Saturday, March 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊማኅበራዊ የጤና መድን ተቀልብሶ በሌላ ሊተካ እንደሚችል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጠቆመ

ማኅበራዊ የጤና መድን ተቀልብሶ በሌላ ሊተካ እንደሚችል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጠቆመ

ቀን:

አዋጅ ወጥቶለትና መዋቅር ተዘጋጅቶለት በሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተግባራዊ ሊደረግ የነበረው ማኅበራዊ የጤና መድን ሥራ ላይ እንዳይውል እክሎች እንደገጠሙት፣ በዚህም ምክንያት በሌላ አሠራር ሊተካ እንደሚችል የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ለፓርላማው ይፋ አደረጉ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንቡ መሠረት ሚኒስትሮችን በመጥራት በሚመለከታቸው ጉዳዮች ላይ የመጠየቅ መብት ያለው ሲሆን፣ ይህንኑ መሠረት በማድረግም ከተሾሙ የሁለት ወራት ዕድሜ ብቻ ያስቆጠሩትን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩን ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነን ሐሙስ ታኅሳስ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠርቷል፡፡

የፓርላማው አባላት ለሚኒስትሩ ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል፣ በአገሪቱ እየተዘረጉ የሚገኙ የጤና መድን ሥርዓቶች ያሉበት ደረጃን የተመለከተው ጥያቄ ይገኝበታል፡፡

ማኅበራዊ የጤና መድን ሥርዓትን ለመዘርጋት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ወጥቶ ወደ ወደ ሥራ በመግባት የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው አናሳ ግንዛቤና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እንቅፋት እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

የጤና መድን አዋጅ ቁጥር 690/2010 ፀድቆ በኋላም ማሻሻያ የተደረገበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የጤና መድን ሽፋን ዋናው ዓላማም ሁሉን አቀፍ የሆነ የጤና ሽፋንን ለማረጋገጥ በመንግሥትና በተጠቃሚው ኅብረተሰብ መካከል ወጪን መጋራት መሆኑን አዋጁ ይጠቅሳል፡፡

በመሆኑም ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በመጀመሪያ ተጠቃሚ የማድረግ ዓላማ ወጥኖ ነበር፡፡ ወደ ትግበራ ለመግባትም የመንግሥት ሠራተኞች ወርኃዊ መዋጮ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው፣ መንግሥትም የራሱን ድርሻና ለጡረታ ባለመብቶች ተጨማሪ መዋጮ የማድረግ ግዴታ ተቀምጦለት ብሔራዊ የጤና መድን ኤጀንሲም ተቋቁሞ ነበር፡፡

‹‹የማኅበራዊ ጤና መድንን ወደ ትግበራ ለማስገባት ያልተቻለው በቂ ቅድመ ዝግጅት ስላልተደረገለት ነው፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ የሠራተኞች ግንዛቤ አናሳ ስለሆነና ብዙ ጥያቄዎችን ሊያስነሳ የሚችል በመሆኑ፣ እንዲሁም ከመድኃኒት አቅርቦትና ከጤና ተቋማት ተደራሽነት ጋር ብዙ መሠራት ያለባቸው ጉዳዮች በመኖራቸው ወደ ትግበራ እንዳይገባ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹ምናልባትም ሌላ አማራጭ ልንከተልና ይኼኛው አሠራር እንዲቀር ልንወስን እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የባለሙያዎች ቡድን በዚህ አዲስ አማራጭ ላይ ጥናት እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛው የጤና መድን አሠራር ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ሲሆን፣ ውጤታማ ስኬቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 18 ሚሊዮን ወይም 18 በመቶ የሚሆነውን የኅብረተሰብ ክፍል መሸፈን እንደቻለ ገልጸዋል፡፡

በ364 ወረዳዎች የተዘረጋው ይህ ሥርዓት ማኅበረሰቡ በጤና መድህን በማሳተፍ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በጤናው ዘርፍ አስቸጋሪ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የመድኃኒት አቅርቦት መሆኑን ሚኒስትሩ አምነዋል፡፡ የመድኃኒት አቅርቦቱን የሚያከናውነው የመድኃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ይህንን ተቋም የግድ ማዘመን ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

መድኃኒት ለመግዛት በዓመት 150 ጊዜ ጨረታ የሚያወጣ ድርጅት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የመድኃኒት አቅርቦት ድርጅቶችን በመምረጥ አብሮ እየሠራ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የረዥም ጊዜ የአቅርቦት ማዕቀፍ ስምምነት ከታዋቂ ድርጅቶች ጋር ለመፍጠር እንደሚሠሩ፣ መድኃኒት አገር ውስጥ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ተጠቃሚዎች ዘንድ እስኪደርስ ድረስ ኮምፒዩተራይዝድ በሆነ ሥርዓት ቁጥጥር የሚደረግበት ሥርዓት ለመዘርጋት ጥረት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...