Friday, December 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊቱርክ በኢትዮጵያ ያሉ የፈቱላ ጉለን ትምህርት ቤቶችን በማሪፍ ፋውንዴሽን ለመተካት ጥያቄ አቀረበች

  ቱርክ በኢትዮጵያ ያሉ የፈቱላ ጉለን ትምህርት ቤቶችን በማሪፍ ፋውንዴሽን ለመተካት ጥያቄ አቀረበች

  ቀን:

  ከፈቱላ ጉለን ንቅናቄ ጋር የተያያዙ በኢትዮጵያ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን አዲስ የተቋቋመው ማሪፍ ፋውንዴሽን ተረክቦ እንዲያስተዳድራቸው ቱርክ ጥያቄ አቀረበች፡፡ ፋውንዴሽኑ በመስከረም ወር 2009 ዓ.ም. በቱርክ ፓርላማ የተቋቋመ ነው፡፡

  በቱርክ ኢስታንቡል ከተማ በተካሄደው የቱርክ-አፍሪካ የኢኮኖሚና ቢዝነስ ፎረም ላይ ንግግር ያደጉት የቱርክ ፕሬዚዳንት ሪሴፕ ታይፕ ኤርዶጋን፣ የአፍሪካ መሪዎች የፈቱላ ጉለን ትምህርት ቤቶችን በማሪፍ ፋውንዴሽን እንዲተኩ ጠይቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እነዚህን ትምህርት ቤቶች የቱርክ የትምህርት ሚኒስቴር መረከብ መጀመሩን አውስተው፣ የአፍሪካ መሪዎች ሒደቱን እንዲደግፉ ጠይቀዋል፡፡

  የቱርክ ዓለም አቀፍ ልማትና ትብብር ኤጀንሲ (ቲካ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሴርዳር ካም ለሪፖርተር እንደገለጹት ፋውንዴሽኑ በሶማሊያ፣ በሱዳን፣ በጋቦንና በጊኒ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ተረክቧል፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋርም ድርድሮች እየተካሄዱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

  እ.ኤ.አ. ሐምሌ 15 ቀን 2016 በቱርክ የተካሄደው ያልተሳካ መፈንቅለ መንግሥት ለ246 ሰዎች መሞትና ለ2,194 ሰዎች መጎዳት ምክንያት መሆኑ ይታወሳል፡፡ ለዚህ ድርጊት ተጠያቂ የተደረገውን የፈቱላ ጉለን ንቅናቄ ከመላው አገሪቱ ጠራርጎ ለማስወጣት የቱርክ መንግሥት ምርመራ እንዲጀምር ምክንያት ሆኗል፡፡ በአሜሪካ ፔንሲልቫኒያ የሚኖሩት ፈቱላ ጉለን መፈንቅለ መንግሥቱን እንደመሩ ቱርክ ትከሳለች፡፡ ሽብርተኝነት በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚያደርሰውን ውድመት በማጉላት የአፍሪካ መሪዎች የፈቱላ ጉለንን ንቅናቄ ለመዋጋት ከቱርክ ጎን እንዲሠለፉ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የፈቱላ ጉለን ንቅናቄ በ170 አገሮች የሚንቀሳቀስ ቢሆንም፣ በአፍሪካ አኅጉር በጣም ሰፊ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ በማስታወስ የአፍሪካ አገሮችን አስጠንቅቀዋል፡፡

  የቲካ ፕሬዚዳንት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፋውንዴሽኑ እ.ኤ.አ. በ2017 በጀት ዓመት ከቱርክ መንግሥት 150 ሚሊዮን ዶላር ይመደብለታል፡፡ በዚህ ምክንያት የአፍሪካ መሪዎች ስለትምህርት ቤቶቹ ዕጣ ፈንታ የሚያሳስባቸው ነገር አይኖርም ብለዋል፡፡ ዶ/ር ካም፣ ‹‹ትምህርት ለአፍሪካ እጅግ አስፈላጊ ነገር እንደሆነ እናውቃለን፡፡ የአፍሪካ መሪዎችም ለትምህርት ቤቶቹ የተሳለጠ ሽግግር እንደሚፈልጉ እንረዳለን፤›› ብለዋል፡፡ የቱርክ መንግሥት ማሪፍ ፋውንዴሽንን ያቋቋመው በዚሁ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

  ከቱርክ ውጪ ለሚኖሩ ቱርኮችና ተዛማጅ ማኅበረሰቦች ጉዳይ ኤክስፐርት የሆኑትና በፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት የሚሠሩት ሙስጠፋ ኢፌ፣ የፈቱላ ጉለን ንቅናቄ የሚደግፋቸው ትምህርት ቤቶች ከመፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፍ በኋላ የገንዘብ ችግር ሊኖርባቸው እንደሚችል ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ‹‹ማንም ሽብርተኛ ድርጅትን የመደገፍ ፍላጎት ሊኖረው አይችልም፤›› ብለዋል፡፡ በትምህርት ቤቶቹ ቀጣይነት የሚፈለግ ከሆነ የአፍሪካ መሪዎች ለማሪፍ ፋውንዴሽን ቢያስተላልፉ እንደሚመከርም ገልጸዋል፡፡

  በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ አያሌው ጎበዜ የቱርክ ጥያቄ ለኢትዮጵያ መቅረቡን አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹ቱርክ በትምህርት ቤቶቹ ላይ ያላትን ጥያቄዎች እየመረመርን ነው፡፡ ጉዳዩን ከሕግ አኳያም እያየነው ነው፤›› ያሉ ሲሆን፣ ጉዳዩ በመንግሥት ደረጃ ውይይት እየተደረገበት ስለሆነ ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

  በሌላ በኩል ቲካ በኢትዮጵያ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎች ላይ የመልሶ መገንባት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ፕሬዚዳንቱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ኤጀንሲው በሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሚገኘውን የኦቶማን ቱርክ ቆንስላ ሕንፃ ለማደስ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ማውጣቱንም ጠቁመዋል፡፡ ሥራው በቅርቡ እንደሚጠናቀቅና በክልሉ የባህል ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግልም አስታውቀዋል፡፡ ቲካ በተጨማሪም በመቀሌ ከተማ የሚገኘው የንጉሥ አል ነጃሺ መቃብር ቦታ ላይ የመልሶ መገንባት ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡

  የቲካ ፕሬዚዳንት ኤጀንሲው በአዲስ አበባ የአዲስ ትምህርት ቤት ግንባታ እንደሚያከናውንም አመልክተዋል፡፡ ቲካ ይህንን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ውስጥ ተሳታፊ ሲሆን፣ በዓመት 15 ሚሊዮን ዶላር በጀት ይመድባል፡፡

  ቲካ በ50 አገሮች 52 ጽሕፈት ቤቶች ያሉት ሲሆን፣ 15 ያህሉ በኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡ ቲካ በትምህርት፣ በጤና፣ በእርሻ፣ በውኃና ሳኒቴሽን፣ በግንባታ አቅርቦት፣ በባህላዊ ቅርሶች ጥበቃና በሌሎች የልማት ፕሮግራሞች ይሳተፋል፡፡

    በዘካርያስ ስንታየሁ፣ ኢስታንቡል፣ ቱርክ

     

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

  ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ...

  እናት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

  መጠባበቂያን ሳይጨምር የባንኩ የተጣራ ትረፍ 182 ሚሊዮን ብር ሆኗል እናት...

  ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

  ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...