Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጀርመኑ ፌርትሬድ ከፕራና ፕሮሞሽን የተጣመሩበት የግብርና ምርቶች የንግድ ዓውደ ርዕይ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በግብርና ዘርፍ፣ በምግብና በመጠጥ፣ በፕላስቲክ እንዲሁም በማሸጊያ ቴክኖሎጂ እንዲሁም በጥሬ ዕቃዎች ላይ ያነጣጠረውና ‹‹አግሮ ፉድ ፕላስት ፓክ ኢትዮጵያ›› የተሰኘ የንግድ ዓውደ ርዕይ ከጥር 26 እስከ ጥር 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

በዚህ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ ለቴክኖሎጂ ሽግግር ሚና ያላቸው ማኅበራትና ከ14 አገሮች የተውጣጡ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ይዘው እንደሚቀርቡ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የዘርፉ ተዋንያንን ጨምሮ ከሁለት ሺሕ በላይ ጎብኚዎች እንደሚታደሙበት ረቡዕ ጥር 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በተከናወነ ጋዜጣዊ መግለጫ አዘጋጆቹ ይፋ አድርገዋል፡፡

የ14 አገሮች ተሳታፊዎች ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚጠቅሙ ምርቶችን በመያዝ የሚሳተፉት ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ ከኦስትሪያ፣ ከፈረንሳይ፣ ከጀርመን፣ ከህንድ፣ ከኬንያ፣ ከኔዘርላንድስ፣ ከታይዋን፣ ከታይላንድ፣ ከቶጎ፣ ከዩክሬይን፣ ከእንግሊዝ፣ ከአሜሪካና ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የተውጣጡ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በዓለም ገበያ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ድርጅቶች በዓውደ ርዕዩ ተሳታፊ እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የዘርፉ ባለድርሻዎችና ጎብኚዎች በመድረኩ ተገናኝተው የንግድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

የንግድ ትርዒቱ በፈረንሳዩ የምግብ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎች ዓለም አቀፍ ትብብር (Adepta)፣ በጀርመኑ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት (GIZ) እንዲሁም በጀርመን ኢንጂነሪንግ ፌዴሬሽን (VDMA) በተባሉት ተቋማት የሚታገዝ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩልም የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ የምግብ፣ መጠጥና ጤና ክብካቤ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ትብብርና ፈቃድ ሰጪነት የተዘጋጀ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት እንደሆነ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከምሥራቅና ከመካከለኛው አፍሪካ በመላቅ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ እንደ ሃይኒከን፣ ኔስሌ እንዲሁም እንደ ዩኒሊቨር ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች መምጣት የጀመሩባት መሆኗን አዘጋጆቹ አስታውሰዋል፡፡ ኩባንያዎቹ  በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር መዋዕለ ንዋይ በምግብና በመጠጥ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በማፍሰስ ላይ ናቸው፡፡ በመሆኑም ‹‹በኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ የንግድ ትርዒት ማዘጋጀት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው፤›› በማለት የጀርመኑ ፌርትሬድ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ማርቲን ማርዝ ተናግረዋል፡፡ የንግድ ትርዒቱ በተለይ በኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት በዘርፉ ያለውን ዕድል ተጠቅመው በመሥራት የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማምጣት ብሎም በቅርቡ ተገንብተው ወደ ሥራ እንደሚገቡ በሚጠበቁት የተቀናጁ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ሚስተር ማርዝ አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በግብርና፣ ምግብ ማቀነባበሪያ በፕላስቲክና በማሸጊያ ዘርፍ ያለውን ነባራዊ የቴክኖሎጂዎች፣ ግብዓትና የምርቶች ፍጆታ እንዲሁም የግብይት ሒደትን በተመለከተ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ እ.ኤ.አ. በ2014 ብቻ ከ200 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በማውጣት የምግብ ማቀነባበሪያና ማሸጊያ ማሽነሪዎችን ከውጭ በማስገባት ከምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች ቀዳሚውን ስፍራ እንደያዘች ተገልጿል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2010 እስከ 2014 ባለው ጊዜ ውስጥም የእነዚህ ምርቶች ፍጆታ የ38 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የፕላስቲክና የማሸጊያ ማሽነሪዎችን ከውጭ በማስገባትም ኢትዮጵያ በምሥራቅና በመካከለኛው አፍሪካ ከሚገኙ አገሮች በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትቀመጥ በዕለቱ የቀረበው ጥናት ያመለክታል፡፡

ይህ አኃዝ የ25 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የፕላስቲክ ጥሬ ዕቃዎችን በማስገባቱ ረገድም እ.ኤ.አ. ከ2010 እስከ 2014 በነበረው ጊዜ ውስጥ 46 በመቶ ዓመታዊ ዕድገትን ያሳየ ሲሆን፣ እነዚህን ምርቶች ለማስገባትም በ2014 ወጪ የተደረገው የውጭ ምንዛሪ መጠን 527 ሚሊዮን ዩሮ እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡

ኢትዮጵያ የግብርና ማሽነሪዎችን ከውጭ በማስገባቱ ረገድ በአካባቢው ከሚገኙ አገሮች ይልቅ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዛ የምትገኝ ሲሆን፣ በምግብና በምግብ ነክ ንግድም የአካባቢው ማዕከል ሆና እንደምትገኝ አዘጋጆቹ ጠቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዓመታዊ የምግብ ምርቶች የገቢ ንግድ መጠን እ.ኤ.አ. በ2009 ከነበረበት 866 ሚሊዮን ዶላር፣ እ.ኤ.አ. በ2015 ወደ 2.738 ቢሊዮን ዶላር በማሻቀብ የ21 በመቶ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት ማሳየቱ ተጠቅሷል፡፡ በኤክስፖርት አፈጻጸማቸውም ውጤታማ ለሆኑት የቡናና ሻይ፣ የቅባት እህሎች፣ አትክልትና የፍራፍሬ ምርቶች የኢትዮጵያ የምግብ ኤክስፖርት ዓመታዊ ዕድገት 13 በመቶ እንደደረሰም በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ተጠቅሷል፡፡

ፌርትሬድ እ.ኤ.አ. በ1991 የተመሠረተ ድርጅት ሲሆን፣ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በፍጥነት በማደግ ላይ ባሉ አገሮች በተለይም በሰሜንና ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅና በምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ውስጥ የንግድ ትርዒቶችን በማዘጋጀት ዕውቅናን ካተረፉ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን ማርዝ አስታውሰዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች