የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ባለፉት አራት ወራት የሰበሰበው ግብር ዝቅተኛ እንደሆነና በዕቅዱ መሠረት መሰብሰብ አለመቻሉ እንዳሳሰበው አስታወቀ፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ባልቻ ኅዳር 13 ቀን 2010 ዓ.ም. የባለሥልጣኑን የአራት ወራት የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ የግብር አሰባሰብ ሒደቱ ባለፉት አራት ወራት ዝቅተኛ ሆኗል፡፡ በዚህ ከቀጠለ ከፍተኛ የሆነ ችግርና ቀውስ ሊፈጠር ይችላል ብለዋል፡፡ በሕጉ መሠረት ሁሉም ዜጎች ግብር እንዲከፍሉ ማድረግ ከባድ ፈተና እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ጉልበት ያለው ግብር የማይከፍልበት አሠራር እየተበራከተ መጥቷል፤›› ብለው፣ ነገር ግን ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ እንዳልሆነና ይህንን ተከታትሎ ወደ ትክክለኛው መንገድ መመለስ ወሳኝ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
‹‹ሕግ የሚጥሱትን ተከታትሎ መስመር ከማስያዝ አንፃር ውስንነት እንዳለ ነው የገመገምነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ባለፉት አራት ወራት ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለመሰብሰብ ያቀደው ገቢ 72 ቢሊዮን ብር ቢሆንም፣ የተሰበሰበው ገቢ ግን 63 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ይህም ከዕቅዱ አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጤናማ የሆነ የገቢ አሰባሰብ ቢኖረን ኖሮ 33 በመቶ ነበር መሰብሰብ የሚገባን፡፡ ይሁን እንጂ 27 በመቶ ብቻ ነው መሰብሰብ የቻልነው፤›› ብለዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዓመቱ እንዲሰበሰብ ያፀደቀው 199.11 ቢሊዮን ብር እንደሆነ፣ ባለሥልጣኑ ደግሞ ዕቅዱን ወደ 230 ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
‹‹ከአጠቃላይ ዓመታዊ የዕድገት ዕቅዱ ጋር ሲነፃፀር መሰብሰብ የቻልነው 12.5 በመቶ ነው፡፡ ይኼ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንደርስበታልን ብለን ካሰብነው 17.2 በመቶ ዕድገት ጋር ስናነፃፅረው በእጅጉ የራቀ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የገቢ አሰባሰብ ጋር ሲነፃፀር ግን የ7.7 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
የአራት ወራት አጠቃላይ አፈጻጸም ሲገመገም በቂ አለመሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረው፣ ይህን ለማስተካከል ኦዲተሮችና የኢንተለጀንስ ባለሙያዎች ብቁ አቅም ፈጥረው እንዲወጡ የተለያዩ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የጥቅምት ወርን ሳይጨምር በ81 ግብር ከፋዮች ላይ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ግብር ከፋዮች መካከል አብዛኛዎቹ መርካቶ የሚገኙ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል 23 የሚሆኑ ግብር ከፋዮችም ሕግ ሲተላለፉ እጅ ከፍንጅ የተያዙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ከጉምሩክ ጋር ተያይዞ አገልግሎት አሰጣጡን ዘመናዊ በተለይም በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ በማድረግ፣ ላኪዎች የተለየ የመስተንግዶ አገልግሎት የሚያገኙበት አሠራር እየተዘረጋ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሒደቱ እየተገመገመና ከቅሬታዎች በመነሳት ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በ2010 ዓ.ም. በአራት ወራት ውስጥ በርካታ የገቢና ወጪ መስተንግዶዎች መሰጠታቸውን ጠቁመው ለወጪ ንግድ 221,217፣ ለገቢ ንግድ 471,236 የመስተንግዶ አገልግሎቶች መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ የወጪ ንግዱም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የአንድ በመቶ ብቻ ዕድገት ማሳየቱን ጠቅሰው፣ በገቢ ንግዱ በኩል ግን የ8.5 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡
አሠራሮችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመተካት ባለሥልጣኑ ረዘም ላለ ጊዜ ይጠቀምበት የነበረውን የተቀናጀ የመንግሥት ገቢ አስተዳደር ሥርዓት (ሲንታክስ) ለማሻሻል እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ከገቢ ግብር አዋጁ መሻሻል ጋር ተያይዘው ምቹ ያልሆኑ ጉዳዮች እንደነበሩ፣ በዚህም 50 ችግሮች ተለይተው በሲስተሙ እንደተስተካከሉ ጠቁመዋል፡፡ ግብር ከፋዩ ከቤቱ ሆኖ ሪፖርት የሚያደርግበት የኢፋይሊንግ ሥርዓት መዘርጋቱንና በቀጣይም የኢፔይመንት ሥርዓት ለመዘርጋት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ የአገሪቱን ጉምሩክ ሥርዓት ዘመናዊና ቴክኖሎጂ ቀመስ ለማድረግም፣ ከዚህ በፊት ያገለግል የነበረውን አሲኩዳ ፕላስ ፕላስ የሚባለው ፕሮግራም ለአገልግሎት ማነቆ እንደሆነ ጠቁመው፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአጋር ድርጅቶቹ ጋር በመሆን ለማስተካከል ጥረት መደረጉን አስረድተዋል፡፡ ሥርዓቱ በልፅጎ በቃሊቲና በሞጆ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በሙከራ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ቀሪዎቹን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ በማድረግ፣ ከዚህ በፊት የነበሩትን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለመፍታት እንደሚቻል እምነታቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በገቢና ወጪ ዕቃዎች ላይ ተገልጋዮች ከዓለም ገበያ ጋር የሚወዳደሩበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርና መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር እየሄዱ የሚያባክኑትን ጊዜ ለመቅረፍ፣ የኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ የአንድ መስኮት አገልግሎት ፕሮግራም ተቀርፆ እንደዳበረ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህ በጀት ዓመት ጥምረት መፍጠር ያለባቸው ሃያ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንደተለዩና እነዚህ ላይ ከሥራ ሒደት ቀረፃ ጀምሮ ሶፍትዌር እየተሠራ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡
ለሁለተኛው ዙር ደግሞ ቀሪ ሃያ ተቋማት እንዳሉና በድምሩ 40 ተቋማት ትስስር እንዲፈጥሩ በማድረግ፣ በገቢና ወጪ አገልግሎቶች ላይ ለውጥ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የታክስ አስተዳደሩ የሕግ ተገዥነትን ከማረጋገጥ አኳያ ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉበት ጠቁመው፣ ይህንንም ክፍተት በግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች ለመፍታት መታቀዱንም አመልክተዋል፡፡
‹‹የንግድ ትርፋቸውን ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ማሳወቅ ከሚጠበቅባቸው 16 ሺሕ ከሚጠጉ ግብር ከፋዮች መካከል ግብራቸውን ያሳወቁት 63 በመቶው ብቻ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ሌሎች 28 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ መክሰራቸውን እንዳሳወጁ ተናግረዋል፡፡
የተጨማሪ እሴት ታክስን በተመለከተም በአማካይ 17 ሺሕ የሚደርሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢዎች ሪፖርት እንደሚያደርጉ፣ ክፍያ የሚፈጽሙት ደግሞ ግን 30 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡ 45 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ተመላሽ የሚጠይቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ተመላሽ ከሚጠይቁት መካከል ደግሞ 25 በመቶ የሚሆኑት ‹ሥራ አልሠራንም፣ የንግድ እንቅስቃሴ የለንም› የሚሉ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይህ በአጠቃላይ አገሪቱ ውስጥ እየተመዘገበ ካለው ኢኮኖሚ ጋር ሲታይ እውነታነት የሌለው ነው፤›› ብለው፣ ጤናማ የሆነ የታክስ አስተዳደር ሥርዓት አለመኖሩን አመልካች መሆኑን ገልጸዋል፡፡