Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ ወረዳዎች ለቀጠለው ግጭት ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጨፌው ወሰነ

  በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ ወረዳዎች ለቀጠለው ግጭት ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጨፌው ወሰነ

  ቀን:

  ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ መደበኛ ጉባዔውን ያካሄደው የኦሮሚያ ክልላዊ ምክር ቤት (ጨፌ) የኦሮሚያ መንግሥት በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ ወረዳዎች በቀጠለው ግጭት ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ወሰነ፡፡

  ምክር ቤቱ ባካሄደው ጉባዔ ዋነኛ የመወያያ አጀንዳ ከነበሩ ጉዳዮች የላቀ ትኩረት የተሰጠው፣ ላለፉት አራት ወራት የቀጠለው የወሰን ግጭት መሆኑ ታውቋል፡፡

  ግጭቱ የተነሳው ከሶማሊያ የሚነሱ ታጣቂዎች በአምስት የኦሮሚያ አዋሳኝ ዞኖች ወረዳዎች ላይ በከፈቱት ጥቃት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

  በምክር ቤቱ ጉባዔ ላይም ጥቃቱን በመሰንዘር የሰው ሕይወት የማጥፋትና ንብረት የማቃጠል፣ ነዋሪዎችን የማፈናቀልና የሶማሌ ክልል ባንዲራን መትከል እንደታየ የተለያዩ የጨፌው አባላት ማንሳታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

  ጥቃቱ እየተሰነዘረ ያለው በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች፣ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ወረዳዎች፣ እንዲሁም በጉጂ ዞን መሆኑን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

  የክልሉ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ ሰባት ነጥቦችን የያዘ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በመጀመሪያ የተቀመጠው ውሳኔ ለችግሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት በተቻለ አቅም ችግሩን በሰላማዊና የአካባቢው የኦሮሞ ሕዝብን ጥቅምና ደኅንነት በዘላቂነት ሊያስከብር በሚችል መንገድ መፍታት የሚል ነው፡፡

  የኦሮሞ ሕዝብን ደኅንነት መጠበቅ የክልሉ መንግሥት ኃላፊነት በመሆኑ፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይል በሕዝቡ ሙሉ ተሳትፎ ተደግፎ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በሚያስችል ሁኔታ ተጠናክሮ ግዴታውን እንዲወጣ ማድረግ ሌላው የውሳኔው አካል ነው፡፡

  የሁለቱ ክልሎችን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት በ1997 ዓ.ም. በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ መሠረት ለችግሩ እልባት ለመስጠት ከተሰጡ የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል፣ ከሁለቱም ክልሎች ችግሮቹ ተባብሰው እንዲቀጥሉ ሚና የነበራቸውን የመንግሥት መዋቅር አካላት ለሕግ ማቅረብ የሚለው ይገኝበታል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከአንድ ወር በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በአገሪቱ ከተቀሰቀሱት ግጭቶች አሳሳቢና በበርካታ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘው በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ ድንበሮች የተቀሰቀሰው ግጭት ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡

  ችግሩን ለመፍታትም የአርብቶ አደርና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከሁለቱ ክልሎች ጋር እየሠራ በመሆኑ፣ በፍጥነት እልባት እንዲያገኝ እንደሚደረግ ገልጸው ነበር፡፡

  ይሁን እንጂ ግጭቱ መጠነኛ መሻሻል ቢያሳይም አሁንም በመቀጠል ላይ መሆኑን ከአካባቢው የተገኙ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

  የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በቅርቡ ከኦሕዴድ ወጣቶች ጋር ባደረጉት ውይይት የድንበር ግጭቱን የተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ ለጊዜው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ ለችግሩ እልባት እንዲሰጥ መደረጉን ተናግረው ነበር፡፡ ከሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ጋር ተወያይተው እንደነበርና ታጣቂዎቹ የሶማሌ ክልልን እንደማይወክሉ እንደገለጹላቸው አስረድተዋል፡፡ ሪፖርተር የአርብቶ አደርና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...