Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናህንድ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ እንደምታቀርብ አስታወቀች

ህንድ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ እንደምታቀርብ አስታወቀች

ቀን:

  • በህንድ ፋይናንስ የተደረጉ የስኳር ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ደካማ መሆናቸው ተገለጸ

በአሥራት ሥዩም፣ ኒውዴልሒ፣ ህንድ

በሦስተኛው የህንድ አፍሪካ የትብብር ፎረም ቃል በተገባው መሠረት፣ ህንድ በአምስት ዓመት ውስጥ ለአፍሪካ እንደምትሰጥ ቃል ከገባችው የአሥር ቢሊዮን ዶላር ብድር ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን አስታወቀች፡፡ ታንዛኒያ የ1.115 ቢሊዮን ዶላር ብድር ቃል ተገብቶላታል፡፡

ከጥቂት ቀናት በፊት በህንድ ርዕሰ ከተማ ኒውዴልሒ በተካሄደውና የህንድ የኢንዱስትሪዎች ኮንፌደሬሽን ከህንድ የኤክስፖርትና ኢምፖርት ባንክ (ኤግዚም ባንክ ኦፍ ኢንዲያ) ጋር በመሆን ዘንድሮ ለ12ኛ ጊዜ ባዘጋጁት፣ የህንድና የአፍሪካ የአጋርነት ፕሮጀክት ጉባዔ ወቅት እንደተገለጸው፣ ኢትዮጵያና ታንዛኒያ ትልቁን የብድር ድርሻ የያዙ አገሮች ሆነዋል፡፡ ለሁለቱ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ሊሰጥ የታቀደው ብድር በአብዛኛው ለመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንደሚውል ጠቁሟል፡፡ ኢትዮጵያ 1.004 ቢሊዮን ዶላር ብድር እንደምታገኝ ሲገለጽ፣ ሞሪሺየስ 864 ሚሊዮን ዶላር፣ ሱዳን 734 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም ሞዛምቢክ 639 ሚሊዮን ዶላር ብድር የሚለቀቅላቸው አገሮች መሆናቸው ታውቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከሁለት ዓመት በፊት ተካሂዶ ከነበረው ሦስተኛው የህንድ አፍሪካ ጉባዔ ወዲህ የህንድ ኤግዚም ባንክ በአፍሪካ በ40 አገሮች ውስጥ ለሚካሄዱ 120 ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ድጋፍ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ሲገለጽ፣ እስካለፈው ዓመት መጠናቀቂያ በተለያዩ 149 የብድር ማዕቀፎች አማካይነት 7.6 ቢሊዮን ዶላር ብድር መልቀቁን ባንኩ አስታውቋል፡፡

ባንኩ ለኢትዮጵያ ያቀረበው የብድር መጠን በጠቅላላው 1.004 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2013 ለኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መሥመር ዝርጋታ ያቀረበውን የብድር መጠን እንደሚያካትት ከባንኩ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ለኢትዮጵያ ከዋሉት ሰባት የብድር ማዕቀፎች መካከል አብዛኞቹ ለስኳር ልማት ፕሮጀክቶች የዋሉ ሲሆን፣ ከባቡር ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ለኃይል ማሰራጫና ማስተላለፊያ ፕሮጀክትም በጥቅሉ 65 ሚሊዮን ዶላር ከባንኩ ተገኝቷል፡፡ ይሁንና ከሰባቱ የብድር ማዕቀፎች አምስቱ ለስኳር ልማት ፕሮጀክቶች የተለቀቁ መሆናቸውን የጠቆሙት የኤግዚም ባንክ ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዲባሲህ ማሊክ፣ ፕሮጀክቶቹ ግን እንደታሰበው ጥሩ አፈጻጸም አላሳዩም ብለዋል፡፡

ባንኩ ነባሮቹን የወንጂና መተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ከማድረግ ባሻገር፣ ለተንዳሆ የተቀናጀ ስኳር ልማት ፕሮጀክትም ብድር ማቅረቡ ተወስቷል፡፡ ይሁንና ተንዳሆ ፕሮጀክት ከሚገመተው በላይ ከመዘግየቱም በላይ፣ በተቋራጮች መካከል አለመግባባትን ያስከተለ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተለይም የህንድ ተቋራጮች እርስ በርሳቸው መካሰሳቸው ለተንዳሆ ፕሮጀክት መዘግየት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ለአገሪቱ ስኳር ፕሮጀክቶች የሚውሉ የ122 ሚሊዮን፣ የ166 ሚሊዮን፣ የ213 ሚሊዮን፣ የ91 ሚሊዮን፣ እንዲሁም 47 ሚሊዮን ዶላር ብድሮች በአምስት የብድር ማዕቀፎች አማካይነት ከህንድ መንግሥት ተለቀዋል፡፡ ይሁንና ባንካቸው ፋይናንስ ያደረጋቸው የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ውጤታማ መሆን እንዳልቻሉ ለሪፖርተር የገለጹት ማሊክ፣ ዋናው የፕሮጀክቶቹ ድክመት በሸንኮራ አገዳ ልማት ላይ የታየው ክፍተት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም የአገሪቱን የሸንኮራ አገዳ እርሻ እንዲያንሰራራ ለማድረግ የሚያግዝ ሥራ ባንኩ እንደሚያከናውን ቃል ገብተዋል፡፡  

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...