Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በጨርቃጨርቅ መስክ የፈነጠቀው አይካ አዲስ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቀኑ ሰባት ሰዓት ነው፡፡ በሃምሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ቱርካዊው ዩሱፍ አይደኒዝ፣ ዓለም ገና ከተማ ወደ ሚገኘው የአይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ቢሯቸው ገና መግባታቸው ነበር፡፡ ፋብሪካው ከአዲስ አበባ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዓለም ገና ከተማ ላይ የተንጣለለ ሲሆን፣ ዩሱፍ አይደኒዝም በፋብሪካው ሕንጻ አምስተኛ ፎቅ ላይ ከሚገኘው ቢሯቸው ቁልቁል በሚታየው መንገድ ላይ የሚሆነውን ይቃኛሉ፡፡

ምንም እንኳ ቀኑን ከሌሎቹ የአዘቦት ቀናት የሚለየው ነገር ባይኖርም አንድ እንግዳ ክስተት ግን ሳይታሰብ ከፋብሪካቸው መግቢያ አካባቢ መታየት ጀምሯል፡፡ ሰዎች እየተበራከቱ፣ እንቅስቃሴያቸውም እየበዛ መጥቷል፡፡ ‹‹ወደ አዲስ አበባ የሚያቀናው መንገድ ላይ ሰዎች በብዛት ሆነው ሲመጡ አየሁ፤›› በማለት በቅርቡ የተከሰተውን በትውስታ ይጥቅሳሉ፡፡

እርግጥም ያ ጊዜ በኢትዮጵያ፣ በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ ፋብሪካዎቻቸውን ለተከሉ ለብዙዎቹ የውጭ ኩባንያዎች በመጥፎ የሚነሳ አስቸጋሪ ቀናትን አስከትሎባቸዋል፡፡ በተለይም በኢሬቻ ግርግር ወቅት የተከሰተውን እልቂት ተንተርሶ በአገሪቱ የታየው ቁጣና ብጥብጥ ለእንደነ አይደኒዝ ያሉ የውጭ ባለሀብቶች የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ‹‹ምን እየተካሄደ ነው ብዬ ስጠይቅ፣ ሰዎች ተቃውሞ እያሰሙ ነው ብለው ነገሩኝ፤›› በማለት ትዕይንቱን ለማስታወስ ይሞክራሉ፡፡ ተቃውሞው እየቀለጠ ጎማ ማቃጠልና መንገድ መዝጋት ደረጃ ሲደርስ፣ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ሲመለከቱም ሚስተር አይደኒዝ ከግርግሩ ሠራተኞቻቸውን እንዴት ያለ ችግር ማስመለጥ እንደሚችሉ ማውጠንጠን ጀምረዋል፡፡ ልብ ያላሉት ነገር ግን ከበታቻቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች የዕለት ሥራቸውን በሚወጡበት ወቅት፣ እሳቸውን ጨምሮ 250 ሚሊዮን ዶላር ያወጡበት ፋብሪካ የሚታደጋቸው የጸጥታ ኃይል ሳይመጣላቸው እንዲሁ አውላላ ሜዳ ላይ መቅረታቸውን ነበር፡፡

‹‹አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከሁሉም አቅጣጫ ጭስ ሲትጎለጎል ማየት ጀመርን፡፡ በአካባቢው ወደሚገኙ የውጭ ኩባንያዎች ስደውልም አብዛኞቹ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተረዳሁ፤›› በማለት ሁኔታውን ይገልጹታል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም የፋብሪካው ማሽኖች ሥራ እንደሚያቆሙ በማዘዝ፣ ሠራተኞችም ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኋን ቀስ በቀስ የፋብሪካውን ቅጥር ግቢ ለቀው እንዲወጡ አድርገዋል፡፡ ሁሉም የፋብሪካው ቴክኒሻኖች በዝግታ ከፋብሪካው ከወጡ በኋላና በአካባቢው ስለደረሰው ጉዳት ሪፖርት ከተደረገ በኋላ ነበር መንግሥት ተጨማሪ የጸጥታ አስከባሪዎችን መላክ የቻለው፡፡

እንደ ዕድል ሆኖም አይካ አዲስ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስበት ከትኩሳቱ መትረፉ እንዳስደሰታቸው ሚስተር አይደኒዝ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ሰባት ሺሕ ያህል ድርጅቱ ሠራተኞች ግን ችግር ይፈጥሩብኛል ብለው እንዳልገመቱም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህ ቤተሰቤ ነው፡፡ የምተማመነው በሠራተኞቼ ነበር፤›› ሲሉም በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡

ለጥቂት ጊዜያት ከሚስተር አይደኒዝ ጋር ቆይታ ያደረገ ሰው ለቢዝነስ በተለይም ለጨርቃጨርቅ ዘርፍ የተለየ አመለካከት ያላቸው ሰው መሆናቸውን ሊገነዘብ ይችላል፡፡ ከ7500 ያላነሱ የአይካ አዲስ ሠራተኞች አብዛኞቹ በፋብሪካው ምክንያት ወደ ሥራ ዓለም የገቡ ናቸው፡፡ ለሥራ የሚመለምሏቸውም ገና ከትምህርት ቤት የወጡትን፣ በብዛትም አሥረኛ ክፍል ያጠናቀቁትን ሲሆን፣ ወዲያውኑ ወደ ሥልጠና ያስገቧቸውና ሲያጠናቅቁ በየሥራ መደቦች ውስጥ ያሰማሯቸዋል፡፡ በአይካ አዲስም ሆነ ምርቱን በሚገዙ የአውሮፓ ኩባንያዎች አማካይነት ለሠራተኞች የሚሰጠው የሥራ ላይ ሥልጠና፣ በጥራት የመሥራትም ሆነ የማምረት ብቃታቸውን በማሻሻል፣ ከሰባት ዓመታት በፈት ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር ይተማመንባቸው የነበሩትን 160 የውጭ ሙያተኞች ቁጥር ወደ 52 እንዲቀንስ አብቅተውታል፡፡

ቱርክኛ ከሚጫነው ንግግራቸው ውስጥ በአብዛኛው የአማርኛ ቃላትና ዓረፍተነገሮች ይደመጣሉ፡፡ አማርኛ ለማውራት ብዙም አይቸገሩም፡፡ አመለካከታቸውን ሥራዬ ብሎ ለተከታተለ ባለፋብሪካው ሰውዬ የውጭ ሰውነት ወይም ባይተዋርነት የማይሰማቸው እየሆኑ መምጣታቸውን ሊገነዘብ ይችላል፡፡ ከአንደበታቸው ‹‹አገራችን››፣ ‹‹መንግሥታችን››፣ ‹‹ሕዝባችን›› የሚሉ ቃላትን ለማድመጥ ብዙ ልፋትን አይጠይቅም፡፡ 20 ሔክታር መሬት ላይ በተንጣለለው ፋብሪካቸው ውስጥ ሲዘዋወሩ ለሠራተኞቻቸው ሰላምታ የሚሰጡትም በአማርኛ ነበር፡፡

በቱርክ ኢስታንቡል ከተማ እ.ኤ.አ. በ1988 የተመሠረተው ተርኪ አይካ ቴክታይል ኮርፖሬሽን፣ ለሩብ ክፍለ ዘመን የተካበተ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ልምድ አዳብሯል፡፡ አይካ ለዓመታት ያደላው ምርቶቹን ለአውሮፓ ገበያ በማርቀቡ ላይ ሲሆን፣ ነገሮች የተቀየሩት ግን ሚስተር አይደኒዝ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በተገናኙበት ወቅት ነበር፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በኢስታንቡል እንዲገናኙ ምክንያት የሆኑት የወቅቱ በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ የዛሬው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ነበሩ፡፡ ‹‹መለስን ያገኘኋቸው በኢስታንቡል አርፈውበት በነበረው ሆቴል ውስጥ ነበር፡፡ በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ባደረግ እንደሚያስደስታቸው ነግረውኛል፡፡ ይህን ከማድረጌ በፊት ግን ኢትዮጵያን መጎብኘት እንዳለብኝም ገልጸውልኛል፤›› በማለት ወደ ኢትዮጵያ የመጡበትን አጋጣሚ አስታውሰዋል፡፡

አመጣጣቸው ከጥሩ መነሻ ቢመጡም እ.ኤ.አ. በ2007 ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ በጎበኙበት ወቅት ያደረባቸው መልካም ስሜት ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ገፋፍቷቸዋል፡፡ አይካ አዲስ በአይካ ቴክስታይል ኮርፖሬሽን ሥር የሚተዳደር ብቸኛው በውጭ አገር የሚንቀሳቀስ እህት ኩባንያ ሲሆን፣ ለሚስተር አይደኒዝም ቢሆን አይካ አዲስ የመጀመሪያው የውጭ አገር ኢንቨስትመንት ተሞክሯቸው ነው፡፡

አይካ አዲስ በ150 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተንጣለለ፣ ዘመናዊና የተራቀቀ ፋብሪካ ሆኖ ለመገንባትና ሥራ ለመጀመር አራት ዓመታት ፈጅቶበታል፡፡ ከበርካታ ሚሊዮን ዶላሮች ባሻገር መላ ትኩረታቸውን የሰጡበት ፋብሪካ ይኸው አይካ አዲስ ፋብሪካ እንደሆነ ሚስተር አይደኒዝ ይገልጻሉ፡፡

ፋብሪካው ሥራ ከጀመረ ከስድስት ዓመታት በኋም እንኳ የውጭ ጎብኝዎች በሚመጡበት ወቅት ራሳቸው መላ ፋብሪካውን ተዟዙረው ማስጎብኘቱን ሥራዬ ብለውታል፡፡ በዚህ እንደሚደሰቱም ከሁኔታቸው መረዳት ይቻላል፡፡ የፋብሪካውን ጥጋጥግ ሳይቀር ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆናቸውም ግርምትን ያጭራል፡፡ ጥቃቅኗ ነገር ሁሉ አታመልጣቸውም፡፡ የሲቪል ሥራዎችና የፋብሪካ ተከላ በሚካሄበት የግንባታ ወቅት ሳይቀር እያንዳንዷን ጥቃቅን ነገር በመከታተል ያስፈጽሙ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ‹‹ትልቅ ፋብሪካ ስገነባ በዘርፉ ያለኝን የ40 ዓመታት ልምድ ማሳየት ነበረብኝ፤›› ይላሉ፡፡ አይካ አዲስ በአውሮፓውያን ዕይታ ሳይቀር ዘመናዊና መጠነ ሰፊ አምራች ተቋም እንደሆነ ያምናሉ፡፡

አይካ አዲስ ሁሉንም የምርት ሒደቶች በአንድ አጣምሮ የያዘና እርስ በርሱ የተሳሰረ ማምረቻ ጣቢያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከጥጥ ፈትል ጀምሮ፣ ዲዛይን የማውጣት፣ ቅድ የማዘጋጀት፣ የስፌት ሥራ፣ የማቅለም ሒደቶችን አካቶ ያለቀ ምርት የማውጣትና የምርት አርማ የማተም፣ የምርት ማሸጊያዎችና የምርት መግለጫ ወረቀቶችን ጨምሮ ሁሉንም የምርት ሒደቶች የሚያጠቃልል ሥልተ ምርት በአንድ ፋብሪካ ውስጥ አካቶ ይገኛል፡፡ ‹‹በአንድ ተቋም ውስጥ የታቀፉ የተለያዩ ፋብሪካዎች ስብስብ ሲሆን፣ እያንዳንዱን ማምረቻም እንደየ ሥራው ጠባይ እንከታተላለን፤›› በማለት ከአንድ ሰዓት በላይ በሚጀው የፋብሪካው ጉብኝት ወቅት አብራርተዋል፡፡

ሁለት ራሳቸውን የቻሉ የፈትል ማምረቻዎች ያሉት አይካ አዲስ፣ አንደኛውን ክር ለማምረት ሲያውለው ሌላኛውን የተቀለመ የጥጥ ለመፍተል ይጠቀምበታል፡፡ በዚህ መንገድ ፋብሪካው በጠቅላላው በቀን 40 ቶን ክር እንዲያመርት ያስችሉታል፡፡ ልዩ ልዩ ማሽነሪዎችን በመጠቀም ከተፈጥሮ ጥጥ፣ ከፖሊስተር፣ ከኒሎንና ከሌሎችም ክር በማምረት ላይ ይገኛል፡፡

በስፌት ሥራው ወቅት ነገሮች መልካቸውን መያዝ ይጀመራሉ፡፡ ልዩ ልዩ መልክና ብዛት ያላቸው ክሮች ወደ ጨርቅነት መቀየር የሚጀምሩትም በስፌት ፋብሪካ ውስጥ ነው፡፡ በቀን 40 ቶን ጨርቅ ማምረት የሚችልባቸው 116 የስፌት ማሽነሪዎች ያለማቋረጥ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ከሚያመርታቸው መካከልም ፖሊስተር፣ ፎጣዎች፣ ድርብ ስፌት ጨርቆች ይጠቀሳሉ፡፡

ከዚህ ሁሉ ግን ሚስተር አይደኒዝ በኩራት የሚመለከቱት የማቅለሚያ ፋብሪካቸው ነው፡፡ በእንፋሎት የሚሠራው ማቅለሚያ ማሽን በዓለም ላይ አዲስ ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ ለማቅለሚያ የሚውሉ ኬሚካሎችን ከማደባለቅ ጀምሮ ለቅመማ የሚውለውን ምጣኔ እስከመለካት ያለውን ሥራ በኮምፒውተር ታግዞ የሚያከናውን መሣሪያ ነው፡፡ በእንፋሎት ማሞቂዎች የሚታገዙት ማቅለሚያ ማሽኖች፣ በቀን 35 ቶን ጨርቅ፣ ዘጠኝ ቶን ክርና የጥጥ ፈትል እንዲሁም 20 ቶን ጨርቅ የመጭመቅና የማጠብ አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ማቅለሚያ ማሽኑ ለማጠብ፣ ለመጭመቅና ለማድረቅ እንፋሎት ብቻ ይጠቀማል ያሉት ሚስተር አይደኒዝ፣ የማቅለሚያ ክፍሉ በሰዓት 20 ቶን እንፋሎትና ሙቅ ውኃ የሚያመነጭ ሲሆን እስከ 70 ቶን የድንጋይ ከሰል ለኃይል ፍጆታው እንደሚጠቀም አብራርተዋል፡፡ አሁን ባለበት ደረጃ ማለሚያው ጨርቅና ክር ለማቅለም እያገለገለ ሲሆን፣ እንደ ሚስተር አይደኒዝ ከሆነ ይህ ዓይነቱ አሠራር በብዙዎቹ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ያልተለደ ነው፡፡ ዘመናዊው ማቅለሚያ ዘመናዊ የማተሚያ ማሽነሪዎችም ተተክለውለታል፡፡ በቀን እስከ ስድስት ቶን የሚደርሱ ከ12 ያላነሱ ልዩ ልዩ ቀለማትን በአንድ ጊዜ የማተም አቅም አለው፡፡

የአልባሳት ማምረቻ ክፍሉ ትልቁን የሰው ኃይል የሚይዝ ሲሆን፣ በፈረቃ የሚሠሩበት፣ የሚቆርጡ፣ የሚሰፉ፣ የሚተኩሱ የሚያሽጉና ሌላውንም ተጓዳኝ ሥራ የሚያከናውኑ 3000 ሠራተኞች የሚራጡበት የምርት ክፍል ነው፡፡ በቀን 75 ሺሕ አልባሳት ይመረቱበታል፡፡ እስከ 80 ሜትር የሚርዝሙ ጨርቆችን የሚያመርቱ አራት የአልባሳት ማምረቻዎች ያሉት ፋብሪካው በዚህ የምርት መስመር ብቻ 45 ሠራተኞችን አሰማርቶ ያለ ማቋረጥ ምርት ያወጣል፡፡

እርስ በርሱ የተቀናጀና ሙሉ ለሙሉ ራሱን የቻለ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ መትከል በጣም ውድ ቢሆንም አይካ አዲስ ግን ምርጥ የሚባለውን ሥርዓት በመከተል ተወዳዳሪና ኤክስፖርት ተኮር ፋብሪካ ለመሆን እንደበቃ ሚስተር አይደኒዝ ይገልጻሉ፡፡ ኩባንያው የሚቀርቡለትን የሥራ ትዕዛዞች በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማቅረብ የሚችልበትን ቀርጠኛ አሠራር የሚከተል በመሆኑም ቺቦን ከመሳሰሉ የጀርመን የአልባሳት ኩባንያ ጋር በመሥራት ምርቶቹን ለማቅረብ አስችሎታል፡፡

ግብዓቶችንና ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ የማስመጣቱ ሒደት በኢትዮጵያ በተለየ መንገድ ጊዜ እንደሚፈጅ የሚጠቅሱት ባለሀብቱ፣ ‹‹ከውጭ ዕቃ አስመጥተን ፋብሪካ ደጃፍ እስኪደርስ ድረስ ሦስት ወር ሊፈጅ ይችላል፡፡ ይህን ያህል ጊዜ መጠበቅ ግን አልችልም፤›› ይላሉ፡፡ በመሆኑም የ30 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው እንደ ኬሚካል፣ ክር፣ አልባሳትና ማቅለሚያ ያሉ ግብዓቶችን በክምችት ለመያዝ መገደዱን አስታውቀዋል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት ጀምሮ የአገሪቱን 60 ከመቶ የጨርቃጨርቅ ኤክስፖርት ድርሻ የተቆጣጠረው አይካ አዲስ፣ የ63 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው ልዩ ልዩ ምርቶችን በመላክ አገሪቱ ካስመዘገበችው የ111.45 ሚሊዮን ዶላር ኤክስፖርት አፈጻጸም ውስጥ ከግማሽ እጅ በላይ ድርሻውን በመያዝ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ እርግጥ አይካ የ100 ሚሊዮን ዶላር ምርት የማምረት አቅም ያለው ቢሆንም አሁንም ድረስ ግን በሙሉ አቅሙ ማምረት ሳይቻለው ቆይቷል፡፡

የሚገጥሟቸውን ፈታኝ ችግሮች በተመለከተ ሲገልጹም አገሪቱ ከወጪ ንግድ ከማግኘት ያቀደችውን የገቢ መጠን ለማሳካት፣ መስተካከል አለባቸው የሚሏቸው ነጥቦች በርካታ ናቸው፡፡ ከሎጂስቲክስ አኳያ የወደብ ክፍያ፣ በአገር ውስጥ ለማጓጓዝ የሚጠይቀው የትራንስፖርት ወጪ በጨርቃጨርቅ መስክ ለተሳመሩ ኩባንያዎች ትልቁን ድርሻ የሚይዙ ችግሮች መሆናቸውን ሚስተር አይደኒዝ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ለምሳሌ ወደ አገር ውስጥ ዕቃዎችን ለማስገባት የወደብ ክፍያው 1150 ዶላር ሲሆን ወደ ውጭ ለመላክ የሚጠይቀው 650 ዶላር ነው፡፡ ይህ ሌሎች ወደቦች ከሚያስከፍሉት 200 ዶላር አኳያ ሲታይ በጣም ውድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ለማጓጓዝ የሚጠይቀውን ወጪ በሚመለከትም፣ ባለ 40 ጫማ ኮንቴይነር ዕቃ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት 2175 ዶላር እንደሚወጣ፣ ወደ ውጭ ለመካልም 1400 ዶላር እንደሚያስከፍል ገልጸው፣ በዓለም አቀፍ ዋጋ አንጻር ከ200 እስከ 300 ዶላር የሚፈጀው የማጓጓዣ በኢትዮጵያ ግን ከሚቻለው በላይ የተጋነነ እንደሆነ በምሬት አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በየአስባቡ የሚከሰተው መጓተትና መጉላላት ለእንደ አይካ አዲ ያሉት ግዙፍ ፋብሪካዎች ከባድ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል፡፡

ይህም ይባል እንጂ የሚብሰው ከባድ ችግር ከጥጥ ጥራት ጋር እንደሚያያዝ ሚስተር አይደኒዝ አበክረው ይናገራሉ፡፡ ‹‹60 ከመቶው የሚሸፍነው ምርታችን ከተፈጥሮ ጥጥ እንደምናመርት ይታወቃል፡፡ ይሁንና የቱንም ያህል የተፈጥሮ ጥት ቢያመርቱ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ አምራቾች የጥራት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት የላቸውም፤›› ያሉት ባለሀብቱ፣ በዚህ ሳቢያ አብዛኛውን የጥጥ ፍጆታ የሚያሟላው ከህንድ በማስመጣት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

የቡታግዝና የከሰል ድንጋይ ዋጋ በኢንዱስትሪው ለሚንቀሳቀሱ አምራቾች እንደ ሬት የሚያስመርሩ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ‹‹ከኢትዮጵያ ጋር ከሚፎካከሩ አገሮች አኳያ የቡታጋዝና የከሰል ድንጋይ ዋጋ ከፍተኛ ሆነው ይገኛሉ፤›› በማለት እስካሁን የተጠቀሱት ማነቆዎች ተደማምረው የአገሪቱን ተወዳዳሪነት ይበልጥ ሊሸረሽሩት እንደሚችሉ ያላቸውን ስጋት ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡

ይሁንና በአገሪቱ ያለው ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ዋጋ ተስፋቸውን ቢገነባውም ተደጋግሞ የሚከሰተው መቆራረጥ ግን ቀዝቃዛ ውኃ ሲችልስበት ቆይቷል፡፡ በመሆኑም አነስተኛ የኃይል ማሰራጫ ጣቢያ በራሳቸው ወጪ ለመትከል መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ሆኖም አይካ አዲስ የማስፋፊያ ግንባታ በአየር ጤና አከባቢ ለማካሄድ መዘጋጀቱን ሚስተር አይደኒዝ አስታውቀዋል፡፡ በአገሪቱ ከሚታየው የጥጥ ምርት አቅርቦትና ጥራት ችግር በመነሳት በኦሞ አካባቢ የፈተጥሮ ጥጥ ለማምረት የሚችሉበት ቦታ ቢረከቡም ፕሮጀክቱ ፈቅ ሊል እንዳልቻለ ታውቋል፡፡

በዓለም የአልባሳት ኢንዱስትሪ ውስጥ በርካታ ፍላጎት ካላቸው ኩባንያዎች ጥያቄ እንደሚቀርብለትና ጥሩ ገበያ እንደገነባም ይናገራሉ፡፡ ‹‹ማሽ አላህ በዚህ ዓመት በቂ ገበያ አግኝቻለሁ፤›› በማለት እ.ኤ.አ. በ2017፣ የ100 ሚሊዮን ዶላር ኤክስፖርት ዕቅዳቸውን እንደሚያሳኩ እርግጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች