Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትሌላኛው የአትሌቲክሱ ራስ ምታት

ሌላኛው የአትሌቲክሱ ራስ ምታት

ቀን:

ኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ በአትሌቲክስ በተለይም በኦሊምፒክ ያሳየችው ድንቅ ክንውን ለዘመናት በታሪክ ምኅዳር፣ በዓለም አደባባይ ደምቃ እንድትታይና በተለይ ‹‹ኢትዮጵያ ማናት?›› ለሚለው ጥያቄ መልስ በመስጠት የራሱ ድርሻ ሲወጣ ቆይቷል፡፡

በ1940ዎቹ በግሪክ በመካከለኛ ርቀት ድል በማድረግ ኢትዮጵያን ካስጠሩት እነ ኢሳያስ በኋላ የመጀመሪያውን ኦሊምፒያዊ ድል ካስገኘው አበበ ቢቂላ ቀጥሎ ማሞ ወልዴ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ እንዲሁም ደራርቱ ቱሉ፣ ፋጡማ ሮባ፣ መሠረት ደፋር፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ቲኪ ገላና፣ አልማዝ አያና እያለ በትውልድ ቅብብሎሽ እየተላለፈ አሁን ለሚገኝበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ካደረገቻቸው ውድድሮች በረጅም ርቀት ስሟን ሳታጽፍ የቀረችበት ጊዜ እስከ ቅርብ ዓመታት ባይኖርም፣ አሁን ላይ ግን ቀድሞ የነበራትን ስምና ዝና እያጣች መምጣቷ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ለዚህም የተፎካካሪዎቿ አገሮች ጠንካራ በመሆናቸውና የአትሌቶቿ ሥልጠና በግል መሆን፣ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት ለውጤቱ ማሽቆልቆል በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ ከሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅቶች ጀምሮ የአትሌቲክሱ ደብዛ ከመጥፋቱ በፊት ‹‹ልንታደገው ይገባል›› በሚል ቅሬታቸውን ሲያሰሙ የነበሩ የቀድሞ አትሌቶች አትሌቲክሱን በኃላፊነት ለመምራት በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ በመስከረም ወር ላይ መንበሩን ተረክበዋል፡፡ ሥልጣን የተረከቡት የቀድሞ አትሌቶች በተለይ በአሁኑ ወቅት የአገርን ስምና የአትሌቶችን ተስፋ እያቀጨጨ ያለውን የአበረታች ንጥረ ነገር (የዶፒንግ)  እንቅስቃሴ ለመግታት ጠንካራ አቋም መደንገጋቸውን ባለፈው ታኅሣሥ ለአገር ውስጥና ለውጭ የሚዲያ አካላት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በአንፃሩ ብሔራዊው ፌዴሬሽንና የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ከሚያከናውኗቸው የታዳጊ ወጣቶች ዓመታዊ ውድድር ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች የዕድሜ ተገቢነት ጉዳይ ሌላኛው የአትሌቲክሱ ራስ ምታት እየሆነ መምጣቱ እየተነገረ ይገኛል፡፡

- Advertisement -

በየዓመት ከሚከናወኑ የወጣቶች ውድደር በተመሳሳይ ዕድሜ አትሌቶችን በተለያዩ ውድድሮች ማሳተፍ እየተለመደ መጥቷል፡፡ በውድድሩ የሚሳተፉት አትሌቶችም የዕድሜ ጥያቄ ሲቀርብላቸው ‹‹በቴሴራ ወይስ በፓስፖርት?›› የሚለው የአትሌቶች ምላሻዊ ጥያቄ የተለመደ ነው፡፡ ችግሩ እንዳለ የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለአምስተኛ ጊዜ በባሕር ዳር ከተማ ከጥር 5 እስከ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ተከናውኖ ተጠናቋል፡፡

በውድድሩ ዕድሜያቸው 18 እና 19 የሆናቸው ወጣት አትሌቶች የሚወዳደሩበት ቢሆንም፣ በመድረኩ ግን ለአራተኛ ጊዜ በተመሳሳይ የዕድሜ እርከን ሲወዳደሩ የነበሩ አትሌቶች ተስተውሏል፡፡

በዓመታዊ የታዳጊዎች፣ የወጣቶች ውድድር የሚስተዋለውን የዕድሜ ችግር የክልልና የከተማ አስተዳደሮች፣ ውጤት አምጥቶ መመስገንን ብቻ ዓላማ ያደረገ መሆኑ ዋንኛው አሉታዊ ጎኑ እንደሆነ የአትሌቲክሱ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተሳታፊ የሆኑ የክለብ አሠልጣኞች እንደሚገልጹት ከሆነ፣ የአወዳዳሪው አካል ቁርጠኛ አቋም እንደሚያስፈልግ ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡

‹‹እኛ በተቀመጠው የዕድሜ እርከን መሠረት ተወዳዳሪዎች ብናሳትፍ ሌሎች ከእኛ ልጆች ጋር ተመጣጣኝ አትሌቶችን ስለማያሳትፉ ችግሩን እንዲጎላ ያደርገዋል፤›› በማለት ሌተናል ኮሎኔል ንጉሤ አየለ የመከላከያ አትሌቲክስ ቡድን መሪ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

እንደ ቡድን መሪው፣ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ አየተባባሰ መምጣቱ ተተኪዎችን ለማፍራት እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን ያሳያል፡፡ በተጨማሪም ሁሉም ክለቦች በታዳጊ ወጣቶችና በአዋቂ ዘርፍ አትሌቶችን አለማቀፋቸው ከፍተኛ ችግር እንዲፈጠር አድርጓል ባይ ናቸው፡፡ ችግሩ በተለይ በሜዳ ተግባር ወንድ ተወዳዳሪዎች ላይ በስፋት እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ በተካሄው የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ የኢትዮጵያ ፌዴሬሽኑ ባወጣው ደንብ መሠረት ተሳታፊ ክለቦች ከዚህ ቀደም በአገር ውስጥ በተደረገ የወጣቶች ውድድር ላይ ተሳትፈው ከተመረጡ በኋላ አገራቸውን ወክለው በአህጉርና በዓለም አቀፍ ውድድር ለመሳተፍ በፌዴሬሽኑ የወጣላቸው ፓስፖርት አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡

በዚህም መሠረት ውድድሩ ከመደረጉ ቀደም ብሎ ክለቦች በተላከው የተሳትፎ ደብዳቤ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ፓስፖርት የወጣላቸው አትሌቶች በዚህኛው ውድድር ላይ ማሳተፍ እንደማይችሉ ቢነገርም፣ በተቃራኒ አንዳንድ ክለቦች እንዲያሳትፉ መደረጉ ትክክል አይደለም በማለት ኮሎኔል ንጉሤ ቅሬታቸውን አክለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ከሰነዘሩት የክለብ አሠልጣኞች፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የረዥም ርቀት አሠልጣኝ አቶ ተፈሪ መኮንን፣ ‹‹አንድ አትሌት በአንድ ክለብ በቴሴራ በ18 ዓመት ከፈረመ በኋላ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ለሌላ ክለብ ሲፈርም ያንኑ ዕድሜ በማስመዝገብ በየዓመቱ በሚደረጉ ውድድሮች ላይ ሲሳተፍ ይስተዋላል፤›› በማለት የአሠራር ሥርዓቱን ይተቻሉ፡፡

በአምስተኛው የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በበኩላቸው፣ ‹‹ችግሩን በቀላሉ ለመፍታት ይቸግራል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን አትሌቶችን በትውልድ ዘመን ወረቀት መሠረት በማጣራት እንዲወዳደሩ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

የዕድሜ ችግር በዓለምና በአህጉር ውድድሮች ላይ በተመሳሳይ መኖሩ፣ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች በትክክለኛው ዕድሜ መሠረት ልሂድ ብትል ተጎጂ የምትሆንበት ዕድል ሰፊ ሊሆን የሚችልበት የሚናገሩ አሉ፡፡

ሻለቃ ኃይሌ ግን፣ ችግሩ በሁሉም አገሮች በመስተዋሉ ምክንያት ፍቱን መፍትሔ እስኪመጣ ፌዴሬሽኑ ለሚያደርጋቸው የወጣቶች ውድድር በአግባቡ ተከታትሎና በዕድሜ ጉዳይ ዕውቅና የሰጣቸውን አትሌቶችን ብቻ እንደሚያሳትፍ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በማያያዝ ፕሬዚዳንቱ በውድድሩ ወቅት በግዙፉ የባህር ዳር ስታዲየም ተመልካቾች አለመገኘቱ ቅር እንዳሰኛቸው አልሸሸጉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...