Saturday, March 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለሪዮ ኦሊምፒክ አትሌቶች የስድስት ሚሊዮን ብር ሽልማት ተበረከተ

ለሪዮ ኦሊምፒክ አትሌቶች የስድስት ሚሊዮን ብር ሽልማት ተበረከተ

ቀን:

  አልማዝ አያና ልዩ ተሸላሚ ሆናለች

በሪዮ ኦሊምፒክና በሪዮ ፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ላገኙ፣ እንዲሁም ለዲፕሎማ ተሸላሚዎችና ተሳታፊ አትሌቶች የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ስድስት ሚሊዮን ብር ሸለመ፡፡

 በብሔራዊ ቤተ መንግሥት መስከረም 19 ቀን 2009 ዓ.ም. በተከናወነው ሥነ ሥርዓት በሪዮ ኦሊምፒክ በተለይም በ10,000 ሜትር የዓለምን ክብረ ወሰን በመስበር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው አልማዝ አያና የወርቅ ‹‹ኒሻን›› እና 1.4 ሚሊዮን ብር የሚገመት ኒሳን የቤት አውቶሞቢል ተበርክቶላታል፡፡ የ23 ዓመቷ አልማዝ የተዘጋጀላትን ሽልማት የተቀበለችው ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እጅ ነው፡፡

የብር ሜዳሊያ ላስመዘገቡት ገንዘቤ ዲባባ፣ ፈይሳ ሌሊሳና በፓራሊምፒኩ    1,500 ሜትር ሁለተኛ የወጣው ታምሩ ደምሴ ለእያንዳንዳቸው 500,000 ብር፣ እንዲሁም የነሐስ ሜዳሊያ ላስገኙት ጥሩነሽ ዲባባ፣ ማሬ ዲባባ፣ ታምራት ቶላና ሐጎስ ገብረ ሕይወት በተመሳሳይ 200,000 ብር ተሸልመዋል፡፡ በኦሊምፒክ አራተኛ በመውጣት (ዲፕሎማ) ላስገኙ አትሌቶች ለያንዳንዳቸው 50,000 ብርና ለተሳታፊ አትሌቶች ደግሞ 26,000 ብር ተበርክቶላቸዋል፡፡

በተያያዘም ለብሔራዊ አሠልጣኞች በየውድድር ዓይነቱ ባስመዘገቡት የሜዳሊያ መጠን ከ100,000 እስከ 15,000 ብር በሽልማቱ ከተካተቱት ይጠቀሳሉ፡፡

  ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሪዮ ኦሊምፒክ ከሌሎች ኦሊምፒኮች ያነሰ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ገልጸው፣ ለወደፊቱ ግን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ በማድረግ ኅብረተሰቡንም ሆነ አገሪቱን ሊያኮራ የሚችል ውጤት ለማምጣት መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

የተገኘው ውጤት ከዕቅዱ አንፃር ዝቅተኛ መሆኑን በመጥቀስ አስተያየት የሰጡት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው፣ የሪዮ ኦሊምፒክ ለሚቀጥሉት ሥራዎች በተለይ ከአራት ዓመት በኋላ ለሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጠቋሚ ነገሮችን ትቶ ያለፈ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ሚኒስቴሩ ለ31ኛው ኦሊምፒያድና ለ15ኛው ፓራሊምፒያድ ለተሳተፉት ቡድኖች ያቀረበው ሽልማት 5.956 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

በሪዮ ኦሊምፒክ ብቸኛዋን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበችው አልማዝ አያና ከሥነ ሥርዓቱ በኋላ በአንድ በኩል ሽልማቱ እንዳስደሰታት፣ በሌላ በኩል ደግሞ እሷ በተለይም አሁን ለደረሰችበት ደረጃ ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል ብላ የምታምነው ባለቤቷና አሠልጣኟ ሶሬሳ ፊዳ ዕውቅና አለመሰጠቱ ቅር እንዳሰኛት ስትናገር ተደምጣለች፡፡

ይህንኑ የአትሌቷን አስተያየት አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሥነ ሥርዓቱ ታዳሚዎች በበኩላቸው፣ አትሌቲክሱን አሁን ከሚገኝበት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ከታሰበ ባለሙያተኞችን በአግባቡና በቅጡ መለየት እንደሚያስፈልግ ያምናሉ፡፡ ምክንያቱን አስመልክተውም በሪዮ ኦሊምፒክ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበችው አልማዝ አያና በሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ወቅት ሳይቀር ልምምዷን ሙሉ ለሙሉ ስታከናውን የቆየችው በባለቤቷ ሶሬሳ ፊዳ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ ይኼ ጉዳይ በአልማዝ አያና እንደማይወሰን ያከሉት አስተያየት ሰጪዎቹ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ሌሎች ውጤት ያልመጣላቸው አትሌቶች በተመሳሳይ ለውጤታማነታቸው በሚመርጡዋቸው አሠልጣኞች ሲሠለጥኑ መቆየታቸውን ጭምር ነው ያስረዱት፡፡ በመጨረሻም መንግሥትም ሆነ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እነዚህን ለመሰሉ የዕውቅና መድረኮች ሰዎችን ለሽልማት ሲያቀርቡ መጀመርያ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ትክክለኛውን አካል በመለየት በተለይም በአሁኑ ወቅት ትልቅ አደጋ ተደቅኖበት ለሚገኘው አትሌቲክስ የኃላፊነት ድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ነው፡፡

በነሐሴ 2008 ዓ.ም. በተካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ስምንት ሜዳሊያዎች ማግኝቷ ይታወሳል፡፡ አልማዝ አያና (ወርቅና ብር በ10,000 እና 5,000 ሜትር)፣ ጥሩነሽ ዲባባ (ነሐስ በ10,000 ሜትር)፣ ታምራት ቶላ (ነሐስ 10,000)፣ ገንዘቤ ዲባባ (ብር 1,500 ሜትር)፣ ማሬ ዲባባ (ነሐስ ማራቶን)፣ ሐጎስ ገብረሕይወት (ነሐስ 5,000 ሜትር) እና ፈይሳ ሌሊሳ (ብር ማራቶን) የገንዘበ ሽልማት ካገኙት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በጳጉሜን 2008 ዓ.ም. በተከናወነው የሪዮ ፓራሊምፒክ ብቸኛውን የብር ሜዳሊያ ያገኘው በዓይን ጉዳት 1,500 ሜትር ሩጫ ተወዳድሮ ሁለተኛ የወጣው ታምሩ ደምሴ ሌላው ተሸላሚ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...