Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የብር ምንዛሪ ማስተካከያ እንድታደርግ አሳሰበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ብሔራዊ ባንክ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል አለ

በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆል እያሳየ ያለውን የወጪ ንግድ ገቢን ለማረቅና የወጪ ንግድ ምርቶች አቅርቦት እንዲጨምር ለማበረታታት፣ ኢትዮጵያ የብር የምንዛሪ ምጣኔን እውነተኛውን የኢኮኖሚ አቅሟን በሚያመላክት ደረጃ ማስተካከል ይገባታል ሲል የዓለም ባንክ ምክር ሰጠ፡፡

ባንኩ ማክሰኞ ኅዳር 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ይፋ ያደረገው አምስተኛው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሪፖርት ካነጣጠረባቸው ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው፣ ሚዛኑን የሳተው የብር የምንዛሪ ምጣኔ ጉዳይ ነበር፡፡ ከሪፖርቱ አዘጋጆች አንዱ የሆኑት ማይክል ጋይገር እንደሚሉት ከሆነ፣ የኢትዮጵያ የምንዛሪ ምጣኔ በተለይ እ.ኤ.አ. በ2010 ከተደረገው የምንዛሪ ማስተካከያ (Devaluation) በኋላ በዝግታ እየቀነሰ መሆኑ የታየ ቢሆንም፣ አገሪቱ በምትከተለው ቅይጥ ምንዛሪ ፖሊሲ ምክንያት (Managed Floating) አሁንም እውነተኛው የብር የምንዛሪ ምጣኔና በሥራ ላይ ያለው ምጣኔ በእጅጉ የተዛነፈ ነው፡፡

በዚህ መሠረት እውነተኛውን የምንዛሪ ምጣኔ የሚለካው ʻሪል ኢፌክቲቭ ኤክስቼንጅ ሬትʼ (Real Effective Exchange Rate) የምጣኔውን መዛነፍ በግልጽ እንደሚያሳይ የገለጹት ሚስተር ማይክል፣ የምንዛሪ ማሻሻያው ከተደረገ በኋላ (2010) እንኳን የብር የምንዛሪ ምጣኔ ቢያንስ በ84 በመቶ ጨምሮ እንደሚታይ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ብር የምንዛሪ ምጣኔውን ስቶ ከሚገባው በላይ መቆለሉን (Overvalue) ጠቅሰው ተከራክረዋል፡፡

እንደ ኢኮኖሚስቱ ጥናት ምጣኔውን በእጅጉ የሳተው ብር ይበልጥ አሳሳቢ የሚሆነው፣ ከወቅቱ የወጪ ንግድ ገቢ ማሽቆልቆል ጋር በጥምረት ሲታይ ነው፡፡ ‹‹ምናልባትም የአገሪቱን የወጪ ንግድ እየጎዱ ካሉ ነገሮች መካከል አንደኛው የዚህ የእውነተኛው የብር የምንዛሪ ያለአግባብ ማበጥ ነው፤›› ያሉት ሚስተር ማይክል፣ የምንዛሪ ማሻሻያ ማድረጉ ብልኃት የተሞላበት አካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የተመጠነ የምንዛሪ ማሻሻያ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነት እንደሚጨምር በጥብቅ የሚመክሩት የባንኩ ባለሙያዎች፣ በስብሰባ አዳራሹ የተገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ልብ ማሸነፍ ተስኗቸው ታይተዋል፡፡ በተለይ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት አቶ ዮሐንስ አያሌው የምንዛሪ ማሻሻያውን ምክር ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርገውታል፡፡ እንደ አቶ ዮሐንስ ገለጻ ከሆነ፣ የምንዛሪ ማሻሻያ ዓይነት መዘዝ ያላቸው የፖሊሲ ውሳኔዎችን ከመወሰን በፊት ማጤኑ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የምንዛሪ ማሻሻያው የሚያስከትለው ጉዳትና ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀው ጥቅም መወዳደር አለባቸው ብለዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ የምንዛሪ ማሻሻያው በሁሉም መንገድ ቢታይ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ያምናሉ፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት የተወሰደውን የምንዛሪ ማሻሻያ ተከትሎ የተቀሰቀሰውን የዋጋ ግሽበት ማስታወስ ያስፈልጋል፤›› ያሉት አቶ ዮሐንስ፣ ‹‹የረጅም ጊዜ ጉዳቱ በግልጽ ከአጭር ጊዜ ጥቅሙ የማይበልጥ ፖሊሲን አንተገብርም፤›› ብለዋል››፡፡    

የኧርነስት ኤንድ ያንግ ማኔጂንግ ፓርትነር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው፣ የምንዛሪ ማስተካከያ ማሳሰቢያው ተገቢ አይደለም ባይ ናቸው፡፡ በስብሰባው ላይ አቶ ዘመዴነህ በሰጡት አስተያየት ባንኩ ይህንን ዓይነት ምክር ሲያቀርብ ይህ ‹‹ለሁለተኛ ወይም ለሦስተኛ›› ጊዜው መሆኑን፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የግብርና ምርቶች ወደ ውጭ በመላክና የካፒታል ዕቃዎች በማስመጣት ላይ የተመሠረተ የወጪ ንግድ ሥርዓት ላላቸው አገሮች የምንዛሪ ማሻሻያ ተገቢ ፖሊሲ አይመስለኝም ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2010 መስከረም ወር ላይ የተደረገው አጠቃላይ የምንዛሪ ለውጥ የብር ምንዛሪን በአንድ ጊዜ በ20 በመቶ ገደማ እንዲቀንስ ያደረገ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱ ብር ከዶላር ጋር የነበረው የምንዛሪ ምጣኔ ከ13.80 ወደ 16.35 ከፍ እንዲል የተደረገ ሲሆን፣ ይህንን ውሳኔ ተከትሎ አገሪቱ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ያህል በሁለት አኃዝ የዋጋ ግሽበት ስትታመስ እንደከረመች የሚታወስ ነው፡፡

እንደ ሚስተር ማይክል ገለጻ ከሆነ ግን፣ እ.ኤ.አ. በ2010 የምንዛሪ ማስተካከያ ማግሥት ግሽበት ተከስቶ ስለነበር ብቻ የምንዛሪ ማስተካከያን አንደ አማራጭ ፖሊሲ ውድቅ ማድረግ ብልህነት አይደለም፡፡ ‹‹የምንዛሪ ማስተካከያው በምን ዓይነት ከባቢያዊ ሁኔታ ነው የሚከናወነው የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፤›› ያሉት ሚስተር ማይክል፣ የ2010 የምንዛሪ ማስተካከያ በተካሄደበት ጊዜ የዓለም አቀፍ የሸቀጦች ዋጋ ጣራ የነካበት ወቅት ነበር፡፡ የባንኩ ኢኮኖሚስት፣ ‹‹ነገር ግን አሁን ያለንበት ነባራዊ ሁኔታ የተለየ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የዓለም አቀፍ የሸቀጦች ዋጋ በእጅጉ ያሽቆለቆለበት ጊዜ እንደመሆኑ መጠን፣ የምንዛሪ ማስተካከያው የተፈራውን ያህል የዋጋ ግሽበት መቀስቀስ እንደማይችል ግልጽ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የባንኩ ሪፖርት የምንዛሪ ማስተካከያ ማድረግ፣ በተለይ እንደ ቻይና ያሉ አገሮች አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት አቋም ላይ ሆነው የተጠቀሙበት የወጪ ንግድ ማበረታቻ መሣሪያ መሆኑን ያትታል፡፡ በዚህ መሠረት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ያለው የምንዛሪ ምጣኔ ከእውነተኛው የኢኮኖሚ አቅም አንፃር ሲታይ ከ70 በመቶ ያላነሰ የተቆለለ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት የአንድ በመቶ የምንዛሪ ማስተካከያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ቢያንስ የ1.06 በመቶ ወጪ ንግድ መሻሻልን፣ በአገልግሎት ዘርፍ እንዲሁ የ0.5 በመቶ መሻሻልንና በግብርና ምርቶች ዘርፍ ደግሞ የ0.3 በመቶ የወጪ ንግድ ዕመርታ ሊያመጣ እንደሚችል ሪፖርቱ በጥልቀት ዳሷል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የባንኩ ዓመታዊ ጥናት ባለፈው ዓመት የስምንት በመቶ ዕድገት ያሳየው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለይ ከነበረው የድርቅ ሁኔታ አንፃር በእጅጉ አበረታች መሆኑን ያትታል፡፡ ‹‹በከፋ ድርቅ ወቅት ይህንን ያህል ዕድገት ማስመዝገብ በእጅጉ አበረታች ነው፤›› ያለው ሪፖርቱ፣ ከዕድገቱ ባሻገር ሌሎች የማክሮ ኢኮኖሚ መለኪያዎችም የኢኮኖሚውን ተፅዕኖ የመቋቋም ጥንካሬ ያሳዩ ናቸው ብሏል፡፡

በነጠላ አኃዝ የተገደበ የግሽበት ምጣኔ ከድርቅ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የእህል ዋጋን መጨመር ሥጋት የተቋቋመ ነበር ያለው ሪፖርቱ፣ የድርቅ ተጠቂዎችን ከመርዳት ጋር ተያይዞ በእጅጉ የጨመረው የመንግሥት ወጪ አጠቃላይ የበጀት ጉድለቱን ያለማባባሱም ሌላው የሚደነቅ ክስተት ነው በማለት አወድሷል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች