Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር በባህር ዳር ተካሄደ

የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር በባህር ዳር ተካሄደ

ቀን:

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሊያከናውናቸው ካቀዳቸው ዓመታዊ የአገር ውስጥ ውድድሮች የግማሽ ማራቶን ውድድር እሑድ ኅዳር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ አካሂዷል፡፡

በውድድሩ የተለያዩ ታዋቂና አዳዲስ አትሌቶች ተሳታፊ መሆን የቻሉ ሲሆን፣ አትሌቶቹም ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ለመሳተፍ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ የአገር ውስጥ ውድድሮች ራሳቸውን የበለጠ ለመገምገም እንደሚያግዛቸውም ተናግረዋል፡፡

በአሥረኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ላይ በመሳተፍ አንደኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው ታምራት ቶላ፣ በአገር ውስጥ የሚዘጋጁ እንደነዚህ መሰል የተለያዩ ውድድሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚደረጉት ፉክክሮች የተሻለ እገዛ እንደሚያደርጉ ነው ያስረዳው፡፡

እንደ አትሌቱ አስተያየት ከሆነ፣ አገሪቱ በዓለም መድረክ ላይ የነበራትን የአትሌቲክስ ታሪክ ከቀድሞ በተሻለ ለመሥራት የአገር ውስጥ ውድድሮችን ቁጥር በመጨመር፣ ቀደም ብሎ ማጠናቀቅ እንደሚያስፈልግም ተናግሯል፡፡

በሪዮው 31ኛው የሪዮ ኦሊምፒያድ የአሥር ሺሕ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት የነበረው ታምራት በአገር ውስጥ የሚደረጉት ውድድሮች ውስንነትና የአትሌቶች በቡድን አለመሥራት ለአትሌቲክሱ ውጤት ማሽቆልቆል ምክንያት እንደሆነ ገልጿል፡፡

በ2008 ዓ.ም. በሰበታ ከተማ በተካሄደው ዘጠነኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው አትሌቱና በእንግሊዝ ካርዲፍ ሲቲ በተዘጋጀው ግማሽ ማራቶን መሳተፉ ይታወሳል፡፡ በውድድሩ ርቀቱን በአንድ ሰዓት 00፡06 ሰከንድ በማጠናቀቅ አምስተኛ ደረጃ ይዞ መጨረሱ ይታወሳል፡፡ በወቅቱም የኬንያውያን የቡድን ሥራ ጠንካራ መሆን የበላይነቱ ሊወሰድበት እንደቻለ ሁኔታውን በቁጭት ያስታውሳል፡፡ በሪዮ ኦሊምፒክ በ10 ሺሕ ሜትር ላይ በቴክኒክ ጉዳይ በእንግሊዛዊ ሞ ፋራ ብልጫ የተወሰደበት እንዳስቆጨውም አልሸሸገም፡፡

ኢትዮጵያ በረዥም ርቀት ያላትን ታሪክ በነበረበት ለማስቀጠልና ከተፎካካሪዋ ኬንያ ጋር በዓለም አቀፍ መድረክ የተሻለ ሆና ለመቅረብ ሁሉም አትሌቶች የውድድር ዕድል ተፈጥሮላቸው በአገር ውስጥ የቡድን ስሜቱን መፍጠር ዋነኛው የቤት ሥራ እንደሆነ አትሌቱ ይናገራል፡፡

በረዥም ርቀት ጠንክሮ እንደሚሠራ የሚናገረው አትሌቱ በ10,000 እና ግማሽ ማራቶን በዓለም አቀፍ ውድድሮች ጠንካራ ሆኖ መቅረብ ዕቅዱ እንደሆነም አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

በ10ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ኦሮሚያ ፖሊስን በመወከል 1 ሰዓት ከ01 ደቂቃ ከ53 ያጠናቀቀው ታምራት፣ በሪዮ ኦሊምፒክ ላይ የተገኘውን የ10,000 ሜትር ውጤት ዘንድሮ በለንደን በሚደረገው የዓለም ሻምፒዮና ላይ አሸናፊ ለመሆን ከወዲህ ጠንክሮ እየሠራ እንደሚገኝ ጭምር አብራርቷል፡፡

በ20ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን የአመራር ኃላፊነት የተረከቡት የቀድሞ አንጋፋ አትሌቶች መመረጥ በተመለከተ፣ አትሌቲክሱ ወደ ተሻለ ደረጃ ማደግ ይችል ዘንድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አልሸሸገም፡፡

‹‹ፌዴሬሽኑ በአትሌቶች መመራቱ አትሌቶች ምን ዓይነት ሥልጠና ማድረግ እንዳለባቸው፣ የሚያጋጥማቸውን ችግር እንዴት መፍታት እንደሚችሉና ውድድሮቻቸውን እንዴት ማከናወን እንዳለባቸው በቅርበት ስለሚያውቁት ለመነጋገር ጭምር ይረዳል›› በማለት አትሌቱ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በቅርበት መጥቶ ስላለው ወቅታዊ የአትሌቲክስ ጉዳይ እያማከረው እንደሆነም ሳይገልጽ አላለፈም፡፡

አትሌቶች ስለሚያደርጉት ልምምድ ያብራራው አትሌቱ፣ ‹‹ውድድር ሳይሆን ልምምድ ማድረግ ከባድ ነው፣ በማለት ልዩነቱን የገለጸ ሲሆን፣ በአንፃሩ በልምምድ ወቅት የአትሌቶችን አቅምና ፅናት ለይቶ ለማወቅ የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ጭምር ተናግሯል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አትሌቶችን ከክልል በማምጣትና ፉክክርን በማስፋት በቀጣይ ለሚደረጉ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ጠንክሮ መሠራት ያስፈልጋልም ብሏል፡፡

በአሥረኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በስተቀር ስምንት ክልሎችና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ 13 ክለቦችና በግል የቀረቡ 79 ሴቶችና 154 ወንዶች በድምሩ 233 አትሌቶች ተሳትፈውበታል፡፡

በሴቶች ታደለች በቀለ ከኦሮሚያ ማረሚያ ርቀቱን 1 ሰዓት፣ 10 ደቂቃ፣ 28 ሰከንድ በሆነ ጊዜ አጠናቃ አሸናፊ ሆናለች፡፡ እሸቴ በከሪ ከኦሮሚያ ፖሊስ 1 ሰዓት፣ 11 ደቂቃ፣ 13 ሰከንድ ሁለተኛ፣ ጉሉሜ ቶሎሳ ከኦሮሚያ ፖሊስ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል፡፡

በወንዶች ታምራትን ተከትለው የገቡት ጌታነህ ጫላ መከላከያ 1 ሰዓት፣ 02 ደቂቃ፣ 28 ሰከንድ ሁለተኛና አረዶም ጥዑማይ ከመሰቦ ሲሚንቶ 1 ሰዓት፣ 02 ደቂቃ 40 ሰከንድ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የውድድሩ አሸናፊ ሆነዋል፡፡

በሻምፒዮናው አሸናፊ ለሆኑት በሁለቱም ጾታ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለወጡ አትሌቶች የሜዳሊያ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን፣ በተጨማሪም በግል ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ለወጡ አትሌቶች ከ20 ሺሕ እስከ ሦስት ሺሕ ብር ባስመዘገቡት ውጤት መሠረት ተሸልመዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...