ከቦብ ማርሌ አደባባይ ወደ ቦሌ 17 ጤና ጣቢያ በሚወስደው መንገድ ከሚገኝ ምግብ ቤት ክብ ሠርተው የጀበና ቡና ከሚጠጡ ተስተናጋጆች ግማሹ ያጨበጭባል፣ ግማሹ ደግሞ ይስቃል፡፡ በመሀል ፀጥታ ይሰፍንና ሁሉም በጥሞና ያዳምጣሉ፡፡ የሁሉም ትኩረት ከመሀከላቸው ባለው ክራር የያዘ ጎልማሳ ላይ ነበር፡፡
ሚሊዮን ታመነ ይባላል፡፡ ራሱን ጓደኞቼ አወጡልኝ በሚለው ስሙ ‹‹ፈላስፋው ዲያጎ›› እያለ የሚጠራው፣ በአዲስ አበባ በቂርቆስ አካባቢ ተወልዶ እንዳደገ ይናገራል፡፡ ትምህርቱንም ዝዋይ ሕፃናት ማሳደጊያ በመጀመር፣ በሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማጠናቀቁን በኋላም በ1994 ዓ.ም. ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ቢገባም በተለያዩ ችግሮች እንዳቋረጠ ያስታውሳል፡፡
የተለያዩ ለዕለት የሚሆኑ ሥራዎችን እየሠራ ቢያሳልፍም፣ የሙዚቃ ፍቅሩ ሁሉንም ማሸነፉን ይገልጻል፤ በምሽት ክበቦች በማዘውተር የሙዚቃ አምሮቱን የሚወጣው ፈላስፋው ዲያጎ፣ አንዳንድ ጥቅሶችን ከመጽሐፍ በመውሰድ ይጠቅሳል፣ ከሙዚቃው ባሻገር ኮሜዲዎችን እያቀረበ ሰዎችን ያዝናናል፡፡ ‹‹ሥራዬ ሁለገብ በመሆኑ ፈላስፋው ዲያጎ የሚለውን ስም ያዩኝ አውጥተውልኛል፤›› ይላል፡፡
ፈላስፋው ዲያጎ፣ ከአናቱ የማይጠፋው የሰሌን ኮፍያው በልብ ቅርጽ የተሠራው መነጽሩ፣ በነጭ ሸሚዝ ላይ በሚያደርገው ቀይ ከረባቱ ይለያል፡፡ በከረባቱ ላይ ደግሞ ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አገኘሁ የሚለውን የቤት ለቤት አጫዋች አገልግሎት ሰጪ የሚል ባጅ አንጠልጥሏል፡፡ በአፉ አካባቢ ትንሽዬ ድምፅ ማጉያ አለች፣ በግራ እጁ መለያ የሆነችው ክራር ይይዛል፡፡ ክራሩ ላይ የተለያዩ መጣጥፎች ተለጥፈዋል፡፡ በወገቡ ላይ ቤልት ስፒከር (ድምፅ ማስተላለፊያ) ታጥቆ በመንቀሳቀስ የተለያዩ ማስታወቂያዎችን ሲለፍፍ ይውላል፡፡
ዲያጎ ሥራውን ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ፣ መገናኛ ባሉ የገበያ ሞሎች፣ ቦሌ፣ 22 እንዲሁም በየትኛውም ቦታ ሰዎች በተሰበሰቡበት አካባቢ በመዘዋወርና የተለያዩ ምርቶችን፣ አገልግሎቶችን በድምፁ በመለፈፍ በማስተዋወቅና ለአንድ ማስታወቂያ 100 ብር በማስከፈል ሲሠራ ይውላል፡፡ አንድ ምግብ ቤት በምሳ ሰዓት ስላለው የምግብ ዓይነትና ዋጋውን በምግብ ቤቱ አካባቢ በመንቀሳቀስ፣ ወደዚህ ምግብ ቤት መጥተው ቢመገቡ የሚያገኙትን አገልግሎት ያስተዋውቃል፡፡
ማስታወቂያውን በሚያቀርብበት ሰዓት በሥራው የተዝናና ካለ ለፈላስፋው ሸጎጥ ያደርግለታል፡፡ በክራሩ ላይ የተለጠፉት ማስታወቂያዎች በባለቤቱ ፈቃደኝነት ክፍያ ይፈጸምባቸዋል፡፡ እንዲህ እየሠራ ከቀኑ 11 ሰዓት ዕቃዎቹን ወደ ሻንጣው በማድረግ ወደ ቤቱ ያዘግማል፡፡
ለየት ወዳለው በየጎዳና እየተንቀሳቀሱ ማስታወቂያ ወደመሥራት እንዴት እንደገባ ሲያወጋ ‹‹በምሽት ክለብ ሥራዬ ብዙም ለውጥ አላመጣሁም፡፡ አንድ ጓደኛዬ ሠርግ እንድናጅብ ከጠራኝ በኋላ ግን ነገሮች ተቀየሩ፡፡ ክራሬን ይዤ በግሌ ሠርግ ሳጅብ፣ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ቀልድ በመቀላቀል ሳዝናና ሽልማት ማግኘት ጀመርኩ፤›› የሚለው ዲያጎ ሰዎችም ቤታቸው ግብዣ ሲኖር እንግዶቻቸውን እንዲያዝናና ሲጠራ ከንዋይ መቋደሱን መቀጠሉን ይናገራል፡፡
በፊት የሚሠራው በድምፅና በክራር ብቻ የነበረ ቢሆንም የሚያበረታቱት ሰዎች ማይክና ቤልት ስፒከር በዕርዳታ ሰጥተውታል፡፡ ይህም ብዙ ሰዎች ባሉበት ማስታወቂያ ሲናገር እንዲደመጥ ረድቶታል፡፡
ሥራውን ሲያቀርብ፣ ‹‹የተመሰከረለት ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ›› በማለት ነው፡፡ ሰዎች ሐሳባቸው እሱ እንደሆነ ከተመለከተ በኋላ እንደ ሰዎቹ ስሜትና ዕድሜ ለጥቂት ደቂቃዎች ዘፈን ያቀርባል፡፡ በይበልጥ ማየትና ማዳመጥ መጀመራቸውን ሲያስተውል ቀልድ ቢጤ ጣል ያደርጋል፡፡ ከማስታወቂያውና ከአንድ ዘፈን በኋላ ሰዎቹን ማሞገስ ይያያዛል፡፡ በመሀል የተከፈለባቸውን ማስታወቂያዎችን በመድገም፣ ‹‹ምርቶንና አገልግሎትዎን ለማስተዋወቅ በአንድ ሰዓት ‹‹100 ሺሕ ብር›› (በእሱ አባባል 100 ብር ማለት ነው) ብቻ ያስከፍላል በማለት አድራሻውን በማስተዋወቅ ይጨርሳል፡፡
የሚሠራባቸው መሣሪያዎች ሲበላሹ ራሱ እንደሚጠግናቸው ገልጾ በሥራው ግን ችግሮች እንደሚገጥሙት ይናገራል፡፡ ‹‹በፊት ሥራዬን ስጀምር በየመንገዱ፣ በታክሲ ተራዎችና በባስ ስቴሽን አካባቢ በመሆኑና ሰዎችም ስለሚሰበሰቡ ሥራዬ በፖሊስ ይቋረጥ ነበር፡፡ መዝናኛ ቦታዎች እንደልብ መግባትም አልችልም ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መታወቂያ ከሰጠኝ ጀምሮ ግን በነፃነት መሥራት ችያለሁ፤›› ይላል፡፡
እንዲህ ዓይነት የማስታወቂያ አነጋገር በአንጋፋው የማስታወቂያ ባለሙያ በአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ በሀሎ ሀሎ እንደተጀመረ ይናገራል፡፡ በዚህ ዘመን ማስታወቂያ በሰዎች እያዞሩ ማስነገር ጥቅም አለው ወይ ብሎ ሪፖርተር የምግብ ቤት ባለቤት የሆነችውን ትዕግስት አበራን ጠይቋት ነበር፡፡ ትዕግስት እንደምትለው፣ በአካል ስለሚነገር ሰዎች ሊሰሙት ይችላሉ፡፡ ሊያዝናናም ይችላል፡፡ ሰምቶ ወደ ቦታው ለመሄድ እምነት የሚያጣ ሊኖርም ይችላል፡፡
ዲያጎ በቀን ከ300 እስከ 400 ብር እያገኘ ወደቤቱ እንደሚገባ ገልጿል፡፡