ የሚይዝ ሆቴል፣ ሬስቶራንት፣ የስፖርት አካዴሚ፣ 250 ሱቆች፣ ስድስት ሺሕ ያህል መኪና የሚያቆም መናኸሪያ እንደሚኖሩት ታውቋል፡፡ በአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ተቋራጭነት እየተገነባ ያለው ይህ ስታዲየም፣ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የሐረሪ ክልል ቤቶች ልማትና የመንግሥት ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡ በታምራት ጌታቸው