Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ክቡር ሚኒስትር

  [አዲስ የተሾሙት ክቡር ሚኒስትር ከአማካሪያቸው ጋር ቢሯቸው እያወሩ ነው]

  • እንኳን ደስ አለዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንደዚህ አትበለኝ ባክህ?
  • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
  • ኧረ ይኼን መጠሪያ ተወው፡፡
  • የቱን መጠሪያ?
  • ይኼ ክቡር ሚኒስትር የሚለውን፡፡
  • ለምን?
  • በቃ እኔ ልለምደው አልቻልኩም፡፡
  • አይጨነቁ ይለምዱታል፡፡
  • እኔ እኮ ከምርምሩ ዘርፍ ስለመጣሁ ይኼን መጠሪያ መልመድ ከበደኝ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ለእርስዎ እንዲያውም ሌላ መጠሪያ ነው የሚያስፈልግዎት፡፡
  • ምን የሚል?
  • ዶክተር ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ኧረ ባክህ በስሜ ጥራኝ?
  • ስነግርዎት ይለምዱታል፡፡
  • ምኑን ነው የምለምደው?
  • የበፊቱም ሚኒስትር እንዲህ ነበሩ፡፡
  • ማለት?
  • ገና ሲሾሙ ክቡር ሚኒስትር አትበሉኝ ይሉ ነበር፡፡
  • ማን በሉኝ ነበር የሚሉት?
  • ታጋይ በሉኝ ይሉ ነበር፡፡
  • ለነገሩ ታጋይ ነበሩ እኮ፡፡
  • ታዲያ የታገሉት ለአገር ሳይሆን ለራሳቸው ነበራ?
  • እንዴት?
  • ስኳር ይልሱ ነበር፡፡
  • ስኳር ያማቸዋል ነው ያልከኝ?
  • ለነገሩ የስኳር በሽተኛም ነበሩ፡፡
  • እ…
  • ግን የተጨማለቁ ነበር፡፡
  • በምን?
  • በሙስና፡፡
  • ሰምቻለሁ፡፡
  • ለማንኛውም ከስምዎት በላይ ሌላ የሚያስጨንቅ ብዙ ነገር አለ፡፡
  • እ…
  • ሙስናው፣ ኔትወርኩ፣ ብልሹ አሠራር ኧረ ስንቱ፡፡
  • እሱስ ልክ ነህ፡፡
  • እነሱ ላይ ማተኮር ነው፡፡
  • አንድ ጉዞ ነበረኝ፡፡
  • መንፈሳዊ ጉዞ ነው?
  • ኧረ ወደ ውጭ ለመሄድ፡፡
  • ከአገር ውጭ?
  • አዎ፡፡ ምነው?
  • አስፈቅደዋል?
  • ማንን?
  • አለቃዎትን ነዋ፡፡
  • የግል ጉዞ እኮ ነው፡፡
  • ቢሆንም ፈቃድ ማግኘት አለብዎት፡፡
  • ለግል ጉዳይም?
  • ጉዞ ለአገር ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም የሚለው መታየት አለበት፡፡
  • ጉዞውማ እኔን ነው የሚጠቅመው፡፡
  • ይኼን እኮ ነው ያልኩዎት፡፡
  • አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ ለማቅረብ ነው የምሄደው፡፡
  • እ…
  • በዚያው ሰዎችን እተዋወቅበታለሁ፡፡
  • የሚቻል አይመስለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ብዙ ሰውም እተዋወቅበታለሁ እኮ ነው ያልኩህ?
  • ለምን በስልክ አይተዋወቋቸውም?
  • የስልክ አበሌ እኮ 300 ብር ነው፡፡
  • በቫይበር ወይም በዋትስአፕ ይደውሏ?
  • ኢንተርኔት መቼ ይሠራል?
  • ወጣ ብለው ይሞክሯ፡፡
  • ከአገር ነው?
  • ከአዲስ አበባ!

  [ክቡር ሚኒስትሩ ለምሳ ቤት ሲገቡ ሚስታቸውን አገኟቸው]

  • እሺ ሥራ እንዴት ነው?
  • ባክሽ ያስፈራል፡፡
  • ምኑ ነው የሚያስፈራው?
  • ሁሉ ነገር፡፡
  • ማለት?
  • በቃ አብዛኛው ሌባና ሙሰኛ ነው፡፡
  • እና ሥራውን አልወደድከውም?
  • እንደዚያ ማለቴ አይደለም፡፡
  • እስቲ የወደድካቸውን ነገሮች ንገረኝ?
  • መኪናዬን በጣም ወድጃታለሁ፡፡
  • እውነት?
  • በቃ በሾፌርም ስለምሄድ ነው መሰለኝ በጣም ተመችታኛለች፡፡
  • ሌላስ?
  • ያው አሁን ያለኝ ክብር ሌላ ነው፡፡
  • ማለት?
  • ሁሉም ክቡር ሚኒስትር ክቡር ሚኒስትር ሲለኝ ነው የምውለው፡፡
  • እሺ ሌላስ?
  • ያው እንግዲህ የተሰጠንን አዲሱ ቤታችንን በጣም ወድጄዋለሁ፡፡
  • ስማ አሁን ማስተዋል አለብህ፡፡
  • ምን ላስተውል?
  • እነዚህ ነገሮች ከአንተ ጋር ላይቀጥሉ ይችላሉ፡፡
  • ማለት?
  • ጊዜያዊ ነገሮች ናቸው፡፡
  • ምን እያልሽ ነው?
  • ዘለቄታዊ ልታደርጋቸው ይገባል፡፡
  • ሴትዮ ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?
  • ተረቱን በደንብ ታውቀዋለህ፡፡
  • የቱን ተረት?
  • ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለውን፡፡
  • አንቺ ጤና ያለሽ አትመስይኝም፡፡
  • በጣም ጤነኛ ነኝ፡፡
  • ሙሰኛ ሁን ነው የምትይኝ?
  • አልወጣኝም፡፡
  • እና ምን እያልሽ ነው?
  • ዕድሉን ተጠቀምበት፡፡
  • እ…
  • ተረቱን ነው የነገርኩህ፡፡
  • እኔ ተረቱን ቀይሬዋለሁ፡፡
  • ምን ብለህ?
  • ሲሾም ያልሠራ ሲሻር ይቆጨዋል ብዬ፡፡
  • ሰውዬ ተረት ኪስ አይገባም፡፡
  • ምን አልሽ?
  • የወደፊቱን አስብ፡፡
  • የወደፊቱንማ የማታስቢ አንቺ ነሽ፡፡
  • የወደፊቱን ካሰብክማ ያልኩህን ታደርጋለህ፡፡
  • ያልሽኝንማ ባደርግ የወደፊቴ ቂሊንጦ ነው፡፡
  • የአንተ ትንሽ መታሰር በቂሊንጦ፣ እኛን ያኖረናል አንበላጦ፡፡
  • አንቺ በጣም ደፋር ነሽ፡፡
  • ነገርኩህ ክቡር ሚኒስትር አስብበት፡፡
  • ምኑን ነው የማስብበት?
  • በጊዜ መመረቅ አለብህ፡፡
  • ከምን?
  • ከክቡር ሚኒስትርነት፡፡
  • ወደ ምንድን ነው የምመረቀው?
  • ወደ ክቡር ኢንቨስተር!

  [የክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ የሥራ ባልደረባ ደወሉላቸው]

  • እንዴት ነህ ወዳጄ?
  • እንዴት ነህ ክቡር ሚኒስትር?
  • ኧረ ይኼን ክቡር ሚኒስትር ተወው፡፡
  • እንዴት ነው አዲሱ ሥራ?
  • እንዳሰብኩት አይደለም፡፡
  • ማለት?
  • በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡
  • ምኑ ነው የሚያስቸግረው?
  • የሙሰኛው ብዛት አንገሽግሾኛል፡፡
  • እሱማ ይታወቃል፡፡
  • እንዴት እንደምመራው አላውቅም፡፡
  • ወዳጄ ምን ነካህ?
  • ምነው?
  • እንኳን አንተ ስንቱ ሙሰኛ ሲመራው አልነበረም እንዴ?
  • እኔም የጨነቀኝ እኮ እሱ ነው፡፡
  • ምኑ ነው የጨነቀህ?
  • አገሪቷ ላብራቶሪ ሆነች፡፡
  • እ…
  • ሁላችንም እየተፈራረቅንባት ምን ትሆናለች ብዬ ነው፡፡
  • ስማ አንተ የታወቀ ተመራማሪ ስለሆንክ ቢያንስ ከሙሰኞቹ ትሻላለህ፡፡
  • እሱንማ አውቃለሁ፡፡
  • ስለዚህ 100 ሚሊዮን ሰው ከጀርባ ሆኖ ያይሃል፡፡
  • እሱ እኮ ነው የሚያስደነግጠኝ፡፡
  • አገሪቷ ከአንተ ብዙ ትጠብቃለች፡፡
  • እኔም ለማገልገል እኮ ቆርጫለሁ፡፡
  • እኔም የደወልኩት ተስፋ እንዳትቆርጥ ለማበረታታት ነው፡፡
  • ብቻ ፈተናው ቀላል አይደለም፡፡
  • ወዳጄ አንተ ስንተ ፈተና ተፈትነህ ያለፍክ ሰው ነህ፡፡
  • ለማንኛውም የቻልኩትን አደርጋለሁ፡፡
  • ከሙሰኞቹ ግን ተጠበቅ፡፡
  • መንቀሳቀሻ ያሳጡኝ እነሱ ናቸው፡፡
  • ምክሬ አንድ ነው፡፡
  • ምንድን ነው ምክርህ?
  • በሀቅ አገልግሎት!

  [አንድ ኢንቨስተር ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገባ]

  • ሰላም ክቡር ሚኒስትር?
  • ማን ልበል?
  • እንኳን ደስ አለዎት ለማለት ነው፡፡
  • ማን ነህ አንተ ግን?
  • እኔ ለዚህች አገር ጠቃሚ ሰው ነኝ፡፡
  • እ…
  • በርካታ ኢንቨስተሮችን ወደ ኢትዮጵያ ያመጣሁ ሰው ነኝ፡፡
  • ደላላ ነህ ማለት ነው?
  • ኧረ ኢንቨስተም አድርጌያለሁ፡፡
  • ስለዚህ ደላላ ኢንቨስተር ነህ ማለት ነው?
  • ክቡር ሚኒስትር ቁልፍ ሰው ነኝ እኔ፡፡
  • የምን ቁልፍ?
  • ለአገሪቷ ቁልፍ ሰው ነኝ፡፡
  • አሁንማ ማን እንደሆንክ አስታወስኩኝ፡፡
  • እ…
  • ከበፊቱ ሚኒስትር ጋር አገሪቷን ስትቦጠቡጧት ነበር አይደል?
  • አይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ተሳሳትኩ?
  • የበፊቱም ሚኒስትር ችግር ነበረባቸው፡፡
  • እሱማ ነበረባቸው፣ ለዚያም ነው የተቀየሩት፡፡
  • እኔ እንደምፈልገው አይሄዱልኝም ነበር፡፡
  • እ…
  • መነሳታቸው ላይቀር በደንብ ሳይበሉ ተነሱ፡፡
  • አታፍርም ትንሽ?
  • ክቡር ሚኒስትር እኔን ሳይዙ ምንም መሥራት አይቻልም፡፡
  • ማን ነው ያለው?
  • አልሰሙኝም እንዴ ቁልፍ ሰው ነኝ እኮ፡፡
  • እንደ አንተ ዓይነቱን ሙሰኛ አልሰማም፡፡
  • ሲስተሙ በእጄ ነው፡፡
  • እያስፈራራሃኝ ነው?
  • ኧረ ምን በወጣኝ?
  • እና?
  • እየመከርኩዎት ነው፡፡
  • የአንተ ምክር በአፍንጫዬ ይውጣ፡፡
  • ለማንኛውም ቁጥርዎትን ይስጡኝ?
  • አሁን የእኔን ቁጥር አታውቀውም?
  • የስልክዎትን አይደለም፡፡
  • ታዲያ የምኔን ነው?
  • የባንክ አካውንትዎን!   

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ሰርጌ ላቭሮቭ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ምዕራባውያንን አጣጣሉ 

  የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ለአፍሪካ አገሮች ላደረጉት...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

  የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ያገኘው ፔይሊንክ አክሲዮን ማህበር ምሥረታውን አካሄደ

  ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያቀደው...

  የተወሳሰበው ሰላም የማስፈን ሒደት

  የደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ብዙም ሳይዘገይ የኬንያው ቀጣይ...

  በግብርና ዘርፍ ለመሰማራት ያቀደው ድርዜማ

  ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ ባሉ የተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች በአክሲዮን ኩባንያ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  [የተቃዋሚ ፓርቲው ትይዩ ሚኒስትር ክቡር ሚኒስትሩ ጋ ደውለው መንግሥት በሙሰኞች ላይ ለመውሰድ ስላሰበው የሕግ ዕርምጃ ሐሳብ እየተለዋወጡ ነው]

  ሄሎ… ማን ልበል? ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ጤና ይስጥልኝ… ማን ልበል? የእርስዎ ትይዩ ነኝ፡፡  አቤት? ያው ፓርቲዬን ወክዬ የፍትሕ ሚኒስትሩ ትይዩ ነኝ ማለቴ ነው፡፡ ኦ... ገባኝ… ገባኝ...  ትንሽ ግራ አገባሁዎት አይደል? ትይዩ...

   [ክቡር ሚኒስትሩ እራት እየበሉ መንግሥትን በሚተቹ ጋዜጠኞች ላይ እየተወሰደ ያለውን ዕርምጃ የተመለከተ መረጃ እየቀረበላቸው ነው]

  ለጋዜጠኞቹ መንግሥትን እንዲተቹ መረጃ የሚሰጧቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው፡፡ እነሱ አይደሉም፡፡ እና የትኞቹ ናቸው? እዚሁ ከተማችን የሚገኙ ምዕራባውያን ናቸው። እንዴት ነው መረጃውን የሚያቀብሏቸው? እራት እያበሉ ነው። ምን? አዎ፣ እራት ግብዣ ይጠሯቸውና መተቸት...

  [ክቡር ሚኒስትሩ ከፕሮፓጋንዳ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢው ጋር ስለ ሰሜኑ የሰላም ስምምነት ትግበራ መረጃ እየተለዋወጡ ነው]

  እኔ ምልህ፡፡ አቤት ክቡር ሚኒስትር? የሰሜኑ ተዋጊዎች ከሠራዊታችን ጋር መቀራረብ ጀመሩ የሚባለው እውነት ነው?  አዎ። እውነት ነው ክቡር ሚኒስትር።  ከማንም ትዕዛዝ ሳይጠብቁ ነው ከእኛ ሠራዊት ጋር መቀላቀል ጀመሩ...