Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ሥነ ፍጥረትዐዞ እና መንጋጋው

  ዐዞ እና መንጋጋው

  ቀን:

  አንዲት እናት ልጇ የዓባይ ወንዝን ሲሻገር በዐዞ በመበላቱ፡-

  ‹‹ግባተ መሬቱን አትድገሙ እናንተ፣

  ታዞ ሄዷል እንጂ ልጄ መቼ ሞተ፤›› በማለት ሙሾዋን ስታወርድ፣ እህቱም፣

  ‹‹ላንድ ቀን ትዕዛዝ ሰዉ ይመረራል፤››

  የእኔ ወንድም ታዞ ዓባይ ላይ ይኖራል፤›› ስትል አባትም፣

  ‹‹ልጄን አትጥሉብኝ ቢያዛችሁ ተሹሞ፣ ዐዞ አያውቅምና ከዚህ አስቀድሞ፤›› በማለት ሙሾአቸውን ሞሽሸዋል፡፡

  ዐዞ በየኅብረተሰቡ በየቋንቋው በልዩ ልዩ መልክ ይገለጣል፡፡ በብሂል ውስም አይታጣም፡፡ ‹‹ማን ያወጣል ሥጋ ካዞ መንጋጋ›› አንዱ ነው፡፡ የአለቃ ደስታ ተክለ ወልድ፣ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት (1962)፣ ዐዞን የባህር አውሬ ሆደ መጋዝ፣ ጋድሚያ እንቅልፋም ያገኘውን ሰውና እንስሳ በጅራቱ እየጠለፈ ወደ ባሕር ውስጥ የሚገባ ብሎ ይፈታዋል፡፡ እንስቲቱ ባሸዋ ውስጥ ዕንቁላል ትወልዳለች፤ ከዚያም ገላግልት (ግልገሎች) ይወጣሉ ሲልም ያክላል፡፡

  ስለዐዞ መንጋጋ ንቁ መጽሔት ካመታት በፊት አንድን ተመራማሪ ጠቅሶ እንደገለጸው፣ የዐዞ መንጋጋ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ከሚኖሩ አራዊት ሁሉ ይበልጥ ከፍተኛ የመቀርጠፍ ኃይል አለው። ለምሳሌ ያህል፣ አውስትራሊያ አቅራቢያ በጨዋማ ውኃ ውስጥ የሚኖረው ዐዞ የመንከስ ኃይሉ ከአንበሳ ወይም ከነብር ጋር ሲወዳደር ሦስት እጥፍ ያህል ከፍ ያለ ነው። በጣም የሚያስገርመው ግን የዐዞ መንጋጋ ትንሽ ነገር እንኳ ሲነካው የሚሰማው ወዲያውኑ ነው፤ ሌላው ቀርቶ ከጣታችን ጫፍ ይበልጥ ቶሎ ይሰማዋል። ዐዞ እንደ ቅርፊት ያለ እጅግ ጠንካራ ቆዳ ያለው ከመሆኑ አንፃር ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?

  ጄደብሊው ዶት ኦርግ በድረ ገጹ እንደጻፈው፣ የዐዞ መንጋጋ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የስሜት ሕዋሳት አሉት። ዳንከን ሊች የተባሉ ተመራማሪ በዚህ ላይ ጥናት ካደረጉ በኋላ ‹‹እያንዳንዱ የነርቭ ጫፍ የሚወጣው በጭንቅላቱ ውስጥ ከሚገኝ ቀዳዳ›› እንደሆነ አስተውለዋል። በመንጋጋው ውስጥ ያሉት ነርቮች በዚህ መንገድ መቀመጣቸው ምንም ነገር እንዳይጎዳቸው የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ የነርቭ ሴሎቹ አንድ ነገር ሲነካቸው ቶሎ እንዲሰማቸው ያስችላል፤ እንዲያውም በመንጋጋው ላይ ያሉ አንዳንድ ነርቮች አንድ ነገር ሲነካቸው የሚሰጡት ምላሽ በጣም ፈጣን ከመሆኑ የተነሳ በመሣሪያ እንኳ መለካት አይቻልም። በዚህም የተነሳ ዐዞ አፉ ውስጥ ያለ አንድ ነገር ምግብ ይሁን አይሁን በቀላሉ መለየት ይችላል። ይህም አንዲት ዐዞ ጫጩቶቿን በአፏ ይዛ ስትሄድ ተሳስታ እንኳ እንዳትጨፈልቃቸው ይረዳታል። የሚያስገርመው፣ የዐዞ መንጋጋ እጅግ ኃይለኛ የመቀርጠፍ ብቃትና ትንሽ ነገር ሲነካው ቶሎ የመለየት ችሎታን አጣምሮ መያዙ ነው።

  • ሔኖክ መደብር

   

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...