[የክቡር ሚኒስትሩ ልጅ ፌስቡክ እያየች ታለቅሳለች]
- ምን ሆነሽ ነው የምታለቅሽው?
- እህ… እህ… እህ…
- አንቺ ምን ሆነሻል?
- በጣም ነው የከፋኝ?
- ማን አባቱ ነው አንቺን ልጄን የሚያስከፋው?
- አንተ ራስህ፡፡
- ምን?
- አንተ ነህ የምታስለቅሰኝ፡፡
- እኔ ደግሞ ምን አደረኩሽ?
- ምን ያላደረከው ነገር አለ?
- አሜሪካ ሄደሽ እንድትዝናኚ አይደል እንዴ ያደረኩት?
- እሱማ አድርገሃል፡፡
- ከዛም ስትመለሺ አውሮፓ ሾፕ እንድታደርጊ አድርጌያለሁ አይደል እንዴ?
- ልክ ነው፡፡
- ይኸው ቻይና ራሴ ይዤ ሄጄ አይደል እንዴ ዩኒቨርሲቲ አስገብቼሽ የመጣሁት?
- እሱንም አድርገሃል፡፡
- ታዲያ እኔ ምን አድርጌ ነው ያስከፋሁሽ?
- ሕዝቤን አስከፍተሃል፡፡
- ምን?
- ሕዝቡ ሲከፋው፣ እኔም ይከፋኛል፡፡
- እኔ ጠፋሁ?
- ምነው ዳዲ?
- የእኔ ኪራይ ሰብሳቢ፡፡
- ኤጭ ዳዲ፡፡
- ፀረ ልማት ሆነሽልኛላ?
- ዳዲ በጣም ነው የሚሰለቸው፡፡
- ምኑ?
- ሁልጊዜ ፀረ ልማትና ኪራይ ሰብሳቢ እያላችሁ ትዘልቁታላችሁ?
- እ…
- በጣም ትሰለቻላችሁ፡፡
- አንዴ ቆይ ይኼን ወሳኝ ስልክ ላንሳ?
- እኔ ስለአገር እያወራውህ ከዚህ በላይ ምን ወሳኝ ነገር አለ?
- ይኼም ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ የደወለላቸውን ጉዳይ አስፈጻሚ ማናገር ጀመሩ]
- ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አቤት፡፡
- ዕቃዎቹ ጂቡቲ ደርሰዋል፡፡
- ሁለቱም ኮንቴይነሮች ጂቡቲ ደረሱ?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ምን ፈልገህ ነው?
- አይ ያው ላሳውቅዎት ብዬ ነው፡፡
- ስማ እኔ ዲመሬጅ መክፈል ሰልችቶኛል፡፡
- በአፋጣኝ እንዲነሱ አደርጋለሁ፡፡
- በጣም ደስ የሚል ዜና ነው የነገርከኝ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከልጃቸው ጋር ማውራት ቀጠሉ]
- ምንድን ነው ዳዲ?
- እ…
- ስለምንድን ነው ያወራኸው?
- አይ የላክናቸው የልዑካን ቡድን ጂቡቲ ደረሱ እያሉኝ ነው፡፡
- አትቀልድ እንጂ?
- ምነው?
- የልዑካን ቡድኑን በኮንቴይነር ነው እንዴ የላካችኋቸው?
- እ…
- ለካ ሕዝቡ ወዶ አይደለም፡፡
- እንዴት?
- በጣም ነው የተማረረው፡፡
- በምኑ?
- በውሸታችሁ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]
- አንቺ ይቺ ልጅ እንዴት ተበላሽታለች?
- ምን አደረገች?
- ከመቼ ጀምሮ ነው ለአገር የምትቆረቆረው?
- ምን ማለት?
- ለሕዝብ ቆሜያለሁ ምናምን ትላለች፡፡
- መብቷ እኮ ነው፡፡
- ምኑ?
- ለሕዝብ መቆምና መቆርቆር ነዋ፡፡
- እንዴ እናትና ልጅ ኪራይ ሰብሳቢ ሆናችሁልኛል ለካ?
- ምን?
- ሁለታችሁም ፀረ ልማት ሆናችኋል፡፡
- ኧረ በፈጠረህ፣ ይኼን ቃል የማልሰማበት ቦታ የት ልሂድ?
- ፀረ ልማት የሆነ አገር ነዋ፡፡
- ስማ ለመሆኑ ሶሻል ሚዲያ ትከታተላለህ?
- ምንድን ነው እሱ?
- እሱንም አታውቅም?
- ምን ኢቢሲ ላይ ያለ ፕሮግራም ነው?
- ኧረ እኔ የምልህ ፌስቡክ ምናምን ነው፡፡
- ይኼ የኒዮሊብራሎቹ ሚዲያ?
- ይኼ እኮ ነው ችግራችሁ?
- እሱ አይደል እንዴ አገር እያፈራረሰ ያለው?
- አገር የምታፈርሱትማ እናንተ ናችሁ፡፡
- ምን?
- እናንተ ናችሁ፡፡
[ለክቡር ሚኒስትሩ ሕንፃቸውን የሚሠራላቸው ኮንትራክተር ደወለላቸው]
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አለቀ?
- ሁሉም ነገር አልቋል፡፡
- መመረቅ ይችላል?
- በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በቃ ዘመድ አዝማድና ወዳጆቻችንን ጠርተን እናስመርቀዋለን፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ስልኩን ዘግተው ከሚስታቸው ጋር ማውራት ቀጠሉ]
- ማን ነው የደወለልህ?
- የሥራ ጉዳይ ነው?
- እኮ ምንድን ነው የሚመረቀው?
- ኮንዶሚኒየም ቤቶች ናቸው፡፡
- አጭበርባሪ፡፡
- ምን?
- ኮንዶሚኒየም ቤት ስታስመርቅ ነው ዘመድ አዝማድና ወዳጆችህን የምትጠራው?
- አንቺ ሴትዮ ምነው ጠመድሽኝ?
- ለምን አልጠምድህ?
- እኔ ከአንድ አይሉ ሁለት ሦስት ቤቶች አልሠራሁልሽም?
- እሱማ ሠርተሃል፡፡
- እሺ ፎቅስ ቢሆን አልገነባሁልሽም?
- አዎ ገንብተህልኛል፡፡
- መጋዘንስ ቢሆን አልገነባሁም?
- ገንብተሃል፡፡
- ታዲያ ምን አደረኩሽ?
- ለራስህማ ታውቅበታለህ፡፡
- ከራስ በላይ ነፋስ አይደል እንዴ ተረቱ?
- እሱ ተረት አሁን ተቀይሯል፡፡
- ምን ተብሎ?
- ከራስ በላይ ሕዝብ!
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሮ አገኙት]
- ምን ሆነሃል አንተ?
- ምን ሆንኩ?
- ከሚስትህ ጋር ተጣላህ እንዴ?
- ከእሷ ጋር ተጣልቼ አላውቅም፡፡
- ታዲያ ምን ሆነህ ነው የከፋህ ትመስላለህ?
- እሱማ በጣም ከፍቶኛል፡፡
- ለምን?
- አገሪቷ ላይ ምን እየሠራችሁ ነው?
- ምን ሠራን?
- እኔ ውጭ ተምሬ የያዝኳትን ዶላር ለአገሬ ሳመጣ፣ እርስዎ ከዚህ ወደ ውጭ ገንዘብ ያሸሻሉ፡፡
- እ…
- እኔ አገር ለማገልገል ደፋ ቀና እላለሁ፣ እርስዎ ራስዎትን ለማበልፀግ ደፋ ቀና ይላሉ፡፡
- በጣም ተናንቀናል፡፡
- ቆየን ከተናናቅን፡፡
[ለክቡር ሚኒስትሩ የመጋዘናቸው ኃላፊ ደወለላቸው]
- አቤት፡፡
- ኧረ ጉድ ጉድ ጉድ፡፡
- የምን ጉድ ነው?
- አቃጠሉት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ደመራውን ነው?
- ደመራው ከተቃጠለ ቆየ እኮ፡፡
- ምንድን ነው የተቃጠለው ታዲያ?
- መጋዘኑ፡፡
- ምን?
- ከነሙሉ ንብረቱ ነው የወደመው፡፡
- መጋዘኔን አቃጠሉት?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለነገሩ ችግር የለውም፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ካሳ እጠይቃለሁ፡፡
- ከማን?
- ከመንግሥት!
[ስልኩ ሲዘጋ ከአማካሪያቸው ጋር ወሬያቸውን ቀጠሉ]
- ክቡር ሚኒስትር ግን ትንሽ አይስማዎትም፡፡
- ምኑ ነው የሚሰማኝ?
- የሕዝብ ብሶት፡፡
- የምን ብሶት?
- የሕዝቡን ገንዘብ በካሳ መልክ ጭራሽ ሊወስዱ?
- መጋዘኔ እኮ ነው የተቃጠለው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የሚሻለው ምን እንደሆነ ያውቃሉ?
- ምንድን ነው?
- ሕዝቡ እግር ላይ ወድቀው…
- ምን?
- ይቅርታ መጠየቅ!
[ክቡር ሚኒስትሩ መኪናቸው ጋ ሄደው ሲያንኳኩ ሾፌሩ አልሰማቸውም፡፡ ከዛም ስልኩ ላይ ሲደውሉለት አይቷቸው በሩን ከፈተላቸው]
- ምን እያደረግክ ነው አንተ?
- አዲስ ስልክ እኮ ገዝቼ ቪዲዮ እያየሁ ተመስጬ ነው፡፡
- ስልክ ብርቅ ነው እንዴ?
- እኔማ የስድስት ወር እቁብ ገብቼ ነው ይህቺን ቴክኖ ሞባይል የገዛሁት፡፡
- ለስልክ ነው የስድስት ወር እቁብ?
- እርስዎማ በስድስት ወር መጋዘን ነው የሚገነቡት፡፡
- ምን ብንገነባም እያቃጠሉት አስቸገሩን?
- በፌስቡክ ሲቃጠል ያየሁት የእርስዎ ነው እንዴ?
- አንተ ይኼን ፌስቡክ ተው አላልኩህም?
- ሕዝቡ የሚከታተለው ፌስቡክን ነው እኮ፡፡
- ኢቢሲን ትቶ?
- ታዲያስ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ተናንቀናል ማለት ነው፡፡
- ሕዝቡ ከናቃችሁ ቆየ እኮ፡፡
- ምን?
- ሕዝቡ ከነቃ ቆየ፡፡
- ለመሆኑ ምንድን ነው የምታየው?
- አንዷ ሠርጓ ላይ የይሁኔን ዘፈን አስከፍታ መንግሥትን ተቃወመች፡፡
- የትኛው የየሁኔን ዘፈን?
- መንግሥትን የመከረበት፡፡
- ምን ብሎ?
- ሰከን በል!
- እውነትም ተናንቀናል፡፡
- ቆየን ስልዎት፡፡
- ምን ይደረግ ነው የሚሉት?
- ክቡር ሚኒስትር ኢሬቻ ላይ የተፈጸመው ምንድን ነው?
- ይኸው ለዩኔስኮ ልናቀርበው የነበረውን በዓል አበላሹብን እኮ፡፡
- ለነገሩ በዓሉማ መቅረቡ አይቀርም፡፡
- ለማን ነው የሚቀርበው?
- ለዩኤን ሴኩዩሪቲ ካውንስል!