Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ለመሸምገል የተሰየመው ጉባዔ አዲስ አመራር እንዲመረጥ ወሰነ

የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ለመሸምገል የተሰየመው ጉባዔ አዲስ አመራር እንዲመረጥ ወሰነ

ቀን:

በመስከረም ወር 2009 ዓ.ም. በእነ አቶ የሺዋስ አሰፋ የተጠራው ጠቅላላ ጉባዔ የፓርቲውን ሕገ ደንብ የተከተለ ቢሆንም፣ ጉባዔው የተካሄደው ምልዓተ ጉባዔው ተሟልቶ መሆን አለመሆኑንና የአመራሮች ምርጫም የተደረገው በሕገ ደንቡ መሠረት መሆን አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ሰነድ ባለመገኘቱ፣ ጠቅላላ ጉባዔው እንደገና ተጠርቶ ምርጫ እንዲካሄድ የሽምግልና ጉባዔው ውሳኔ ማሳለፉ ታወቀ፡፡

ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር)፣ የሕግ ባለሙያ አቶ ተማም አባቡልጉ፣ አቶ ታዲዎስ ታንቱ፣ የአቶ ከተማ ይፍሩ ወንድም አቶ ይልማ ይፍሩና አቶ ብርሃነ ሞገሤ የተካተቱበት ጉባዔ ውሳኔውን ያሳለፈው ቅዳሜ ኅዳር 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ነው፡፡

ጉባዔው ቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በነበሩት ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር)  የሚመራውን የፓርቲውን ቡድንና ፓርቲውን በአሁኑ ጊዜ በሊቀመንበርነት እየመሩት በሚገኙት አቶ የሺዋስ አሰፋ የሚመራውን ቡድን ሐሳብ፣ በጽሑፍና በቃል በመቀበልና በማወያየት ውሳኔ ለማሳለፍ መቻሉን የውሳኔ ሰነዱ ያመለክታል፡፡ ሁለቱም ወገኖች በተመረጡት ሽማግሌዎች ውሳኔ እንደሚስማሙ ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ፣ ጉባዔው የሁለቱንም ወገኖች የቅሬታ ሐሳብ በጽሑፍ መውሰዱን ጠቁሟል፡፡ በመሆኑም ከፓርቲው የተሰረዙ አባላት የፓርቲውን ሕገ ደንብ በተከተለ አግባብ መሆን አለመሆኑን፣ እነ አቶ የሺዋስ ያካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ በሕገ ደንቡ አግባብ መሆን አለመሆኑንና ያላግባብ ባክኗል በተባለው 290,092 ብር ላይ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት፣ ጉባዔው ጭብጥ ይዞ ምርመራውን ማካሄዱን ውሳኔው ያሳያል፡፡

አቶ ይልቃል ጌትነት፣ አቶ ወረታው ዋሴ፣ አቶ ስለሺ ፈይሳ፣ ወ/ሪት ወይንሸት ሞላና አቶ ጌትነት ባልቻ ከአባልነት ስለተሰናበቱበት ሁኔታ የመረመረው ጉባዔው፣ በፓርቲው ሕገ ደንብ መሠረት ዕርምጃው የተወሰደው የሥነ ሥርዓት ኮሚቴ አባላት ቁጥር ተሟልቶና ደንቡን ተከትሎ መሆኑን ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

አቶ ይልቃል እንዲሰናበቱና የወሰዱትን ገንዘብ እንዲመልሱ የተወሰነ ቢሆንም፣ መባረራቸው ለጠቅላላ ጉባዔ ቀርቦ እንዲፈጸም መታዘዙ ደንቡን የተከተለ መሆኑን፣ የሽምግልና ኮሚቴው በውሳኔ ገልጿል፡፡ አቶ ይልቃል ይግባኝ የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ሕገ ደንቡ የሚፈቅድ ቢሆንም ይግባኝ ስለመጠየቃቸው ያሉት ነገር ባይኖርም፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከጻፉት ደብዳቤ ላይ ግን ይግባኝ ስለማለታቸው መረዳቱን ጉባዔው አብራርቷል፡፡

በእነ አቶ የሺዋስ በኩል ከተጻፈ ሰነድ ኮሚቴው እንዳረጋገጠው፣ አቶ ሲሳይ ካሴ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ መሆናቸውንና የአቶ ይልቃልን መሰናበት ስላላመኑበት አልፈርምም በማለታቸውና የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላት ቁጥር ሦስት ብቻ በመሆኑ፣ ከሰባት አባላት ከሦስት በላይ መፈረም እንዳለባቸው ደንቡ ስለደነገገ ተቀባይነት እንደማይኖረውም ጉባዔው ወስኗል፡፡ በእስር ላይ የሚገኘው የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬና ሌሎች ሦስት አባላት የሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ምልዓተ ጉባዔ ሳይሟላ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ይኼም የፓርቲውን ሕገ ደንብ የጣሰ መሆኑን ገልጿል፡፡ እነ አቶ ይልቃል በአጣሪ ኮሚሽኑና አጠቃላይ ጉባዔው ውጤት ውሳኔ ባይስማሙም፣ መብታቸውን በሕግ ለማስከበር ከመንቀሳቀስ ይልቅ ፓርቲውን ጥለው ወጥተው የራሳቸውን አንጃ ለመፍጠር አካሄድ መሄዳቸው የፓርቲውን ሥራና ዓላማ የሚጎዳ ጥፋት መሆኑን ጉባዔው በውሳኔው ጠቁሟል፡፡  

በመስከረም ወር 2009 ዓ.ም. በመኢአድ ጽሕፈት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የተካሄደው የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ሕገ ደንቡን የተከተለ መሆኑን የሽምግልና ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡ ነገር ግን ምርጫውን በሚመለከት ምልዓተ ጉባዔው ተሟልቷል አልተሟላም የሚል ውዝግብ በእነ አቶ ይልቃልና በእነ አቶ የሺዋስ በኩል የሚቀርብ ክስ ቢኖርም፣ ማስረጃ ሊቀርብ ባለመቻሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በጋራ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርተው አዲስ ምርጫ ማካሄድና አመራሩን በመምረጥ ፓርቲውን በሰላማዊ መንገድ ማስቀጠል እንዳለባቸው ጉባዔው የመፍትሔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ እነ አቶ ይልቃል ‹‹ሸንጎ›› በማለት የሚመሩትን ስብስብ በትነው ወደ ሰማያዊ ፓርቲ መመለስና ከእነ አቶ የሺዋስ ጋር በመስማማት የሥራ ድልድል እንዲሰጣቸው ጉባዔው ምክረ ሐሳቡን አቅርቧል፡፡ እነ አቶ ይልቃልም የሽምግልና ጉባዔው ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ ከእነ ማሻሻያው መቀበላቸውንና በጽሑፍ ማረጋገጣቸውን ጉባዔው በውሳኔው ገልጿል፡፡   

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...