የኢትዮጵያ የለንደን ኦሊምፒክ ደረጃ 22ኛ ሆነ
ዓመት በፊት በለንደን በተዘጋጀው 30ኛ ኦሊምፒያድ በ3,000 ሜትር መሰናክል የነሐስ ሜዳለያ ያገኘችው ኢትዮጵያዊቷ ሶፍያ አሰፋ፣ ሜዳሊያዋ ወደ ብር ከፍ ማለቱን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
በለንደን ኦሊምፒክ በርቀቱ አሸናፊ የነበረችው ሩሲያዊቷ ዩሊያ ዛሪፖቭ ዶፒንግ (አበረታች ንጥረ ነገር) መጠቀሟ በመረጋገጡና ውጤቷ በመሠረዙ ሦስተኛ የነበረችው ሶፊያ በሽግሽግ ወደ ሁለተኛ ከፍ እንድትል ተደርጓል፡፡ ሁለተኛ የነበረችውና ብር ሜዳሊያ አግኝታ የነበረችው ቱኒዚያዊቷ ሀቢባ ግሪቢ የወርቁን፣ አራተኛ የነበረችው ኬንያዊቷ ሚልካ ቼሞስ የነሐስ ሜዳሊያ እንዲያገኙ መወሰኑን ታውቋል፡፡
ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ በቤጂንግና በለንደን ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተወዳዳሪ ከነበሩ ከ1,000 በላይ አትሌቶች ላይ ባደረገው ዳግም የደም ናሙና ምርመራ ሩሲያዊቷ ዛራፖቫ፣ ስትሪዮድ ትሪናቦል የተባለ ንጥረ ነገር መጠቀሟ ስለተረጋገጠ ውጤቷ ተሰርዟል፡፡
ሩሲያዊቷ ከአትሌቲክስ ከመታገዷ በተጨማሪ መጋቢት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት (ካስ) በሰጠው ውሳኔ ከሐምሌ 13 ቀን 2003 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2005 ዓ.ም. የዓለም ሻምፒዮናን ጨምሮ ያስመዘገበችው ውጤቷም ተሰርዟል፡፡
ከስድስት ዓመት በፊት በዳጉ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 3,000 ሜትር መሰናክል ባለወርቅ የነበረችው ዛሪፖቫ፣ እንደለንደኑ ሁሉ ድሉን ለቱኒዝያዊቷ ሀቢባ ስትሰጥ፣ ሦስተኛ የነበረችው ኬንያዊቷ ቼሞስ ሁለተኛ፣ አራተኛ የነበረችው መርሲ ዋንደኩ ሦስተኛ በመሆን ብርና ነሐሱን አግኝተዋል፡፡ ነሐሴ 24 ቀን 2003 በተካሄደው በዚሁ ውድድር ስድስተኛ የነበረችው ሶፊያ አሰፋ ወደ አምስተኛ ከፍ ብላለች፡፡
በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ በ3,000 ሜትር መሠናክል ሩጫ በሞስኮ ኦሊምፒክ በ1972 ዓ.ም. ነሐስ ሜዳሊያ በማጥለቅ፣ ቀዳሚ ከነበረው ሻምበል እሸቱ ቱራ ቀጥላ ሁለተኛዋ የሆነችው ሶፍያ አሰፋ በሴቶች የቀዳሚነት ታሪክን አቅልማለች፡፡
ኢትዮጵያ በወቅቱ በለንደን ኦሊምፒክ 3 ወርቅ፣ 1 ብር እና 3 ነሐስ በማግኘት በደረጃ ሰንጠረዡ 24ኛ ሆና ማጠናቀቋ የሚታወስ ሲሆን፣ በተደረገው ሽግሽግ የሶፊያ ነሐስ ወደ ብር በመለወጡ በ3 ወርቅ፣ በ2 ብር እና በ2 ነሐስ ሁለት ደረጃ በማሻሻል 22ኛ ላይ መቀመጧን ተመልክቷል፡፡
ሦስቱን ወርቆች ቲኪ ገላና በማራቶን፣ ጥሩነሽ ዲባባና መሠረት ደፋር በ10,000ሜ እና በ5,000ሜ፤ ደጀን ገብረመስቀል በ5,000ሜ ብር፣ ጥሩነሽና ታሪኩ በቀለ በ5,000ሜ እና በ10,000ሜ ነሐስ ሜዳሊያ ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ከአፍሪካ በ3 ወርቅ፣ 2 ብርና 1 ነሐስ ቀዳሚ የነበረችው ደቡብ አፍሪካ፣ በሶፊያ ብር ምክንያት ደረጃውን ለኢትዮጵያ አስረክባ ወደ 23ኛ ወርዳለች፡፡
ከኢትዮጵያ ከሜልቦርን (እ.ኤ.አ.1956) እስከ ሪዮ (2016) በተካሄዱትና በተካፈለችባቸው 13 ኦሊምፒያዶች የተስተካከለውን ውጤቷን ጨምሮ 22 ወርቅ፣ 10 ብርና 21 ነሐስ በድምሩ 53 ሜዳሊያዎችንም ሰብስባለች፡፡
ሶፊያ የብር ሜዳሊያዋን ሐሙስ ጥር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በድሪምላይነር ሆቴል የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባሏ ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይና የስፖርት ሹማምንት በሚገኙበት በሚደረግ ሥነ በዓል እንደምታጠልቅ ታውቋል፡፡
ከአራት ዓመት በፊት ጥር 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለለንደን ኦሊምፒክ ውጤታማ አትሌቶች በተለይ ብርና ነሐስ ላገኙ 50 ሺሕና 40 ሺሕ ብር ሲሸልም ሶፍያ 40 ሺሕ መሸለሟ ይታወሳል፡፡ በሜዳሊያ ሽግሽግ መሠረት የገንዘብ ሽልማት ሽግሽግ ይኖር ይሆን? እየተሰነዘረ ያለ አስተያየት ነው፡፡
ሶፊያ ዓምና በኮንጎ ብራዛቪል በተደረገው የመላው አፍሪካ ጨዋታ በተመሳሳይ ርቀት ወርቅ፣ እንዲሁም በ2005 ዓ.ም. በሞስኮ በተካሄደው ያለም ሻምፒዮና የነሐስ ሜዳሊያ ማስመዝገቧ ይታወሳል፡፡