Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ክቡር ሚኒስትር

  • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንዴት ነህ?
  • በጣም ደህና ነኝ፤ ሁሉም ሰላም ነው?
  • ኧረ በጣም ሰላም ነው፡፡
  • ስብሰባው እንዴት ነበር?
  • የትኛው ስብሰባ?
  • ከዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች ጋር የነበራችሁ፡፡
  • በጣም አስደናቂ ነበር፡፡
  • እ…
  • አንተ አልነበርክም እንዴ?
  • አዎን እኔ አንድ የጥናት ጽሑፍ አዘጋጅ ነበር፡፡
  • የጥናት ጽሑፍ?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • የጥናት ጽሑፍማ ቀረበ፡፡
  • የት ክቡር ሚኒስትር?
  • እኛ እኮ ከአስማተሪዎቹ ጋር የተወያየነው በጥናት ጽሑፍ ላይ ተመሥርተን ነው፡፡
  • እ… ያ ሦስት ዓመት ያለፈበት፡፡
  • ስማ ብቻ ውይይቱ በጣም ልማታዊ ነበር፡፡
  • ማለት ክቡር ሚኒስትር?
  • የአገሪቷን የትምህርት ጥራት እንዴት እንደሚሻሻል በሚገባ ነው የተወያየነው፡፡
  • ከእናንተ ጋር ውይይት ምን ለውጥ ያመጣል ብለው ነው፡፡
  • እንዴት ማለት?
  • ያው አድሮ ቃሪያ ናችኋ፡፡
  • ስማ አሁን ኢኮኖሚያችን እኮ ከግብርና ወጥቶ ወደ ኢንዱስትሪ ተሸጋግሯል፡፡
  • ምን እያሉ ነው?
  • በቃ ቃሪያ ምናምን የሚሉ ተረትና ምሳሌዎች ቀርተዋል፡፡
  • አይ ክቡር ሚኒስትር ቀልደኛ ነዎት፡፡
  • ለማንኛውም ስብሰባችን የተሳለጠ ነበር፡፡
  • እኔ ግን የሰማሁት ሌላ ነበር፡፡
  • ምን ሰማህ?
  • በጣም እንደተዋረዳችሁ፡፡
  • ማን ነው የነገረህ?
  • ስብሰባው ውስጥ የነበሩ ጓደኞቼ፡፡
  • ፀረ ልማት አስተማሪዎች ናቸው ማለት ነው?
  • ኧረ በትክክል የሰሙትን ነው የነገሩኝ፡፡
  • ይኼ የበሬ ወለደ ወሬ ነው፡፡
  • ቅድም ኢኮኖሚያችን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ተሸጋግሯል ሲሉ አልነበረ እንዴ?
  • በደንብ ተሸጋግሯል፡፡
  • አይ በሬ ምናምን እያሉ ሲተርቱ ብዬ ነዋ፡፡
  • እና የኢንዱስትሪ ፓርካችን ወለደ ወሬ ነው ልበልህ?
  • ለነገሩ እንደዚያ ማለት ይችላሉ፡፡
  • እንዴት ሆኖ?
  • ያው በሬ እንደማይወልደው ሁሉ፣ የአገሪቷ ኢኮኖሚ ሁሉንም ተጠቃሚ እያደረገ አይደለም፡፡
  • ቀልድ ግን አያምርብህም፡፡
  • እሱስ እውነትዎትን ነው፤ ቀልዱ የሚያምረው በእናንተ ነው፡፡
  • እ…
  • ይኸው ሕዝቡ ላይ እየቀለዳችሁ አይደል እንዴ?
  • ከዚህ በላይ ምን እናድርግ?
  • ለመሆኑ ምን አደረጋችሁ?
  • አዳምጡን አላችሁ ሰበሰብናችሁ፡፡
  • ሕዝቡ እኮ ያለው ሰብስቡን ሳይሆን አዳምጡን ነው ያለው፡፡
  • ምን ማለት ነው?
  • የምትሰበስቡት የሕዝቡን ሐሳብ ለመስማት እንጂ የእናንተን ሐሳብ ለመጫን አይደለም፡፡
  • ወይ ጣጣ፡፡
  • ለማንኛውም እናንተ ትምህርት ቤት ነው መግባት ያለባችሁ፡፡
  • በዚህ ዕድሜያችን ትምህርት ልንማር?
  • ለነገሩ ብትማሩም ለውጥ አታመጡም፡፡
  • ለምን?
  • ስለማይገባችሁ!

  [የክቡር ሚኒስትሩ የእህታቸው ልጅ ቢሯቸው መጣች]

  • እንዴት ነህ ጋሼ?
  • አንቺ በጣም አደግሽ፡፡
  • ምን ታደርገዋለህ ጋሼ?
  • የት ነው ያለሽው?
  • እየተማርኩ ነው ጋሼ፡፡
  • የት ነው የምትማሪው?
  • ዩኒቨርሲቲ ነዋ፡፡
  • የአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲ?
  • አዎና ጋሼ፡፡
  • የእኔ የመጀመሪያ ልጅ ጓደኛሽ እኮ ቻይና ነው የምትማረው፡፡
  • ታዲያ እኔ ቻይና መማር የምችልበት አቅም የለኝም፡፡
  • እኔ አስተምርሻለኋ፡፡
  • እንዴት አድርገህ?
  • ስንትና ስንት ስኮላርሽፕ አይደል እንዴ ለመንግሥት የሚመጣለት?
  • እ…
  • አየሽ ያቺ እናትሽ እኮ አፍራሽ ስለሆነች ነው ያራራቀችን፡፡
  • በል እናቴን ለቀቅ አድርጋት፡፡
  • ከእኔ ሥር ሥር ባትጠፋ ይኼኔ የት ደርሳችሁ ነበር፡፡
  • ጋሼ አንተ የት ደረስክ?
  • ይኸው በየቦታው አይደል እንዴ ሕንፃ የገነባሁት፡፡
  • አይ መፍረሻው የደረሰ መሰለኝ፡፡
  • ማን አባቱ ነው የሚያፈርሰው?
  • መሠረቱ አሸዋ ነው ብዬ ነው፡፡
  • ኧረ አለት ድንጋይ ላይ ነው የሠራሁት፡፡
  • ጋሼ ሕዝብ ሲነሳብህ አሸዋ ላይ መገንባትህ ይገባሃል፡፡
  • አንቺም እናትሽም አፍራሾች ናችሁ፡፡
  • ለማንኛውም ከአስተማሪዎቻችን ጋር የነበራችሁ ስብሰባ እንዴት ነበር?
  • እጅግ ልማታዊ ነበር፡፡
  • እኔ ግን የሰማሁት የተገላቢጦሽ ነው፡፡
  • ምን ሰማሽ?
  • አስተማሪዎቹ አመፁባችሁ አሉ፡፡
  • ምን?
  • አንዳንድ ቦታ እንደ ሕዝቡ አናወራም ብለው በፀጥታ ተቃወሟችሁ አይደል?
  • ሕዝቡ አውራ ሲባል አያወራም?
  • አውራ ፓርቲ ብቻ በሚያወራበት መድረክ እንዴት ያውራ?
  • ምን?
  • አሁን ከተማሪው ጋርም መሰብሰባችሁ አይቀርም አይደል?
  • ይመስለኛል፡፡
  • እንግዲያው ከተማሪውም ከዚህ የባሰ ተቃውሞ ነው የሚጠብቃችሁ፡፡
  • ለምን?
  • ማውራት ብቻ አይጠቅምማ፡፡
  • ታዲያ ምንድን ነው የሚጠቅመው?
  • ማዳመጥ!

  [ክፉኛ የተገመገሙ የክቡር ሚኒስትሩ ጓደኛ ሚኒስትር ደወሉላቸው]

  • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንዴት ነህ ወዳጄ?
  • ምንም አልተረፍኩም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ሆንክ?
  • በቃ ከታተፉኝ፡፡
  • ማለት?
  • ግምገማው ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንዴት ማለት?
  • አንዴ ሲያወጡኝ…
  • እሺ፡፡
  • አንዴ ሲያፈርጡኝ…
  • ወይ ጉድ፡፡
  • አንዴ ሲሰቅሉኝ…
  • እ…
  • አንዴ ሲቀብሩኝ…
  • ተላለቅን በለኛ፡፡
  • በቃ ሁሉም ጉዴ ነው የወጣው፡፡
  • እ…
  • ያለኝ የፎቅ ብዛት ሲወራ…
  • ደሞ ብዛትህ ተነሳ?
  • ያለኝ ሀብት መጨመሩ ሲወራ…
  • ስኳርህም እዛው ጨመረ?
  • ብቻ ምን ልበልዎት?
  • እኔንማ በቃ ይጨርሱኛል ማለት ነው?
  • ያስቡበት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አብረውን እንዳልበሉ እንደዚህ ይጫወቱብን?
  • ክቡር ሚኒስትር የእኛም አበላል ቀላል አይደለም፡፡
  • ያው ተረቱ ያልበላ ተጐዳ ስለሚል እኮ ነው፡፡
  • እሱማ እኔም ሲሾም ያልበላ የሚለውን ተረት ይዤ ነው የጨረገድኩት፡፡
  • እና የተሳለ መጥረቢያ ነው የሚጠብቅህ እያልከኝ ነው?
  • በሚገባ ይዘጋጁበት፡፡
  • ገና ከአሁኑ መጨመር ጀመረ፡፡
  • ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
  • ደምና ስኳሬ!

  [ክቡር ሚኒስትሩ ዶክተራቸው ጋ ደወሉ]

  • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ኧረ አንተ ጋ መምጣት አለብኝ፡፡
  • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
  • በጣም ጨምሮ ነው፡፡
  • ደመወዝ ተጨመረልዎት እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
  • ኧረ ደምና ስኳሬ ነው፡፡

  [ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር መሄድ ጀመሩ]

  • ወዴት እንሂድ ክቡር ሚኒስትር?
  • ሆስፒታል ነው የምንሄደው፡፡
  • ውይ ምነው ክቡር ሚኒስትር?
  • በቃ ሁሉ ነገር ደስ አላለኝም፡፡
  • ምን ሆኑ?
  • ስኳሬ ጨምሮ ነው፡፡
  • ስኳር ይልሳሉ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
  • ስኳሬ ጨመረ ሲሉኝ ብዬ ነው፡፡
  • ሙሰኛ እያልከኝ ነው?
  • እሱን እርስዎ አሉ፡፡

  [ክቡር ሚኒስትሩና ሾፌሩ የሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ ሲገቡ በርካታ ቪ8 መኪኖች ቆመዋል]

  • ኪኪኪ…
  • ምን ያስገለፍጥሃል?
  • የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት እዚህ ሆነ እንዴ?
  • ምን እያልክ ነው?
  • እስቲ መኪኖቹን ይመልከቱ አብዛኞቹ ሚኒስትሮች እዚህ ናቸው ማለት ነው፡፡
  • እ…
  • ሁላችሁም ታማችኋል ማለት ነው?
  • እ…
  • ለነገሩማ ሕዝቡም ታሟል፡፡
  • ምን ሆኖ?
  • በእናንተ ምክንያት፡፡
  • እኔ አሁን ከአንተ ጋር የማወራበት አቅም የለኝም፡፡
  • የእርስዎ በሽታ እኮ ይታወቃል፡፡
  • ምንድነው?
  • ሙሌት!

  [ክቡር ሚኒስትሩን ዶክተራቸው እያናገራቸው ነው]

  • ምን ሆኑ ክቡር ሚኒስትር?
  • ጥሩ ስሜት እየተሰማኝ አይደለም፡፡
  • ከሁለት ቀን በፊት ነው እኮ የመረመርኩዎት?
  • ሁሉም ነገሬ ከፍ ብሏል፡፡
  • በቃ እሺ ደምዎትን ልውሰድ፡፡

  [የክቡር ሚኒስትሩን የምርመራ ውጤት ዶክተራቸው ይዞ መጣ]

  • ምንድን ነው በሽታዬ?
  • ክቡር ሚኒስትር የሁላችሁም በሽታ ተመሳሳይ ነው፡፡
  • እንዴት?
  • ሌሎቹም የእርስዎ ጓደኞች ተመሳሳይ በሽታ ነው የያዛቸው፡፡
  • አንድ ዓይነት ነገር ነው እንዴ የምንበላው?
  • የምትበሉት አገርማ ተመሳሳይ ነው፡፡
  • የምትበሉት አገር ነው ያልከኝ?
  • የምትበሉት ነገር ተመሳሳይ ነው፡፡
  • ለመሆኑ በሽታችን ምንድን ነው?
  • ሙሌት ነው፡፡
  • ሙሌት ደግሞ ምንድን ነው?
  • ሙስና፣ ሌብነትና ትምክህት!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

  የትጥቅ  መፍታት ሒደትና የሰላም እንቅፋቶች

  የትግራይ ተራሮች ከጦር መሣሪያ ጩኸት የተገላገሉ ይመስላል፡፡ በየምሽጉ አድፍጠው...

  በሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው

  ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ በክልሎችም ሊቋቋም ነው በቅርቡ ተቋቁሞ ወደ...

  የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚመራና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ተቋም የመመሥረት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ

  የኢንሹራንስ (መድን) ዘርፍን የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...

  ዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን በበይነ መረብ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ

  በሁሉም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሐ ግብሮች የሚመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር! ቀድሜ ቀጠሮ እንዲያዝልኝ ስጠይቅ እንደገለጽኩት በተቋሙ ሠራተኛ ተወክዬ ነው የመጣሁት። እንዴ? አንተ የእኛ ተቋም ባልደረባ አይደለህም...

  [የተቃዋሚ ፓርቲው ትይዩ ሚኒስትር ክቡር ሚኒስትሩ ጋ ደውለው መንግሥት በሙሰኞች ላይ ለመውሰድ ስላሰበው የሕግ ዕርምጃ ሐሳብ እየተለዋወጡ ነው]

  ሄሎ… ማን ልበል? ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ጤና ይስጥልኝ… ማን ልበል? የእርስዎ ትይዩ ነኝ፡፡  አቤት? ያው ፓርቲዬን ወክዬ የፍትሕ ሚኒስትሩ ትይዩ ነኝ ማለቴ ነው፡፡ ኦ... ገባኝ… ገባኝ...  ትንሽ ግራ አገባሁዎት አይደል? ትይዩ...

   [ክቡር ሚኒስትሩ እራት እየበሉ መንግሥትን በሚተቹ ጋዜጠኞች ላይ እየተወሰደ ያለውን ዕርምጃ የተመለከተ መረጃ እየቀረበላቸው ነው]

  ለጋዜጠኞቹ መንግሥትን እንዲተቹ መረጃ የሚሰጧቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው፡፡ እነሱ አይደሉም፡፡ እና የትኞቹ ናቸው? እዚሁ ከተማችን የሚገኙ ምዕራባውያን ናቸው። እንዴት ነው መረጃውን የሚያቀብሏቸው? እራት እያበሉ ነው። ምን? አዎ፣ እራት ግብዣ ይጠሯቸውና መተቸት...