Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናአቶ መላኩ ፈንታ በአገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት መማረራቸውን ለፍርድ ቤት ተናገሩ

  አቶ መላኩ ፈንታ በአገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት መማረራቸውን ለፍርድ ቤት ተናገሩ

  ቀን:

  ‹‹ለዚች አገር ነፍሳችንን በሰጠን ወንጀለኞች ተደረግን›› አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ

  በተጠረጠሩባቸው የሙስና ወንጀሎች በሦስት መዝገቦች ክስ የተመሠረተባቸውና ላለፉት ሦስት ዓመታት በክርክር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የኢትዮጵያ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ተስፋ መቁረጣቸውንና መማረራቸውን በፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

  አቶ መላኩ መማረራቸውን የተናገሩት፣ በመዝገብ ቁጥር 141356 በተመሠረተባቸው ክስ ላይ ክሱን ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ብይን ለመንገር ማክሰኞ ኅዳር 6 ቀን 2009 ዓ.ም. የቀጠረ ቢሆንም፣ በዕለቱ ብይኑን መንገር አለመቻሉን ገልጾ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ ተከትሎ ነው፡፡

  ፍርድ ቤቱ በጽሕፈት ቤት በኩል ለአቶ መላኩና ሌሎቹም ተከሳሾች ‹‹ተከላከሉ ወይም መከላከል ሳያስፈልጋችሁ በነፃ ተሰናብታችኋል›› የሚለውን ብይን እንደሚሰጥ ተከሳሾቹ የጠበቁ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ግን ለፍትሕ አሰጣጥ ይረዳ ዘንድ ቀሪ ማስረጃ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም በመዝገብ ቁጥር 141356 ከተከሰሱት ውስጥ ከ8ኛ እስከ 11ኛ ያሉ ተከሳሾች (ነጋዴዎች) በሚሌ፣ በአዳማና በቃሊቲ የፍተሻ ቦታዎች ላይ ጭነት የጫኑ ተሽከርካሪዎቻቸው እንዳይፈተሹ በማድረጋቸው፣ በመንግሥት ላይ የደረሰው ጉዳት ወይም ሊያገኝ የነበረው የቀረጥና የመሳሰሉት ክፍያ ምን ያህል እንደሆነ፣ ባለሥልጣኑ አጣርቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ መስጠቱን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

  ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠቱን እንዳስታወቀ ለወትሮው በጠበቆቻቸው አማካይነት ከመናገር በስተቀር ዝምታን የሚመርጡት አቶ መላኩ ሳግ እየተናነቃቸው ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ ‹‹ከፍትሕ ውጪ እንደታሰርኩ አውቃለሁ፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከአንድ ዓመት በላይ ጥናት አድርጎና ጨርሶ ክስ እንደመሠረተ ገልጿል፡፡ እኔም ለሥርዓቱና ለፍትሕ ሥርዓቱ ስል እመላለሳለሁ፡፡ አሁን ግን ሰው እየገደላችሁና የገዳዮች መሣሪያ እየሆናችሁ ነው፡፡ ይኼ በአገር ሥርዓት ላይ ወንጀል መሥራት ነው፡፡ እኔ የተከሰስኩት በውሸት ጨዋታ እንጂ ምንም የፈጸምኩት ወንጀል የለም፡፡ ይኼ መዝገብ ለብይን የተቀጠረው በየካቲት ወር 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ ጨዋታው ስላላለቀ ገና ብዙ እየተሠራ እንጂ፣ እኛ ፍርድ ቤቱ አሁን ትዕዛዝ የሰጠበትን ጉዳይ በመጀመሪያ የክስ መቃወሚያችን ላይ ግልጽ እንዳልሆነ አመልክተን ፍርድ ቤቱ ግልጽ ነው ብሎ ብይን ሰጥቶበታል፡፡ ለምን እንመላለሳለን? ማረሚያ ቤቱ የሚያመላልሰን ሕዝቡ በሚከፍለው ታክስ ነው፡፡ እባካችሁ ውሳኔ ስጡኝና እዚያው ልቀመጥ፤›› በማለት በምሬት ተናግረዋል፡፡

  ‹‹ለዚች አገር ነፍሳችንን የሰጠን ሰዎች ወንጀለኞች ተደረግን፤›› በማለት የተቃውሞ አቤቱታቸውን ያሰሙት ደግሞ የቀድሞ የባለሥልጣኑ ሕግ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረዋህድ  ወልደ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡

  ክሱ ልብ ወለድ መሆኑን፣ እዚህ ደረጃ የደረሰውም የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን በማጋጋላቸውና ሕዝብ ስለፈረደባቸው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ገብረዋህድ፣ የተከሰሱት ውጭ በነበራቸው ልዩነት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ግለሰቦች በመንገሳቸው ያለምንም ምክንያት ሊከሰሱ መቻላቸውንም አስረድተዋል፡፡

  ሌሎቹም ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካይነት እንደተናገሩት፣ ደንበኞቻቸው ከሦስት ዓመታት በላይ በእስር ላይ ናቸው፡፡ ‹‹ውሳኔ ሳያገኙ ስንት ዓመት ነው የሚቆዩት? አሥር ዓመት ወይስ ስንት?›› በማለትም ጠይቀዋል፡፡

  ዓቃቤ ሕግ በክሱ ባልገለጸበትና በምስክሮቹና በማስረጃ ሰነዶቹ ባላስረዳበት አካሄድ ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግን ሥራ ለምን እንደሚሠራ እንዳልገባቸው የጠየቁት ጠበቆቹ፣ ፍርድ ቤቱ ክሱን ውድቅ አድርጎ ብይን ሊሰጥ ይገባ እንደነበር ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

  ፍርድ ቤቱም በሰጠው ምላሽ ይኼንን ትዕዛዝ የሰጠው ክሱን ከመሠረቱ ለመመርመር ወይም ሌላ ትንታኔ ለመስጠት ሳይሆን፣ ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት ወሳኝ ስለሆነበት እንደሆነ አስረድቶ፣ ባለሥልጣኑ በአሥር ቀናት ውስጥ የታዘዘውን ሰነድ አዘጋጅቶ ኅዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲያቀርብ ትዕዛዙን አፅንቷል፡፡ የቀረበለትን ሰነድ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለኅዳር 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ያገኘው ፔይሊንክ አክሲዮን ማህበር ምሥረታውን አካሄደ

  ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያቀደው...

  የተወሳሰበው ሰላም የማስፈን ሒደት

  የደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ብዙም ሳይዘገይ የኬንያው ቀጣይ...