Saturday, April 20, 2024

ድርድሩ የት ድረስ ይዘልቃል?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያወጡት መግለጫ ተነቧል፡፡ ድርድሩ የተሳካ ይሆን ዘንድ የሁሉም አካላት ድርሻ እንዲያይል የሚጠይቅ ነው፡፡ ኢሕአዴግም እንደ ከዚሁ በፊት ለይስሙላ፣ ለሚዲያ ፍጆታና ለማይረባ የፖለቲካ ትርፍ እንዳያውለው ያሳስባል፡፡

ዕድል የተሰጣቸው ጋዜጠኞች ይጠይቃሉ፡፡ አንዲት እንስት ትንሽ ለየት ብላ የተቀላቀለችበት የፖለቲካ አመራሮች ቡድን አባላትም እየተፈራረቁ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ጥያቄዎች ከተሰጡ ምላሾች በላይ እውነታውን የሚናገሩ ይመስላሉ፡፡

‹‹የእኔ ጥያቄ. . .›› ይቀጥላል የጀርመን ሬድዮ ጋዜጠኛ፣ ‹‹የኃይል ሚዛኑን ለማመጣጠን ማለትም በእናንተና በገዢው ፓርቲ መካከል ያለው ከፍተኛ የአቅም ልዩነት ሲታይ፣ የታሰበው ነገር ድርድሩ ነው ለማለት ያስችላል ወይ? ውይይት ቢባል አይቀልም?›› በማለት ጥያቄ ያነሳል፡፡ መድረክ ላይ ካሉት አመራሮች መካከል የመኢአድ ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴ፣ ‹‹እውነት ነው የኃይል ሚዛኑ የሚመጣጠን አይደለም፡፡ እኛ በእጃችን ያለው ብቸኛ ነገር ሐሳብና ብዕር ነው፡፡ ኢሕአዴግ ግን ጠመንጃም ገንዘብም በእጁ ነው፤›› ምላሻቸውም አልተቋጨም፡፡ ‹‹ነገር ግን ድርድሩ የሚካሄደው በጉልበት አይለደም፡፡ አንዳንድ መርሆዎችን መሠረት አድርጎ ነው የሚካሄደው፤›› በማለት ይመልሳሉ፡፡

‹‹ፓርቲ ምንም ያህል አቅም ቢኖረው ብቻውን አገር ሊመራ እንደማይችል፣ ግንኙነታችን የአቅም ጉዳይ ሳይሆን የፖለቲካ መበላለጥ ነው፡፡ የተሻለ ሐሳብ ይዞ የመጣ አካል ቅቡል የሚሆንበት መድረክ ይሆናል የሚል ተስፋ ነው ያለን፤›› በማለት ያክላሉ፡፡

እዚህ ላይ ያላቸውን አስተያየት ገታ አድርጎ፣ ‹‹ድርድር ብሎ መጥራት ይቻላል ወይ?›› የሚለው ሌላ የጋዜጣዊ መግለጫው ተካፋይ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ንግግር ሳይጀምሩ ፊታቸው ላይ ትንሽ የግራ መጋባት ስሜት ይታይባቸዋል፡፡ ‹‹ጥያቄው ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር ድርድሩ በቀላሉ የተገኘ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ የሚወስን ነው የሚሆነው፤›› ሲሉ ምላሽ መስጠት ጀመሩ፡፡

አቶ በዛብህ ይቀጥላሉ፡፡ ‹‹ከ1997 ዓ.ም. በኋላ ሁሉም ነገር ዝግ ነበር፡፡ ምንም የሚያንቀሳቅስና የሚያፈናፍን ነገር አልነበረም፡፡ ብዙ ጊዜ ሄዶ ሄዶ ይኼ እንዳይሆን ደጋግመን አሳስበናል፣ የሚሰማ አልነበረም፡፡ ባለፈው ዓመት የተነሳው ሁከት ከዚሁ አካሄድ የመነጨ ነው፡፡ ስለዚህ ድርድሩ በሕዝቡ ግፊት የተገኘ ድል ነው፡፡ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤›› አሉ፡፡

ጥያቄዎቹ አሁንም ቀጥለዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ደግሞ የድርድሩን አግባብነት (ሞራል) ትንሽ ዞር አድርጎ አምጥቶታል፡፡ ‹‹ሁከቱን በመቀስቀስም ሆነ በመፍታት እናንተ አልነበራችሁበትም፤›› በሚል መንደርደሪያ ይነሳና በዚህ ሕዝባዊ ተቃውሞ የነበራቸውን ድርሻ ያሳንሳል፡፡ ‹‹ታዲያ እናንተ በዚህ ጉዳይ ላይ ሕዝቡን ወክላችሁ የመደራደር የሞራል ብቃት አላችሁ ወይ? ማለቴ ሸክሙን ትችሉታላችሁ ወይ?›› ምላሽ ከሰጡት መካከል አቶ ተሻለ ሰብሮ (የኢራፓ ሊቀመንበር)፣ ‹‹በተቃውሞው ወቅት ቀጥተኛ የሆነ ተሳትፎ ባይኖረንም ይኼ ነገር አደገኛ አካሄድ እንደሆነ ስንጠይቅና ስናስጠነቅቅ ቆይተናል፡፡ ኢሕአዴግ የፓርላማ ወንበሮችን ጠቅልሎ ሲወስድ አሳስቦን ነበር፡፡ አሁን ግን ጥያቄው ከተቃዋሚዎች ወጥቶ ሕዝቡ ራሱ ገንፍሎ አውጥቶታል፡፡ ያ ማለት ግን እኛ አይመለከትንም ማለት አይደለም፡፡ ሕዝቡን ወክለን መደራደር እንችላለን፡፡ የፖለቲካ አስኳሉና ክሬሙ ያለው ግን ማን እጅ ላይ ነው? በኢሕአዴግ ነው፤››  ብሏል፡፡  

ብዙዎቹ የፓርቲ አመራሮች በዚህ ላይ ተጨማሪ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በተለይ የኢዴፓ ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ በአሁኑ ወቅት በሕጋዊ መንገድ ከመደራደር ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ የድርድሩ ውጤት ምን ድረስ ይኼዳል በማለት ለቀረበው ጥያቄም፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሺዋስ አሰፋ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት የተደረጉ ድርድሮች ውጤታቸው በዜሮ ነው የተባዛው፡፡ የአሁኑ እንደዚያ እንደማይሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ አሊያም ግን የሕዝቡ ጥያቄ እስኪመለስ ድረስ መጠየቃችንን እንቀጥላለን፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ አንቀጾችን ማሻሻልና አስፈላጊም ከሆነ ሕገ መንግሥቱን እስከ መቀየር ድረስ እንሄዳለን፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ከድርድር በፊት

ባለፈው ዓመት የተነሳው ሁከት በአመዛኙ በኦሮሚያ ቆይቶም በአማራ ክልሎች ቢታይም፣ ጥያቄዎቹ በመላ አገሪቱ ሲንፀባረቁ ይስተዋላል፡፡ አምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ተጠናቆ ኢሕአዴግ አጠቃላይ አሸናፊነቱን ባወጀበትና መንግሥት በመሠረተበት ማግሥት እንደህ ዓይነት ሁከት መቀስቀሱ ብዙ ጥያቄዎች ያጭራል፡፡ የብዙ ተመልካቾችን ቀልብም ስቧል፡፡ ይኼ በአብዛኛው ውጭ በሚገኙ በመንግሥት ‹‹በአሸባሪነት›› የተፈረጁ ድርጅቶችና በእነሱ የፕሮፓጋንዳ ሚዲያ እንደሁም በሶሻል ሚዲያ የተመራው አመፅ፣ ለበርካቶች ሕይወት መጥፈትና ለአገር ሀብት መውደም ምክንያት የሆነ ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት ሆኗል፡፡  

ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ፣ መንግሥትም እንደ መንግሥት ችግሩን ወደ ውጭ አቀጣጣይ ኃይሎች ከመግፋት ይልቅ ሙሉ ለሙሉ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ውጤት መሆኑን የመቀበል አዝማሚያ አሳይቷል፡፡ በእርግጥ በተቃዋሚዎችና በፖለቲካ ታዛቢዎች የተከሰተው ቀውስ ቴክኒካዊና የመልካም አስተዳደር ችግር ብቻ ሳይሆን፣ የሥርዓትና የዴሞክራሲ ቀውስ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በብዙዎች ትችት የደረሰበት የልማታዊ መንግሥት ውጤት መሆኑን ያምናሉ፡፡ በችግሩ ክብደትና አደገኛነት ከእነዚህ አስተያየቶች ጋር የሚስማማው ኢሕአዴግ ግን፣ ችግሩ የሥርዓት ቀውስ እንደሆነና የርዕዮተ ዓለም ለውጥ  እንደሚያስፈልግ አይቀበልም፡፡ በአጭሩ ለኢሕአዴግ ዛሬም የአፈጻጸም ጉድለት ነው፡፡

ባለፈው ክረምት የኢሕአዴግ አራት አባል ፓርቲዎች በየፊናቸው ባካሄዱት ግምገማ መሠረት የሁከቱ መነሻ የመልካም አስተዳደር ጉድለት መሆኑን፣ ስለዚህም  የልማታዊ መንግሥት በአግባብ አለመፈጸም አንዱ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡

የመድረክ አመራር አባል አቶ ገብሩ አሥራት በቅርቡ ለገበያ ባዋሉት መጽሐፍም ሆነ ቀደም ሲል ለሪፖርተር እንደገለጹት ግን፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባል እሳቤ የሐሳብ ልዩነትና ነፃነት የማይፈቅድ፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ከብዙኃን ፓርቲ (መድበለ ፓርቲ) ሥርዓት ጋር ሙሉ ለሙሉ የሚቃረን ነው፡፡ ለእሳቸውና መሰል ትንታኔ ለሚያቀርቡ አካላት ቀውሱ የሥርዓት መበስበስ ውጤት ነው፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች በተነሳው ሁከት ነጥረው የወጡ ጥያቄዎች የተለያየ ገጽታ ያላቸው ቢመስልም፣ የ1997 ዓ.ም. ምርጫን ተከትሎ የተወሰዱ ዕርምጃዎች ውጤት ይመስላሉ የሚሉ አሉ፡፡ በተለይ ደግሞ የፕሬስና የሐሳብ ነፃነትን ያፍናሉ ተብለው ሥጋት የተደረጉት የፕሬስና የፀረ ሽብር አዋጆች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ተቃዋሚዎች መሬት ላይ የረባ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ በማኮላሸት ገዢው ፓርቲ የዘረጋው አንድ ለአምስት በመባል የሚታወቀው ሰንሰለትም ተጠቃሽ ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

 በምርጫው 2002 ዓ.ም. ማግሥት በኢሕአዴግ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት እንደተነተነው፣ ጤነኛ ተቃዋሚዎች እስኪፈጠሩ ድረስ ኢሕአዴግ አውራ ፓርቲ ሆኖ ለ40 እና 50 ዓመታት ሥልጣን ላይ የሚቆይበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ተገልጾ ነበር፡፡ ይህንን በመቃወም የተጻፉና የተነገሩ ትችቶች ውኃ የሚቋጥሩ ተደርገው አልተወሰዱም፡፡ አንዳንድ አክራሪ አቋም የያዙ የፖለቲካ አመራሮች መንግሥትን በጉልበት ለመገልበጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተው ሲንቀሳቀሱ ይኼንን ሁከት መቀስቀስ የቻሉ ሲሆን፣ አገር ውስጥ የሚገኙ ሕጋዊ የፖለቲካዊ ድርጅቶች የነበራቸው ድርሻ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡

ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ በማንሳት የሕግ የበላይነትን በቅድመ ሁኔታነት በማስቀመጥና መሠረታዊ የፖለቲካ ድርድር ሲጠይቅ ከቆየው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ (መድረክ) ውጪ፣ ብዙዎቹ ተቃዋሚዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለውጥ እናመጣለን ብለው ነበር፡፡ እነዚህ ተፈራርመው የገዢውን ፓርቲ አሸናፊነት ተቀብለው የቆዩ ናቸው፡፡ መኢአድ ወዲያው ከምክር ቤቱ ቢወጣም ሌሎች በአሁኑ የድርድሩ መድረክ ጥሪ የተደረገላቸው 20 ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምክር ቤቱ የቆዩ ናቸው፡፡ ከመድረክ ውጪ ሌሎች ፓርቲዎች ሁለት ጎራ ለይተው ተዘጋጅተዋል፡፡

የድርድሩ ስፋትና ጥልቀት የድርድሩ ጥያቄዎችና የሕዝቡ ተቀባይነት ወደፊት የሚታይ ቢሆንም፣ በዜሮ ተባዝተዋል ከተባሉት የቀድሞ የድርድር ሙከራዎች ለየት የሚያደርገው በጠላትነት ተፈርጆ የቆየው የመድረክ ስብስብ እንዲሳተፍ መፈቀዱ ነው፡፡

የረፈደበት ድርድር?

በ2007 ዓ.ም. በኬንያ በተከሰተው የምርጫ ቀውስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራድረው የሥልጣን ክፍፍል አድርገዋል፡፡ በዚምባብዌም በፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤና በተቃዋሚው መሪ ሞርጋን ሻንጋራይ መካከል በተደረገው ድርድር መሠረት የሥልጣን ክፍፍል ተደርጎ ነበር፡፡ በአብዛኛው በተለይ በአፍሪካ የፖለቲካ ድርድር ውጤት ወደ ሥልጣን ሲያመራ ይስተዋላል፡፡ ብዙዎች የሚተቹት ውጤት ቢሆንም፣ የሚያጋጥሙ የፖለቲካ ትኩሳቶችን በማብረድ ግን ሁነኛ መፍትሔ ሲሆን ይስተዋላል፡፡

ረቡዕ የካቲት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ተደራዳሪዎችና አደራዳሪዎች የመምረጥ ሥራ ይከናወናል የተባለለት የውይይትና የድርድር መድረክ በምን ዙሪያ እንደሚሆን ግልጽ ቢሆንም፣ የድርድሩ ዋና አንኳር ጉዳዮች አልተገለጹም፡፡ በኢሕአዴግ ባህል ድርድርን እንደ ሥልጣን ክፍፍል ማድረግ ተቀባይነት የለውም፡፡ የርዕዮተ ዓለም ለውጥ ለማድረግም ዝግጅነት የለውም፡፡ ድርድሩ ምን ውጤት እንደሚኖረው ለብዙዎች ግራ የሚያጋባ ሆኗል በማለት አስታየት የሚሰጡ አሉ፡፡   

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዚም ጥናት ተቋም የዶክትሬት ዕጩ አቶ ናሁሰናይ በላይ ድርድሩ ውጤታማ የሚሆንበትንና የማይሆንበትን ሁኔታ ተመልክተዋል፡፡ ተመራማሪው እንደሚሉት፣ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ የተከሰተው ተቃውሞ የተመራው ኃላፊነት በማይሰማቸውና በውጭ የሚኖሩ አካላት ነው፡፡ በአገር ውስጥ ያሉት ተቃዋሚዎች የሚመሩት ተቃውሞ ቢሆን፣ ጤነኛና ኃላፊነት ባለው መንገድ ይመራ ነበር፡፡

አቶ ናሁሰናይ እንደሚሉት ሕጋዊ ተቃዋሚዎች ከአገሪቱ የፖለቲካ ውጪ እንዲሆኑ የተደረጉት በገዢው ፓርቲ በኢሕአዴግ ነው፡፡ በመሆኑም ተቃዋሚዎች ሚናቸውን እንዳይጫወቱ ተጠያቂው ራሱ ገዥው ፓርቲ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹በመሆኑም. . .›› የሚሉት አቶ ናሁሰናይ፣ ‹‹በመሆኑም በድርድሩ ኢሕአዴግ ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ከመለሰ አሁን ውጤት ይኖራል፤›› ብለዋል፡፡ የመጀመርያው ድርድሩ በአጭር ጊዜ ተቃዋሚዎች በአገር ውስጥ እንደ ልባቸው እንዳይንቀሳቀሱ እንቅፋት የሆኑ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ማስወገድ ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የተነሳው ሁከት ጊዜና ጥልቀት ሲታይ የኢሕአዴግን የመንግሥት ቅቡልነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነው ብለው፣ ባለፉት ምርጫዎች የሕግ የበላይነትን የሚቃረኑ አካሄዶችን በማስወገድ ለመጪው ምርጫ ነፃ የዴሞክራሲ ተቋማት መገንባት፣ ነፃ ፍርድ ቤቶች ማቋቋምና የምርጫ ቦርድ ማቋቋምን በተመለከተ ለድርድ መቅረብ አለባቸው በማለት ያሳስባሉ፡፡ ‹‹በአጭሩ ሕገ መንግሥቱ ሳይደናቀፍ ተግባር ላይ መዋል አለበት፤›› ይላሉ፡፡ በዋናነት ድርድሩ እዚህ ላይ ትኩረት እንዲደረግ በመሞከር ድርድሩ ለይስሙላ ሳይሆን በእውነታ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ይጠይቃሉ፡፡ እ

ላለፉት 25 ዓመታት በተለይ የፖለቲካ ክስተቶችን በጀርመን ድምፅ ሬዲዮ በመዘገብ የሚታወቀው ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር የተለየ አቋም ያንፀባርቃል፡፡ ‹‹ድርድሩ መቼም ቢሆን የሚጠላ አይደለም፡፡ ይኼኛው ድርድር ደግሞ ውጤታማ ይሆናል የሚል ግምት የለኝም፤›› ይላል፡፡

የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት ባህሪ ሀቀኛ ድርድር እንደማይፈቅድ ያምናል፡፡ እንደ እሱ እምነት ድርድር መካሄድ ያለበት ከሕዝቡ ጋር ነው፡፡ ይህ በሌለበት ከተቃዋሚዎች ጋር መሆን የለበትም፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ የተጣላው ከሕዝቡ ጋር ነው፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ከጫፍ እስከ ጫፍ ችግሩን እየገለጸ ነው፡፡ ብቸኛው መድኃኒት ይኼንን የሕዝብ ድምፅ ከልብ ማዳመጥና መመለስ ነው፤›› ይላል ተቃዋሚዎች የሚጠይቁት ውሱን እንደሆነ በማመን፡፡ ‹‹ለዓመታት ጋዜጠኛ ሆኜ የታዘብኩት ተቃዋሚዎች የሕዝብ ጥያቄ ሲያቀርቡ አይቼ አላውቅም፡፡ እገሌ ይፈታ እገሌን ልቀቁልን የሚል ነው ጥያቄያቸው፤›› ይላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ቅርንጫፎች ናቸው፡፡ የሕዝቡ እሮሮ፣ የፍትሕ ማጣት፣ የውኃ ጥማትና የልማት ተጠቃሚ አለመሆን ጉዳዮች ዋነኛ ጥያቄዎች ናቸው ይላል፡፡ ‹‹በእርግጠኛነት እንደራደር የሚሉ ተቃዋሚዎች ትንሽ ሥልጣን ቢሰጣቸው፣ ጨርሰው የሚረኩ ይመስለኛል፤›› ብሏል፡፡ ዋናው ችግር ግን የሚለው ዮሐንስ፣ ኢሕአዴግ ውስጥ ይኼንን ችግር ሊረዳ የሚችል አመራር አለ ብሎ አያምንም፡፡ 

ረቡዕ የካቲት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ኢሕአዴግና ታቃዋሚ ፓርቲዎች ውይይት ያካሂዳሉ፡፡ የስብሰባው አመራር ሥርዓት፣ ስብሰባው በማን እንደሚመራ፣ በታዛቢዎች ማንነትና በጋዜጣዊ መግለጫ አሰጣጥ ላይ ባቀረቡት ፕሮፖዛል መሠረት ይነጋገራሉ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በሦስት ስብስቦች ተደራጅተዋል፡፡ የመጀመሪያው ቡድን ስድስት ፓርቲዎች፣ ሁለተኛው ደግሞ አሥራ አንድ ፓርቲዎችን አቅፈዋል፡፡ መድረክና ሌሎች ሦስት ፓርቲዎች በተናጠል ይቀርባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -