Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መጨረሻ የሌለው ጥበቃ!

እነሆ ጉዞ ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ። ምድር ትውልድን በትውልድ እየተካች የደከመውን በሞት ሸኝታ ለጋውን እያሳደገች ፋታ አሳጥታ ታራውጠናለች። ተስፋ አይሞትምና እውነት ለመሰለን ሁሉ እየደከምን በባዶ እንደ መጣን በባዶ እስክንሸኝ እንደክማለን። ዕርቃናችን እንደ መጣን ዕርቃናችንን እንቀበራለን። በዚህ የጅማሬና የፍፃሜ ዘመኑ በሰው የሕይወት ቆይታ የሚታየው እጅግ አድካሚ ሠልፍ ብቻ ነው። ገሚሱ ተርፎት ሲደርብ ገሚሱ አንዳችን ሳይኖረው፣ አንዱ ሞቆት ሲጨነቅ ያኛው ውርጭ በማጣት ሰቀቀን ጭምር እየተቀጣ ይኖራል። አንዱን ሥጋ አንቆት ሲያወራጨው ሌላውን የሥጋ አምሮት ያንፈራፍረዋል፡፡ እሴትን ሲሸራርፍ ነው የሰው ልጅ ዘመኑ እዚህ የደረሰው!

መተሳሰብ ጠፍቶ ለራስ ብቻ የሚሮጠውን ከጎዳናው ላይ ቆመው ሲያዩት ያሳቅቃል። ምንም ባልበደለ፣ ከፍጥረቱ በድህነት የሚማቅቀውን ዓይተን ሳንጨርስ ያለ ፅድቁ ንዋይ ተርፎት በድሎት የሚንፈላሰሰውን ስናይ ጉድ ማለት ብቻ! ማጣትና ማግኘት የጎዳናው ነባር አራጋቢዎች ናቸው። ከዚህ ሁሉ በላይ ስሜት የሚያደማ ሀቅ ቢኖር ልጅነት ሲገረጅፍ፣ አበባነት ሲጠወልግ ማየት ነው። ይኼም ቢሆን የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ ማብራሪያ አያጣም። ማብራሪያው ሁሉ የፖለቲካ አጥር የሚታከክ ነው። የማጣትም ሆነ የማግኘት፣ የደስታና የሐዘን ስሜቶች ሳይቀሩ ሁሉም መነሻቸው ከዚያ ፖለቲካ አጥር ሥር ነው። አገዛዝ ሲያደቃት በኖረ አገር ጥያቄዎች ሁሉ የፖለቲካ መሆናቸው ምን ይገርማል?!

ታክሲያችን መንቀሳቀስ ከመጀመሯ ፀጉሩን የመፍተል የእጅ አመል ያስቸገረው ወያላችን ሒሳብ ይል ጀምሯል። “ብንሰጥህስ ሌላ ሥራ ይዘህ ለመቀበል እንዴት ይመችሃል?” ይሉታል አንድ አዛውንት እየሳቁ። ወያላው የንግግራቸው አቅጣጫ የት ጋ ሄዶ እንዳረፈ ገብቶታል። “አይ ሰው! ስንት የሚተሳሰብበት ነገር እያለ ነቀፌታ ላይ ጊዜውን ያጠፋል። እንዲያው ምን ይሻላል?” ይላል ወያላው በምፀት እየሳቀ ወደ ሾፌሩ ሰገግ ብሎ። ሾፌራችን፣ “ኧረ በጣም! ትንሽ ፂምህ ሲረዝም ፀረ ልማት የማትመስለው፣ ፀጉርህ ከፍ ሲል ከዘመኑ ዴሞክራሲ ሽሽት እንደ ጀመርክ አድርጎ  የማይቆጥርህ እኮ የለም፤” ሲለው ወያላው ቀበል አድርጎ “የዴሞክራሲውን ነገር እንኳን ተወው። ግን እንዳልከው በገዛ ራስህ ተፈጥሮና ኑሮ ለተከዝከው የሚተረክዝብህ ብዙ ነው። እውነት የፀጉር መንጨባረርን የሚጠላውን ያህል ሙስናን ቢጠላ ይህ ሕዝብ የት በደረሰ ነበር?” ይላል።

“ታዲያስ እንደ እሱ ያለው ቁም ነገር ላይ ሚዛን የሚደፋ ድጋፍና ጥላቻ ቢኖረንማ ስንት ነገር አስተካክለን ነበር እስካሁን። ምን ዋጋ አለው ስንት ሥራ እያለ ሰው ሥራው ስለሰው ሆነ እንጂ። ድራማውም ፖለቲካውም ሰው በሰው. . .” እያለ አንድ ጎልማሳ አስተያየቱን ያዋጣል። ‘ስለሰው ስለሰው ቀድጄ ልልበሰው’ ብሎ ወያላው ዜማውን ጩኸት አድርጎ ያንባርቅብናል። “ኧረ ተረጋጋ! ሥራ ላይ መሆንህን አትርሳ፤” ይለዋል ሾፌሩ። “ምን ላድርግ ብለህ ነው? ሁሉም የራሱን ነገር እያዋደደ ሲያወራ ስለምበሽቅ እኮ ነው። ከእኔ ወንድሜ ይሻላል፣ ልጄ ይሻላል ይባላል እንጂ ከአብራካቸው እንዳልወጣን ለምንድነው እንዲህ የሚጨፈጭፉን?” ሲል የምሩን መናደዱ ታወቀበት። “እነማን ናቸው እነሱ እንዲህ የሚያናግሩህ?” ሲለው ጎልማሳው፣ “ካለኛ ሰው አገር አስተዳዳዳሪ፣ ተመራጭ፣ ባለራዕይ፣ ለሕዝብ አሳቢ፣ ዴሞክራት፣. . . የሚሉን ናቸዋ!” ብሎ ወያላው ሒሳብ ለሚሰጡት ሰዎች መልስ ማዘጋጀት ነበረበት። አዛውንቱ በትዝብት ከመመልከት ሌላ ቃላት ሲቀምሩ አይታዩም። ሌላ ማንም ሰው ሊናገር የዳዳው የለም። ትዝብት ብቻ ነው ፊቱ ላይ የሚታየው። መተዛዘብ ብቻ!

ታክሲያችን እየፈጠነች ነው። ጨዋታችንም ቀስ በቀስ ሥር ሰደደ። “ወይ አዲስ አበባ! ተተኮሰች እኮ እናንተዬ?!” ትላለች ሦስተኛ ወንበር ላይ የተቀመጠች ወጣት። “በምን?” ይላታል ከአጠገቡዋ። “በልማት ነዋ። የባቡርና የአስፓልት መንገድ ሥራው፣ የሕንፃውን ግንባታ አታየውም እንዴ ከተማውን ታርሶ?” ትለዋለች በየዋህነት ምን ይጠይቀኛል ዓይነት። “እኔን የሚገርመኝ ግን አዲስ አበባ በተጣደፈች ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል በፈጣን የልማት ሥራ ተወጥሯል መባሉ ብቻ ነው። ለመሆኑ ለቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል ከህዳሴው ግድብ ፕሮጀክትና ውር ውር ከሚል በስተቀር ሌላ ምን ልማት አለ? ወይ ሰው ዓለማ ወይ አገሪቷ!” ሲል ከመጨረሻ ወንበር አንዱ፣ “ኧረ እናንተ ሰዎች የምታወሩትን ልብ በሉ። ደግሞ ብለን ብለን በገዛ እጃችን ሌላ መዋጮ እናስጀምር እንዴ? ለስንቱ አዋጥተን ልንችለው ነው?” ይላል ጎልማሳው።

“ስለመዋጮ ተወራ እንዴ?” ሲል የቀደመው ተናጋሪ፣ “ያው ነው ከዓባይ ሌላ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል የልማት ሥራ የለውም ካልን ኢሕአዴግ በምን እንደሚመጣብን ምን እናውቃለን? ወረቀት በተወደደበት ያሰቡትን በተግባር የሚያሳዩት ከስንት አንድ በሆኑበት ዘመን ራዕይ አላልቅበት ያለ መንግሥት እኮ ነው ያለን፤” የምትለው ከሾፌሩ ጀርባ ያለች የቀይ ዳማ ናት። “ራዕይ ሲበዛማ ጥሩ ነው። ራዕይ አስፈጻሚ ሲሰበሰብ ግን ችግር ነው፤” ብሎ ሳይጨርሰው ጎልማሳው፣ “ለማንኛውም ለመዋጮ መጨነቅ ድሮ ቀርቷል። መጀመርያም ስንናገር የሚሰማን አጥተን እንጂ ገንዘቡ ያለው ምድረ ኪራይ ሰብሳቢ ኪስ እንደሆነ ታይቷል፤” ይላል አጠገቧ የተቀመጠ ተሳፋሪ። ‹‹ወይ አገሬ ሌላውን የአፍሪካ አገር ያላየ አገር ተዘረፈ ብሎ አፉን ሞልቶ ሲናገር አይገርምም? ቢያንስ እዚህ የወጣበትና የተሠራው ላይመጣጠን ይችል ይሆናል፡፡ ሌላው ዘንድ እኮ ጭራሽ በጀቱ የት እንደገባ ይታወቃል? ናይጄሪያና ኬንያን ያላየ ሁሉ. . .›› እያለ ያጉተመትማል፡፡ ዝብርቅርቅ በሚመስለው የታክሲያችን ጭውውት በቀጫጭኑ ተፈትለው የሚታዩት የሽሙጥ አገላለጾች ብቻ ናቸው። በዘመነ ዴሞክራሲ አገር ምድሩ በሽሙጥ የተጠመደው በጤና ነው?! እስኪ እንጠያየቅ!

ሾፌሩን አንዳች የሚያቁነጠንጠው ነገር ሰቅዞ ይዞታል። ምቾት አጥቶ እረፍት የነሳት ጃጉዋር ታክሲያችን ቅጥ ባጣ አካሄድ ወሰድ መለስ ትላለች። ወያላው ጭምር ግራ ገባው መሰል “ምነው?” ይለዋል። “ምን እባክህ ይኼ ቀበቶ እኮ ሊመቸኝ አልቻለም። እዚህ አገር አዋጁና ሕጉ ሁሉ ሰው ማሰሪያ ነው፤” ብሎ ይመልሳል ሾፌራችን። “እንዴ በትራፊክ አደጋ የሚቀድመን አገር እንደሌለ እያወቅክ ቀበቶ አስሮ ማሽከርከርን ነፃነት ከማጣት ጋር ታወዳድራለህ?” ትላዋለች አጠገቡ የተቀመጠች ወጣት። “ኧረ ተይኝ እባክሽ። አሁንስ አላሠራ ያለን ይኼ ጥቃቅንና አነስተኛ ሕግ ነው። ሕዝብ በትራንስፖርት ዕጦት ዕርምጃው ተገትቶ፣ እንዳሻው እንዳይሮጥ ታስሮ የማይታያቸው ሁላ ይህችን ቀበቶ አድርጉ አታድርጉ እያሉ ላይ የሚበረቱት ናቸው የሚገርሙኝ፤” እያለ ወይ አንደኛውን ቀበቶ ማድረግን ያወገዘ ንግግር አልተናገረ፣ ወይም ጥቃቅኑ ነገር ላይ የሚያተኩረውን ሕግ አውጪና አስከባሪ አካል አልተቸ እንዳሻው ደባልቆ ይቀደዳል።

“አሁን ስለትራንስፖርት ችግር ያነሳኸው እውነት ቢሆንም መንገድ ትራንስፖርት ሥራዬ ብሎ መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ቢታወቅም፣ ቀበቶ ከማሰር ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። መጀመርያ የራስን ኃላፊነት መወጣት ነው። እውነት እንዲህ የእኛ ተሠልፎ መዋል የሚያሳስባችሁ ከሆነ እናንተስ የምትሠሩት ሥራ ልክ ነው እንዴ? ተው! አንተዛዘብ ተው!”  የሚለው ደግሞ ወፍራም ኮስታራ ተሳፋሪ ነው። ሾፌሩ ምንም መልስ አልሰጠም። ነገሩ ባላሰበው አቅጣጫ እየዞረ ነበር። አጠገቤ የተቀመጠች መጠጥ ያለች ወይዘሮ፣ “ክፉ ልምድ!” ትላለች በሹክሹክታ። “የራስን ቀበቶ ሳያጠብቁ የራስን ቀዳዳ ሳይደፍኑ ሌላው ላይ ለመፍረድ መሽቀዳደም። ሕዝብ መንግሥትን፣ መንግሥት ሕዝብን፡፡ ከሰው እንዳልተወለድን። ግን እንዴት ያለ እርግማን ነው አንተዬ?” ስትለኝ ድንገት ራሴን በአሉታ ወዝውዤ አያታለሁ።

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። መገናኛ ቅልጥ ያለ የልማት
ሥራ የሚጧጧፍበት ብሎም ደማቅ የጎዳና ገበያ ቀጣና ከሆነ ውሎ አድሯል። “ጉድ በል ዓይናችን እያየ እኮ ሆነ አሁንማ ለውጡ። የሚገርመኝ ትናንት የነበረውን ዛሬ ሳጣው ዛሬ ያጣሁትን ነገ ሳገኘው ነው፤” ትላለች አንዷ ወይዘሮ። “እውነት ለመናገርማ ለውጡ እየመጣ ነው። ዓለም ራሱ ጊዜው የአፍሪካ ነው አይደል እያለ ያለው?” ብሎ ከመጨረሱ ጎልማሳው፣ “አውነት ነው። የቁሳዊውንና የመንፈሳዊውን ሥልጣኔና ዕድገት ብናጣምረው ደግሞ. . .” ብሎ ከመጨረሻ ወንበር አንድ ወጣት ሲናገር ይሰማል። የልማቱና የለውጡ የይበል ጨዋታ ለአንድ ጊዜው ተቀይሮ ምሬትና ትችት ለማድመጥ አሁንም ደቂቃ አልፈጀም። አንዱ ስልኩ እንቢ ብሎት ‘ኔትወርኩ’ን እያማረረ ቴሌን ያሳጣል። አንዷ፣ “አሁን ደግሞ ከዚህ ስንት ሰዓት ይሆን ታክሲ ጠብቄ ተሳፍሬ የምሄደው?” እያለች ስትጨነቅ ይሰማል።

ወዲያው ከወደ ጋቢና፣ “በየወሩ ነው እንዴ የቤት ኪራይ የሚጨምሩት እርስዎ ሰውዬ?” እያለ በስልክ ያጮሃል። ተንፍሰን ሳንጨርስ የሚያካልበን የችግር አባዜ ጉልበቱን አድሶ በየአቅጣጫው ተሳፋሪውን ሲወጥረው፣ “እንዲያው ምን ተሻለን እናንተ? መፍትሔው ሁሉ ጊዜያዊ ነው እሱንም የሚሰማ ሲገኝ። ኧረ እንዴት ልንኖር ይሆን ወደፊት?” ይባባል ጀመር ተሳፋሪው። ታክሲያችን ጠርዝ ይዛ ስትቆምና ወያላው፣ “መጨረሻ! ውስጥ አይገባም!” ብሎ ሲያወርደን አጠገቤ ተቀምጣ የነበረችው ተሳፋሪ፣ “ሌላ ሌላውን የምጠብቀው አንሶን መፍትሔ ስንጠብቅ ዘመናችን ይለቅ? መጨረሻ የሌለው ጥበቃማ ደስ አይልም፤” ያለችው ጆሮዬ ገባ። ‘መጨረሻ የሌለው ጥበቃ እስከ መቼ?’ እንበልና ወደ ሚቀጥለው ጉዞ እንሻገር እንጂ፡፡ እህ ምን ይደረጋል? መልካም ጉዞ! 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት