– ሞሊኖ የሚባል ኩባንያ ግዙፍ የምግብ ማቀነባበሪያ ለመገንባት አጋር እንደሚፈልግ አስታውቋል
በዘካርያስ ስንታየሁ፣ ኢስታንቡል፣ ቱርክ
ቤዲሳ ግሩፕ የተባለው ግዙፉ የቱርክ ኩባንያ፣ በአንድ ቢሊዮን ዶላር ካፒታል የጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክትን የ75 ከመቶ ድርሻ ለመውሰድ ድርድር መጀመሩን አስታወቀ፡፡ ኩባንያው በዚህ ዓመት መጨረሻ ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት ይፈርማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የቤዲሳ ግሩፕ ሊቀመንበር ቢናይ ቦራን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው ላለፉት ሦስት ዓመታት ከመንግሥት ጋር ድርድር በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ‹‹ድርድሮቹ ፍሬ እያስገኙ በመሆናቸው፣ የበለስ አንድና ሁለት ፕሮጀክቶችን 75 በመቶ ድርሻ ለመያዝ እየተቃረብን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከአዲስ አበባ 576 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአማራ ክልል በአዊ ዞን፣ ጃዊ ወረዳ በቀን 25 ቶን የሸንኮራ አገዳ በመፍጨት ስኳር የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ለመገንባት፣ ጣና በለስ የተቀናጀ የስኳር ልማት ፕሮጀክት በበለሳ ወንዝ ዳርቻ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡
የበለስ አንድና ሁለት ፕሮጀክቶች አጠቃላይ ወጪ 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ሲገመት፣ ከዚህ ውስጥ ቤዲሳ ግሩፕ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ያላነሰውን ገንዘብ ለማቅረብ ተዘጋጅቷል፡፡ የተወሰነውን የፕሮጀክቶቹን ወጪ ከራሱ ለመሸፈን፣ ቀሪውን ከአገር ውስጥና ከውጭ ባንኮች ለማሟላት እንዳቀደ አስታውቋል፡፡ በስኳር ኮርፖሬሽንና በቤዲሳ ግሩፕ መካከል የሚፈረመው ስምምነት ዕውን ከሆነ፣ እ.ኤ.አ. በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ፋብሪካዎቹ አገዳ የመፍጨት ሥራ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡ በሁለቱ የስኳር ፕሮጀክቶች በ50 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ የሸንኮራ አገዳ ተክል፣ እንዲሁም የውኃ ማስተላለፊያ ቦይ ግንባታ ሥራ ከበለሳ ወንዝ ተጠልፎ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ቀደም የተወሰኑ ሥራዎች መጀመራቸው ይታወሳል፡፡
የቤዲሳ ግሩፕ ሊቀመንበር በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የተነሳሱት የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢናሊ ዩልዲሪም፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ፌይዝ ኡልሶይ በሰጧቸው ምክር ተነሳስተው እንደሆነ ለሪፖተር አብራርተዋል፡፡
ከስኳር ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው በአገሪቱ በየዓመቱ 700 ሺሕ ቶን የስኳር ፍጆታ አለ፡፡ ከዚህ ውስጥ 440 ሺሕ ቶን ስኳር በአገር ውስጥ ፋብሪካዎች እየተመረተ በመቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ሆኖ መንግሥት እየገነባቸው በሚገኙ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች አማካይነት በአገሪቱ የሚታየውን የስኳር አቅርቦት እጥረት ከማሟላት በተጨማሪ፣ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ማሰቡን በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ አስቀምጧል፡፡ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የአብዛኞቹን ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ እንዲያከናውን ኮንትራቶች ቢሰጡትም በጊዜ ሊያጠናቅቅ ባለመቻሉ፣ ከተሰጡት አሥር ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ ሰባቱን ተነጥቋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት የስኳር ፋብሪካዎችን ለመገንባት ፈተና እንደገጠመው እናውቃለን፡፡ ዓለም አቀፍ አጋሮች ይፈልግ ስለነበር እኛም በአጋርነት ለመሥራት ፍላጎት አድሮብናል፤›› በማለት ሊቀመንበሩ ቦራን አብራርተዋል፡፡ የኩባንያው ዓለም አቀፍ ተሞክሮም ስኳር ወደ አፍሪካ አገሮችና ወደተቀረው ዓለም ለመላክ ጥሩ ዕድል እንደሚፈጥር ቦራን አክለዋል፡፡
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረው ቤዲሳ ግሩፕ በቱርክና በሳዑዲ ዓረቢያ በርካታ የዋሻ መንገዶችን፣ የአርት ጋለሪዎችንና ግድቦችን በመገንባት ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ አካብቷል፡፡ በሥሩ በሚያስተዳድራቸው ኩባንያዎች አማካይነት ከ59 ያላነሱ አገሮችን አዳርሷል፡፡
በሌላ በኩል ሞሊኖ ሜካኒካል ኢንዱስትሪ ኤንድ ትሬድ የተባለ ሌላ የቱርክ ኩባንያ ኢትዮጵያ የምግብ ማቀነባበሪ ኮምፕሌክስ ለመገንባት አጋር ኩባንያ እያፈላለገ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ የኩባንያው ምክትል ፕሬዚዳንት ሳሊም አላይቤዩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው በኢትዮጵያ አቅም ያላቸውና በዘርፉ ልምድ ያካበቱ ኩባንያዎችን እያፈላለገ ነው፡፡ ሊገነባ የታቀደው የምግብ ማቀነባበሪያ ግዙፍ ኮምፕሌክስ፣ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የአፍሪካ ገበያን ለመቆጣጠር አልሟል፡፡ የሚገነባው ማቀነባበሪያ በ55 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል የሚቋቋም ሲሆን፣ በብዛት በወጪ ንግድ ላይ እንደሚያተኩር ይጠበቃል፡፡
ከቱርክ ወደ አፍሪካ የምግብ ውጤቶች ለመላክ የሚጠይቀው ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ ፋብሪካውን በኢትዮጵያ ለማቋቋም እንዳስገደዳቸው የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ለማቀነባበሪያ ፋብሪካው ግንባታ የሚመጥን አጋር እንዳገኙ ወዲያውኑ ሥራውን እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው ትክክለኛውን አጋር እንደሚያገናኟቸውና የቢሮክራሲ ውጣ ውረዱም እንደሚቃለልላቸው ተስፋ እንደሰጧቸው ገልጸዋል፡፡
ሞሊኖ እ.ኤ.አ. በ1995 የተቋቋመ በዱቄት ማምረት ቴክኖሎጂ ዘርፍ ልምድ ያካበተ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው ከዱቄት በተጨማሪ የፓስታ ማምረቻ ግብዓቶችን፣ የጥራጥሬ ማከማቻ ጎተራዎችን፣ የዘርና የቅባት ማበጠሪያዎችንና ማሸጊያዎችን የሚያመርትባቸው ፋብሪካዎችም አሉት፡፡