Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እስከ መቼ በከባድ ማርሽ?

እነሆ መንገድ። ከጎተራ ወደ ስታዲየም ልንጓዝ ነው። አያ ትርምስ የውጥንቅጥ አባት፣ ጎዳናውን ዛሬም አለቅ እንዳለ ነው። ያም ያስኬዳል። ይሄም ያስኬዳል። ተጓዥ እግሩ ሳይዝል ሐሳቡ ተምታቶ መሀል መንገድ ላይ ቆሟል። እርግጥ ሰው መሄዱን ይሄዳል። አርፍዶ በመሄድ መንገድ ላይ እያመሸ ጀንበር እንቅልፏን ለጥጣ አድራ ማልዳ ስታፋሽክ፣ ያው ገለባ ኑሮ በመባዘን ሜዳ ተሽቀዳደሙ ይለናል። እንዲያው በአጭሩ ሁኔታችን ሁሉ ከንቱ ይመስላል። ‹‹ተወኝ እስኪ አንተ። ይህቺም በአቅሟ መኪና ተብላ ነው የምትነዘንዘኝ? ይከፈለሃል አትጨቅጭቀኝ፤›› ቀጠን ረዘም ያለች ደርባባ ከወያላው ጋር ገጥማለች። ‹‹ይቺም መኪና ተብላ› ነው ያልሽው? ሱዳን ሄደሽ ሰጋር በቅሎ ገዝተሽ ነይ፤›› ወያላችን እንደ ድርያ ወገቡ ላይ ሰፍቶ የሚንሳፈፍ በሲባጎ የታሰረ ቦላሌውን ወደላይ እየጎተተ ይመልስላታል። ‹‹ድንቄም ታሪክ አዋቂ! ባቡር ሲመጣ ነው ሰጋር በቅሎ የምትጠቁመኝ? ጠቁመህ ሞተሃል። ካልክስ አሸባሪ ጠቁም። ምኑ ነው እናንተ!›› እሳት እንደያዘው የኤሌክትሪክ ገመድ ተንጣጣች።

ነገሩን የምር አድርጋው (የተተናኳሹ ሳያንስ የተተነኮሰው እየባሰ ፍዳ አየን ዘንድሮ)፣ ‹‹እስኪ አሁን የተከበርኩበት አገር ለማች ለማች እያሉ ዓይን ዓይኗን እያዩዋት፣ መሀል አዲስ አበባ መንግሥት ለቼቭሮሌትና ለመርሰዲስ አሽከርካሪዎች መንገድ ሠርቶ  የወለቀ ልቡን ሳይጠግን ከሱዳን በቅሎ አምጪ ይለኛል? ምናለበት እዚህ አንኮበር ቢለኝ? እዚህ ሰላሌ ፍቼ ቢል? ስንት ከጋሪው የተቀያየመ ጎዳና ተዳዳሪ ፈረስ እያለ?›› ብላ ነገሩን ስታቀልጠው ‹‹ኧረ ረጋ በይ! እንኳንም ሊቢያ አላለሽ፤› ይላታል አጠገቧ ከሾፌሩ መቀመጫ ጀርባ የተሰየመ ጎልማሳ። በአጥፍቶ ጠፊ ‹ኮሜንት› የተካነ ‹ፌስቡከር› ዓይኑን ‹ስማርት ፎኑ› ላይ እያንከራተተ፣ ‹‹እውነቴን ነው! በቅሎ ማለቱም አንድ ነገር ነው። ከዘንድሮ የትራንስፖርት አበሳ እንኳን በቅሎ ኤሊም አትናቅም። ከዚያ በተረፈው ‹ሰው ባለው ነው› እያሉ ሐሜተኛን ዝም ማስባል መቻል አንዱን የሚሊኒየም የልማት ግብ እንደማሳካት የሚቆጠር ነው፤›› ይላል። ከኩመካው ጀርባ የማን እጅ አለበት ተብሎ እንዳይታጎር የፈራ ተሳፋሪ ይርበተበታል። ቆይ ግን በ‹ሆረር ፊልም› መሳቅ የጀመርነው ‹ቴረር ፊልም› በገሀድ ስለምንሠራ ይሆን እንዴ? ነገሩን ነው!

ጉዟችን ሊጀመር ነው። ሾፌራችን የታክሲዋን ሞተር እያስጓራ ልባችንን አንጠልጥሎታል። ‹‹እንዴት ነው ነገሩ? ሔሊኮፕተር ላይ ነው እንዴ የተሳፈርነው? ወደፊት ለመሄድ ይሄ ሁሉ ነዳጅ ማባከን እስኪ አሁን ሙስና አይደለም ይባላል?››  ሦስተኛ ወንበር ከአጠገቤ የተቀመጠ ቀላጅ መሳይ ይለፈልፋል። ‹‹ምን ይታወቃል ዘንድሮ? የሚወስድህንም ሆነ የምትሄድበትን እኮ መለየት ይከብዳል፤›› ስትል መጨረሻ ወንበር የተቀመጠች እንስት በስላቅ ታብራራለች። ‹ቀቀቀቀ› ይላል ማርሹ አልገባ ብሎ። ‹‹ወይኔ! ‹ፈርስት ክላስ› በተሳፈርኩ ኖሮ…›› ማኅበራዊ ድረ ገጽ ውስጥ ሰጥሞ ገሀዱ ማኅበራዊ ትዕይንት ሰልችቶት ከተመሰጠው ወጣት አጠገብ የተሰየመች ወጣት ትቆጫለች።

‹‹እዚህ ሕዝባዊ ‹ክላስ› የጎደለ ነገር አለ?›› ፌዘኛው መሳይ ይጠይቃታል። ‹‹አትሰማም እንዴ ሸንኮራ ሲቆረጥ። እዚህ አገር ከፊት ካልተቀመጥክ አልያም ካልተወለድክ መረቁ የተጠጣለት ደረቁ ነው እኮ የሚታደልህ። እሱንም ቅን ሾፌር ካጋጠመህ፤›› ትለዋለች። ‹‹ኧረ ሠላማዊ ሰልፍ ጠርተው ያዋከቡን ይበቃል። ደግሞ በተቀመጥንበት ልታሳፍሱን ነው?›› ሻሽ ካሰረች ቀዘባ አጠገብ መጨረሻ ወንበር ላይ የተሰየመች ወይዘሮ ትናገራለች። ይኼን ጊዜ ሾፌሩ በሩን ከፍቶ ይወርዳል። ወይዘሮዋ፣ ‹‹የፈራሁት ሊደርስ ነው መሰል?›› ስትል በራሷ የፈጠረችውን አጉል ፍርኃት አንዳንድ ተሳፋሪዎች ላይ ታጋባለች። የሾፌሩን መውረድ ተከትሎ ወያላውም ወርዶ ወደ ሾፌሩ አመራ። ‹‹ምን ይማከሩብናል አይዘውሩትም? ሃሎ አትሄዱም?›› ከወያላው ጋር የተናቆረችው ደርባባ ትጮሃለች። ‹‹እስኪ ቢያልፍብንም ጊዜ እንስጣቸው፡፡ የመኪናውን ችግር እያጣሩ ይሆናል፤›› ሲል አጠገቤ ያለው ሊያረጋጋት ይጥራል። ‹‹አደራ ሰው መሆናችንም አብሮ ይጣራ፤›› ብሎ ደግሞ፣ ‹የመኪናው ችግር ይጣራ› የተባለውን ብሶት ማስተንፈሻ የሚያደርገው ጎልማሳው ነው። ‹የባሰው ብቻ ነው የሚሳፈረው?› እስክንል ድረስ የማንሰማው የለም!

‹‹1—2—3›› ሾፌሩና ወያላው ተጋግዘው አንደኛ ማርሽ ያስገባሉ። ለካ ወያላው የወረደው አንደኛ ማርሽ በጉልበት ስለሚገባ ኖሯል። አንዳንዱ ከት ብሎ ይስቃል። ሳቅ እንዲህ በቀላሉ ድርሽ የማይልበት ደግሞ ያላየውን፣ ‹‹ኧረ ባቡር ይግደለኝ›› ሲል ሌላ ነገር ይመስልበታል። ደርባባዋ፣ ‹‹አይዞህ አይገልህም። አንዱ ፌርማታ ላይ አስመድበንህ ወፍ ታባርራለህ፤›› ትለዋለች እየሳቀች። ‹‹አግኝቼ ነው? ሰው በአገሩ ተምሮ ዲግሪ ይዞ ሥራ መቀጠርን ተይውና ወፍ የማባረር ዕድል እየራቀው መስሎን የሚሰደደው…›› ይላታል ተለሳልሶ። ‹‹መጀመሪያ ነዋ ዲግሪ እይዛለሁ ሲል ወፎች ስጡን የሚጨርሱት፤›› አጠገቤ የተቀመጠው ነገረኛ ጣልቃ ይገባል። ነገሩ ያላማራት ወይዘሮ ትርበተበታለች።

ይኼን ጊዜ ወያላው እየተንደረደረ ገብቶ በሩን ይዘጋል። ሾፌሩ አስጓርቶ እንደመንኮራኩር ታክሲዋን ማንደርደር ጀምሯል። ‹‹ጥድፊያው የተቃጠለብንን ጊዜ ለመካስ ነው?  ከአንደኛ ማርሽ ለመሸሽ?›› ሲል ገጹ ላይ ሊለጥፈው ያሰበውን በቃል ይለዋል ፌስቡከሩ።

ጋቢና የተቀመጡት ወጣቶች ደግሞ ‹‹እኛን አግዙኝ ብትል እኮ ተዘጋጅተን ነበር፤›› ሲሉ አጠገቡ  ተቀምጠው ወያላው ዞሮ መምጣቱ ቅር እንዳሰኛቸው ያስረዳሉ። መጨረሻ ወንበር ደግሞ ‹‹ጋይስ› ሰው መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ኪሱ አልችል ሲለው ታክሲ በመግፋት ለማካካስ ሙከራ ጀመረ እንዴ? የሙከራ ሥርጭቱን ከዋናው መለየት አስቸገረን እኮ?›› ብላ አንዲት ቆንጆ ብቻዋን በሳቅ ትፈርሳለች። ‹‹እንዲህ ስቀሽ ስቀሽ ትን ያለሽ እንደሆን፣ ደቅ አድራጊሽ እኔ ነኝ አትራፊሽ ማን ይሆን?›› ሲል ጎልማሳው ያሽሟጥጣታል። ጉድ እኮ ነው! በዚህ አያያዝ ነው ስደት የሚቆመው ጎበዝ?!

 ወያላው እያዋከበ ሒሳብ መቀበል ጀምሯል። የሾፌሩን ትግልና የታክሲዋን አሮጌነት ከግምት ውስጥ አስገብታ አካሄዳችን ያልጣማት ወይዘሮ፣ ‹‹ኧረ እናንተ ሰዎች ዛሬ ተገልብጠን ጉድ እንዳንሆን?›› ትላለች። ‹‹ከአቅም በላይ የተጫኑትንና የተጫኑንን ይጭነቃቸው እንጂ ብንገለበጥ ባህር አይበላን። በምላስ የተላሰ የመሰለ አስፋልት ላይ ነው ፈልሰስ የምንለው። በበኩሌ አብዛኞቻችን ከምንተኛበት ፍራሽ ይኼ አስፋልት የተሻለ ሳይመቸን አይቀርም፤›› ይላል ጎልማሳው። ‹‹በበኩሌ አሟሟቴ ነው የሚያስጨንቀኝ። እንዳልሆን ሆኜ ማለፌ ሳያንስ ቢቻል አገር ባይቻል ሠፈር በእንባ እንዳይራጭልኝ በመኪና አደጋ መሞት አልፈልግም፤›› ስትል ባለሻሿ፣ ‹‹ሞት መቼም ልማዱን አይተው። ግን ከተለመደ ሞት ያልተለመደው በልጦ በረሃና ባህር ለበላው እንደምናዝነው፣ በመኪና አደጋ በየቀኑ የሚያልቀውን ነፍስ ያቃለልነው መስሎ ይታየኛል። ቆይ ግን የሐዘናችን ምንጩ ሞት ነው አሟሟት ነው? እኔ እኮ መለየት ከበደኝ?›› ስትል ቆንጂት ትጠይቃለች።

‹‹እሱ ሳይሆን ቁም ነገሩ ቋሚ ቆሞ ሲሄድ ሁሉን የምር አድርጎ በልቶ ለማይጨርሰው ሀብት እህት ወንድሙን አስለቅሶ፣ ሕዝብና መንግሥት አናክሶ ሳያስበው ማለፉ ነው። በረባ ባልረባው ክልትው እያልን (ያውም በዚህ ጊዜ) ሞት በጥጋብ ውስጥ ተሸሽጎ በሚናጠቀን ክፉ ቀን ልብ መግዛት ያቃተን ሚስጥሩ አይገባኝም፤›› አለች ወይዘሮዋ። ‹‹ደላላችን በዝቶ ነዋ። ምን እናድርግ? ከመሠረታዊ እስከ የቅንጦት ምኞታችን ያለገንዘብ ምንም ናችሁ የሚሉን ደላሎችንን መቋቋም ከበደን። ይኼው ነው! ታዲያ በዚህ መሀል ሰው የመሆን ትርጉሙ ቢጠፋብን ይገርማል? ፍትሕ ስንል ያለስም፣ ያለዝና፣ ያለሥልጣን የለም ካሉን፣ ሚስት ካለጥሪት ዝንብህን እሽ አትልም ከሆነ ጨዋታው፣ ‹እሺ ለአንድ ራሴ ጠግቤ ልደር› ስንል እንኳን እህል አፕታይት ቆላፊው ጫት ሳይቀር ዋጋው አሻቅቦ የ‹ኢንቨስተር ዲዘርት› ሲሆን ካየን፣ ግራ እንደተጋባን ሞት ቢቀድመን ይገርማል? አሟሟታችን ቢከፋ ይደንቃል?›› ብላ ደርባቢት አነበነበች። ‹‹ወይኔ በዘንድሮ ምርጫ በዕጩነት ቀርቤ ‹ጫት በነፃ አድላለሁ› ብል ኖሮ ያዋጣኝ ነበር ማለት ነው?›› የሚለኝ ከጎኔ የተቀመጠው ነው። አንዳንዱ ሰው ምን እንደሚያወራም አላስተውል አለ እኮ እናንተ! ይኼ ያልታረመን ሐሳብ ‹ፖስት› እና ‹ሼር› የማድረግ አባዜ ገና የበለጠ ፈር እንዳያስተን ያስፈራል!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጋቢና ከተቀመጡት አንዱ ‹ወራጅ› ብሎ ወረደ። ሾፌራችን ወደ አንደኛ ማርሽ ላለመመለስ የቻለውን ያህል ቢጥርም አልሳካ ብሎት ጋቢና የቀረውን ወጣት ትብብር ይጠይቃል። ሾፌሩ ዝቅ ብሎ የሆነ ነገር ሲይዝ ተሳፋሪው ‹ቀቀቅ› አድርጎ አስገባ። ‹‹ወይ ኑሮ ወይ ኑሮ› አለች አስቴር አወቀ…›› አጠገቤ የተቀመጠው ፌዘኛ አያርፍም። ‹‹አንተው ኑሮ በአንደኛ ማርሽ ልትል ፈልገህ ከንፁኃን ባታነካካን ደስ ይለኛል። በበኩሌ ከደሙ ንፁህ ነኝ…›› ብሎ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠው ወጣት ይቆጣል። ‹‹ሄይ! ምንድነው ነገር ማክረር የሚታየውን እንደሚታየው፣ የሚሰማውን እንደሚሰማው የመናገር መብታችን ሕገ መንግሥታዊ መሰለኝ፤›› ሻሽ ጠምጣሚዋ ባሰች። ‹‹ጎበዝ ዘንድሮ አካፋን አካፋ ካላልን ዋጋ የለንም። አለባብሰን አርሰን ከትውልድ ትውልድ አረም ስንነቅል ያቃጠልነው ዘመን ይበቃል፤›› ስልኩ ባትሪ ጨርሶበት ቀና ብሎ አይናችንን ማየት የቻለው የ‹ፌስቡክ› ሱሰኛ ይከተላል። ‹‹እኮ ምንድነው አረሙ? የምን ፈራ ተባ ነው ተናገሩታ…›› ቅድም በትንሽ ትልቁ ስትባባ የነበረችው ወይዘሮ አሁን የቀለጠች ‹አክቲቪስት› ሆናለች። ጊዜ ሰውን ይለውጠዋል ማለት እንዲህ ሳይሆን ይቀራል?

ጎልማሳው ጣልቃ ገብቶ ማይክ ይዟል። እንዲህ ይላል ‹‹እንዲያው ለመሆኑ እንደ አገር መራመድ ስላልቻልን፣ እንደ ሕዝብ መጓዝ ስላቃተን አይመስለችሁም በግል ከኑሮ ጋር አባሮሽ እየገጠምን የምንሰቃየው? በፍትሕ፣ በዴሞክራሲ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ወደ ተሻለ ደረጃ ለመራመድ እንደ ታክሲያችን አንደኛ ማርሽ ላይ መከራ የምናየው ልባችን አንድ ባይሆን፣ የላላ ኅብረት፣ ጥብቅ የተቃርኖ ብሎን ቢያግደን አይይመስላችሁም? ሕፃን አዋቂው የአውሮፓን ምድርና የምዕራባውያንን ሥልጣኔ እንደ መንግሥተ ሰማይ ክብር እየቆጠረ ፍዳውን የሚያየው? ምናለበት ታጥበን ጭቃ የሚያደርገንን ከባድ ማርሽ በመደማመጥና በመወያየት ተባብረን ብናቀለው?” ብሎ ሳይጨርስ ወያላው ራሱን እያከከ ‹‹መጨረሻ›› አለ። ተሳፋሪዎች ለመውረድ በእሽቅድምድም ሲራኮቱ የከባድ ማርሹን ‹ቲዮሪ› በቅፅበት የዘነጉት ይመስላሉ። ‹እኮ እስከ መቼ በከባድ ማርሽ?› መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት