Thursday, March 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሐዋሳ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የብረታ ብረት ፋብሪካ ተገነባ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የአንድ ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው አራት ፋብሪካዎች በመጪው ዓመት ሥራ ይጀምራሉ

አለታ ላንድ ቢዝነስ ግሩፕ የተባለ ኩባንያ፣ በመጪው ዓመት ወደ ሥራ ከሚያስገባቸው አራት ትላልቅ ፋብሪካዎች መካከል የ560 ሚሊዮን ብር ካፒታል የሚጠይቀውን የብረታ ብረት ፋብሪካ ግንባታ በማገባደድ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

 የግሩፕ ኩባንያው ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ሲላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሐዋሳ ከተማ ሲገባ ትልቅና የመጀመሪያ የሆነውን ብረት ማቅለጫ ፋብሪካን ጨምሮ የፓስታና መኮረኒ ማምረቻ፣ በገላን ከተማ የወረቀት ፋብሪካ እንዲሁም በዱከም የውበት መጠበቂያ ኮስሜቲክሶችን የሚያመርት ፋብሪካ ግንባታዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የሁሉም ፋብሪካዎች ግንባታ በመገባደድ የማሽን ተከላ መጀመሩን አቶ ሀብታሙ አብራርተዋል፡፡

በሐዋሳ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው አለታ ላንድ የብረት ማቅለጫ ፋብሪካ ከ13 ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ በሆነ ቦታ ላይ የሰፈረ ሲሆን፣ በዓመት 300 ሺሕ ቶን ብረት የማምረት አቅም እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር ለ200 ሰዎች የሥራ ዕድል ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በክልሉ በዚህ ደረጃ የብረት ማቅለጫ ፋብሪካ ሲገነባ የመጀመሪያው እንደሆነና ይህ ፋብሪካ ለግንባታ የሚሆኑ ብረቶችን በደቡብ ክልል ማምረት መቻሉ ከሌሎች አካባቢዎች የሚጓጓዘውን መጠን እንዲቀንስ በማድረግ የግንባታ ሥራዎችን እንደሚያፋጥን አቶ ሀብታሙ ይናገራሉ፡፡ ይህ ፋብሪካ ከስምንት እስከ 24 ሚሊ ሜትር መጠን ያላቸውን የአርማታ ብረቶች በማምረት የክልሉን የብረታ ብረት ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ለሌሎች ገበያዎችም ሊያቀርብ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በሐዋሳ ከተማ የሚገነባው ሌላው ፕሮጀክት የፓስታና የዱቄት ፋብሪካ ነው፡፡ በ190 ሚሊዮን ብር ካፒታል የሚገነባው ይህ ፋብሪካ በ2010 ዓ.ም. ሥራ ይጀምራሉ ከተባሉት ውስጥ ሲመደብ፣ ከውጭ የሚገባውን የፓስታና የማካሮኒ መጠን ለመተካት እንደሚያግዝና ለ200 ሰዎችም የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

በገላን ከተማ በ10 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ80 ሚሊዮን ብር ካፒታል ግንባታው ተገባዶ እንደሌሎች ፋብሪካዎች ማሽን እየተገጠመለት ያለው የወረቀት ፋብሪካ ነው፡፡ ይህ ፋብሪካ ለማንኛውም ዓይነት የሕትመት አገልግሎት የሚውል ወረቀት የሚያመርት ሲሆን፣ በዓመት ሰባት ሺሕ ቶን ያመርታል ተብሏል፡፡ ለ60 ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚሰጥም ይጠበቃል፡፡

ግሩፕ ኩባንያው እየገነባቸው ከሚገኙት አራተኛው የሆነው ለውበት መጠበቂያ የሚሆኑ ቅባቶች ማምረቻ ፋብሪካ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ለውበት መጠበቂያነት ከሚውሉት ቅባቶች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው፣ የፋብሪካው ግንባታ ሲጠናቀቅ በዚህ መስክ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ ሲበጠቅ፣ 80 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ በ12 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አብዛኛው የፋብሪካው ግንባታ ተጠናቆ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ዝርጋታ የማሽን ተከላ እየተካሄበደት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ከ80 በላይ ሠራተኞች እንደሚቀጥርም ይጠበቃል፡፡ ሁሉም የአለታ ላንድ ግሩፕ ፋብሪካዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሥራ የሚጀምሩ ከሆነ፣ ከ540 በላይ በተለያየ ደረጃ ያሉ የሚሰማሩ ሠራተኞች ያስፈልጓቸዋል፡፡  

አቶ ሀብታሙ እንደሚናገሩት፣ ኩባንያው በአባታቸው የቡና ንግድ መነሻነት ቀስ በቀስ እዚህ የደረሰ ሲሆን፣ ወደፊት የሚከፈቱትን ፋብሪካዎች ጨምሮ ሰባት ድርጅቶች በሥሩ ያሉት ሲሆን በንግድ፣ በእርሻ ሥራ፣ በፋብሪካ፣ በመዝናኛ እንዲሁም በአስመጪና ላኪነት ሥራ ላይ የሚሳተፉ ድርጅቶችን ያስተዳድራል፡፡ በጉዟቸው በጣም ፈታኝ አጋጣሚዎችን በማለፍ አሁን ለሚገኙበት ደረጃ መድረሳቸውን በማስታወስ፣ አሁንም ግን ሊፈቱ ያልቻሉ ችግሮች ድርጅቶቻቸውን እያጋጠሟቸው እንደሚገኙ አቶ ሀብታሙ ይናገራሉ፡፡ የሠራተኛው የባለቤትነት ስሜት መቀዛቀዝ፣ የተማረ የሰው ኃይል እንደልብ አለማግኘት ለድርጅቱ ፈተና እንደሆኑበት ጠቅሰዋል፡፡

በመንግሥት በኩልም መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አውስተው በቅርቡ በሐዋሳና በዱከም በመዝናኛው ዘርፍ አዳዲስ ይዘቶችን በማምጣት ግንባታቸው ተጠናቆ ለሕዝብ ክፍት የሚሆኑ ተቋማት እንዳሉም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አለታ ላንድ ግሩፕ የቤተሰብ ድርጅት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል የሚያንቀሳቅስ፣ በሥሩም ከአራት ሺሕ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች እንደሚያስተዳድር ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዋጭ ቢዝነሶችን በማስጠናት እስከ መጪው 2030 ላለው ጊዜ ዕቅድ በመንደፍ በተለያዩ ዘርፎች እስከ 20 ሺሕ  ሠራተኞችን የሚያስተዳድሩ ድርጅቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየሠሩ ስለመሆናቸውም የኩባንያቸው ሰነዶች ይጠቁማሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች