Saturday, March 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ብክነትና ብክለት!

እነሆ ዛሬ የምንጓዘው ከመገናኛ ወደ ቦሌ ነው። ሁሉም ሠፈር አቋራጭ እንጂ አገር አቋራጭ ባለመሆኑ ከአንድ ራሱ በቀር ተጎታች ሳይኖረው ይሳፈራል። ወያላው ራቅ ብሎ ቆሟል። “የት ነው?” እያለ እርስ በርሱ ተጠያይቆ የሚሳፈረው መንገደኛ ብዙ ነው። “የመረጃ እጥረት ብሎ ብሎ ታክሲ ተራ ገባ?” ብሎ ቢል አንድ ወጣት መንገደኛ፣ “ከላይ ከተጀመረ ወደ ታች  መውረዱ መች ሊከብድ?” ሲል አዋዝቶ አንድ ጎልማሳ መለሰ፡፡ “ሰው ምን አንደሚታየው እንጃ ታክሲዋን ሲሳፈር የአሜሪካን አፈር የረገጠ ይመስለዋል እኮ?” ይለዋል አንድ ጎልማሳ አብሮት ለሚጓዘው ጓደኛው። “እንዴት?” ሲለው፣ “አትታዘብም ታክሲ ውስጥ በነፃነት ሰው እንዴት እንደሚጨዋወት?” በአግራሞት እያየ ጠየቀው። “መብቱ ወረቀት ላይ ብቻ ነው ቢባልም የትም ይሠራል። ይልቅ የሚገርመኝ የሰው ታክሲ ሲሳፈር የሚያመጣው የማውራት ድፍረት ነው፤” እየተባባሉ ቀጠሉ። አዳማጩ ጆሮውን አንቅቷል። የሚጥለውን እየጣለ የመረጠውን የሚለቅመውን ልቦውና ይቁጠረው። አላምጦ መብላትና መስማት ሕመሙ ሲከብደን አላውቀው ብለናል። አዳሜ ሳያላምጥ ሲውጥ ከነገር እስከ እንጀራ እያነቀው አላሳዝን ማለት ጀምሮላችኋል። አለመተዛዘን ለካ እንዲህ ቅርብ ነው? እንበል ይሆን?

“በዚህ ኑሮ እንጀራ እያነቀን ሲባክን፣ ነገር እያነቀን ስንባክን ጉድ አይደል? ብክነትና ብክለት ምነው መንገዱን ሞላው?” ሲል እንሰማለን ከኋላ ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ጎልማሳ። “መባከን የመንገድ አንዱ ምልክት ነው ሲባል ስትሰሙ በመልካም አስተዳደር ዕጦት ደሞ የብዙ ሰው አቅምና ዕድሜ ሲባክን አይታያችሁም?” ትላለች ከጎኔ የተቀመጠች ባለ ጉዳይ መሳይ ወይዘሮ። ታክሲያችን አጠገብ ካለው የቀለበት መንገዱ ቋሚ ግንብ ሥር ማንም አያየኝም ባይ ሰካራም ሽንቱን በሰመመን ይሸናል። በጭራሽ አላየንም። “እግዚኦ!” ይላል በኃፍረት ተሸማቆ አብዛኛው መንገደኛ። ኃፍረቱ ከድምፁ ቃና ይፈልቃል። ሰካራሙን ላለማየት የታክሲዋ ጣራና መሬት ላይ ያፈጣል። “እኔ እኮ የሚገርመኝ ክልክል ነው ሲባልም ይቻላል ሲባል ተቃራኒ መሆን የምንወደው ነገር ነው? ማጨስ ክልክል ነው፣ ማለፍ ክልክል ነው፣ ወዘተ ሲባል ቡራ ከረዩ። እልህ ያንቀናል። መለወጥ ይቻላል፣ ድህነትን ማሸነፍ ይቻላል ሲባል ቁዘማና መታከት። ምንድነው የሚሻለን?” ሲል፣ “ፉከራና ቀረርቶ እንጂ እሺ ባይነትና ሥራ ስላለመደብን አይመስልህም?” አለው ጎልማሳው። ‹ስንቱን አሳለፍኩት ስንቱን አየሁት› ይላል የትዝታው ንጉሥ ከወደ ስፒከሩ!

  አሥራ ሁለታችንም ተሳፋሪዎች ቦታችን ከያዝን ከየት ማለት ጀመርን። ከብዙ ዓይነት የሕይወት መንገድ፣ አስተሳሰብና እምነት ያለቀጠሮ ታክሲያችን ውስጥ መሰባሰባችን እየቆየ የሚደንቀን ጥቂት ነን። “ማን ወደማን ይሆን የሚገሰግሰው፣ መቼም ያገናኛል መንገድ ሰውና ሰው፤” እንዲሉ ጉዞ ሰበብ ሆኖ ሰው ከሰው እንዲህ ያለቀጠሮ ይገናኛል። ታዲያ የቀናው እስከ ጫፍ ይጓዛል፣ ይፋቀራል፣ ይዛመዳል፣ ይወልዳል ይከብዳል። ዕድለ ጠማማ ከሆነ ግን ከመፋቀር መጉደሉ ሳያንስ፣ በሰላም መለያየት ሳይቀናው ተቧጭሮና ተጣልዞ በገላጋይ ይሸኛል። ይህ ነው መንገድ ማለት። ንክኪ የሚባል የሕይወት ጥበብ እዚህ ውስጥ ነው ፈትሉ። የሚያውቀው ሲያውቀው ያላወቀው ሲያልፈው የሕይወት ፍሰትን የሚያስቆመው የለም። ትናንት ዛሬ እንደ ደረሰች፣ ዛሬ ነገን ልታደርስ ከንፋ ታከንፈናለች።

ሽበታሙ ሾፌራችን የመቀመጫ ቀበቶውን አጠባብቀው ሞተሩን አስነስተዋል። እሳቸውም የወያላውን ብቅ ማለት እንደ ሎተሪ ዕጣ በጉጉት የናፈቁ መስለዋል። ወያላው በበኩሉ የቆመበት አልታይ የደረሰበት አልታወቅ ያለ ይመስላል። “የት ሄደ ደግሞ?” ይላል ሾፌሩ በለሆሳስ። ጥበቃችን ግን ሊከስትልን አልቻለም። “ወያላችን ቀረ ብለን እንዝፈን እንዴ? መቼም ሳይዘፈንለት ወይም ሳይዘፈንበት የቀረው እሱ ብቻ ነው መሰለኝ፤” አለ ቀጠን የሚል ወጣት። አጠገቡ የተቀመጠ እሱን መሳይ፣ “ተው ተው የሚቀርብን እንደ ኢኮኖሚያችን በሁለት አኃዝ በጨመረ ቁጥር ለስንቱ ዘፍነን እንችለዋለን?” ብሎ በስላቅ ሲመልስለት፣ “አይዞህ ተምረው ሲከስሩ እንጂ ዘፍነው ሲከስሩ እያየን አይደለም፤” ብሎ ከማዶ ጎልማሳው ጮኸ። አሽሙር በጩኸት መቼ ተጀመረ ደግሞ? 

 “ግን አንተ አባባልህ ምን ለማለት ነው?” ስትል ኮሶ መሳይ ፊት ነገረኛ ሴት ወያላው ላይ አፈጠጠች። ወያላው ሒሳቡን እንደተቀበለ ወዲያው መልስ እያስረከበ፣ “ውሳኔ ሲዘገይ አስተማሪነቱና ማስፈራሪያ መሆኑ ያጠራጥራል። ደሞም ተመጣጣኝ ፍርድ ስለማንሰማ ነው እንዲህ የሚዘገንን ወንጀል ሲደጋገም የምናደምጠው። ለምን አስተማሪ የሚሆን ከበድ ያለ ፍርድ በቶሎ አይሰጥም?” አላት በየዋህነት መንፈስ ነገሩ አብሰልስሎት። “አትፍረድ ይፈረድብሃል ብያለሁ ዛሬ!” ሲል ጎልማሳው ጣልቃ ገብቶ ይሰማል። “መንግሥት እኮ ዳኛ አይደለም፤” አሉት ሽማግሌው ሾፌር ዞረው ሳያዩት።

“እሱን እንኳን ይተውት ዳኛ በዕጩነት አቅርቦ የሚያፀድቀው ማን ሆነና?” ሲል ከሁለቱ ከፊት የተቀመጡ ወጣቶች አንደኛው ጎልማሳው፣ “ሕገ መንግሥቱን አክብራችሁ ተጫወቱ እንጂ?” ብሎ ለብቻው ሳቀ። ወያላው ይኼኔ አንድ ጥቅስ ጠቆመን። “ዴሞክራሲ እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም” የሚል። “አይ እናንተ! አሁን እንዲህ ያለው ሥራ እውነት ከሰው ይመስላችኋል? አይደለም። ሰው እንዲህ አይጨክንም እርኩስ መንፈስ ካልተዳበለው በቀር?” ብለው አዛውንቱ መንፈሳዊ እሳቤያቸውን እያብራሩ ከአሥረኛው ጨዋታ ጎትተው አወጡን። ረዘም ቀጠን የሚል እስካሁን ትንፋሹን ያልሰማነው ሌላ ወጣት፣ “እውነታቸውን ነው። ዕውን ከሰው ቢሆንማ የሙስና፣ የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ችግር በአንድ ቀን አይፈታም ነበር?” አለ ሁላችንንም ከግራ ቀኝ እየቃኘ። እንዳለው ከእኛ የመፍትሔ መልስ ያደምጥ ይመስል።

ትንሽ እንደ ተጓዝን መንገዱ ተጨናነቀና ቆምን። የተጣደፈው ‘ኤጭ’ ታው እያየለ ዙሪያ ገባውን ሲቃኝ የሚያመካኝበት ነገር የሚፈልግ ይመስላል። (በረባ ባረባው መካሰስ ሆኖ አደል ኑሯችን?) ስንቆም እየባሰበት የመጣው የቀትር ፀሐይ ተሳፋሪውን ቀስ እያለ አንጫጫው። “ቆይ አሁን ይኼን ማሰብ ያቅታችኋል?” ስትለው ጦር ጠማኟ ሴት ወያላው በትዝብት ተመልክቷት፣ “እኔን ነው? ብሎ ወደ እሷ ዞረ። “ምን አለበት መስታውቶቹን ጥቁሩን ተለጣፊ የፀሐይና የብርሃን መከላከያ ብትለጥፉበት? ለነገሩ መሰብሰብ እንጂ ማውጣት የት ታውቃላችሁ?” አለችው ከአስተያየት ባለፈ ግዴታው እንደሆነ ሁሉ።

“ሰው በየተቋሙ ጉቦ ሲጠየቅ እንዲህ የማይጮኸው ለምን ይሆን?” ይላል አሁንም ጥጉን ይዞ የሚጓዘው ጎልማሳ። እየቆየን የአዕምሮ ሕመም ያጠቃው ሰው መሆኑን አውቀናል። ወያላው በመናደድ ፈንታ ሳቅ እያለ፣ “እሱ ለባለሥልጣናት ብቻ ነው የተፈቀደው። ለእኛ ሲፈለግ ተጋርዶ ሲያሻ የሚገለጥ መጋረጃ ነው የሚፈቀደው፤” ብሏት ዞረ። “እንዴ የሥልጣን ምንጭ እኮ እኛ ነን፣ ሕዝብ ነው. . .” እያለች ልትቀጥል ስትል፣ “ረጋ በይ እንጂ እህቴ። ሁላችንም ስለሥልጣን ገብቶን ስለአንዳንድ ሙሰኛ ባለሥልጣኖቻችን ግን ግራ የገባን ነገር በርትቷል። ስለዚህ ማር ማር ስለሚለው ነገር እያወራሽ ቁጭታችንን አታባብሽብን፤” ሲላት ደንገጥ አለች። ‘በለፈለፉ በአፍ ታሰሩ’ ያለው ቀልደኛ ወያላ ትዝ አለኝ!

መዳረሻችን እየተቃረበ ነው። ሐያት ሆስፒታልን አልፈን እየተጓዝን ሾፌሩንና ወያላውን የሚያውቁ ባለታክሲዎች ፍጥነታቸውን ከእኛ ጋር አስተካልው ተጣሩ። ሾፌሩ ዓይቷቸው ወያላውን “ኳስ የት እንደምናይ ቅጠራቸው፤” ብሎ ነገረው። ወያላው ነፍሱን አላውቅ ብሎ በመስኮት ወጣና የተቀላቀለበት ሙዚቃውን ለቀቀው። አንዴ ‘ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም’ ሲል ደግሞ ወዲያው ለውጦ ‘ድሌ ማታ ነው ድሌ’ ብሎ ያሞቃል። ቀጥሯቸው ሲያበቃ ገባና መስኮቱን ዘጋ። “የቻሉትን ሞክረው ተመልሰው ካላሰረፉህ በዚህ ዓይነት ሥራ አትሠራም?” አለው አጠገቡ ያለው ተሳፋሪ። ይኼኔ ወያላው ተቆጣ። “ምን? የምን ሙከራ ነው? እኛ ምንፈልገው ዋንጫ ነው። የሄድነውም ለዋንጫ ነው። ስሙ ራሱ ‘የአፍሪካ ዋንጫ’ አይደል እንዴ? ማን ከማን ያንሳል? ማንስ ከማን ይበልጣል?” ብሎ ሁላችንንም አየን። ሽበታሙ ጎልማሳ፣ “እውነትህን ነው። ሲያጠቡ ጠቦ መቅረት ነው ትርፉ። የራዕይ ደግሞ ጠባብ የለውም፤” ካለ በኋላ፣ “ይኼ የበታችነት ስሜት ከየት እንደወረሰን ነው ሊገባኝ ያልቻለው። የትናንቱ የረሃብ ታሪክ ነው እንዳንል የአክሱም የኩሽ ሥልጣኔ ባለቤቶች ነን። ስለራሳችን የምናውቀውን መጥፎ ነገር ማሰብ ትርፉ ሽንፈት መጥራት መሆኑን ማወቅ ያለብን ሰዓት ላይ ያለን አይመስላችሁም?” ብሎ፣ “እኔን እዚህ ጫፍ ላይ ጣለኝ፤” አለው። እሱን አውርደን እኛም ልንወርድ ከመቆማችን ወያላው “የዋንጫ እንጂ የደረጃ ራዕይ የለም!” ብሎ “መጨረሻ” አለን። ‹‹በስንቱ ባክነን በስንቱ ተበክለን እንዘልቀው ይሆን?›› የሚለው ጥግ ላይ በዝምታ ተቀምጦ የነበረ አንድ ወጣት ነበር፡፡ መልካም ጉዞ! 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት