Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየፕሪሚየር ሊጉ ደረጃና የተጨዋቾች ክፍያ

የፕሪሚየር ሊጉ ደረጃና የተጨዋቾች ክፍያ

ቀን:

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች በክረምት የተዘዋወሩ ተጫዋቾችን ዝርዝር ከወርሃዊ የደሞዝ ክፍያቸው ጋር ይፋ አድርጓል፡፡

ሃያኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በቀደሙት ጊዜያት ከነበረው የተጨዋች ክፍያ ሒደቱ በመሻሻል አንድ ተጫዋች በአንድ ክለብ ለሚያደርገው የሁለት ዓመት ቆይታ በወርሃዊ ክፍያ እንዲቀመጥ ሐምሌ 2007 ዓ.ም. ባወጣው የዝውውር ደንብ መፅደቁ ይታወሳል፡፡

በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት የአንድ ተጨዋች ወርሃዊ ክፍያ 120 ሺሕ ብር መድረሱ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የላከው መረጃ ያመለክታል፡፡

የዝውውር ደንቡ ከተቀመጠ በኋላ ክለቦች ለተጫዋቾች የሚከፍሉት ገንዘብና በሜዳው ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ ወይም በሊጉ ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ አለመስተዋሉ በብዙዎቹ ዘንድ ጥያቄ ማስነሳቱም አልቀረም፡፡

በፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች በዝውውር ወቅት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ አውጥተው በውድድር ዓመቱ መርሐ ግብር የሊጉን ወገብ ማለፍ ሲሳናቸው ይስተዋላል፡፡ ይኼው ለስፖርቱ ቤተሰብ መነጋገሪያ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡

የፕሪሚየር ሊጉን ጨዋታ በመመልከት የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው አቶ ዘውዱ ዓለሙ፣ ‹‹የቀደሙ ተጫዋቾች ጨዋታ ካጠናቀቁ በኋላ የፅዳት በሚል ክፍያ ተቀብለው የሚጫወቱት የጨዋታ ደረጃ አሁን ከሚታየው እንቅስቃሴ በላይ ማራኪ ነበር፤›› በማለት የነበረውን ልዩነት ይናገራሉ፡፡

እንደ አቶ ዘውዱ አስተያየት ከሆነ፣ ጥያቂው ለምን ተጫዋቹ ይኼን ያህል ገንዘብ ወጣባቸው ሳይሆን፣ በአንጻሩ ተመጣጣኝ የሆነና ደጋፊዎችን ከስታዲየም እንዳይቀር የሚጋብዝና ተመልካቾችን የሚማርክ ጨዋታ ማሳየት እንደሚያስፈልግ ያምናሉ፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው የተጫዋቾች ዝውውር መረጃ መሠረት 73 ተጫዋቾች በክለባቸው ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ የሚያቆያቸው የውል ስምምነት ተቀብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከተዘረዘሩት ወርሃዊ የደመወዝ መጠን ከደደቢት እግር ኳስ ክለብ ወደ አርባ ምንጭ በ2008 ዓ.ም. የተዘዋወረው ታደለ መንገሻ 125 ሺሕ ብር ተካፋይ በመሆን ቀዳሚ ሥፍራውን መያዝ ችሏል፡፡ በዛው ክለብ ውስጥ የሚገኘው እንዳለ ከበደ እንዲሁ 104 ሺሕ ብር ወርሃዊ ክፍያ ያገኛል፡፡ ከደቡብ አፍሪካው ክለብ ወደ አገሩ የተመለሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፊት አጥቂ ጌታነህ ከበድ 100 ሺሕ ብር የሚከፈለው ሲሆን፣ ናይጄሪያዊ የፊት አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ በተመሳሳይ የ100 ሺሕ ብር ተከፋይ በመሆን ቀዳሚዎቹ ሆነዋል፡፡

ከዳሸን ቢራ ወደ ደደቢት የተዘዋወረና ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ተካፋይ እንደሆነ የተነገረለት አስራት መገርሳ 83 ሺሕ በወር ሲከፈለው፣ አርባ ምንጭ ከነማ የሚገኘው ተሾመ ታደለ 79 ሺሕ፣ ወንደሰን ሚልክያስ ከዚያው ክለብ 72 ሺሕ ብር በየወሩ ከሚከፈላቸው ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር እንደየደረጃው እስከ 5,000 ብር ድረስ የሚከፈላቸው ተጨዋቾችም አሉ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ተጫዋች ወደ ፕሮፌሽናል ደረጃ ለመድረስ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉ አቶ ዘውዱ ያምናሉ፡፡ ለዚህ መልስ ይሆን ዘንድ ብዙ የቀድሞ ተጨዋቾች በችግር ተመተው ፊስታል በመሰብሰብና የተለያዩ ቦታዎች በመዞር የገንዘብ ድጋፍ በመጠየቅ ኑሮዋቸውን የሚገፉ መኖራቸውንም ለአብነት ያነሳሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ተጋፍጠው ወደ ክለብ ገብተው ከአሠልጣኞቻቸው ትኩረትን በማጣትና በተለያዩ የግል ጥቅማ ጥቅሞች ባለመስማማታቸው ችሎታቸውን ሳይጠቀሙበት ወደ ሌላ ዘርፍ የተሰማሩ ተጫዋቾች ስለመኖራቸው ጭምር ያክላሉ፡፡

ከዚህ በተቃራኒ በሌሎች አገሮች በተለይም እግር ኳስ ባደገባቸው አገሮች ብዙ ችግሮችን ተጋፍጠው ትልቅ ደረጃ በመድረስ ክለባቸውንና አገራቸውን በአግባቡ ሲያገለግሉ መመልከት አዲስ አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ በተመለከተ የተለያዩ የእግር ኳሱ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ከሆነ፣ በፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች በክረምት ላይ ከሚያወጡት ከፍተኛ ገንዘብ ባሻገር የተጫዋቾችን እንቅስቃሴ በማሳደግ ተፎካካሪ ሲሆኑ አይታይም፡፡

በየውድድር ዘመኑ የሚነሳው የእግር ኳሱ መቀዛቀዝ ጥያቄ የዚሁ ነፀብራቅ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ለዚህም የዳኝነት፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የፕሮግራም አወጣጥ፣ የክለቦች መዳከም፣ የተጫዋቾች ብቃት መውረድ ተጠቃሽ መሆናቸው ጭምር የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም ክለቦች ለተጫዋቾች ከሚያፈሱት ክፍያ አንጻር በውድድሩ ላይም የሚያሳዩት እንቅስቃሴ አለመጣጣም ምላሽ የሚያስፈልገው መሆኑ አመላካች ነው፡፡

በውድድር ዓመቱ 16 ክለቦች በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ የክለቦች መጨመር ከታች ለሚመጡት ክለቦች ዕድል ከመፍጠር አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ቢታመንም፣ ክለቦች የበለጠ ራሳቸውን በመገምገምና ዕቅዶቻቸውን በማስቀመጥ የተሻለ እግር ኳስ በመፍጠር ረገድ አሁን ብዙ እንደሚጠበቅ የሚናገሩ አሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...