Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከማኅበር ወጥተን ፌዴሬሽን መሆናችን እንደ አገር እያሰብን እንደ አገር እንድንሠራ ያስችለናል››

  አቶ ፍትሕ ወልደሰንበት፣ የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎቶች ሰጪ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት

አቶ ፍትሕ ወልደሰንበት በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ማስተርስ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፣ በUSAID/IQPEP ኃላፊ ሠርተዋል፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ የዞን አምስት ሲሆኑ የውድድር ዝግጅት ኮሚሽነር፣ የባለ አራት ኮከቡ የሴንትራል ሐዋሳ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅና የሐዋሳ ከተማና አሁን በአዲስ የተመሠረተውን የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ለብዙ ዓመታት ማኅበር ሆኖ የቆየውና በቅርቡ ወደ ፌዴሬሽን ያደገውን የሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሠሪዎችና በተያያዥ ጉዳዮች እንዲሁም ወደፊት ፌዴሬሽኑ ምን ሊሠራ እንዳቀደ ታምራት ጌታቸው አቶ ፍትሕን  አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሆቴሎች ማኅበር መቼ ተመሠረተ? ምን ዓላማ በማድረግ ነበር የተመሠረተው?

አቶ ፍትሕ፡- በኢትዮጵያ እንደ ሌሎች ማኅበር ምስረታ ሁሉ ዓላማው በሆቴል ኢንዱስትሪ ያለውን ሁኔታ አንድ በመሆን ችግር ቢመጣ ለመቋቋምና እርስ በርስ ለመረዳዳት በ1967 ታሪክ እንደሚያስረዳው 17 የሚሆኑ በታሪክ የሆቴል ባለቤቶች ነበር የተመሠረተው፡፡ በወቅቱ ስሙ የኢትዮጵያ ሆቴል አሠሪዎች ማኅበር ይባል እንጂ ሆቴሎች በብዛት የነበሩት አዲስ አበባ ውስጥ ስለነበሩ ማኅበሩም አገልግሎቱ በዚሁ አካባቢ የተወሰነ ነበር፡፡ በወቅቱ ነፃ ገበያ ስላልነበር መንግሥት የወሰነውን ዋጋ በመደራደር እንዲያሻሸል በማድረግ ብዙ ችግሮችን በመቋቋምና በመፍታት በቅርቡ እንደ አዲስ በ2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሠሪዎች ማኅበር ተብሎ እስከተቋቋመበት ድረስ አንጋፋ ማኅበር ሆኖ ነበር የቀጠለው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ አዲስ ለማቋቋም ለምን አስፈለገ? መሰል አገልግሎት ሰጪ የሚባሉትስ እነማን ናቸው?

አቶ ፍትሕ፡- የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሠሪዎች ማኅበር ብለን ከስድስት ወር በፊት ነበር እንደ አዲስ የተመሠረተው፡፡ በቅርቡ ደግሞ ፌዴሬሽን እስከሆነበት ድረስ ከስሙ ስንጀምር ዛሬ የሆቴሎች ቁጥር ብቻ ሳይሆን ከእነሱ ጋር የሚሠሩ ካምፓኒዎች ቁጥር መብዛታቸውና ተደራሽነቱም በየክልሉ በማድረግ እንደ አገር በማሰብ ለአገር ለመሥራት ነው፡፡ ሌላው መሰል የሚባሉት ደግሞ አስጎብኚዎች ሱፐር ማርኬቶች፣ የመኪና አከራዮች፣ የጉዞ ወኪሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ሎጆች፣ የሆቴል ዕቃ አቅራቢዎችና ሌሎችም እነዚህ ማለት አንድ ቱሪስት ሲመጣ ከአየር መንገድ ጀምሮ ሆቴል፣ ለጉብኝት፣ ዕቃ የሚገዙበት ሱፐርማርኬትና የሚንቀሳቀስበት መኪና ሁሉም ማለት ይቻላል፡፡ ከሆቴል ኢንዱስትሪ ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ቁርኝት ያላቸው ናቸው፡፡ ከእነሱ ጋር ማኅበር መመሥረት ኢንዱስትሪውን ከማሳደግ ባሻገር በተበጣጠሰ መልኩ ከመንግሥት ጋር የነበረው ግንኙነት በአንድ ድምፅ ለማሰማትም ይሁን ለመደራደር የተሻለ ስለሚሆን ነው ትልቁ ምስል ደግሞ የቱሪዝሙን ዕድገት ስለሚያቀላጥፈው ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም በአንድ ስለሚገኙ፣ አገልግሎት ለማግኘት ደንበኛው ሳይንገላታ መገልገል ይችላል፡፡ ብዙ ሒደት ውስጥ ደግሞ ልምድ ልውውጥ ይኖራል፡፡  ሥራዎች እንዳይደራረቡ ይረዳል፣ በማናቸውም ሥራ ላይ የአገልግሎት አሳጣጥ ችግር ቢኖር ተጠያቂነቱም ችግሩንም ወዲያው ለመፍታት ቀላል ነው፡፡ በአጠቃላይ የነዚህ በአንድ ላይ መጣመር በኢንዱስትሪው ትልቅ ለውጥ ያመጣል ብለን በማሰብ ነው እንደ አዲስ ፌዴሬሽኑ እንዲመሠረት ያሰብነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ወደ ፌዴሬሽን አድጓል፡፡ ምንድነው ልዩነቱ ማኅበሩ አይበቃም?

አቶ ፍትሕ፡- ማኅበር ማለት በቅርበት ያሉ ሰዎች የሚያቋቁሙት ነው፡፡ አገልግሎታቸውም በዛው ቦታ የሚወሰን ነው፡፡ ፌዴሬሽን ማለት ደግሞ የማኅበሮች ስብስብና እንደማኅበር ሳይሆን የሚታሰበው እንደ አገር ነው ችግሮችን ለመፍታት፣ ለመቋቋም፣ ከመንግሥት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ፌዴሬሽን ትልቅ ድምፅና አቅም ይኖረዋል፡፡ በእነዚህና በመሰል ምክንያቶች እነዚህን ማኅበር ወደ ፌዴሬሽን ማሳደግ ትልቅ ጥቅም ነው ያለው፡፡ የኢትዮጵያ ሕግም በተመሳሳይ ሥራ የተሰማሩ ማኅበሮች ወደ ፌዴሬሽን እንዲያድጉ ከዛም ፌዴሬሽኖች ወደ ኮንፌዴሬሽን እንዲያድጉ ይደነግጋለ፡፡ ስለዚህ የእኛም ፌዴሬሽን በማደጉ በመላው ኢትዮጵያ በመንቀሳቀስ መሥራት ያስችለዋል፡፡ ይህም ከአገር ውስጥና ብልጭ ካሉ አቻ ፌዴሬሽኖች በመገናኘት በየቀኑ የሚያድገውን የሆቴል ኢንዱስትሪ ልምድ በመለዋወጥ የአገራችንን የሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሠሪዎች እኩል ማራመድ ያስችለናል ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ከመንግሥት ጋር ኢንዱስትሪውን በተመለከተ ለሚወጡ ፖሊሲዎችና በተለያዩ ጉዳዮች ይማከራል፣ ይደራደራል፣ የአባላቱን ጥቅም ያስከብራል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በምን ያህል ማኅበራቶች ነው ፌዴሬሽን መሆን የቻለው? ምን ያህል ሠራተኛ ይዟል?

አቶ ፍትሕ፡- ፌዴሬሽኑ የተመሠረተው 13 በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የሆቴል የሪዞርት እንዲሁም መሰል አገልግሎት ሰጪ ማኅበራቶች ነው፡፡ አንዱ ማኅበር በስሩ ምናልባት 20 ሆቴሎችን አንዱ ደግሞ 50 ተቋማትትን ለሌሎች የተለያየ ቁጥር የያዙ አሉ፡፡ በእነዚህ ውስጥ ደግሞ በትንሹ አንዱ ሆቴል ወይም ተቋም ከ30 እስከ 300 የሚደርሱ  ሠራተኞችን ይይዛሉ፡፡ ገና መጠይቅ ልከን እየጠበቅን ቢሆንም በሥራቸው በርካታ ሠራተኛ እንደሚንቀሳቀሱ ይገመታል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ፌዴሬሽኑ ለመግባት የግድ በማኅበር መሆን አለበት?

አቶ ፍትሕ፡- በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለ እንደ ማኅበርም እንደ ግለሰብም መግባት ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት የአሠሪዎች ማኅበርም ይሁን ፌዴሬሽን በሆቴል በኩል ሠራተኛን ያለማደራጀት ችግር እንዲሁም ቋሚ የሥራ ዕድል የመንፈግ ሁኔታዎች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ እንደማሳያ በሁለት ትላልቅ ሆቴሎች የተጠረ አለመግባባት በፍርድ ቤት የታየበት ጊዜ ነበር፡፡ አዲሱ ፌዴሬሽን ይህንን ችግር እንዴት ሊፈታው ተዘጋጅቷል፡፡ ሠራተኛስ ተበድያለሁ ብሎ ወደእናንተ መምጣት ይችላል?

አቶ ፍትሕ፡- አዲሱ ፌዴሬሽን የመጀመሪያ ሥራው የሚሆነው ከዚህ በኋላ የተለመደ አሠራሮችን በማስቀረት የሆቴል አሠሪን ማብቃት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕግ በአብዛኛው ወደ ሠራተኛው ነው የሚደለው ይህም በአሠሪው ላይ ጫናን ያመጣል፡፡ የሠራተኛ ማኅበራትን እንዳይቋቋሙ የሚከለክለውም ምናልባት በዚህ ምክንያት ይመስለኛል እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ሲመጡበትም በእጅ ወይም በጠበቀ ነው ለመከላከል የሚሞክረው በአብዛኛው የአሠሪው አዋጅን ምን እንደሚል ብዙም ግንዛቤ የለውም፡፡ በዚህም መብቱንና ግዴታውን ለመውጣትም ይቸግረዋል፡፡ በእነዚህ ምክንያት ሁሌ ጭቅጭቅ ይፈጠራል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታትም የአሠሪ መብትና ግዴታው የሠራተኛው መብትና ግዴታው የሚለውን ጨምሮ የሠራተኛ ማኅበር ቢያቋቋሙ ሁለቱም እንዴት እንደሚጠቀሙ ለአባሎቻችን ትምህርት በመስጠት ችግሩ የሚቀርፈው ይመስለኛል፡፡ ሌላው ሥራው ቀጥይነት እስካለውና 45 ቀን ከሞላው አንድ ሠራተኛ ምንም ክርክር የለውም በነጋታው ቋሚ የማድረግ የሆቴል ባለቤቱ ግዴታ ነው፡፡ ይህን ባያደርግ ሕጉ አይደግፈውም፡፡ ይህም ከዕውቀት ማነስ የሚፈጠር በመሆኑ ለዚህም ትምህርት በመስጠት የሚስተካከልበትን መንገድ አቅደናል፡፡ አንድ ሠራተኛ ወይም የሠራተኛ ማኅበር በአሠሪዬ እንደዚህ ዓይነት በደል ወይም የሕግ ጥሰት ተፈጽሞብኛል ካለ ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሽኑ ማምጣት ሙሉ መብት አለው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ሒደት ውስጥ ያጋጠሟችሁ ችግሮች ምንድናቸው?

አቶ ፍትሕ፡- ከተቋቋመ ገና አጭር ጊዜ በመሆኑም የጎላ ችግሮች አላጋጠሙንም፡፡ አንዳንድ ሆቴሎች ወደ ፌዴሬሽኑን ለመቀላቀል ከመዘግየት በስተቀር፡፡ መንግሥትም ጥሩ እያገዘን ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ አርስዎ የሚመሩት ፌዴሬሽን ግዙፍና በውስጡም በርካታ የሰው ኃይል ያለበት ነው፡፡ ወደፊትም ትላልቅ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች እየመጡ ነው፡፡ እንዲሁም መሰል ተቋማ ኢንዱስትሪውን ሰላማዊ ለማድረግ ወደፊት ምን አስቧል?

አቶ ፍትሕ፡- ይህ እኛ ብቻችንን የምንሠራው ሥራ አይደለም፡፡ የእኛን ጉዳይ ከሚመለከተው ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጀምሮ ባህልና ቱሪዝም የሠራተኛ ኮንፌዴሬሽን በርካታ ከኢንዱስትሪው ጋር የተያያዙ በመተጋገዝ፣ በመተባበር፣ የምንፈጽመው ጉዳይ ነው፡፡ በኛ በኩል እንደ ፌዴሬሽን የሚሠራቸው በርካታ ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ የአሠሪውን መብት ክማስጠበቅ ጀምሮ አንዳንድ ሕጎች እንዲሻሻሉና አዳዲስ እንዲወጡ በማድረግ ቀጣይ በኢንዱስትሪው ለመሳተፍ የሚመጣ ማንኛውም አካል ምንም ችግር ሳይገጥመው መሥራት እንዲችል ማድረግ ነው፡፡ ከአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ባለፈ ሥራውን የሚያሻሽልበትና ደረጃ የሚጠብቅበትንና አገራችንን እንዴት የቱሪዝም መዳረሻ እናድርጋት? ብሎ እንዲያስብ ማስተባበርና ሥልጠና መስጠትም የኛ ሥራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ሰሞኑን በተከሰተው ሁከት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተጎድቷል፡፡ አንዳንድ ሆቴሎችም ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ ለነዚህ ምን እያደረገ ነው?

አቶ ፍትሕ፡- ችግሩ የተከሰተው እኛ ማኅበራችንን ወደ ፌዴሬሽን ገና እያቋቋምን ባለበት ወቅት ቢሆንም ዝም ብለን ቁጭ አላልንም፡፡ የተጎዱ ሆቴሎችን የጉዳታቸውን መጠን መረጃ እያሰባሰብን ነው ያልነው፡፡ ይህንን በማጠናከር ወደ ባህልና ቱሪዝም በመላክ ከሚመለከተው ጋር ስለወደፊቱና ስላለፈው መነጋገርና የመፍትሔ ሐሳቦችን ማስቀመጥ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...

‹‹ኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቀልበስ የፖሊሲ ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ›› ዓለም ባንክ

በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ...