Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ያለው አሠራር ዕድል አይሰጥም›› አቶ ፍቅሬ ዘውዴ፣ የዲጂታል ኦፖርቹኒቲ ትረስት በኢትዮጵያ ዳይሬክተር

አቶ ፍቅ ዘውዴ ይባላሉ፡፡ የዲጂታል ኦፖርቹኒቲ ትረስት በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ድርጅቱ የተቋቋመው በ1994 ዓ.ም. ካናዳ ውስጥ ነው፡፡ በወጣቶች የሊደርሺፕ ክህሎትና በሥራ ፈጠራ ዙሪያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች አምስት የአፍሪካ አገሮች ይሠራል፡፡ የተቋቋመው የወጣቶችን ሥራ አጥነት ለመቀነስ እንዲሁም ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶችን ለሥራ ብቁ የሚያደርጉ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት ተፈላጊውን የሰው ኃይል ለማብቃት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከተቋቋመ ሰባት ዓመታትን ቢያስቆጥርም በደንብ መስራት የጀመረው ከ 3 አመታት ወዲህ ነው፡፡ ድርጅቱ ባለፈው ሣምንት በራስ አምባ ሆቴል በሥራ ፈጠራ ሥኬት ያስመዘገቡ ሰዎች ለወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ልምዳቸውን የሚያጋሩበት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዕለቱ ከተገኙ ወጣቶች በቀላሉ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ የቢዝነስ ሐሳቦችን የማፍለቅ ውድድርም ተካሂዶ ነበር፡፡ የድርጅቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን ዳይሬክተሩ አቶ ፍቅሬ ዘውዴን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ የሚያተኩረው በምን በምን ጉዳዮች ላይ ነው?

አቶ ፍቅሬ፡- ወጣቶች ተቀጥሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የተለያዩ ሥልጠናዎች እንሰጣለን፡፡ ቢዝነስ የመፍጠር፣ ቢዝነስን የማሳደግ፣ ቢዝነስን ከደንበኞች ጋር የተዋሃደ እንዲሆን የሚያስችሉ የተለያዩ ሥልጠናዎች እንሰጣለን፡፡ በቀላል አገላለፅ ቢቻል ተቀጥረው አለዚያ የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ክህሎት በሥልጠና እንዲያዳብሩት እናደርጋለን፡፡ በተለይ የተማሩ ወጣቶች ላይ ስንሠራ አይሲቲን ለቢዝነሳቸው እንዲጠቀሙ ተጨማሪ የአይሲቲ ሥልጠና እንሰጣቸዋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በሴቶች ላይ በተለየ የምትሠሯቸው ፕሮግራሞች አሉ? እስቲ በሴቶች ዙሪያ ስለምትሠሯቸው ሥራዎች ይንገሩን?

አቶ ፍቅሬ፡- የምንሰጣቸውን ሥልጠናዎችና የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት አገልግሎቶች በተቻለ መጠን ሴቶች ባሉበት ሆነው እንዲደርሳቸው የምናደርግበት አሠራር አለን፡፡  የሥልጠናዎችን ተደራሽነት በተመለከተ ሴቶች በመደበኛ የሥልጠና ፕሮግራም ላይ ለመገኘት በተለያዩ አጋጣሚዎች ላይመቻቸው ይችላል፡፡ ስለዚህም እነሱ ባሉበት አካባቢ፣ በሚመቻቸው ሰዓት ሥልጠናውን በግሩፕ የሚያገኙበትን ሁኔታ እናመቻችላቸዋለን፡፡ በተጨማሪም ምን ዓይነት ሥልጠና ብንሰጣቸው የተሻለ እንደሚሆን ከእነሱ መረጃ በመሰብሰብ ሥልጠና የሚሰጥበትን መንገድ በመቀየስ የበለጠ የተመቸ እንዲሆን እናደርጋለን፡፡ ሴቶች እርስ በርሳቸው እንዲረዳዱ፣ ሥኬታማ ከሆኑ ሴቶች ጋር የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ የምናደርግበትንና ጠቃሚ ሆነው ያገኘናቸው አሠራሮችም አሉን፡፡ የተለያዩ ፕሮግራሞቻችንን የምናደርሰው ኢንተርኖቻችንን በመጠቀም ነው፡፡ የሴቶች ሴቶችን መርዳትን ታሳቢ በማድረግም ቢያንስ 50 በመቶ የሚሆኑ ኢንተርኖቻችን ሴቶች እንዲሆኑ የምናደርግበት ሁኔታም አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንተርን ሆነው በድርጅታችሁ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶችን እንዴት ነው የምትመለምሉት?

አቶ ፍቅሬ፡- ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የወጡ ወጣቶችን ነው የምንወስደው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ምሩቆች ነገር ግን ወደ ሥራው ዓለም ያልገቡ ናቸው፡፡ ካለን ውስን አቅም አንፃር በየዓመቱ የምንቀበለው 122 እስክ 130 ወጣቶችን ነው፡፡ ለአንድ ወር ያህል ተከታታይ የአሠልጣኞች ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ከዚያም ለአንድ ዓመት ያህል ከእኛ ጋር እንዲሠሩ እናደርጋለን፡፡ ከእኛ ጋር በሚቆዩበት የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም ከሥር ከሥር በአመራርና በአይሲቲ ላይ ያላቸውን ዕውቀት እንገነባለን፡፡ የአንድ ዓመት ጊዜያቸውን በሚያጠናቀቁበት ወቅት በተለያዩ ሥራዎች ለመሠማራት ብቁ ይሆናሉ፡፡ ከእኛ ጋር ተመርቀው በመውጣት ገበያውን ይቀላቀላሉ፡፡ ተፈላጊው ክህሎት ስላላቸውም በቀላሉ ሥኬታማ ይሆናሉ፡፡ አንዳንዶቹ ኢንተርኖቻችን ገና ሳይመረቁ በተለያዩ ተቋማት ይቀጠራሉም፡፡ ሌሎች የትምህርት ዓይነቶችን እንዲማሩ የሚነሳሱበትና የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን የሚቀጥሉም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከአዲስ አበባ ውጭ በተለያዩ የክልል ከተሞች ትሠራላችሁ? የምትሠሩ ከሆነ አካባቢዎቹን የምትመርጡበት መሥፈርቶች ምን ምን ናቸው?

አቶ ፍቅሬ፡- ምንሠራው የወጣት ሥራ አጦች፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት በሚበዙባቸው በአዲስ አበባ፣ በመቀሌ፣ በባህር ዳር፣ በአዋሳና በአርባምንጭ ከተሞች ነው፡፡ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ከተቋቋመና መሥራት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከ25,000 የሚበልጡ ወጣት ሴቶችና ወንዶችን መድረስ ችለናል፡፡ሥልጠናውን ለማዳረስ የምንሞክርበት ሁኔታ ፒር ቲቺንግ (የአቻ ለአቻ ሥልጠና) በመሆኑ ግን ውጤታማ ነው፡፡ ከአንድ አካባቢ ወስደን የምናሰለጥነው አንድ ኢንተርንም በአካባቢው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ የሚፈጥርበት ዕድል መኖሩም የተሻለ ውጤታማ ያደርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራ ፈጠራ ዙሪያ ያሉ ችግሮች ምንድን ናቸው?

አቶ ፍቅሬ፡- በጣም ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ዋናው ሥራ የሚሠራበት ቦታ አለማግኘት ነው፡፡ ጥሩ የቢዝነስ ሐሳብ ኖሯቸው ወደ ተግባር ለመለወጥ መሥሪያ ቦታ በማጣት ብዙ የሚቸገሩ አሉ፡፡ ቦታ ቢያገኙም በአገሪቱ ባለው አመቺ ያልሆነ የአከራይ ተከራይ  ግንኙነት ለመሥራት የሚቸገሩ ብዙ ናቸው፡፡ የኪራይ ዋጋ እስከ 40 በመቶ በአንዴ የሚጨምሩ አሉ፡፡ ይኼ የገበያ ሁኔታውን ለመገመት አዳጋች ከማድረጉ ባለፈ የትርፍ ህዳጋቸው በጣም እንዲቀንስ ያደርገዋል፡፡ ቢሮክራሲም ሌላው ችግር ነው፡፡ አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም ከምዝገባ ጀምሮ ብዙ ውጣ ውረዶች አሉ፡፡ የሚጠየቁ ሰነዶችም ብዙ ናቸው ገደብ የላቸውም፡፡ አንድ ሰው አንድ የቢዝነስ ሐሳብ ይዞ ሲነሳ ሐሳቡን እስካልተገበረው ድረስ ምን ያህል ውጤታማ እንደሚሆን ለማወቅ አይችልም፡፡ ለዚህም አንድ ዓመት ወይም ስድስት ወር የመሞከሪያ ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ ነገር ግን ያለው አሠራር ዕድል አይሰጥም፡፡ ገና ከመጀመርያው ሕንፃ ይኑርህ፣ ቤት ይኑርህ፣ ይህን ክፍል የሚባል ነገር አለ፡፡ እነዚህ በጣም ተስፋ የሚያስቆርጡ ናቸው፡፡ ፋይናንስም ሌላው መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ የኛ ዒላማ ወጣቱ ነው፡፡ ወጣቱ ደግሞ ገንዘብ ሲበደር የሚያስይዘው ኮላትራል (ማስያዣ ንብረት) የለውም፡፡ ለዚህም መነሻ ገንዘብ በማጣት ስራውን ከጅምሩ ይተዉታል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ይፈታሉ ተብለው የተቋቋሙ  የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እንኳን ያለ ኮላተራል ብድር አይሰጡም፡፡ እንዲያውም ባንኮች ከሚጠይቁት ማስያዣ የበለጠ የሚጠይቁበት አጋጣሚ አለ፡፡ ወጣቶች የሚያመጡትን አዲስ የቢዝነስ ሐሳብ ወደ ተግባር ለመለወጥ ድጋፍ የማድረግ ነገርም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለዚህም በማኅበረሰቡ ሌላ ትልቅ ለውጥ መፍጠር የሚችለውን ሐሳብ ወደ ጎን ብሎ ተቀጣሪ ሆኖ የመሥራት ነገር አለ፡፡ እነዚህ ትልቅ ነገሮች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ የቴክኒክ ድጋፎችን ከማድረግ ባለፈ ወጣቶቹን በገንዘብ የሚደግፍበት አሠራር አለ?

አቶ ፍቅሬ፡- እኛ በመሠረቱ የገንዘብ ድጋፍ አንሰጥም፡፡ ነገር ግን ይህን አገልግሎት ከሚሠጡ ከተለያዩ ተቋማት ጋር አብረን በመሥራት የሚሰጡት የፋይናንስ ድጋፍ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ሥልጠናና ክትትል እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ የሚሰጡ የኢንተርፕሩነርሺፕ ሠልጣኞች በወኔ ተሞልተው አንድን ሥራ እንዲጀምሩ የሚያነሳሳ እንጂ በሥራው ላይ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ችግሮችም እንዳሉና እንዴት መወጣት እንዳለባቸው ጭምር የሚያሠለጥኑ አይደሉም የሚሉ አሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምን ይመስላል?

አቶ ፍቅሬ፡- እንዲህ ዓይነት ነገር የሚፈጠረው የሚሰጡ ሥልጠናዎች የፅንሰ ሐሳብ ብቻ ሲሆኑ ነው፡፡ እኛ ግን ዝም ብለን ሌክቸር አንሰጥም፡፡ እኔ ኢንተርፕሩነር መሆን እችላለሁ ወይ ብሎ ራስን እንዲጠይቅ የሚያስችል ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ በሥልጠናዎች ላይ ሥኬታማ የሆኑ ሥራ ፈጣሪዎች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ እናደርጋለን፡፡ ይህ ምን ምን ዓይነት ችግሮች መኖራቸውን እንዲገነዘቡ እንዴትስ ማለፍ እንዳለባቸው እንዲያውቁ ያስችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን ያህል ጊዜ ነው ሥልጠና የምትሰጡት?

አቶ ፍቅሬ፡- ሥልጠናዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ለመጀመርያ ጊዜ ሠልጣኞች ከሦስት እስከ አራት ሳምንት እንዲሰለጥኑ ይደረጋል፡፡ ከዚያ በኋላ ለአንድ ወር ያህል ክትትል እናደርግላቸዋለን፡፡ ሌሎቹ ግን ከአንድ እስከ ሁለት ሳምንት የሚሰጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ብቻ በቂ ባለመሆናቸው በሚፈልጉት መጠን ድጋፍ የሚያገኙበት አሠራርም አለን፡፡ እነሱ ፍላጎት ኖሯቸው እስከመጡ  ከሶስት ወር እስከ ስድስት ወራት ድረስ አስፈላጊውን አገልግሎት እንሰጣቸዋለን፡፡

 

ሪፖርተር፡– ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ምሩቆችን ለስራ ብቁ ለማድረግ የምትሰሩትስ ካለ?

አቶ ፍቅ፡-  ብዙ ጊዜ ከኮሌጆች፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ለሥራ ብቁ የሚያደርጋቸውን ዕውቀት ጨብጠው አይወጡም፡፡ በተለይም የኮሙኒኬሽን፣ የኔት ዎርኪንግ፣ ደንበኛ አያያዝ የመሳሰሉት ክህሎቶች ላይ ደካማ ናቸው፡፡ ቀጣሪዎቹ የሚፈልጉት ያህል ዕውቀት የላቸውም፡፡ ቀጣሪዎች የሚፈልጉት ሌላ፣ የትምህርት ተቋማት የሚያዘጋጁት የሰው ኃይል ሌላ ነው፡፡ ይኼንን እንደ አንድ ክፍተት ተመልክተን እየሠራንበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አለ ለሚሉት ችግር ማለትም የትምህርት ተቋማት የሰው ኃይል ከማፍራት አኳያ ያለባቸው ከፍተት እንዴት ተፈጠረ? ቀጣሪዎችስ ሠራኞች ምን ዓይነት ክህሎት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ?

አቶ ፍቅ፡- የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የተለያየ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ይፈልጋሉ፡፡ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ጨርቃጨርቅ ላይ ቴክኒካል ክህሎት ያለው ሰው ይፈልጋል፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ፡፡ ሁሉም ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ከሠራተኞች የሚፈልጉት አንድ ዓይነት መስፈርት አለ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ የኮሙኒኬሽን ክህሎት ነው፡፡ ሠራተኛው እንዴት ነው ደንበኞችን የሚያስተናግደው? እንዴት ነው ራሱን የሚገልጸው? የሚለው ጉዳይ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ በተለይም ደግሞ ለወጣቶች የሕይወት ክህሎት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የተለያዩ ችግሮች ሲገጥማቸው እንዴት መወጣት ይችላሉ? እነዚህ እነዚህ ሁሉ አብረው የሚሄዱ ዕውቀቶች ናቸው፡፡ እኛም በዚህ ረገድ የሚኖረውን ክፍተት ለወጣቶች ሥልጠና በመስጠት ለመሙላት እንጥራለን፡፡ ከዚህም ሌላ ቴክኒካል የሆኑ የኢንተርፕሩነር ሥልጠናዎችን እንሰጣለን፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ላይ ችግር አለ፡፡ በሁሉም ቦታዎች ላይ ያለው የትምህርት ጥራቱ ደካማ እንደሆነ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ እያደገ ከሚሄደው የኢንዱስትሪዎች ፍላጎት ጋር የተጣጣመ የትምህርት አሰጣጥም የለም፡፡ ተማሪዎች የሚማሩበት መንገድም የተግባር ትምህርትን ያላካተተ የፅንሰ ሐሳብ ትምህርት ብቻ መሆኑም ትልቅ ችግር ነው፡፡ የፅንሰ ሐሳብ ትምህርቶች ከተግባር ጋር አያይዘው ስለማይማሩ ወደ ሥራው ዓለም በሚገቡበት ወቅት በትምህርት ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር ለመለወጥ እንዲችሉ ያደርጋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡– የትምህርት ጥራቱ ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዴት ነው?

አቶ ፍቅሬ፡- እኛ ካጤንነው ጊዜ ጀምሮ የትምህርት ጥራቱ እየደከመ እየደከመ ነው የመጣው፡፡ በተለይም ደግሞ ብዛት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራት ከተጀመረ በኋላ የትምህርት ጥራቱ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ ብዛት ላይ ማተኮሩ የመምህራን ቁጥርና የተማሪዎች ቁጥር እንዳይጣጣምም አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ ፍቅሬ፡- የተለያዩ ስትራቴጂዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ዋናው የትምህርት ሥርዓቱን ከጥራት፣ ከይዘትና ከተደራሽነት አኳያ መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ አሁን በብዛት እየተሠራ ያለው ተደራሽነት ላይ ነው፡፡ ተደራሽነትን ደግሞ ከሌሎች ነገሮች ጋር ሚዛናዊ አድርጎ ማስኬድ ካልተቻለ አደገኛ ነው፡፡ የዚህ ጥቅሙና ጉዳቱ የሚታየው ከዓመታት በኋላ ነው፡፡ ከዓመታት በኋላ አደገኛ ነገር ከማየት አሁኑኑ ነገሮችን በጥሞና አስቦ መሥራት ግድ ነው፡፡ መምህር ሳይኖር 30 ዩኒቨርሲቲ ቢከፈት ምንድነው ጥቅሙ? በአሁኑ ወቅት በደንብ ያልሠለጠኑ መምህራን እንዲያስተምሩ ሲደረግም ይታያል፡፡ ያለው የተጠያቂነት ሥሜትም በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ክፍል ገብቶ ሳያስተምር ሁለትና ሦስት ወር ሌላ ቦታ ቆይቶ ቅዳሜና እሑድ ገብቶ የአንድ ሴሚስተር ኮርስ ጨርሶ መሄድም ተለምዷል፡፡

ሪፖርተር፡- ለመፍጠር ያሰባችሁትን ያህል ለውጥ  መፍጠር ችለናል ይላሉ?

አቶ ፍቅሬ፡- እኛ የምንፈልገው ፈጣንና በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች ሥራ መፍጠር የሚችሉ ወጣቶችን ማፍራት ነው፡፡ ይኼንን ማሳካት የአንድ ድርጅት  ሥራ ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡     

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...

‹‹ኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቀልበስ የፖሊሲ ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ›› ዓለም ባንክ

በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ...