Wednesday, April 17, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ዜጐችን ለስደት የሚዳርጉ አሳማኝ ምክንያቶች መፍትሔ ይፈለግላቸው!

የዜጐችን ስደት በተመለከተ አገራችን ኢትዮጵያ መንታ መንገድ ላይ ቆማለች፡፡ የአገሪቱን ዜጐች ለስደት የሚያነሳሳው ምክንያት የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ነው የሚሉ ወገኖች ያሉትን ያህል፣ አገሪቱ ለዜጎቿ የምትመች ባለመሆኗ በምሬት እየተሰደዱ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ስደትን ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ አውጥተን ምክንያታዊ በሆኑ ትንተናዎች በመታገዝ ካልፈተሽነው በስተቀር፣ ለመፍትሔ የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ማግኘት አዳጋች ይሆናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሰው አገር ይኖራሉ፡፡ በየጊዜውም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐች ባገኙት መንገድ ሁሉ እየተሰደዱ ነው፡፡ አገሪቱ ለዘመናት ከተጫናት ድህነት ለመላቀቅ በምታደርገው ጥረት መጠነኛ የሆነ የገጽታ ለውጥ ብታደርግም፣ አስከፊውን ድህነት ለማስቆም አልተቻለም፡፡ በተለይ ወደ አውሮፓ፣ ወደ መካከለኛው ምሥራቅና ወደ ደቡብ አፍሪካ ዜጐች በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካይነት እየነጐዱ ነው፡፡ አደጋው በከፋበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እንኳ ስደቱ ቀጥሏል፡፡ ለምን ማለት ተገቢ ነው፡፡ ስደቱን ለማስቆም ምን ማድረግ ይገባል ማለትም አለብን፡፡ ችግሩን ከሥር መሠረቱ ለይቶ ለማወቅ ጠቃሚ ነው፡፡

መንግሥት አሁን የደረሰውን አሳዛኝ ክስተት ተንተርሶ፣ ዜጐች ከአደጋ ራሳቸውን ለመጠበቅ በሊቢያም ሆነ በሜዲትራኒያን ባህር፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የተፈጸሙትን ሰቆቃዎች እንደ ማስጠንቀቂያ እንዲያዩት ያሳስባል፡፡ ሕገወጥ ደላሎችንም በምክንያትነት ያቀርባል፡፡ በአገሪቱ የተፈጠረውንም መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአገራቸው ሠርተው እንዲለወጡ ይመክራል፡፡ በሌላ በኩል ግን አሁንም በጣም የተንሰራፋው ድህነት የብዙዎችን ተስፋ እያጨለመ ነው፡፡ ከአቅም በላይ የሆነው ሥራ አጥነት ለብዙዎች ከሚቋቋሙት በላይ ነው፡፡ በየጊዜው እየናረ የሚሄደው ኑሮ ብዙዎችን እያስመረረ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥረው አድሎአዊነት የምሬት ምንጭ ነው፡፡ በፖለቲካው ንፍቀ ክበብ ውስጥ የሚታየው አማራጭ አልባነትና የአንድ ወገን የበላይነት ብቻ መኖር ቅሬታውን እያጎላው ነው፡፡ የሥራ ዕድልን እያቀጨጨ ነው፡፡ የፖለቲካው መሳሳብ ለብዙዎች አግላይ ሆኗል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከገጠር ወደ ከተማ የሚካሄደው ፍልሰት ከመጠን በላይ ከመሆኑ የተነሳ ለመቆጣጠር አልተቻለም፡፡ በርካታ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች በመከፈታቸው ምክንያት የምሩቃን ቁጥር ከአቅም በላይ እየሆነ ነው፡፡ ወጣት የሚበዛባት ኢትዮጵያ በተጠና የሥራ ፈጣሪነት ክህሎትና ዕውቀት ባላቸው ዜጐች አማካይነት ችግሮቿን መፍታት ካልቻለች፣ ስደት ወደፊትም ብሔራዊ ችግር ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ለዚህ ደግሞ አሳማኝ የሆኑ የስደት ምክንያቶች መሬት ወርደው ሁሉን አሳታፊ የሆነ ምክክር ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ መፍትሔ የሚገኘው ጥሬ ሀቁ ላይ መነጋገር ሲቻል ብቻ ነው፡፡

በገጠር በቤተሰብ መበራከት ምክንያት የአርሶ አደሮች ማሳ እየጠበበ በሚሄድበት ጊዜ ወጣቶች መሬት አልባ ስለሚሆኑ ወደ ከተማ ይፈልሳሉ፡፡ በከተማ የሥራ ዕድሉም የተጣበበ ስለሚሆን ወደ ውጭ መሰደድን አማራጭ ያደርጋሉ፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶችም ተቀጥሮ ከመሥራት ጀምሮ ሥራ ለመፍጠር በሚያደርጉት ጥረት መሰናክሉ ስለሚበዛ የሚታያቸው ስደት ነው፡፡ በአነስተኛና በጥቃቅን ተደራጅቶ ለመሥራት መሬት፣ የባንክ ብድርና ገበያ ማግኘት በጣም አዳጋች በመሆኑ ወጣቶች ለሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ተበድረውም ሆነ ከቤተሰቦቻቸው ወስደው ካቅማቸው በላይ የሆነ ክፍያ እየፈጸሙ ይሰደዳሉ፡፡

ይህንን ዓይነቱን አደጋ የበዛበት ስደት ከሚያባብሱ ዋነኛ ችግሮች መካከል ደግሞ ተጠቃሽ የሚሆነው ተስፋ ቆራጭነት ነው፡፡ ይህ ተስፋ ቆራጭነት የሚመጣው ደግሞ ወጣቶች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በአስተዳዳሪዎች የሚፈጸሙ በደሎች ሲበዙ ነው፡፡ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት የሚያስተባብላቸው፣ ነገር ግን የሰላ ትችቶች የሚቀርቡበት በገጠር ከማዳበሪያና ከምርጥ ዘር ጀምሮ እስከ ዕርዳታ እህል ድረስ ሥርዓቱን በማይደግፉት ላይ ክልከላ መደረጋቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ በደል ሲፈጸም መንግሥት በተለያዩ መዋቅሮቹ አማካይነት ችግሮቹን መፈተሽ ባለመቻሉ ለወጣቶች ምሬት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ እንጀራ የሚፈልግ ሰው በመገፋቱ ምክንያት የፖለቲካ ስደተኛ ይሆናል፡፡ ይህም በተደጋጋሚ ጊዜያት በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ብዙ የተባለበት ነው፡፡ የፖለቲካ ትስስር ያላቸው ብቻ ተጠቃሚ በመሆናቸው ምክንያት ብዙኃን እየተገለሉ ነው ሲባል ከማስተባበል ይልቅ ችግሩን ማረም ይበጃል፡፡ ይህም ጠንከር ያለ ዕርምጃ ይፈልጋል፡፡

ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባ ከተማ ጭርንቁስ ሠፈሮች ውስጥ የሚኖሩ ወጣቶች በተባባሰ ድህነት ውስጥ ስለሚኖሩ፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስደትን ይመርጣሉ፡፡ በተለያዩ ሙያዎች ሥልጠና ያገኙ ወጣቶች ሳይቀሩ ሥራ አጥተው ይቦዝናሉ፡፡ ብዙዎቹም በመጠጥ፣ በጫት፣ በሺሻና በሌሎች ዕፆች ቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ በተስፋ መቁረጥ ውስጥም ሆነው እነዚህ ወገኖች አጋጣሚውን ካገኙ መሰደድ ነው ፍላጐታቸው፡፡ በቅርቡ በስደተኛ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው አረመኔያዊ ግፍ አገሪቱን ማቅ አልብሷት እንኳን፣ የመጣው ይምጣ ብለው ለመሰደድ የተዘጋጁ ብዙዎች መሆናቸው ይነገራል፡፡ በሠለጠኑበት ሙያ ለመሥራት፣ መንጃ ፈቃድ ለማውጣትና ለመሳሰሉት አቅም በማጣታቸው መሰደድን አማራጭ ማድረጋቸውንም እየተናገሩ ነው፡፡ ዜጐች በአገራቸው ለምን ተስፋ ይቆርጣሉ? ዕድሎች ለምን አይመቻቹላቸውም? መጠነኛ ገንዘብ ኖሮአቸው ለመሥራት ሲፈልጉ እንኳ እንዲበረታቱ ለምን የተለየ አሠራር አይዘረጋም? ችግሮቹን ከሥር ከመሠረታቸው በማየት መፍትሔ ለምን አይፈለግም?

መንግሥት ዘወትር የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚፈጥሩዋቸው ምሬቶችን በተመለከተ ሲያወሳ ይሰማል፡፡ በተግባር ግን የሚታይ ለውጥ የለም፡፡ በተወሰኑ አካባቢዎች የታዩ ስኬቶች የኢትዮጵያ ወጣቶች መለያ እንደሆኑ ተደርጐ ሲቀርብ ይታያል፡፡ ችግሩ የብዙኃን አይደለም ተብሎ ይሸፋፈናል፡፡ እንዳለፈው ሳምንት ዓይነት አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ግን ለብጥብጥ መነሻ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ በአጠቃላይ ዜጐች ውስጥ የሚሰሙ ቅሬታዎችና እሮሮዎች በታመቁ ቁጥር ድንገት ሲፈነዱ ከቁጥጥር ውጭ ሆነው በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ ወጣቶች በአፍላነታቸው ጊዜ ሲከፉና አደጋ የበዛበትን ስደት አማራጭ ሲያደርጉ እንደ አገር ሊከብደን ይገባል፡፡ ለመፍትሔውም መጨነቅ አለብን፡፡ መፍትሔውም ከወገንተኝነት የፀዳ ውሳኔ ነው፡፡

አገሪቱ ከድህነት ማጥ ውስጥ ለመውጣት እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ናት፡፡ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ የሚታዩት አዝማሚያዎችም ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡ ነገር ግን የዛሬው ልፋት የዛሬውን ወጣት ማዕከል ካላደረገ ልፋቱ ሁሉ ውኃ መውቀጥ ነው፡፡ ልማቱ ሰብዓዊ ፍጡራንን ጭምር ያካት ሲባል የአገሪቱ ዜጐችን ታሳቢ ማድረግ አለበት ማለት ነው፡፡ ዜጐች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሲከበሩ፣ ከአገሪቱ ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሲጠቀሙ፣ ሐሳባቸውን በነፃነት ሲገልጹ፣ ለቅሬታዎቻቸው በቂ ምላሽ ሲያገኙ፣ በገዛ አገራቸው የባለቤትነት ስሜት ሲሰማቸው፣ የፈለጉትን በሰላማዊ መንገድ መደገፍ ወይም መቃወም ሲችሉና በአገሪቱ ሁሉም ጉዳዮች ውስጥ ያለአድልኦ ሲስተናገዱ ስደትን ሙሉ በሙሉ ማቆም ባይቻል እንኳ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ይቻላል፡፡ ለአገሪቱ ወጣቶች ስደት አንድ ምክንያት ብቻ እየመዘዙ ዲስኩር ማሰማት ከትርፉ ይልቅ ጉዳቱ ይብሳል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በበርካታ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ስምምነት የለም፡፡ ብሔራዊ ጉዳዮቻችን ከስሜታዊነት ባልፀዱ አመለካከቶች እየተቃኙ ናቸው፡፡ በጋራ ጉዳያችን ላይ ተስማምቶ አንድ አቋም ለመያዝ ቀርቶ መነጋገር እንኳን ባለመቻሉ ክፍፍሉ አስጊ እየሆነ ነው፡፡ አንዱ ሌላው ላይ ጭቃ እየለጠፈ በጥላቻ በመፈራረጅ ላይ ጊዜውን ስለሚያጠፋ የወጣቶቻችንን ችግር በቅጡ ለማየት አልተቻለም፡፡ የፖለቲካው ምኅዳር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከመበጀት ይልቅ መጠፋፊያ መስሏል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰሞኑን በተስተዋሉ ክስተቶች ላይ እንኳን፣ በግራም በቀኝም ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች በጊዜያዊነት መግባባት አቅቷቸው በየፊናቸው የመሰላቸውን አቋም ሲያራምዱ ታይተዋል፡፡ ይኼ እንደ አገር ሲታይ አስጊ ነው፡፡ ወጣቶቻችንን የስደት አለንጋ እያንገበገባቸውና ሕይወታቸውም እጅግ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ሲያልፍ፣ አንድ ላይ ሆኖ ለመምከር አለመቻል ትልቅ በሽታ ነው፡፡ ጽንፍ በረገጡ አቋሞች ምክንያት አንገብጋቢ የሆኑት ብሔራዊ ጉዳዮች እየተዘነጉ ከቀጠሉ ጉዞው የት ድረስ ይቀጥላል? ውጤቱስ ምንድነው? ካልተባለ ችግር አለ፡፡ ይህ በብርቱ ይታሰብበት፡፡ ጨርሶ ከመተው ዘግይቶም ቢሆን መጀመር የግድ ይላል፡፡

ወጣቶቻችን ትልቅ ትኩረት ይሰጣቸው፡፡ የዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር መሆናቸው ይታመን፡፡ ከተመሪነት ይልቅ ለመሪነት ይዘጋጁ፡፡ አገሪቱ ያላት አንጡራ ሀብት እነሱ ላይ ኢንቨስት ይደረግ፡፡ መብቶቻቸው ይከበሩ፡፡ አድልኦ አይፈጸምባቸው፡፡ በአገራቸው አንገታቸንው ቀና አድርገው የሚሄዱ ኩሩ ዜጎች ይደረጉ፡፡ አላስፈላጊ ከሆኑ ደባል ሱሶች ጥበቃ ይደረግላቸው፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ዕድሉ ይመቻችላቸው፡፡ በአገራቸው ጉዳይ ንቁና ዋነኛ ተዋናይ ይሁኑ፡፡ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለዚህ አገራዊ ጥሪ ርብርብ ያድርጉ፡፡ ለስደት መንስዔ የሆኑ አሳማኝ ምክንያቶች መፍትሔ ይፈለግላቸው!        

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...